=======
አለማወቅ ኃጢአት አይደለም።አለማወቅ በማወቅ ስለሚስተካከል ችግር የለውም።ባለማወቅ ውስጥ ተጀቡኖ ወደ ድንቁርና መምዘግዘግ ነው ጥፋት የሚሆነው።የኢትዮጵያ የቀደመ ዘመን ስኬቷ የሚያውቋት ምሑራን (በየዘመኑ የነበሩት ጠቢቦቿ) ስለነበሯት ነው።ምሑር፣አዋቂ፣ጥበበኛ የሚሉት ቃላት ከሆነ የአውሮፓና የአሜሪካ ዩንቨርስቲ መመረቅ ብቻ ባልሆነበት ዘመን፣የኢትዮጵያ ነገስታቷ፣የእምነት መሪዎቿ እና ጸሓፊዎቿ ሁሉ ከልጅነታቸው ታሽተው፣ተሞርደው እና ስለው የሚወጡባቸው የዕውቀት ማዕድ የሚቋደሱባቸው ሁነኛ ማዕከላት ነበሯቸው። አውሮፓ እና አሜሪካ ደርሶ የጥናት ጹሑፍ አስረክቦ ከእዛ በኋላ አንድም መጽሓፍ ሳያነቡ አልያም በተማሩት ትምሕርት የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ምንም ሳይሞክሩ እየተቹ የሚኖርበት ዘመን አልነበረም። ኢትዮጵያ በቀደመው ዘመኗ ለነገስታትነት የሚታሰብ ወይንም የንጉሱ ልጅ በመሆኑ ንግስናው ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል ተብሎ የሚታሰብ ልጅ በልጅነቱ ለመንፈሳዊ፣አስተዳደራዊ እና የሕግ ትምህርት ወደ ገዳማት ይላካል።ከመንፈሳዊው ጋር አቅሙ ሲጠነክር ወታደራዊ ትምህርትም አብሮ እንዲካን ከፈረስ ግልብያ እስከ ተኩስ፣አደን እና ትግል ሁሉ ይሰለጥናል። ከስር ታሽቶ፣ተሞርዶ እና ተስሎ እንጂ አሁንም በሁለት እና ሦስት ወረቀቶች ምሑር ተብሎ ጎልምሶ፣ምሑር ተብሎ እንዲያረጅ አይፈቀድለትም። እነኝህን መንፈሳዊ እና የጦር ትምሕርቶች ተምሮም በእየጊዜው ያለው ችሎታ በራሱ በህዝቡም በመኳንንቱም ከሚናገረው፣ከሚፈርደው ፍርድ፣ከሚወስነው ውሳኔ እና ከጦር ሜዳ ውሎዎቹ ሁሉ አንጻር ይለካል እንጂ አበቃ ደቀቀ የሚባል ነገር የለም።
ከ20ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያ ሩብ ጀምሮ ግን ምሑር ማለት እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ የተናገረ፣ከአውሮፓ እና አሜሪካ ዩንቨርስቲ የወጣ፣አለባበሱ ከአገሩ ባህል ይልቅ የሸሚዝ ኮሌታው ላይ ክራቫት ያንጠለጠለ ሆኗል። ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበሯትን አገር በቀል ዕውቀት የያዙ እየተገፉ የውጭውን የተካኑ ብቻ ቦታ አገኙ። በደራሲ ከበደ ሚካኤል ዘመን የነበሩ የውጭ አገር መምሕራን ይህንን አስተሳሰብ እንዴት እንደሚያቀላጥፉት አንድ የዘመኑ የዐይን ምስክር ሲናገሩ። ዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤት የነበሩ የውጭ አገር መምህራን በጊዜው ከገጠር የመጣ እኛ ጋሼ የምንለው ሰው በአገሩ ሸማኔ የተሰራ ኩታ አድርጎ በመግባቱ እንዲሳቅበት አድርገው መሬት እንዲቀመጥ ሲያደርጉ እኛ ጉርድ ሸሚዝ በክራቫት ያደረግነው ወንበር ላይ እንድንቀመጥ ያደርጉን ነበር ማለታቸውን የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያስታውሳል።
ይህ ሥር የያዘ የራስን ዝቅ አድርጎ የማሳየት ቅኝ ገዢያዊ አስተሳሰብ እየቆየ ውጭ ተምረው የመጡ ገንዘባቸው እያደረጉት መጡ።በተለይ በሚገባ በማያውቋት፣በአጥሯ ስር ደጋግመው በማለፋቸው የሚያውቋት የሚመስላቸው ወይንም አባቴ ቄስ ነበር፣እኛ ሰፈር ቤተክርስቲያን ነበር ወዘተ በሚሉ አነጋገሮች የሚታወቁ ''ምሑራን'' ነን ባዮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሥራ ባሕል አስተምሮ፣መርህ እና መመርያ ሳይረዱ ለራሳቸውም ሳያውቁት በከባድ የጭፍን ጥላቻ ውስጥ እራሳቸውን የሚያሰቃዩ እና ቤተክርስቲያኒቱን በሥራ ባሕል አስተምሮ ሊተቹ ሲሞክሩ ያስገርማሉ።
መጀመርያ በቤተክርስቲያኒቱ አጥር ስር ደጋግሞ በማለፍ ወይንም አባቴ ቄስ ነበር ወዘተ በማለት አንድም ቀን ሌላው ቢቀር እንደ "ምሑር" ቤተክርስቲያኒቱን ሳያጠኑ የቡና ላይ ትንታኔያቸው ባዶ ጩኸት ሆኖ እራሳቸውን ያደነቁሩበታል:: ልማት ከማኅበራዊ መስተጋብሩ ጋር ያለው ቁርኝት አይገለጥላቸውም::የቤተክርስቲያን ችግር አስተምሯዊ፣ስርዓታዊ ወይንም የሥራ ባሕል ያልተከለች መሆን ሳይሆን ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የተቀያየሩ መንግስታት የሙስና እና ሃይማኖት የለሽ ወይንም ቀሳጭ እንቅስቃሴ የቤተክርስቲያን አስተዳደር እንዲበላሽ በር መክፈቱ ብቻ እንደሆነ ገና አልበራላቸውም። የአስተዳደር መበላሸት የመሰረተ ዕምነት እና የቤተክርቲያኒቱ ዋና አንኳር መርህ ችግር አይደለም።
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዋና የሥራ መርህ እግዚአብሔር ለአዳም ያዘዘው 'ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ' የሚለው ትዕዛዝ ነው።ቤተክርስቲያን መነኮሳቷ ወደገዳም ሲመጡ እንዲያነቡት እና እንደ አንድ ተሞክሮ ተምረውት እንዲገቡት የምታደርጋቸው መጻሕፍት (መጽሓፈ መነኮሳት) ሥራ አምላካዊ ትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት መራቅያ አንዱ መንገድ መሆኑን አበክሮ ያስተምራል፣ያስጠነቅቃል፣በብዙ የቀደሙ የመነኮሳት ተሞክሮዎች ጭምር ያስተምራል።ቤተክርስቲያኒቱ በሰንበት ዕለታት ህዝቡን ከረፋዱ ሦስት ሰዓት (በአገር ቤት ያለው የቤተክርስቲያን አገልግሎት) ሁሉን አጠናቃ ወደ ቤቱ ታሰናብተዋለች።ቀኑን እንዴት እንደሚውል መወሰን የህዝቡ ፈንታ ነው።
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በህዝቡ የሥራ ባሕል ላይ አዎንታዊ አስተምሮ እንዳላት ይህም በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሶሾሎጂ ዲፓርትመንት መምሕር እና ተመራማሪ ዶ/ር የራስ ወርቅ የጻፏቸውን ጥናቶች መመልከት፣በዓላት ላይ መምህር ዲ/ን ብርሓኑ አድማሴ የጻፈው ጥናታዊ መጽሓፍ ማንበበ በትንሹ ዓይን ይገልጣል። ከእዚህ ባለፈ ከቡና ላይ ወሬ ይልቅ እንደምሑር ተነስቶ ማጥናት ነው።የልማት ጥናት በድፍን የቡና ላይ ወሬ አያምንም።መሬት ወርዶ ማጥናት ለእዚህም በቂ አቅም መኖር ይጠይቃል። ከጥናታዊ አካሄድ ውጭ በግምት ያውም አንድ መጽሓፏን እንደ ምሑር መባል ሳይመረምሩ በአጥሯ ስር ስላለፉ ወይንም አባቴ እዚህ ቤተክርቲያን አገልጋይ ሆኖ ቤተክርስቲያኒቱን እቤት ውስጥ በሚወራ ወሬ አውቃታለሁ የሚሉ የትንተና መነሻዎች ትዝብት ላይ ይጥላሉ።ላሊበላ በወሬ አልተገነባም፣የኢትዮጵያ በሺህ የሚቆጠሩ የጥልቅ ዕውቀት ምንጭ የሆኑትና አሁን በኢትዮጵያ ገዳማትም፣በውጭ አገር ሙዚየሞችም የሚገኙ የሕግ፣የፍልስፍና፣የስነከዋክብት፣የህክምና እና የሃይማኖት ግዙፍ ጥራዝ መጻሕፍት ቡና በማንቃረር የተጻፉ አይደሉም።የቤተክርስቲያኒቱ የሥራ ባሕል መሰረት ያደርጉ አባቶች ጊዜያቸውን ሥራ ላይ አውለው የሰሯቸው የሥራ ውጤቶች ናቸው። በማናውቀው፣ባላጠናነው እና በአግባቡ ባልመረመርነው ጉዳይ አውሮፓ እና አሜሪካ ሰርተፍኬት አግኝተን ስለመጣን ወደ ጥልቅ የድንቁርና አዘቅት ውስጥ በግምት መግባት የለብንም። ገባ ብሎ መመርመር፣ማንበብ እና መመልከት ይቅደም።አባቶቻችን ''ከመጠምጠም መማር ይቅደም '' የሚሉት ለእዚህ ነው።
ከእዚህ በታች በአንድ ገዳም ውስጥ ያለውን የሥራ ባሕል የሚያሳይ ልዩ ሪፖርት ይመልከቱ።