Friday, August 14, 2026

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ፣ የአፈጀው የአዛውንቶች ክበብ፣ ''ፅንዶ'' እና ቅምጥሎቹ ''ባንዳ'' ዩቱበሮች በአውሮፓና አሜሪካ።



+++++++++++++
ጉዳያችን ወቅታዊ ምጥን
+++++++++++++

መንደርደርያ

ኢትዮጵያ በዘመን አቆጣጠሯ ስንሔድ የሐያ አንደኛውን ክ/ዘመን የመዠመርያ ሩብ ክፍለዘመን ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ብቻ ቀርተዋታል። ያለፈው ሐያኛውን ክፍለዘመን በአጭሩ ለማስቀመጥ የነፃነት እና የሉዓላዊነት ክብሯን ለማስጠበቅ ከጣልያን ሁለተኛ ወረራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት። የነፃነት ድሉን ተከትሎ የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ ተንተርሶ እራሷን ነጥራ ለማውጣት የታገለችበት ጊዜ ሲሆን በእዚህ ትግል ውስጥ ንጉሱ በሐገር ውስጥ ከጎጃም እስከ ትግራይ በሽፍትነት፣ከባሌ እስከ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በተቃውሞ፣ከቤተመንግስት እስከ የመንግስት ፍንቀላ ሙከራ ተደርጎባቸዋል። በእዚህ ሁሉ መሃል ግን የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ለኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጣኔ እና ትምሕርት በር ለመክፈት ዕድሉን ያገኘ መንግስት ነበር። ከንጉሱ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በርዕዮተ ዓለም ንትርክ ውስጥ ገብታ ብትቸገርም ለሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ያልተመቸች ሀገር ሆና ኖራለች።

ኢትዮጵያ ለታሪካዊ ጠላቶቿ አመቺ የሆነችው በኢሕአዴግ ሕወሓት ዘመን ነው። ይሄውም በቀዳሚነት የባሕር በሯን ትታ መሪዋ አቶ መለስ የባሕር በር '' የገበያ ጉዳይ ነው '' በሚል ትርክት እየተነገራት፣ሀገሪቱ የአስተዳደር ክልሏን በብሔር ከፋፍላና ''እስከመገንጠል '' የሚለውን ሕግ በአንቀፅ 39 ላይ ሰንቅራ የምትሔድ አሳዛኝ ሀገር ሆና ኖራለች። በእዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ተቋማት የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የሆነ አካባቢ የግል ቤት እስኪመስል ድረስ ከመቀረጹ በላይ የመከላከያ ሰራዊቷ በዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ ዘመኑን ያልዋጀ እና እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ የነበረበት ጊዜ ነበር። በእዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣው።

ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ

አሁን ያለንበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ከምንግዜውም በላይ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መዘውር በእጅጉ ከመራቁም በላይ የማይገመት አካሄዱ እና የግቡ እርቀት እና ምጥቀት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተለያየ ተልዕኮ የያዙ ጠላቶቿን ግራ ያጋባ ሆኗል።
ፖለቲካው በመጀመርያ ደረጃ የጠራ አቋሙን በግልጽ አስቀምጧል ይሄውም በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያን ሕብረብሔራዊ አንድነት ማረጋገጥ ሲሆን በውጭ የኢትዮጵያን ጥቅም በማንኛውም መንገድ አሳልፎ በማይሰጥ መልኩ ማስከበር ነው። በሀገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ ክኢሕአዴግ የቀድሞው ሕወሃት ሰራሽ የጎሳ ፖለቲካ ጋር እየተማታ አልፎ አልፎ መንገራገጭ ቢገጥመው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሐዲዱን በትክክል እንደያዘ ለመረዳት ብዙ ምርምር አይጠይቅም። ለእዚህ ደግሞ ዋና መሰረቱ የአብዛኛው ሕዝብ በተለይ በለየለት ጎሳዊ ፖለቲካ የተንገላታው ወጣት ሕብረብሔራዊ አንድነትን አጥብቆ መፈለጉ እና ይህ ብቻ ኢትዮጵያን ሊያሻግር መቻሉን የማመኑ ዕውነታ ነው። 

እዚህ ላይ መሰመር ያለበት ጉዳይ የአክራሪ ብሔርተኞች የፖለቲካውን መዘውር ለመቆጣጠር ጥረት አያደርጉም ወይንም ለማድረግ አልሞከሩም ማለት አይደለም።ነገር ግን ይህ ሙከራ ባብዛኛው ከሽፏል። የቀረው የያዘው የጎጥ በሽታ እስኪለቀው በትንንሽ ማባበያ ''ሕክምና'' እየተደረገለት ነው።ይህ ሂደት ቀጥሎ ተተኪው ትውልድ በሕብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ የኢትዮጵያን ተቋማት በሚገባ በኢትዮጵያዊነት ማረስረስ ሲጀምር የጃጀው ኢትዮጵያን የማመስ ፖለቲካ በራሱ ተሽመድምዶ ይንኮታኮታል። አሁን በምናየው መልኩም ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እስከ የኢትዮጵያ ሙዜሞች፣ከትምሕርት ፖሊሲ እስከ ውጪ ፖሊሲ በዘመነ ኢህአዴግ እና የቀድሞው ሕወሃት የተጎሳቆለው ኢትዮጵያዊነት በሚገባ እየተቀነቀነ ነው። ይህ ሂደት ሃገር ይሰራል፣የተሳሳተ ትርክት ያርማል፣ ትውልድ ያጋምዳል።

ባፈጀ አስተሳሰብ የሚዳክረው የአዛውንቶች ክበብ  ''ፅንዶ'' ተልዕኮው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንጂ መንግስት መቀየር አይደለም።

ከስሙ ስያሜ ገና ''ፅምዶ'' ይባል ''ፅንዶ'' ገና የሚጨቃጨቀው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የዳቦ ስም እንደ 1969 ዓም የኢሕአፓ እና መኢሶን ''እናሸንፋለን '' ይባል '' እናቸንፋለን'' የሚለው ጭቅጭቅ ያልተላቀቀ ነገር ግን ከባዕዳን የሚገኝ ድርጎ በአንድ ጣሳ ውስጥ እንዲገኝ ያደረገው የዘመናችን ግራ የተጋቡ የአዛውንቶች ክበብ ሆኖ ብቅ ብሏል። ስካር እና ምኞት፣ ማለም እና ዕውነታ የተደባለቁበት ስብስብ ነው። ስብስቡ ''የጨነቀ ዕለት'' የሚሉት ነው። መሰረተ ሀሳቡን ከማኅበራዊ ትስስር እና ከቋንቋ ጋር ሊይስተሳስረው የሚሞክርበት ዐውድ በራሱ የዕውር ድንብር አካሄድ ነው። ፅንዶ የድፍረቱ ድፍረት ከአማራ እና ሌሎች ክልሎችንም ስነ ልቦና ሰልቦ በእርሱ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ስር ለማሰለፍ ሲታትር ሰዎቹ የት ነው የነበሩት ያስብላል።

ቅምጥሎቹ ባንዳ ዩቱበሮች በአውሮፓና አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ሽርሽር 

ይህ የአዛውንቶች ያፈጀ የጎጥ ጥምረት ወላጅ አባቱ ኢትዮጵያን ማተራመስ የምፈልጉቱ ታሪካዊ ጠላቶች ቢሆኑም በትግራይ እና በኤርትራ ሕዝብ እንዲሁም በዐማራው እና ኦሮሞው ደም እየነገዱ ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉት ቅምጥሎች ተግባር ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቅምጥሎቹ ከሚኖሩበት ሀገር ሶፋ ላይ ሳይወርዱ በዩቱብ የኢትዮጵያን ወጣቶች ተዋጉ እያሉ ሲለፍፉ ያመሻሉ። በቀጣይ ቀን ቅምጥሎቹ ዩቱበሮች በአሜሪካና አውሮፓ የኢትዮጵያውያን የእግርኳስ ውድድር ላይ ከልጆቻቸው ጋር ሲምነሸነሹ ማምሸታቸውን፣ ወይን እና ውስኪ መጠጣታቸውን እና ለልጆቻቸው የገዙትን መጫወቻ ከራሳቸው ጋር ካደረጉት የቴክሳስ ኮፍያ ጋር ብቅ እያሉ በአራዳ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ '' ይላጡበታል '''። 

ለመሆኑ ሕሊና በእዚህ ደረጃ ተሸጦ ተቀርጥፎ ይበላል እንዴ? የአማራ ክልል ወጣት ተነሳ ሙት እያልክ ጦርነት ቀስቅሰህ እና በሚልዮን የሚቆጠር በተለይ የጎጃም ወጣት ከሦስት ዓመታት በላይ ከትምሕርት ገበታ እርቆ እና ትምሕርት እንደ ውሃ ጠምቶት እያለቀሰ፣እናት አባቱ በጥጋበኛ አጋች እየታገተ እና ገንዘብ አምጣ እየተባለ መከራውን እያየ፣ቅምጥሎቹ ባንዳ ዩቱበሮች በአውሮፓና አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ልጆቻቸው ከትምሕርት ዕረፍት ጋር ይዘው ወዝ ወዝ ሲሉ ማየት የእዚህ ዓይነት የባንዳነት እና ባሳደገች ሀገር ላይ የመጨከን ዓይን ያወጣ አውሬነት ለገንዘብ ሲሉ እንዴት ተዘፈዘፉበት ያስብላል። እነኝህ ባንዳ ዩቱበሮች የድፍረታቸው ድፍረት ትናንት የኢትዮጵያ አንድነት እያሉ ሲያወሩን በሰማንበት አንደበት ዛሬ ላይ የጎጥ ፖለቲካ እያቀነቀኑ ብቻ ሳይሆን ከጠላት ሀገር ጋር መሞዳሞድ እና ኢትዮጵያን በአደባባይ መሸጥ ከፍ ሲልም የባሕር በሯ መዘጋትን እና የመጣባትን መከራ በተድበሰበሰ የስልጣን ጥያቄ እና አዲስ አበባ ላይ ጎርፍ አየን በሚል የቱቦ መደፈን እና መዘጋት ጉዳይ እያነሱ ሊያጃጅሉን ይሞክራሉ። ለራሳችሁ የመጃጃል መብታችሁን ብናከብርም ኢትዮጵያን ለማሻሻጥ የምታደርጉትን የባንዳነት ተግባር ግን አይደለም ይህ ትውልድ መጪው ትውልድም በይቅርታ የሚዘለው ጉዳይ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ለገዛ ልጆቻችሁም ''የባንዳ ልጆች '' ከመባል አያስጥላቸውም።

ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የተኙ ለመሰሏችሁ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ልጆቹን በጦርነት የማገዱትን የአዛውንት ክበቡን ፅንዶ፣ ያሳደገቻቸው እናታቸው ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ የባሕር በር ተዘግቶበት እያዩ ዛሬም ለእናታቸው መውጫ በር ለመዝጋት የሚራወጡቱ እና ባንዳ ዩቱበሮችን ተግባሮቻቸውን ሁሉ በአንክሮ እየተከታተለ፣ ትዕግስቱን ከመፈታተን በላይ ከደሙ አልፎ አጥንቱን እያጋሉት መሆኑ አልገባቸውም። ይህ እንቆቅልሽ የሆነ ምድር ነው  ኢትዮጵያ፣ ይህ የተኛ ሲመስልህ እንደ አንበሳ አጓርቶ፣እንደ ግስላ የሚነሳ ሕዝብ ያለበት ሀገር ነው። ኢትዮጵያ ና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማራ፣በትግራይ እና በኦሮሞ ስም እያላችሁ በስሙ የነገዳችሁ ብቻ ሳትሆኑ ለባዕዳን ለመሸጥ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የምታደርጉትን የአዛውንቶች ክበብ ስብስብም ሆነ በዩቱብ የባንዳነታችሁን ላንቃ የምትለቁበት ሁሉ ዕወቁት። የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተኛም።ኢትዮጵያም አልተኛችም።እንዴት ተነስቶ ባንዳነትን እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተውተረተሩትን ሁሉ እንደሚቀጣ ያውቅበታል።ከእዚህ በፊትም ሲነሳ ታውቁታላችሁ።ሀገሩ ተገማች አይደለም። ሕዝቡም እንዲሁ።
++++++++++++++/////++++++++++++++


No comments:

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ፣ የአፈጀው የአዛውንቶች ክበብ፣ ''ፅንዶ'' እና ቅምጥሎቹ ''ባንዳ'' ዩቱበሮች በአውሮፓና አሜሪካ።

+++++++++++++ ጉዳያችን ወቅታዊ ምጥን +++++++++++++ መንደርደርያ ኢትዮጵያ በዘመን አቆጣጠሯ ስንሔድ የሐያ አንደኛውን ክ/ዘመን የመዠመርያ ሩብ ክፍለዘመን ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ብቻ ቀርተዋታል። ያለፈው ሐ...