ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 17, 2014

''የኦሮሞ ማህበረሰብ ከምንም በላይ ፣ በባሕሉ የሚመቸውና የሚቀበለው የአንድነትን እና የፍቅርን ፖለቲካ ነው። “እገሌ ከዚህ ዘር ስለሆነ፣ ወይንም ይሄ ቋንቋ ስለሚናገር ከአገራችን ይዉጣ፣ ይሄ ምድር የኦሮሞ ብቻ ነው …” የሚባለው አክራሪዎችና ካድሬዎች የሚረጩት እንጂ ከሕዝቡ የሚመጣ አይደለም።'' ግርማ ካሳ

 የኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህላዊ አለባበስ ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ-ገፅ 


በኦሮሞዉና በአማርኛ ተናገሪው መካከል ጥላቻ እንዲሰርጽ ተብሎ አንድ የተጻፈ መርዛማ መጽሐፍ አለ። የቡርቃ ዝምታ የሚባል መጽሃፍ። የዚህ መጽሀፍ ደራሲ አቶ ተስፋዬ ገበረ አብ ይባላሉ። የሕወሃት/ኢሓአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ጊዜ የጻፉት መጽሀፍ ነው። በቅርቡ “በሞጋሳ ኦሮሞ ሆኛለሁ” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ምን ያህል የሞጋሳ ሚስጠር እንደገባቸው ግን አላውቅም።
ከአራት መቶ አመታት በፊት፣ የኦሮሞ ጦረኞች አንድ አካባቢን በሚቆጣጠሩና በሚማርኩ ጊዜ፣ አንድ የሚያደርጉት ሥርዓት ነበር። የጎሳው ሽማግሌዎች ከተማዋ ሲገቡ ከዚያ ጊዜ ጀመሮ ያቺ ክከተማ ኦሮሞ ትሆናለች። በከተማዋም የሚኖረው ህዝብ፣ በሽማግሌዎቹ ፊት ያልፋል። በዘሩ ከሌላ ወገን ቢሆንም፣ በአለቃዉ ያለፈ ሰው ሁሉ ኦሮሞ ይሆናል። ይህ ስርአት ሞጋሳ ይባላል። ኦሮሞነት ከዘር ጋር ግንኙንት እንደሌለው የሚያስተምር የኦሮሞ ባህል !

ሞጋሳ የሚያሠባስብ ነው። አንድ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌላውን እንደ እራስ አድርጎ ማቀፍ ነው። ኦሮሞነት ሌላውን ማሳነሳ፣ ሌላውን ማባረር፣ ሌላውን መጥላት አይደለም።
እርግጥ ነው አንዳንድ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ በኦሮሞነት ስም ሌሎችን የመጥላት ፖለቲካ ያራምዳሉ። ከሌሎች የመለየት፣ ሌሎችን የማግለል፣ የመከፋፈል፣ የጥላቻ ፖለቲካ ያራግባሉ። የኦሮሞ ባህል ግን ፣ የሞጋሳ ባህል ግን ፣ አንድ የሚያደርግ ባህል ነው። እነርሱ ከሚናገሩትና ከሚረጩት መርዝ ጋር ግንኙነት የለውም።
ሌላው በአማርኛም ሳይቀር የምንጠቀማት ቃል አለች። ጉዲፈቻ። ጉዲፈቻ ማለት የሌላውን ሰው ልጅ እንደ ራስ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው። ጉዲፋቻ የሚለውን ቃል በአማራኛ መጠቀማችን በራሱ የሚያሳየው፣ የሌላውን ልጅ እንደራስ አድርጎ የማቀፍ ባህል፣ በኦሮሞው ማህበረሰብ ዉስጥ ምንም ያህል ስር የሰደደ ባህል እንደሆነ ነው። የኦሮሞው ማህበረሰብ፣ ትግሬ ይሁኑ አማራ፣ ጉራጌ ይሁኑ ከፊቾ ፣ ከሌላ ዘር የሆኑትን እንደራሱ አድርጉ የሚያሳድግ ማህበረስብ ነው። ከሌላው ጋር የተዛመደ፣ የተዋለደ፣ የዘረኝነት ነገር የሌለበት ማሀብረሰብ ነው።

ላለፉት 23 አመታት ግን በሽታ ገባ። የኦሮሞ ማህበረሰብን ከሌላው ለማጣላት ብዙ ተሞከረ። የባለስልጣናቱ ካድሬዎች ሆን ብለው በኦሮሞው እና ኦሮሞ ባልሆነው ማህብረሰብ መካከል ልዩነቶች እንዲፈጠሩ ቀን እና ሌሊት መስራት ጀመሩ።
ለአማርኛው ተናጋሪዎች “ ኦሮሞዎቹ ዘረኞች ናቸው። አማርኛን ይጠላሉ። ይጨርሷቹሃል። ያርዱዋቹኋል” የሚል እድምታ ያለው መልእክት በጎን ያስተላልፋሉ። ለኦሮሞ ደግሞ ” እነርሱ ነፍጠኞች ናቸው። በቋንቋህ እንዳትናገር ሊያደርጉህ ነው። ሊያጠፉህ ነው። የድሮው የአማራ የበላይነትን ሊያመጡብህ ነው። አሃዳዊ ስርዓት ሊጭኑብህ ነው” ይሉታል። አማርኛ ተናጋሪዎች በአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ላይ ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ደግሞ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ጥርጥሬ እንዲያድርባቸውና እና እንዳይግባቡ እያደርጓቸው ነው። ኦሮሞዎች አማርኛ እንዳይማሩ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ አማርኛ ብቻ እንዲናገሩ ተደርጎ፣ የአንድ አገር ልጆች ሆነን እንዳንግባባ ተደርገናል። መነጋገር ስላልቻልን፣ አንዳንች ስለአንዳንች የሚነጉን የአገዛዙ ካድሬውዎችና ዉጭ ያሉ አንዳንድ አክራሪዎች ናቸው። ነገሮችን እየጠመዘዙ ስለሚነግሩንም እርስ በርስ እየታመስን ነው።

መንቃት ይኖርብናል። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በኛ ላይ የሽረቡትን ወጥመድ ማፈራረስ አለብን። የኦሮሞ ባህል፣ የኦህደድ ካድሬዎች ወይንም ዉጭ ያሉ አንዳንድ ለኦሮሞ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግን በጥላቻ የተሞሉ አክራሪዎች እንደሚነግሩን አይደለም። ኦሮሞነት ዘረኝነት አይደለም። ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌሎች እንደ ራሱ አድርጎ መቆጠር ነው። ኦሮሞነት የሚለያይ ሳይሆን የሚያሰባስብ ነው። የኦሮሞነት ፖለቲካ የጉዲፈቻና የሞጋሳ ፖለቲካ ነው።

የኦሮሞ ማህበረሰብ ከምንም በላይ ፣ በባሕሉ የሚመቸውና የሚቀበለው የአንድነትን እና የፍቅርን ፖለቲክ ነው። “እገሌ ከዚህ ዘር ስለሆነ፣ ወይንም ይሄ ቋንቋ ስለሚናገር ከአገራችን ይዉጣ። ይሄ ምድር የኦሮሞ ብቻ ነው ….ወዘተረፈ” የሚባለው አክራሪዎችና ካድሬዎች የሚረጩት እንጂ, ከሕዝቡ የሚመጣ አይደለም። የኦሮሞ ማህበረሰብ በባህሉ ሌላውን የሚቀበል፣ እንደራሱ አድርጎ የሚያኖርና የሚያሳድግ ነው። ለዚህም ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣው።

አፋን ኦሮሞ የማናውቅ ካለን፣ እንማር። አማርኛ የማናውቅ ካለን፣ አማርኛ እንማር፡ ብዙ ቋንቋ ማውቅ በረክት ነው። ሌላ ቋንቋ መማር አያሳንሰንም። እንደ ወንድማማቾች፣ ለመግባባት፣ ለመነጋገር፣ አብረን አገራችንን ለማሳደግ ቋንቋ አለማወቃችን እንቃፋት ሊሆንብን አይገባም።

ምንጭ - ሳተናው ድረ-ገፅ http://satenaw.com/amharic/?p=2525 

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።