ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, November 23, 2014

የታወቀ የጀርመን የፊልም ኩባንያ ከ20 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ “ዘ ኢትዮጵያን” የተሰኘ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩር ፊልም ሊሰራ ነው።ፊልሙ በአገሪቱ ባህልና የአየር ፀባይ ተማርኮ በኢትዮጵያ በቀረ ጀርመናዊ እውነተኛ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል፡፡ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ይሳተፉበታል።

ፎቶ - ሳያት ደምሴ (ይህንኑ ፊልም አስመልክቶ ኢትዮ-ሲኒማ ሪቪው ድረ-ገፅ ላይ ከወጣው ፖስተር የተወሰደ)

ሳያት በኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከፍተኛ ተከፋይ ትሆናለች  
ፊልሙን የሚቀርፀው የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው
የታወቀ የጀርመን የፊልም ኩባንያ ከ20 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ “ዘ ኢትዮጵያን” የተሰኘ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩር ፊልም ሊሰራ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ዕውቋ ድምፃዊና ተዋናይት ሳያት ደምሴ ከታዋቂ የጀርመን ተዋናይ ጋር በፊልሙ ላይ በመሪነት ትተውናለች፡፡ ሳያት ደምሴ በኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከፍተኛው ክፍያ እንደሚከፈላት የፊልሙ ዝግጅት አስተባባሪ ዮሐንስ ፈለቀ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በጀርመናዊው ደራሲ ሄንሪክ ሄዲንት የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ውስጥ የተካተተው “The Ethiopian” የተሰኘው ታሪክ ወደ ፊልም እንደሚቀየር የታወቀ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአገሪቱ ባህልና የአየር ፀባይ ተማርኮ እዚሁ በቀረ ጀርመናዊ እውነተኛ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል ተብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ ከሳያት ደምሴ በተጨማሪ አንጋፋዋ አርቲስት ሃና ተረፈና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተዋንያን እንዲሁም ሶስት ታዋቂ ጀርመናዊ ተዋንያን ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ “ሳያት ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ተዋንያን ከፍተኛ ክፍያ ያገኛሉ” ብሏል - አስተባባሪው፡፡ የፊልሙ ዳይሬክተር ታዋቂው ጀርመናዊ ፈርዲናንድ ለኢራች ሲሆን ፊልሙን በመቅረፅ ዕውቁ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ “ሙቪ ዘ አርት ኦፍ ኢንተርቴይንመንት”፣ በፕሮዱዩሰርነት ደግሞ “ኮንስትሬይን ፊልም ፕሮዳክሽን” እንደሚሳተፉ አስተባባሪው ገልጿል፡፡ 

ኢትዮጵያ የተሟላ መሰረተ ልማት (ኢንተርኔት፣ ደረጃውን የጠበቀ ሆቱል፣ የቀረፃ ቦታና ሌሎች) የሏትም በሚል ፊልሙ በኬንያ ሊሰራ እንደነበር የጠቆመው አስተባባሪው “እንዴት የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮረ ፊልም ኬኒያ ውስጥ ይሰራል” የሚል ከፍተኛ ሙግት ከተካሄደ በኋላ በኢትዮጵያ እንዲሰራ መወሰኑን ገልጿል፡፡ የፊልሙ ቀረፃ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋና በሃረር እንደሚከናወን አስተባባሪው አክሎ ገልጿል፡፡ 
ምንጭ - ኢትዮ ሲኒማ ሪቪው ድረ ገፅ 
         - አዲስ አድማስ ጋዜጣ  ኅዳር 13/2007 ዓም (22 November, 2014) ዕትም 
  •  

No comments: