በዚህ አጭር ዘገባ ውስጥ የሚከተሉትን ያገኛሉ።
ንጉስ ሃራልድ አምስተኛ የኖርዌይ ንጉስ- ስለ ንጉስ ሃራልድ በጥቂቱ
- የንጉስ ሃራልድ አባት ንጉስ ኦላቭ እና ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የት ተዋወቁ?
=====================
ጉዳያችን ልዩ ሪፖርት
Gudayachn Special Report
=====================
የኖርዌይ ንጉሥ ሃራልድ አምስተኛ ባለፈው ሳምንት ልዩ የደም ሕመም ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ በ89 ዓመታቸው ዛሬ ማረፋቸው ታውቋል።በኦስሎ የሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዛሬ ዓርብ ነሐሴ 22፣2018 ዓም ( ነሐሴ 28/2026 ዓም እኤአ) በኦስሎ ዩንቨርስቲ ስር በሚገኘው ብሔራዊ ሆስፒታል (ሪስክ ሆስፒታል) የኖርዌይን ንጉስ ሃራልድ 5ኛ ማረፍ ከማለዳው በ06:35 የኦስሎ ሰዓት አቆጣጠር ከተገለጸ በኋላ በቤተ መንግሥቱ ጣሪያ ላይ ያለው የንጉሣዊ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ሆኗል። የንጉሱ የቀብር ስነ ስርዓት እስኪከናወን ድረስም በኖርዌይ የሐዘን ቀን የታወጀ ሲሆን፣የንጉሱን ማረፍ የሰሙት ኖርዌጃውያን ከማለዳ ጀምሮ ወደ ቤተ መንግስት በመጉረፍ አበባና የኖርዌይን ሰንደቅ ዓላማ በማስቀመጥ ላይ ይገኛሉ።
ሃራልድ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በኖርዌይ የተወለዱ የመጀመሪያው ንጉሥ ሲሆኑ። ልጃቸው ሃኮን በ53 ዓመታቸው ንግስናውን መተካታቸውን ከኖርዌይ የመጣው ዘገባ ያመለክታል።
ንጉስ ሄራልድ 5ኛ በስልጣን ዘመናቸው የኖርዌይ ንጉሣዊ አገዛዝ ስለ ንጉሣዊው ቤተሰብ የፋይናንስና የጤና ጉዳዮች የበለጠ እኩልነትና ግልጽነት እንዲያሳይ ያደረጉ ንጉስ ናቸው ሲሉ የኖርዌይ ታሪክ ምሁርና የቲቪ2 ንጉሣዊ ዘጋቢ ኦሌ-ጆርገን ሹልስሩድ-ሃንሰን ይናገራሉ።
==========
ንጉስ ሃራልድ የተወለዱት የካቲት 21 ቀን 1937 ዓም እኤአ በኦስሎ አቅራቢያ በሚገኘው የስካጉም እስቴት ውስጥ ነው። አምባገነኑ አዶልፍ ሂትለር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ የናዚ ጀርመን ኖርዌይን ወረራ ባዘዘበት ጊዜ የሦስት ዓመቱ ልጅ ነበሩ።
የሃራልድ እናት ከልጆቻቸው ጋር ወደ ስዊድን ድንበር አቋርጠው ሸሽታ በፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት ግብዣ ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል።
ልዑል ሃራልድ በጦርነቱ መጨረሻ ከቤተሰባቸው ጋር ወደ ኖርዌይ ተመልሰው እና ትምህርት እና የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎታቸውን አጠናቀዋል። በ1957 እኤአ ሃራልድ የዘውድ ልዑል ሆኑ፣ ከ1960 እስከ 1962 ዓም እኤእ በኦክስፎርድ በሚገኘው ባሊዮል ኮሌጅ ማህበራዊ ሳይንስ፣ ታሪክ እና ኢኮኖሚክስ ተምየተማሩት ንጉስ ሃራልድ 5ኛ ወደ ትዳር ሕይወታቸው የገቡበት አጋጣሚም አስገራሚ ነበር።
ነገሩ እንዲህ ነው፡ በአንድ ግብዣ ላይ የአንድ ነጋዴ ልጅ ሶንጃ ሃራልድሰንን የተዋወቁት የዛንጊዜው ልዑል ሃራልድ፣ እሷን ለማግባት እስኪፈቀድላቸው ዘጠኝ ዓመታት መጠበቅ ነበረባቸው። በመጨረሻም ሶንጃን ማግባት ካልቻሉ ላጤ ሆኖነው እንደሚቆዩ ለአባታቸው እንደነገሯቸው፣ ንጉሥ ሃራልድ በአንድ ወቅት ለኖርዌይ የህዝብ ብሮድካስተር (ኤንአርኮ) ተናግረው ነበር።ሆኖም አባታቸው በመጨረሻ ፈቃዳቸውን ስለ ሰጡ ጥንዶቹ በኦስሎ ካቴድራል ነሐሴ 29 ቀን 1968 ዓም እኤአ ተጋቡ።
በሐምሌ 2011 እኤአ ንጉስ ሃራልድ ኖርዌይ ከባድ ፈተና በገጠማት ጊዜ ማለትም በጽንፈኛው ብሬቪክ በኦስሎ ውስጥ በመኪና ቦምብ ስምንት ሰዎችን ሲገድልና፣ በኡቶያ ደሴት ወደሚገኝ የወጣቶች ካምፕ በመሔድ 69 ወጣቶች (ባብዛኛው የአርባይድስ ፓርቲ ወጣት ክንፍ አባላት ያሉበት ብዙዎቹ በአስራዎቹ ውስጥ የነበሩቱን) ከገደለ በኋላ በኖርዌይ በደረሰው ሃዘን ንጉስ ሃራልድ ሕዝቡን ያጽናኑበት መንገድ ዛሬም ድረስ በብዙ ኖርዌጅያውያኖች ዘንድ ሲታወስ ይኖራል። ንጉሱ በእዚሁ ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር የእንባ ሳግ ለቅሶ እየተናነቃቸው በቴሌቭዥን ባሰሙት ንግግር እንደ አባት፣ አያት፣ ባል እና ንጉሥ ለተጎጂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው በቀጥታ በተላለፈ የቴሌቭዥን መልዕክታቸው ሁኔታውን ሲገልጹ ፡ "የህመማችሁን ጥልቀት መገመት እችላለሁ። የዚህች ሀገር ንጉሥ እንደመሆኔ መጠን ለእያንዳንዳችሁም እጨነቃለሁ" ብለዋል።
እኤአ በ2016 ዓም ደግሞ ንጉሱ ሃራልድ የሰው ልጅ ዘር አንድ መሆኑን እና በኃይማኖትም ላይ ልዩነት መደረግ እንደሌለበት በገለጹበት ንግግር ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡ ''ኖርዌጂያውያን "ከአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን እና ፖላንድ፣ ከስዊድን፣ ከሶማሊያ እና ከሶሪያ የመጡ መሆናቸውን ማወቅ አለብን '' ብለዋል።
ንጉስ ኦላቭ እና ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ
በኢትዮጵያ እና በኖርዌይ መካከል ረዘም ያለ ታሪካዊ ግንኙነት አለ።ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ እና የኖርዌይ ንጉሳዊ ቤተሰብ በቅርብ የተዋወቁት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጀመርያ አካባቢ ለንደን ላይ ነበር።በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ የጣያንን ኢትዮጵያ መውረር በወቅቱ የዓለም ማኅበር ተብሎ ለሚጠራው የዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ለማቅረብ ለአቤቱታ እንግሊዝ ነበሩ።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ኖርዌይን የጎበኙት በ1954 ዓም እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር ነበር ።በመቀጠል የኖርዌይ ንጉስ ኦላቭ ኢትዮጵያን በ1959 ዓም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ይፋዊ ጉብኝት አደረጉ።ኖርዌይ ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን ምፅዋ እና አሰብ ላይ ስትመሰርት በስልጠና የረዳች የመጀመርያ ሀገር ነች።
የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጉብኝት በኦስሎ ኖርዌይ እኤአ 1954 ዓም
ዛሬ ለኖርዌይ ሕዝብ ታላቅ የሃዘን ቀን ነው።ለአዲስ ዓመት በልዩ የማጽናኛና የማበረታቻ ቃላት ለሕዝቡ መልዕክት የሚያስተላልፉት፣በግንቦት 17 ቀን በቤተመንግስታቸው ሰገነት ላይ ሆነው ከሕጻናት እስከ አዋቂ በሰገነቱ ስር ሲያልፍ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ሰላምታ እየሰጡ በልዩ ፈገግታ የሚቀበሉት ንጉስ ሃራልድ አርፈዋል። ለንጉሱ ዕረፍተ ነፍስን ለቤተሰቦቻቸውና ለኖርዌይ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን።
====================////==============
No comments:
Post a Comment