የቡክናፋሶ ዋና ከተማ ኦጋዱጉ ወጣቶች አምባገነኑን መሪ ካባረሩ በኃላ በድል ስሜት ውስጥ (ፎቶ ኤ ኤፍ ፒ)
Women pose with an armored personnel carrier in Ouagadougou. (Issouf Sanogo/AFP/Getty Images)
በልጅነቴ የሰሞኑ የቡክናፋሶው ''የጥቁር አብዮት'' ሳይነሳ፣ድሮ አክስቴ የነገረችኝን ተረት እንዲህ አስታውሰዋለሁ -
በድሮ ጊዜ አንድ በጣም ሃብታም ሰው ነበር።ይህ ሰው ታድያ ሁል ጊዜ የሞቱ ነገር ያሳስበው ነበር።እናም ለምን ሞትን አግኝቼ ምልክት ሳይሰጥ እንዳይወስደኝ አልነግረውም ብሎ አሰበ። ያሰበው አልቀረም ሞትን
''ካንተ ጋር ቃል ኪዳን መፈፀም እፈልጋለሁ'' አለው።
''የምን ቃል ኪዳን?'' ሞት ጠየቀ።
''እኔ ሳላውቅ እና ቀድመህ ሳታስጠነቅቀኝ እንዳትወስደኝ'' አለ ሀብታሙ ሰው።
ሞት ''ቃል ለምድር ለሰማይ ሳልነግርህ አልወስድህም'' ማለለት።ሀብታሙ ሰው ተደሰተ።ተዝናና፣በላ፣ ጠጣ፣ደስም አለው።
በዛው ሰሞን የሐብታሙ ሰው አንዲት የታመመች ግልገል በግ መሞቷን ከውጭ ሲገባ ነገሩት።
''አሁን ስንት ከብት የሞላኝ ሰው ቁም ነገር ብላችሁ ስለ አንዲት ግልገል ትነግሩኛላችሁ?'' ብሎ ሳቀ።
ከሳምትን በኃላ ከማዶ ሀገር ያሉ ሽማግሌ መሞታቸው ተሰማ። ከሕዝቡ ጋር ከንፈር እየመጠጠ እጆቹን ወደኃላ አጣምሮ በእርጋታ በመራመድ አስከሬኑን ሸኘ በመጨረሻም ቀበረ።
ከሶስት ቀን በኃላ ጎረቤቱ ታመው መሞታቸውን ሰማ።አዘነ፣ልጆቻቸው አሳዘኑት፣እየተመላለሰ እናታቸውን አፅናና።።ከስድስት ወር በኃላ የሚወደው አገልጋይ ሞተ።አዘነ ግን ለብዙ ጊዜ ይታመም ስለነበር ህመሙን አማረረ።
ከአመት በኃላ እራሱ ታመመ አልጋ ላይ አንድ ወር ተኛ በመጨረሻ ሞት ሊወስደው መጣ።
ሀብታሙ ሰው ሞትን ''አዝናለሁ ሳልነግርህ አልመጣም ብለህ ቃልህን አጥፈህ መጣህ?'' አለው።
ሞት መለሰ ''ቃሌን አላጠፍኩም።ከአመት በፊት ነግሬሃለሁ'' አለ።
ሀብታሙ ሰው እራሱን ያዘ ''ውሸት! ውሸት!" አለ።
ሞት እረጋ ብሎ ይዞ የሚሄድበትን ማሰርያ ገመድ እያዘጋጀ እንዲህ አለ ''እኔ አልዋሸሁም።መጀመርያ ግልገልህን በመውሰድ ነገርኩህ፣ቀጥዬ ማዶ የሚኖሩትን ወዳጅህን በመውሰድ አስጠነቀኩህ፣ በመቀጠል ጎረበትህን እና አገልጋይህን አከታተልኩ።በእዚህ ሁሉ መሃል ግን አንተ አልነቃህም።እራስህንም ለማስተካከል አልሞከርክም።እስኪ አሁን የእኔን ጥፋት ንገረኝ'' አለ ሞት ለመውሰድ እግሩን እያሳሰረ።
አሁን የቡክናፋሶን የ27 ዓመት ማስፈራራት በሰዓታት የህዝብ አመፅ መናድ ያየ በስልጣን ይቀልዳል? ከቡክናፋሶ በፊት በቱንስያ፣በአልጀርያ፣በግብፅ የህዝብ ማዕበል ያየ ''አልሰማሁም ነበር'' ማለት ይችላል? እርግጥ ነው ሞትና ስልጣን አንድ አይደሉም።ግን ለአምባገነኖች ከስልጣን መውረድ ከሞት የከበደ ስለሚሆንባቸው አንድ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።
ጉዳያችን
ጥቅምት 23/2007 ዓም (ኖቬምበር 2/2014)
No comments:
Post a Comment