ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, November 26, 2014

የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ''ሶቨሪን ቦንድ'' ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?



ኢትዮጵያ ከእዚህ በፊት ከመንግሥታት፣አህጉራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ወስዳለች።አሁን ያለባት የብድር መጠን ከ20 ቢልዮን ዶላር ወይንም ከ400 ቢልዮን ብር በላይ መሆኑ ይታወቃል።ወደ ''ሶቨሪን ቦንድ'' እንድትገባ በዝግ ምክርቤት ወሰነ የተባለው የብድር አይነት ግን ኢትዮጵያ ከግል አበዳሪዎች ሁሉ በደላሎች ብድር እየፈለገች እንድትበደር የሚያደርግ፣በሙስና ለተሰነገ ሀገር ፈፅሞ የማይመከር ነው።ለመሆኑ የሶቨርን ቦንድ ምን ማለት ነው? ''ኢንቨስቶፕድያ እንዲህ ይገልፀዋል።

''ሶቨሪን ቦንድ'' ማለት በመንግሥታት  በውጭ ምንዛሪ የሚቀርብ የብድር ዋስትና ሲሆን የውጭ ምንዛሪው በጠንካራ አለም አቀፍ ገንዘብ (ሃርድ ከረንሲ) የተደገፈ ነገር ግን ለቦንድ ያዥው የበለጠ አደጋ ያለው '' ይላል 

''DEFINITION OF 'SOVEREIGN BOND'
A debt security issued by a national government within a given country and denominated in a foreign currency. The foreign currency used will most likely be a hard currency, and may represent significantly more risk to the bondholder.'' www.Investopedia.com

ምዕራባውያን እና ሶቨርን ቦንድ 

ብድሩን የምዕራብ ሃገራት ፍላጎት የታዳጊ ሀገሮች ወደገበያው መግባት ነው። ምክንያቱም አበዳሪ ሁል ጊዜ ተበዳሪ  ማግኘት ስራው ነው።ይህ ማለት ተበዳሪ በአዋጭም ይሁን በማያዋጣ መንገድ ላይ ቢሆን ለአበዳሪ ጉዳዩ አይደለም። አበዳሪ ገንዘቤ ባይመለስ በምን ሌላ አስገዳጅ ነገር ውስጥ አስገብቼ ያልታሰበ ሲሳይ ይገኛል? ነው ጥያቄው።ለእዚህ ነው የ''ፋይናንሻል ታይምስ'' ጨምሮ የኢትዮጵያን ወደ እዚህ ብድር መምጣት አሰማምሮ የፃፈው።ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ተጠጋች የሚለውን ስጋት ለማራቅ ''በሶቨሪን ቦንድ'' መያዙ ለወደፊት 'ስልታዊ ጥቅም' አለውና።በሌላ በኩል ይህ ብድር የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ማስፈፀምያ አንዱ ስልት ነው።

ግሪክን ያየህ ተቀጣ

 ግሪክ ባለፉት ሁለት ዓመታት የምጣኔ ሃብቷ ያን ያህል ያሽቆለቆለው ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ሃገራት ስር በተለይ ጀርመን ስር እንድትንበረከክ የተደረገው በእዚሁ ''ሶቨርን ቦንድ'' አማካይነት ነው።የሀገሪቱ ህዝብም አደባባይ ወጥቶ የገዛ መንግስቱን የተቃወመው በእናንተ ሙስና ምክንያት ሀገሪቱ ከማትችለው ብድር ውስጥ አስገባችሁ በሚል ነበር።ይህንን ለመረዳት ''የሶቨሪን ብድር ቀውስ የዘመናዊዋ ግሪክ አሳዛኝ ሁኔታ''  ''The Sovereign Debt Crisis: A Modern Greek Tragedy'' በሚል ርዕስ የወጣውን ''የሴንት ሉዊስ ባንክ'' ፅሁፍ ያንብቡት።


ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ የመውደቅ እድል አለው 

በኢትዮጵያ ላይ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ፍላጎት ያላቸው ሀገሮች በግለሰብ ወይንም በኩባንያ ስም ከአውሮፓ ወይንም ከአሜሪካ ብቅ ቢሉስ? ለምሣሌ የገንዘብ ችግር የሌለባቸው እንደ ሳውዲ አረብያ ያሉ ሀገሮች ገንዘባቸውን በባንክ ከማስቀመጥ በእደዚህ አይነት ብድር ለድሃ ሃገራት  ቢሰጡ ያተርፋሉ።ኢትዮጵያ ላይ በብዛት ብድር ሰጥተው መልሰው የነገር መቆስቆሻ ሊያደርጉት እና እስከ ጦርነት የሚያደርስ ብሎም በሉዓላዊነታችን  ላይ የሚጋረጥ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል።በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚነሱ ግጭቶች ደግሞ ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲደርስ ምንም አይነት የዲፕሎማሲ ድጋፍ የማያስገኝ ስለሆነ አበዳሪዎች በዓለም መድረክ የመሰማት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ለእዚሁም ምክንያቱ ኩባንያዎቹ በተለያየ ጥቅም ከብዙ ሃገራት ጋር የጀርባ ንግግር ስላላቸው እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ብድሩን መክፈል አለባት የሚሉ ቃላትን እንጂ ሌሎች ሁኔታዎችን የምያገናዝብበት ዕድል ፈፅሞ አይፈጥርለትም።በመሆኑም ሕጋዊ በሚመስል መንገድ ሀገር ለአደጋ ያጋልጣል ማለት ነው።

ባጭሩ የሶቨሪን ብድር በአለማችን የገንዘብ ስርዓት ውስጥ ያለ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ግን የሚገቡበት አግባብ የራሱ የተገደበ መስመር መያዝ ይገባው ነበር። ይህ የተገደበ መስመር ማለት-

 1/ ስለ ብድሩ ምንነት፣አስፈላጊነት እና የመክፈል አቅም በዝርዝር በስሙ ለሚበደሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ መነገር ነበረበት፣
2/ ህዝቡ በጉዳዩ ላይ መወያየት ነበረበት፣
3/ ሙስናው ቅጥ ባጣበት ሀገር እዴት ሊሰራ እንደሚችል መጤን ነበረበት፣
4/ብድሩ ለየትኛው ፕሮጀክት እና  ምን ያህል እንደሚወሰድ ለሕዝብ መታወቅ ነበረበት፣
5/ መንግስት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን በሕግ ገድቦ ማስቀመጥ ነበረበት። ለምሳሌ ገንዘብ ባነሰው ቁጥር በደላላ አበዳሪ እየፈለገ የሚበደር ከሆነ መጨረሻው የት ሊሆን ነው?
6/ ኢትዮጵያ ብድሩን ተበድራ ለመክፈል የምታስበው ከየት እና ምንን ታሳቢ አድርጎ ነው? የሚለው  በግልፅ ለሕዝቡ መቅረብ ነበረበት።

እነኝህ ሁሉ ባልተደረጉበት ሁኔታ ኢትዮጵያን አፏን ለጉመው፣የመገናኛ ብዙሃንን ዘግተው፣የግል ጋዜጦችን አሽገው፣ፓርላማውን በዝግ ስብሰባ አስፈራርተው በእኛ እና በልጆቻችን ስም የመበደር መብት እንዴት ያለ ሕዝብን የመናቅ ደረጃ ነው? በትክክል ከላይ ከተባለው አንፃር ስንመለክተው አደጋ ላይ ነን።ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በተድበሰበሰ መንገድ የሚሰራው ሥራ ''ምን ያህል ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የያዙ ሰዎች አመራር ላይ አሉ?'' ብሎ የመጠየቂያው ጊዜ ነው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከእራሷ ሀብት አፍርታ፣ወደውጭ የሚላክ ምርት ጨምራ የውጭ ምንዛሪ አግኝታ የመኖር አቅሟን ላለፉት 23 ዓመታትም መፍጠር አለመቻሏ አመላካች አንዱ መንገድ ይህ አሁን በቅርብ ቀናት ውስጥ አውሮፓ ላይ  ''ልንበደር ነው አድገናል'' የሚለው መግለጫ በኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናት ሊሰጥ መሆኑ ነው።የእድገታችን መገለጫ መበደር እንዴት ሊሆን ይችላል? ፖለቲካዊ ዝናን ለማግኘት የተገቡባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ግን ጠቃሚ የነበሩትን እንደ በምግብ እራስን መቻል፣ወዘተ ፕሮጀክቶች ችላ እንዲባሉ አላደረገም ወይ? ይህ የተሳሳተ የፖሊሲ ውሳኔ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለን አይደለም ወይ?  ነገሩን በአንክሮ ለተከታተለው ሰው አሳዛኝ ነው።ጥያቄው ግን አይቆምም የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ''ሶቨሪን ቦንድ'' ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (ኖቬምበር 27/2014)

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...