Monday, September 28, 2026

የመስቀል ደመራ በዓል በንግስት ዕሌኒ ሀገር በግሪክ ቅዳሜ መስከረም 16፣2019 ዓም በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።በግሪክ የምትገንኘው የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤቱታቸውን ደግመው አቀረቡ።

========
ልዩ ሪፖርታዥ
========


በእዚህ ርዕስ ስር የሚከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።እነርሱም ፡ 
  • የመስቀል ደመራ ለምን ይከበራል?
  • ግማደ መስቀሉ  ወደ  ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?
  • የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል በአቴንስ፣ግሪክ የነበረው ገፅታ(ቪድዮ) እና ደመራውን ለማስተጓጎል የተደረገው ጥረት ክሽፈት።
  • በደመራው ላይ ከምእመናን የተጠየቀው እና ለቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ በተመለከተ የቀረበ ቅሬታ (ቪድዮ)
=========

የመስቀል ደመራ ለምን ይከበራል?

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት ዕሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327ዓ.ም ወደኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለከብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡ የአይሁድ ወገን እንቢ ቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታት አስቆፍሪው ብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየት ባለመቻሉ ከሦስቱ ተራሮች አንዱ ነው ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ አዘዘቻቸው፡፡የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከጌታ ሞት እያመነ በተቸገሩ ግዜ ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል አይሁድ አዝዘው ስለነበር ከሁለት መቶዓመት በላይ ጥራጊ ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡

ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙ ዕጣንም በመጨመርና በማቃጠል ከአኢየሩሳሌም ወጣ ብለው ያሉትን ኮረብቶች  አሳያት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰገደ ጢስ" ጢሱሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡  የሞተ ሰው አምጥተው በሁለቱ መስቀሎች ላይ በተራ ቢያስቀምጡት አልተነሣም፡፡ በመጨረሻ  በአንዱ መስቀል ላይ ቢያስቀምጡት ያን ጊዜየሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም የጌታን መስቀል ለዩት፡፡ ዕሌኒም የጌታ መስቀል እንደሆነ አወቃ ሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ግዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ በዚህምምክንያት ይህ ታላቅ የድኅነት ምልክት የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራ በመደመር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡

ግማደ መስቀሉ  ወደ  ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?


ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖሩ በግብጽ ያሉ ሙስሊሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሲሔድ በእስክንድርያ የሚኖሩ ክርስትያኖች ላይ ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ"ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና  ኃይልህን አንሥተህአስታግስልን ብለው ጠየቁት ዳግማዊ ዓጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅርአስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን ፈሩተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁከሆኑት ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ" የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተውበሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙበዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡ 

እግዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችምከ12,000 ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤአድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግንመልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡፡ በግብጽ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ 12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ ወርቅፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንምየምለምናችሁ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስየተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነውየሚል ነበር፡፡

በእስክንድርያም ያሉ ምዕመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለውየፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄትወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብርበሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸውእያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሏቸው፡፡

የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል በአቴንስ፣ግሪክ የነበረው ገፅታ እና ደመራውን ለማስተጓጎል የተደረገው ጥረት ክሽፈት።

በአቴንስ ግሪክ የምትገኘው የኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ለብዙ አስርተ ዓመታት የመስቀል ደመራን በዓል የምታከብረው በአቴንስ ከተማ ዛፕዮ አደባባይ ላይ ነው። በአደባባዩ በሺህ የሚቆጠር ምእመን በፍቅር እና በአንድነት የሚያከብርበት አደባባይ ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም በተመሳሳይ በዓሉን ለማክበር የፈቃድ ወረቀት ቤተክርስቲያኒቱ ስትጠይቅ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልያስ የቤተክርስቲያኒቱ ጥያቄ እንዳይሰማ ከእዚህ በፊት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ደም በማፍሰስ፣ቅዳሴ እንዳይቀደስ እና ኪዳን እንዳይደርስ ፊሽካ በመንፋት እና የቤተክርስቲያኒቱን ንብረት በመዝረፍ የሚታወቁ ግለሰቦች ጋር ባላቸው ቅርበት እነርሱ ለተደራጁበት ኪኖቲታ በሚል ለተመዘገቡ አደባባይ እንዲፈቀድ የግሪክ የሃይማኖት ሚኒስቴርን በተሳሳተ መረጃ በመጠየቃቸው ቤተክርስቲያኒቱ የመስቀል ደመራ በዓልን እንዳታከብር እንቅፋት መፍጠራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ምእመናንን አሳዝኖ ሰንብቷል። ሊቀ ጳጳሱ ከእዚህ በፊትም ክረምቱን እነኝሁ ግለሰቦች በሆቴል እየሰበሰቡ ''የእኔ'' የሚሉት ስብስብ ለመፍጠር መሞከራቸውን እና ይህም ከአንድ ጳጳስ የማይጠበቅ መሆኑን ከሕዝቡ የተውጣጡ ግለሰቦች ጭምር በወቀሳ ካሉበት ሆቴል ድረስ ሄደው ቢነግሯቸውም፣ አሁንም ይህንኑ ምእመኑን የሚለያይ ተግባር ቀጥለውበት የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን እንዳያከብሩ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ፈጽመዋል።

ይህ ብቻ አይደለም። የዛፕዮ አደባባይ ለመያዝ የሄዱበት ሂደት ሕገወጥ እንደሆነ በግሪክ መንግስት ቢሮዎች ከተገለጠ በኋላ የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን በከተማው ማዕከላዊ ቦታ በኮሮዶር አደባባይ በዓል ለማክበር ስትዘጋጅ አሁንም ጸረ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እና ኢትዮጵያ ጠል ከሆነ ግለሰብ ጋር በመመሳጠር በዓሉ እንዳይከበር ለ15 ቢሮዎች ግልባጭ የተደረገበት የዕግድ ሙከራ ቢያደርጉም የግሪክ መንግስት ጉዳዩን በአንክሮ መርምሮ እና በአቴንስ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ስር ባሉ ምእመናን ላይ የተፈጸመው የቡድን ወንጀልም ምርመራ እንደሚያስፈልገው ካመነበት በኋላ ምእመናን በኮሮዶር አደባባይ በዓሉ እንዲከበር በድጋሚ ፈቅዷል።በእዚህ የማደናቀፍ ሒደት ላይ በዓሉ ሲከበር የግሪክን የጸጥታ ቢሮ ለማሳሳት የተሳሳተ ስልክ ይደውሉ የነበሩት ግለሰቦች ጭምር ላይ በሃሰት ፖሊስን እና የደሕንነት ቢሮን ለማሳሳት በተደረገ ሙከራ ጥብቅ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ቪድዮ፡ የመስከረም 16፣2019 ዓም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በአቴንስ፣ኮሮዶር አደባባይ



ይህ በእንዲህ እያለ በእዚሁ በቅዳሜ መስከረም 16፣2019 ዓም በአቴንስ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በግሪክ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ችግሮች እንዳይፈቱ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ግሪክ መጥተው እንዲያገለግሉ የተመደቡት ሊቀ ስልጣናት አባ ኪሮስ ጸጋዬ ተገቢውን የመግቢያና የመስራይ ቪዛ አግኝተው እንዳይመጡ አሁንም የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልያስ ችግር መፍጠራቸውን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቅዱስ ፓትርያሪካችን አቡነ ማትያስ በግሪክ ለምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን በአድልዎ እና ከጥፋት ቡድኖች ጋር እያበረ ቤተክርስቲያንን የማይጎዳ እንዲሁም የተሰጠውን ጴጥሮሳዊ አገልግሎት በአግባቡ የመወጣት አቅም ያለው ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብ በመስቀል ደመራው የተሰበሰበው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ምእመን በአንድ ድምጽ ከእዚህ በፊት በተደጋጋሚ ካሰማው ድምጽ በተጨማሪ በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ላይም በአንድ ድምፅ ጮሆ አሰምቷል።

ቪድዮ ፡ መስከረም 16፣2019 ዓም በአቴንስ ኮሮዶር አደባባይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ከምእመናን የተላከው መልዕክት



በመጨረሻም ይህንን ሁሉ ስሞታ ቸል ያሉት አቡነ ኤልያስ በሕገወጥ መንገድ የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን እንዳታከብርበት ባደረጉበት በዛፕዮ አደባባይ የራሳቸውን ደመራ ለመደመር መስከረም 17፣2019 ዓም ሙከራ ያደረጉ ሲሆን፣ አሁንም በግሪክ የሚኖሮ ኢትዮጵያውያን እና ግሪካውያን ጭምር በወንጀል ተግባራቸው ከታወቁ ግለሰቦች ጋር ለማድረግ የሞከሩት የመስቀል ደመራ በምእመናን ድርቅ ከመመታት አልፎ፣አንድ ግሪካዊ የቪድዮ እና የፎቶግራፍ አንሺ በአደባባዩ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሲያከብሩበት የሚያውቀው አደበባይ፣አደባባዩ በሰው ድርቅ መመታቱን ለእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የገለጸበት ዓረፍተ ነገር እጅግ አስገራሚ ነው። ባለሙያው ባጭሩ ያለው የሚከተለውን ነበር።'' በዛፕዮ ታሪክ የእዚህን ያህል የሰው ድርቅ አይቼ አላውቅም።በአዘቦት ቀን ቢያንስ እርግቦች አደባባዩን ይሞሉታል።የዛሬው የሚያስፈራ ድባብ ያለው መንፈስ መስሎ አመሽ።'' በማለት ገልጦታል። ሁሉንም ለታሪክ እና ለመጪው ትውልድ ከትበን አስቀምጠነዋል።
================////=============


No comments:

የመስቀል ደመራ በዓል በንግስት ዕሌኒ ሀገር በግሪክ ቅዳሜ መስከረም 16፣2019 ዓም በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።በግሪክ የምትገንኘው የአቴንስ ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤቱታቸውን ደግመው አቀረቡ።

======== ልዩ ሪፖርታዥ ======== በእዚህ ርዕስ ስር የሚከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።እነርሱም ፡  የመስቀል ደመራ ለምን ይከበራል? ግማደ መስቀሉ  ወደ  ኢትዮጵያ እንዴት መጣ? የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል...