Thursday, April 30, 2026

በአቴንስ፣ግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ላለፉት 40 ዓመታት በላይ ስትጠቀምበት የነበረውን ፖሊጎኖ የሚገኘው ቤተክርስቲያን በፖሊስ ታሸገ።የቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ ምላሽ እየተጠበቀ ነው።



የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን የታሸገችበት የጉግል የእንግሊዝኛ ትርጉም እና የግሪክኛ ዋናው ኮፒ።

በግሪክ አቴንስ የምትገኘው እና ወደ ግማሽ ክ/ዘመን አገልግሎት ስትሰጥ የነበረችው እና በአቴንስ ፖሊጎኖ የምትገኘው የኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያንን ሐሙስ ሚያዝያ 22፣2018 ዓም በግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር መታዘዛቸውን በገለጹ የአቴንስ ኪፕሴሊ ወረዳ ፖሊሶች መታሸጉ ታውቋል።

መንደርደርያ

በአቴንስ የምትገኘው የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በተለይ ከ1994 ዓ/ም ጀምሮ  የሰነድ ተቀባይት ችግሯን መፍትሔ ለመስጠት ሰበካ ጉባኤው በላከው ደብዳቤ በብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የተሰጣት ሲሆን ይኽውም የሶማቲዎ (ማኅበር) የግብር መለያ ቁጥር (Tax No) 997874156  “AΙΘΙΟΠΙΚΗΣΟΡΘΟΔΟΞΗΣ ΕΚΚΛΗΣΙΑΣ ΤΗΣ ΑΘΗΝΑΣ” በሚል ንብረት ለማፍራት፣ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ፣ በግብርና ተያያዥ ክፍያዎች አፈጻጸም ዙሪያ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ቤተክርስቲያኒቱ እውቅና አግኝታለች። ይህንን እውቅና የዛሬ አስር ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስት ሰዎች አሳሳች ደብዳቤ ቀድመው በመጡት አባ ወልደሚካዔል ጣውዬ ላይ ተደርበው በመጡት አባ ገብረየሱስ ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱ ፍቃድ በክስ ምክንያት ለማወዛገብ ተሞክሮ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስም የተመዘገበው እና በሶማትዮ ማኅበርነት የሚታወቀው አደረጃጀች ዛሬም በግሪክ መንግስት እውቅና ያለው ብቻ ሳይሆን በመተዳደርያ ደንቡም ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ ትምሕርቶችን ከግሪክ አልፎ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ማስፋፋት እንደሚችል በጸደቀለት ደንብ ተገልጿል። ከእዚህ በተለየ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደንብ እና ስርዓት መሰረት ያለው አደረጃጀች በውስጥ ደንቡ መሰረት የሚነሱ ማናቸውም የሃይማኖት ክርክሮች እና ጥያቄዎች የሚፈታው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና መሰረት ብቻ እና ብቻ እንደሆነ ደንቡ ያዛል።ይህም በቤተርክስቲያኒቱ ላይ ለሚነሱ የሃይማኖት ቅሰጣዎች ሁሉ ዕድል የማይሰጥ ሆኖ የተደራጀ ጠንካራ አደረጃጀት ያለው ነው።

የአቴንስ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ለምን ታሸገች?

የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን የፌስቡክ ገጽ በዛሬው ዕለት በግሪክ ፖሊስ ስለታሸገችው የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስመልክቶ በለጠፈው ጽሑፍ ላይ እንደሚከተለው ገልጾታል፡ 

''በቅድምያ የከበረ መንፈሳዊ ሰላምታ እያቀረብን ላለፉት ከአራት አስርተ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውያን ሲገለገሉበት የነበረው በአቴንስ ፖሊጎኖ የምትገኘው የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ስትገለገልበት የነበረው ቤተክርስቲያን በግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር መታዘዙን በመግለጽ ፖሊስ ዛሬ ሚያዝያ 22፣2018 ዓም ማሸጉ ታውቋል። ጉዳዩን በቤተክርስቲያኒቱ ጠበቃ በኩል የፖሊስ ጣቢያው የተጠየቀ ሲሆን ፖሊስ ከግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር መታዘዙን እንደገለጠለት ለማወቅ ተችሏል።

ቤተክርስቲያኒቱ ከየካቲት 16/2018 ዓም ጀምሮ ቅዳሴ እንዳይቀደስ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ፊሽካ በማጮህ፣ተአምረ ማርያም እንዳይነበብ፣ኪዳን እንዳይደርስ የመረበሽ ተግባር ሲፈጸም የነበረ ሲሆን፣ቅዱስ ሲኖዶስ በየትኛውም የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዳይገቡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቀሲስ አየለ እና በሀገረስብከቱ ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልያስ ድጋፍ የሚደረግላቸው በቤተክርስቲያናችን አገልግሎት ላይ ተደጋጋሚ የመረበሽ ስራ የሰሩት ግለሰቦች የአካባቢውን ማኅበረሰብ እንዲረበሽ ማድረጋቸውና የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤልያስ ከሃይማኖት ሚኒስቴር ጋር የሚያደርጉት ምእመናንን የሚከስ እና የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ከግሪክ ለመንቀል ከሚሰሩ ግለሰቦች ጋር ያደረጉት ያልተገባ ግንኙነት እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ የተመደቡት አባት ሊቀስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ በቶሎ እንዲዘገዩ የተደረጉ አሻጥሮች ሁሉ ተደምሮ ቤተክርስቲያኒቱ እንድትታሸግ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ቤተክርስቲያናችን በከፍተኛ ሃዘን ትገነዘባለች።

በመሆኑም ምእመናን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተርክስቲያን ላይ የሆነው ሁሉ አሳዛኝ ቢሆንም፣ ወደ ቤተክርስቲያን ላይ የተወረወረውን ድንጋይ መልሰን ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ግንብ የምንሰራበት እንጂ የምንተክዝበት ስላልሆነ እና ችግሮችን ወደ መልካም እድል በመጠቀም ምእመናን ከእዚህ በፊት ከነበራችሁ ትጋት በበለጠ ለቤተክርስቲያናችን  ማበብ በአዲስ መንፈስ የምንነሳበት መሆኑን አውቀን በእግዚአብሔር ቸርነት፣በእመቤታችን ኪዳነምሕረት አማላጅነት ለቤተክርስቲያናችን በአዲስ መንፈስ እና በጸና ልቦና እንድንነሳ ቅድስት ቤተክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች።''

ከላይ ከቤተክርስቲያኒቱ ፌስ ቡክ ገጽ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ለቤተክርስቲያኒቱ መዘጋት ቀዳሚ ሚናውን የሚጫወቱት ጉዳያችን ከእዚህ በፊት ''የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን የሰሞኑ ከራሞት ልዩ ሪፖርታዥ'' ላይ እንደተብራራው የአማሳኙ ቡድን ከሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ባገኘው አረንጓዴ መብራት አማካይነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንድትታሸግ ሆኗል።

የምእመናኑን እና የቤተክርስቲያኒቱን ችግር የሚፈታ የሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያለህ!

በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ላይ የደረሰው እንግልት በቃላት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ሀገረስብከቱ በቂ ክትትል አድርጎ ችግሩን የሚፈታለት ሊቀ ጳጳስ አላገኘም። እስካሁን ከተመደቡለት ሊቀጳጳሳት ውስጥ የመፍትሄ ሃሳብ በማመንጨት በቆዩበት አጭር ጊዜ የሞከሩት የጣልያን እና ፈረንሳይ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሲሆኑ። አሁን መቀመጫቸውን በስዊድን ያደረጉት እና የግሪክም ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ ኤልያስ ላለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ዛሬ የታሸገችውን የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን የጎበኙት ባለፈው ዓመት አስታራቂ አባቶች ወደ አቴንስ ሲመጡ እና በቅርቡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ትዕዛዝ እና ደብዳቤ ምክንያት በማድረግ ወደ አቴንስ ካደረጉት ያልተሳካ ጉዞ ውጪ ቤተክርስቲያኒቱን ከአስር ዓመታት በላይ ቀድሰውባት አያውቁም።

ጉዳያችን ከወር በፊት ይህንኑ አስመልክታ በጻፈችው ላይ እንዲህ ብላ ነበር፡

"እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።" (የሐዋርያት ሥራ 20:28) የሚለው ቃል ዛሬ በግሪክ በሚኖሩ ምእመናን ጆሮ ላይ የሚጮህ ድምፅ ነው። በግሪክ ምእመናን ለዓመታት አልቅሰዋል፣ገንዘባቸውን አውጥተው የገዙትን ገዳም ገዳም አድርጎ የሚባርክላቸው አባት አጥተው ተንከራተዋል፣ ለቤተክርስቲያን ያወጡት ገንዘብ በሌቦች ተወስዶ ከሌባ ጋር ሲተናነቁ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በተጻፈ ደብዳቤ ለሰረቁት የእውቅና ደብዳቤ እየተሰጠ ባለፈው ዓመት ምእመኑን ሲያገለግሉ የኖሩት ካሕናት ስልጣነ ክሕነታቸው ''ከምእመን ያለፈ ስልጣን የሌለው ግለሰብ በጻፈልኝ ደብዳቤ መሰረት'' በሚል ለመያዝ ማስፈራርያ ተጽፏል። ቤተክርስቲያኒቱ ከግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በድብቅ እና የአማሹ ቡድን በሚሰሩት ደባ የታጀለ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱ ክብር በግሪክ ቢሮዎች ውስጥ ዝቅ ያለ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ሌላው ቀርቶ አሁን በፖሊጎኖ የምትገኘው የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ከባለቤቷ የግሪክ ቤተክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት ቤተክርስቲያኒቱን ለአማሹ ቡድን ለመስጠት በሚደረገው አድሏዊ ሕገወጥ ግንኙነት ምክንያት የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ግንኙነት በመደረጉ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲፈጠር ሆኗል።በእዚህም ሳብያ የግሪክ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪም በጉዳዩ ተማረው ቅሬታ አቅርበዋል።''

መፍትሔው 

በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ችግር ለመፍታት ከቡድናዊ ስሜት የራቀ፣ለሌቦች እና ለዘራፊዎች ምንም ዓይነት መለሳለስ የማያሳይ፣ምእመናንን በፍቅር እና በትኅትና የሚያይ እና ከፍተኛ የቤተክርስቲያን አስተዳደር አቅምና ልምድ ያለው ሊቀጳጳስ በፍጥነት ለግሪክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊመድብ ይገባል። አሁን ያሉት ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልያስ ከ90 ዓመታት በላይ የሆኑ እና በቤተክርስቲያን ዝርፍያ በሚታወቁ አማሾች ጋር በመወገናቸው የቤተክርስቲያኒቱን ችግር የማይፈቱበት ደረጃ ደርሰዋል። ላለፉት አምስት ዓመታት ያልፈቱት ችግር ከአሁን በኋላ ይፈቱታል ተብሎ አይታሰብም። አቡነ ኤልያስ የቤተክርስቲያን አጥፊዎች ጋር የገጠሙበት እና ሕጋዊ የሚመስል ሽፋን ለመስጠት አንዴ ''የቅዱስ ሲኖዶስ አስፈጻሚ ኮሚቴ'' ሌላ ጊዜ ሦስተኛ ወገን ቅሬታ ያላቸው እያሉ የሄዱበት ሂደት ሁሉ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ክብር በግሪክ ዝቅ ያደረገ ብቻ ሳይሆን የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሁሉ የሚያውክ ተግባር ከግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴር ቢሮ ጋር የነበራቸው የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ ያልጠበቀ የአስተዳዳሪ ምደባ ሁሉ የታየ እጅግ አሳዛኝ ጉዳይ ነው።

በመሆኑም ለግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ችግር ለመፍታት ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሄ ሰጪ ሊቀጳጳስ መመደብ እና በቅዱስ ሲኖዶስ የተመደቡት ሊቀስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ ወደ ግሪክ እንዲመጡ በቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ የሚሉት ቀዳሚ ናቸው።ይህ ውሳኔ የርክበ ካሕናት ጉባዔ በፊት በአስቸኳይ እና በጊዜያዊነት መወሰን የቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ ተግባር መሆን አለበት። ምእመኑም የጠየቀው ይሄው ነው።
=============////========





No comments:

በአቴንስ፣ግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ላለፉት 40 ዓመታት በላይ ስትጠቀምበት የነበረውን ፖሊጎኖ የሚገኘው ቤተክርስቲያን በፖሊስ ታሸገ።የቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ ምላሽ እየተጠበቀ ነው።

የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን የታሸገችበት የጉግል የእንግሊዝኛ ትርጉም እና የግሪክኛ ዋናው ኮፒ። በግሪክ አቴንስ የምትገኘው እና ወደ ግማሽ ክ/ዘመን አገልግሎት ስትሰጥ የነበረችው እና በአቴንስ ፖሊጎኖ የምትገኘው የ...