=============
ጉዳያችን ልዩ ሪፖርት
=============
=============
ኢትዮጵያና ግሪክ
ኢትዮጵያና ግሪክ ወደኋላ ከአምስት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላቸው ጥንታውያን አገሮች ውስጥ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ውስጥ ናቸው።800 ዓዓ አካባቢ የኖረው የግሪክ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያን በጽሑፉ ከትቧታል። በግሪክ አይቲዮፕያ የጠይም ሰው መገለጫ ነው። ኢትዮጵያ እና ግሪክ የጥንቱ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይቦረቦር ክፍለ ዘመናትን በኩራት የተሻገረ ባሕል ባለቤቶች ናቸው።ከእዚህ በዘለለ ወደ የጥንቱ የዓለም ታሪክ ስንሄድ ኢትዮጵያ በቀይባህር ላይ ባላት የበላይነት፣ግሪክ ደግሞ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ባላት ስልታዊ ወሳኝ አቀማመጥ አንጻር ከንግድ ግንኙነት በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ጉልህ ነበር።
በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ እና ግሪክ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረበት ነበር።ንጉሱ በ1947 ዓም ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ሲገቡ የአቴንስ ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥር በአደባባይ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጸረ ፋሽሽት ትግል አኩሪ ገድል የፈጸመው የግሪክ ህዝብ በአውሮፓ ደርሶ እንደነበረው ጦርነቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1945 ዓም እንደተጠናቀቀ ረሃብ ገብቶ ነበር። በእዚህ ጊዜ ታድያ አፄ ኃይለሥላሴ አቴንስ ከተማ ተገኝተው ቁጥሩ ብዙ የሆነ የቁም ከብት ገዝተው ህዝቡን በአደባባይ ስጋ አብልተዋል። ይህ ሥጋ ህዝቡን ያበሉበት ቦታ አሁን ድረስ አቢሲኒያ አደባባይ ይባላል።የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም ቦታው ድረስ ሄዶ በአደባባዩ ዙርያ ያሉ ባለሱቆችን ለምን የአቢሲንያ አደባባይ ተባለ ብሎ ሲጠይቃቸው ይህንኑ ንጉሱ የሰሩት የቸርነት ሥራ አስታውሰው ነግረውታል።
ግሪኮች በቀድማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጊዜ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ በመኖር በንግድ፣በመምህርነት፣በግንባታ እና በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።በምሕንድስናው ዘርፍ መሃል አዲስ አበባ የሚገኘው የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ዲዛይን እስከ የንግድ ባንክ ህንጻዎች ግሪካውያን አሻራቸውን አስቀምጠዋል። እዚህ ላይ የሱፐርማርኬት ባለቤቱ እና ከቤቴ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተለይቶኝ አያውቅም ያሉት አቶ ባምቢስን ማስታወስ ይቻላል።ይህ ሁሉ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ግን ኢትዮጵያውያን እና ግሪካውያን ግንኙነት ላይ በጣም የጠለቀ ግንኙነት አይታይም።አዳዲሶቹ የሁለቱ አገሮች ትውልዶች በሚገባ መተዋወቅ እንዲችሉ የባሕል ልውውጥ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ማሳደግ አለባቸው። እዚህ ላይ በኢትዮጵያ ይኖሮ የነበሩ ግሪካውያን የመሰረቱት የግሪክ ኢትዮጵያውያን ማኅበርን መጥቀስ ይቻላል። ማኅበሩ በየጊዜው የኢትዮጵያውያንን ባሕል እና ታሪክ በማስተዋወቅ የተጋ ማኅበር ሲሆን በአቴንስ የሚገኘውን የአቢሲንያ አደባባይ ሕጋዊ ይዞታ እንዲጠበቅ እና የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴን ሃውልት ለማሳነጽ እንቅስቃሴ ላይ ያለ ማኅበር ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግሪክ ሕጋዊ ዕውቅና እንዴት አገኘች?
በአቴንስ የምትገኘው የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በተለይ ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ የሰነድ ተቀባይት ችግሯን መፍትሔ ለመስጠት ሰበካ ጉባኤው በላከው ደብዳቤ በብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የተሰጣት ሲሆን ይኽውም የሶማቲዎ (ማኅበር) የግብር መለያ ቁጥር (Tax No) 997874156 “AΙΘΙΟΠΙΚΗΣΟΡΘΟΔΟΞΗΣ ΕΚΚΛΗΣΙΑΣ ΤΗΣ ΑΘΗΝΑΣ” በሚል ንብረት ለማፍራት፣ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ፣ በግብርና ተያያዥ ክፍያዎች አፈጻጸም ዙሪያ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ቤተክርስቲያኒቱ እውቅና አግኝታለች። ይህንን እውቅና የዛሬ አስር ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስት ሰዎች አሳሳች ደብዳቤ ቀድመው በመጡት አባ ወልደሚካዔል ጣውዬ ላይ ተደርበው በመጡት አባ ገብረየሱስ ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱ ፍቃድ በክስ ምክንያት ለማወዛገብ ተሞክሮ ነበር።
ይህም ሆኖ ግን በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስም የተመዘገበው እና በሶማትዮ ማኅበርነት የሚታወቀው አደረጃጀች ዛሬም በግሪክ መንግስት እውቅና ያለው ብቻ ሳይሆን በመተዳደርያ ደንቡም ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ ትምሕርቶችን ከግሪክ አልፎ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ማስፋፋት እንደሚችል በጸደቀለት ደንብ ተገልጿል። ከእዚህ በተለየ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደንብ እና ስርዓት መሰረት ያለው አደረጃጀች በውስጥ ደንቡ መሰረት የሚነሱ ማናቸውም የሃይማኖት ክርክሮች እና ጥያቄዎች የሚፈታው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና መሰረት ብቻ እና ብቻ እንደሆነ ደንቡ ያዛል።ይህም በቤተርክስቲያኒቱ ላይ ለሚነሱ የሃይማኖት ቅሰጣዎች ሁሉ ዕድል የማይሰጥ ሆኖ የተደራጀ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው ነው።
በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ዛሬም ከምንጊዜውም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን የአፈጻጸም ጥብቅ ክትትል ትፈልጋለች።
ቅዱስ ሲኖዶስ በመጋቢት/2017 ዓም አቡነ ጢሞቲዎስ እና አቡነ ጴጥሮስ ያሉበት ልዩ ልዑክ ግሪክ ድረስ ልኮ የግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጉዳይ ለማየት ተሞክሯል። ከብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት የአቴንስ ጉዞ ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ክሕነታቸው ተይዞ የነበረው የአባ ወልደሚካኤልን ስልጣነ ክሕነት የመለሰ ሲሆን ለአቴንስ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በሕገ ቤተክርስቲያን መሰረት አዲስ አስተዳዳሪ ሊቀስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬን መድቦ፣በአሁኑ ጊዜ ምእመናን የአዲሱን አስተዳዳሪ መምጣት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።ይህ በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱ የምትገኝበት ተጨባጭ እውነት ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በኋላ በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዙርያ የሚከተሉት ሁኔታዎች ተከስተዋል እነርሱም ፡
- አቴንስ ፖሊጎኖ የምትገኘው ለአራት አስርተ ዓመታት የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በአጽራረ ቤተክርስቲያን በሆኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ ፊሽካ ከመንፋት እስከ ደም ማፍሰስ ወንጀል በፈጸሙ እና አሁንም ጉዳያቸው በሕግ የተያዘ ግልሰቦች እና እራሱን ኪኖቲታ በማለት በሚጠራ የዕድር አደረጃጀት በፈጠሩት ሁከት አማካይነት ቤተክርስቲያኒቱ በግሪክ መንግስት እንድትዘጋ ሆነ።
- ቤተክርስቲያኒቱ ከተዘጋጅ ወዲህ በአቴንስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚያስቀድሱበት ቦታ በተለይ በአቴንስ ከተማ ውስጥ አለመኖሩና ቤተክርስቲያኒቱን በግሪክ በሕጋዊነት እንዲያገለግሉ የተመደቡት ሊቀስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ ወደ ግሪክ በቶሎ አለመምጣት መጪው የፍልሰታ የፆም ወቅት ሳይቀር ምእመናን ተቸግረው እንደሚያሳልፉ ቅዱስ ሲኖዶስም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
- ይህ በእንዲህ እያለ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ኤልያስ ኪኖቲታን ማዕከል ያደረገ በሆቴል ያደረጉት ''ጉባዔ'' ምእመናንን በሚገባ ማሰባሰብ ያልቻለ ብቻ ሳይሆን በቅዱስ ሲኖዶስም ምንም እውቅናም ሆነ የጉባዔው ምንነትም ሳይታወቅ ሳምንታት ነጎዱ።
- ቤተክርስቲያኒቱ በስሟ የተገዛውን ከስድስት ሺህ ካሬ በላይ ስፋት ያለው በአውሮፓ የመጀመርያዋ የሆነውን ገዳም በተመለከተ ምን ደረሰ፣ይህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ንብረት ነው ብሎ የሚከታተለው ሊቀጳጳስም ሆነ ሀገረስብከት ሳይኖረው ስምንት ዓመታትን ያሳለፈበት እውነታ ዛሬም መሬት ላይ ያለ ዕውነታ ነው።
- አቡነ ኤልያስ በግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግሪክ ያላቸው የኃላፊነት ደረጃ በግልጽ እንዲነገረው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የግሪክ ኤምባሲ ከቤተክሕነት ጋር ተገናኝቶ እንዲገለጽለት ጠየቀ።
- በእዚህ መሰረት ኤምባሲው ወደ ቤተክሕነት ልዑክ ልኮ የአቡነ ኤልያስ የኃላፊነት መጠን በቤተክርስቲያን ሲጋበዙ መባረክ ብቻ መሆኑ ተገለጸለት።
- በግሪክ ለምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሚመደበው በቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑ ለግሪክ የኃይማኖት ሚኒስቴር በድጋሚ ተገለጸ።
አሁን ቅዱስ ሲኖዶስ በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንጻር ምን ማድረግ አለበት?
ቅዱስ ሲኖዶስ አሁንም በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንጻር የሚከተሉትን አፋጣኝ ተግባራት ቢያከናውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን በግሪክ እንድታብብ ወሳኝነት ይኖረዋል። እነርሱም፡
- የሊቀስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ የግሪክ ጉዞ በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ክትትል በሚከተሉት ሁለት መንገዶች መከታተል እና ማስፈጸም ይችላል።
- በአዲስ አበባ የሚገኘው የግሪክ አምባሳደርን ቅዱስ ፓትርያሪካችን ጠርተው ቤተክርስቲያኒቱ የመደበቻቸው አባት ወደ ግሪክ ተጉዘው በፍጥነት አገልግሎት እንዲጀምሩ እንዲያደርጉ ውይይት ማድረግ እና ለግሪክ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ደብዳቤ በመጻፍ ቤተክርስቲያኒቱ ቅሬታዋን ማቅረብ አለባት።
- የግሪክ ሀገረ ስብከት አንዱ የገጠማት ችግር ሀገረስብከቱን አስተባብሮ የቤተክርስቲያንን ችግር ከመፍታት ይልቅ በግል እና የሀገረስብከቱን መዋቅራዊ አቅም ባገለለ መልክ ከግለሰቦች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ብቻ ለመምራት የሚሞከረው የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አካሄድ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ሀገሩን እና ዘመኑን የዋጀ የሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ምደባ አሁንም በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ የምትጠብቀው አሁንም አንገብጋቢው ጉዳይ እና ቅዱስ ሲኖዶስም ከእዚህ አንጻር የጉዳዩን አንገብጋቢነት ለመረዳት መዘግየቱ አሁንም ድረስ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ የቤተክርስቲያኒቱን አባቶችም ሆነ ምእመናንን ግራ ያጋባ ጉዳይ ነው።
- በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ምደባ ጉዳይ ከቤተክርስቲያን ጉዳይነት በዘለለም የሀገር ገጽታ ከእዚያም ሲያልፍ የኢትዮጵያና የግሪክ የረጅም ጊዜ ትስስር ነጸብራቅም ስለሆነ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ዴስክ እና በጣልያን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በጥብቅ ተከታትሎ ሊያስፈጽመው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ባጠቃላይ በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጉዳይ በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ በመላው ዓለም ከሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮች በቀዳሚነት እና አንገብጋቢነት የሚገኝ መሆኑን ተመልክቶ ጥብቅ ክትትል አለማድረጉ ቤተክርስቲያንን በእጅጉ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት የሚያስጠይቅ የጊዜያችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ደግመን አሁንም እንደልጅነት ለብፁዓን አባቶቻችን ለማሳሰብ እንወዳለን።
=======================///=============