ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, March 23, 2023

የተወካዮች ምክርቤት (ፓርላማው) አሰራሩ እና ውሳኔ አሰጣጡ የ21ኛውን ክ/ዘመን የሚመጥን፣ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ፓርላማዋን ከከፈተች ከ80 ዓመታት በላይ እንደሆናት በሚያሳይ ልክ አይደለም።

አሁን በአራት ኪሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፓርላማ ህንጻ በ1928 ዓም 

===========
ጉዳያችን
==========

የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በድረገጹ ላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ ታሪክ በሚለው ርዕሱ ስር እንዲህ የሚል ተጽፏል - 

''የቀዳማዊ  ኃይለሥላሴ  የመጀመሪያው ሕገ መንግስት  ከታወጀበት  ሐምሌ  9  ቀን  1923 ዓ.ም በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 1924ዓ.ም የመጀመሪያው ፓርላማ መከፈቱን የታሪክ ድርሳናት ያሰረዳሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የፓርላማ ስርዓት በኢትዮዽያ  ሲሰራበት የቆየ  ሲሆን፤መገለጫዎቹ እንደ የመንግስታቱ ባህሪያ   የተለያዩ ናቸው.....በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፅሁፍ ሕገ-መንግስት የወጣው በቀዳማዊ  ኃይለሥላሴ  ዘመነ መንግስት  በ1923 ዓ.ም  ሲሆን፤ የንጉሠ ነገሥቱ የንግስ በዓል  ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም  ከተከበረ በኋላ፤ ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም.  ንጉሱ በፊርማቸው ሕገ መንግስቱን  አፅድቀው፤ በፍቃዳቸው ለኢትዮዽያ ህዝብ የሰጡት የመጀመሪያው  ሕገ  መንግስት  በመባል ይታወቃል።

ይህ ሕገ መንግስት  ያስፈለገበት  ምክንያት ኢትዮዽያ ከነበረችበት ጥንታዊና ልማዳዊ አመራር ወጥታ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር እንድትሻገር ብሎም ኢትዮዽያ በህገ መንግስት የምትተዳደር ንጉሳዊ አገር ነች ተብላ በዓለም እንድትታወቅ ለማድረግ ነው። ከታላላቅ መሳፍንትና መኳንንት ወገን 11 የኮሚቴ አባላት በንጉሱ ተመርጠው በራስ ካሳ ሊቀመንበርነት በየዕለቱ እየተሰበሰቡ በአምስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተመስርተው በሕገ መንግስቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ ፤ የሕገ መንግስቱ ረቂቅ ተዘጋጅቷል'' ይላል።

ኢትዮጵያ ፓርላማዋን አሁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኝበት በአራት ኪሎ ላይ የተከለችው ገና ጣልያን ኢትዮጵያን ሳይወራት ነው። ከላይ የምትመለከቱት የፓርላማው ህንጻ የነበረው ዕይታ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት በ1928 ዓም የነበረው ነው። ኢትዮጵያ የራሷ ፓርላማ ሲኖራት አፍሪካ ሙሉ በቅኝ ግዛት ውስጥ የሚዳክር ነበር።አፍሪካ ብቻ አይደለም።የደቡብ አሜሪካ እና የመካከለኛው እና ሩቅ ምሥራቅ ሃገሮችም በቅኝ ተገዢዎች ስር ነበሩ። ችግሩ የኢትዮጵያን ክብር፣አባቶቻችን ቀደም ብለው የሰሩት ገና ያልገባን፣ የሃገራችን ታላቅነት ገና ያልገባን ብቻ ሳንሆን የነበረውን አልቀን እና አሻሽለን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚገባን ሲሆን ያለውን አጨቅይተን እና አዋርደን የምንኖር ትውልድ መሆናችን ያሳዝናል።

ለእዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ትናንት መጋቢት 13፣2015 ዓም የኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) የህወሃትን ከሽብርተኝነት ፍረጃ ያነሳበት ሂደት ምን ያህል የፓርላማውን ታላቅ ታሪክ እና በ21ኛው ክ/ዘመን እንደሚገኝ ፓርላማ እራሱን በሚመጥን ደረጃ አለማሳየቱ የሚያሳዝን የሆነበትን ሁኔታ ስመለከት ነው። 

በእዚህ ጽሑፍ ላይ ህወሃት ሽብርተኛ መባሉ እና ውሳኔው መነሳቱ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም። ምክንያቱም ህወሃት ሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የወሰነው ገና ከስልጣን ሳይወርድ ነው። ህወሃት ሽብርተኛ ለመሆኑ የ27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ሥራ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በትግራይ፣በአፋር እና በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው በዘመናችን ያልታየው ሰውን ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሣት እና ዕጽዋት ሳይቀር ለማጥፋት በአውሬነት ስሜት የተንቀሳቀሰ ለመሆኑ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክር ነው። እዚህ ላይ ግን መነሳት ያለበት የኢትዮጵያ ተወካዮች ምክርቤት ህወሃትን ከሽብርተኝነት ሰርዣለሁ ሲል የሄድበት ሂደት ምን ያህል የፓርላማውን ደረጃ የማይመጥን መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ነው። 

ለመሆኑ ፓርላማው ይህንን ህወሃትን ከሽብርተኝነት ሲሰርዝ መሄድ የነበረበት ሦስቱ ሂደቶች ምን ምን ነበሩ?

1/ የምክርቤቱ አባላት በሚገባ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ቢያንስ ለተወሰኑ ቀናት አልተወያዩም

የተወካዮች ምክርቤት ከህወሃት መውደቅ በኋላ ብዙ መሻሻሎች ያሳያል የሚል የብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ነበር።የምክር ቤቱ አባላት በ27 ዓመታት ውስጥ ከነበሩት በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በአመለካከት ስብጥር የተሻለ ለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ነገር ግን አሁንም የሚናገሩት የካድሬ መንፈስ የተላበሱት እንጂ ሌላው ሲሞግት ብዙ አልታየም። የምክር ቤቱ አባላት ሃሳብ አቀራረብ በራሱ ዛሬም እንደ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በተቀመጡበት እጅ አውጥተው አፈጉባዔው በሰጧቸው ደቂቃ ብቻ መሆኑ አሰልቺም ሃሳብንም በደንብ ለማንሸራሸር የሚያመች አይደለም። 

ዛሬም ፓርላማው ድንገት ወይንም በአጭር ጊዜ የሚመጡለት አጀንዳዎችን አክለፍልፎ ማሳለፍ እንጂ ጉዳዩን የሚመረምርበት ጊዜ የለውም። ይህ ህወሃትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ ውሳኔ ለፓርላማው ታሪክም ተጠያቂ ላለመሆንም ሂደቱ ትክክል መሆኑም እርግጠኛ መሆን ነበረበት። ፓርላማው በአንድ ቀን ይህንን ያህል ግዙፍ ጉዳይ በተወሰኑ ሃሳቦች ሰምቶ እጅ አውጥቶ ወሰንኩ ማለቱ በራሱ አስቂኝ ሂደት ነው። የእዚህ ዓይነት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም አባላት ሃሳብ ካላቸው የፈጀውን ቀን ይፍጅ መስማት አለበት። የሁሉንም የመስማት የጊዜ ጥበት ቢኖር ከየክልሉ ቢያንስ የሦስት አባላት ሃሳብ እየወጡ ቆመው የሚናገሩበት መድረክ አዘጋጅቶ ለህዝብ በቀጥታ እየተላለፈ ሃሳባቸውን ማቅረብ አለባቸው። ህዝብም በምን ያህል ሙግት ጉዳዩ እንዳለፈ የማወቅ ሙሉ መብት አለው። ፓርላማዎች በብዙ ዓለማት በአጀንዳው ላይ አባላቱ የተወሰኑ ደቂቃዎች ቆመው ንግግር እንዲያደርጉ እና ሃሳባቸውን የሚያስረዱበት አግባብ ያዘጋጃል። ከ80 ዓመታት በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ፓርላማ ይህንን አሰራር እንዴት በ21ኛው ክ/ዘመን ሆኖም መማር አልቻለም? 

2/ ምክርቤቱ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው ሃሳባቸውን እንዲሰጡ እና ይህ ሃሳብም ለህዝብ እንዲገለጥ አላደረገም።

አንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮች ቀላል ክርክር የሚፈልጉ ብቻ አይደሉም። መዘዛቸው ለትውልድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ የሚተርፍ ችግር ይዘው እንዳይመጡ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ፣የብዙ ባለሙያዎች ሃሳብ፣የተራው ህዝብም ሃሳብ ሁሉ ያስፈልጋል።ትናንት በህወሃት የሽብር ፍረጃ መነሳት ጉዳይ ላይ ቢያንስ ለሳምንት ያህል በተያዙ መርሃግብሮች ምክርቤቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ከፍተኛ መኮንኖች፣ የደህንነት ሚኒስትሩ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የሕግ ባለሙያዎች፣በጦርነቱ የተጎዱ የክልል ባለስልጣናት እና ከውጭጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር የፍረጃው መነሳት አንደምታ፣በሃገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ላይ ያለው ተጽዕኖ ጭምር እንዲብራራለት መጠየቅ ከእዚህ በኋላ ቀደም ብሎ ጉዳዩን አስመልክቶ በመሰረተው አጥኚ ኮሚቴ (ይህ ኮሚቴ ፓርላማው የለውም) ጋር ተመካክሮ እና ተከራክሮ የጋራ አቋም መያዝ እና ድምጽ መስጠት ነበረበት። 

የእዚህ ዓይነት አካሄድ ለፓርላማ አባላቱ ለሚሰሩት ሥራ ብቻ ሳይሆን ለውሳኔያቸው ምክንያታዊነት እና ለሃገር ጠቃሚነት የሚያረጋግጡበት መንገድ ነው። ትናንት የታየው ግን የካድሬ ንግግር በሚመስል መንገድ ህወሃትን ከሽብር ፍረጃ ማንሳት የትግራይን ህዝብ ሽብርተኛ የተባለ ይመስል የሚናገሩ አንዳንድ ልወደድ ባይ አባላት የተመለከትንበት ነው።የህወሃት ከሽብርተኛ ፍረጃ መነሳት ማለት የትግራይ ህዝብ ቀድሞም ባልተፈረጀበት ፍረጃ ሌላ ስም የተሰጠው አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ምክርቤቱ እንዴት ያሉ የካድሬ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንዳሉ ማሳያ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የእዚህ ምክር ቤት አቅም ያላቸው አባላቱ እንዳይናገሩ የካድሬው ቀደም ቀደም ማለት ብዙ ነገር የሸፈነ ይመስላል።ስለሆነም ፓርላማው አባላቱ በአንድ ሃገራዊ አጀንዳ ላይ ሃሳባቸውን ቆመው በጽሑፍ ወይንም በቃላቸው የሚያቀርቡበት መድረክ ማመቻቸት እና የተመረጡ አባላት ሲከራከሩ እና ሃሳብ ሲንሸራሸር ማየት እንፈልጋለን። በእዚህ ሂደትም ይህንን የሚያዩ ወጣቶችም ሆኑ ታዳጊዎች ስለ ፓርላማ ብዙ እንዲማሩ ቢደረግ የተሻለ ነው።

3/ ምክርቤቱ ሰነድ አልመረመረም

በትናንትናው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ምክርቤቱ በአንድቀን የቀረበለትን አጀንዳ ጉዳዩን በደንብ እንደመረመረ ሁሉ እጅ ሲያወጣ ያስገርማል። በህወሃት ከሽብርተኛ መነሳት ጉዳይ ላይ ምክርቤቱ ቀድም ብሎ ጉዳዩን የሚመለከት ኮሚቴ መመስረት፣በእዚህ መሰረት የፕሪቶርያ እና የናይሮቤ የስምምነት ሰነዶች በደንብ ማጥናት እና መተንተን፣በመቀጠል ስለአፈጻጸማቸው ትግራይ ድረስ ልዑክ ልኮ መሬት ላይ ያለውን አፈጻጸም መመልከት ይህ ባይሳካለት የመከላከያ ሚኒስትር ኢታማዦር ሹም ፓርላማ ቀርበው ከፕሪቶርያ ስምምነት አንጻር የቱ ተፈጸመ የቱ አልተፈጸመም፣ለምን የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና በቂ ምላሽ ማግኘት ይገባው ነበር።ይህ ሁሉ ግን አልሆነም።ይህ ከሰማንያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ፓርላማ ላላት ሃገር አሳፋሪ ነው።

ፓርላማው ወደፊት እንዲያሻሽል የምንፈልገው።
  • አባላቱ የሃገሪቱ የመጨረሻ የህዝብ ተወካይ፣ሕግ አውጪ እና አጽዳቂ መሆናቸው ከልብ እንዲሰማቸው እና እንዲታወቃቸው መሆን አለበት። የድርጅታዊ አሰራር እና የሸፍጥ አጀንዳ አቀራረቦችን ግልጽ በሆነ ተቃውሞ እና ''አካፋን አካፋ''በሚል አቀራረብ የመናገር ባሕል ማዳበር አለባቸው።
  • አንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮችን እና አጀንዳዎችን ጉዳዩን ከያዘው የመንግስት መስርያቤት፣ባለስልጣን (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ) ላይም ቢሆን አጀንዳውን በስልጣናቸው ነጥቀው ወደ ውሳኔ እንዲደርስ የማድረግ፣የመመርመር እና ውሳኔ እንዲሰጥበት የማድረግ ሂደት ሊለምዱ ይገባል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የአውቶብስ ግዢ ላይ ብዙ ንትርኮች ሲደረጉ ፓርላማው ዝም ብሎ ያይ ነበር።በእዚህ ጊዜ ፓርላማው ኮሚቴ ሰይሞ ጉዳዩ ተመርምሮ እንዲቀርብለት ማስደረግ ይችል ነበር።ይህ ለምሳሌ ቀረበ እንጂ በርካታ ጉዳዮች እንዲሁ ታልፈዋል።
  • ፓርላማው አንዳንድ ወሳኝ ሃገራዊ አጀንዳዎች በደንብ እንዲብላሉ በጉዳዩ ላይ ሃሳብ የሚያቀርቡ ለቀናትም ቢሆን ተዘጋጅተው መጥተው አለኝ ያሉትን ሃሳብ የመናገርያ አትሮኖስ ለአባላት ተዘጋጅቶ መናገር መቻል አለባቸው። እነኝህ ንግግሮች ደግሞ በቀጥታ ለህዝብ የሚደርሱ መሆን አለባቸው።ፓርላማዎች ለህዝብ ክፍት ናቸው።የብዙ ሃገሮች ፓርላማ ውሎ በቀጥታ ስርጭት ነው የሚተላለፉት።ሌላው ቀርቶ የፓርላማዎች ላይኛው ፎቅ ሁል ጊዜ ለማንም ህዝብ መጥቶ የሚባለውን እንዲመለከት ክፍት ይደረጋሉ።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀሩት ሦስት ዓመታት ገና ብዙ ወሳኝ ሃገራዊ አጀንዳዎች ይኖሩታል።የእስካሁኑ አለፈ።ከአሁን በኋላ ግን አቀራረቡም ሆነ የአጅነዳ አመራረጡ እና አባላቱ ቆመው የሚናገሩበት በቂ ደቂቃዎች ማመቻቸት ላይ እንዲሰራ መደረግ አለበት።የእዚህ ዓይነት አሰራርን የማዘመን ፋይዳ ከ80 ዓመታት በላይ የፓርላማ ታሪክ ላላት ኢትዮጵያ የሚያንስባት እንጂ የሚበዛባት አይደለም።በውሸት የካድሬ ወሬ የኖሩ መንግስታት አሳልፈን የእውነት የሆነ በሃሳብ ላይ የሚሞግት ፓርላማ ለማየት የሰማይ ያህል እንዴት ይህ ትውልድ እንዲርቀው ይፈረድበታል? ከምክር ቤቱ አፈጉባዔ ጀምሮ እያንዳንዱ አባል ለፓርላማ አባላት ያለው ክብር እንዲስተካከል ፓርላማውም እራሱን ያሻሽል፣አዳዲስ ሃሳብ እያፈለቀ ህጎችን እና አሰራሮችን ያሻሽል።የፈዘዘ እና በካድሬ ንግግር ብቻ ስልጡን የሆነ ፓርላማ ሃገር እንድታንቀላፋ ያደርጋል።በመጨረሻ እራሱም አንቀላፍቶ ያልፋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ፓርላማ ምን ያህል በንጉሱ ዘመን ከነበረው ሳይቀር የወረደ እንደሆነ ለማየት አንድ በንጉሱ ዘመን በፓርላማ የነበረውን አንድ ጥያቄ እና አባላቱ ምን ያህል ለመረጣቸው ህዝብ እና ለሃገራቸው ንቁ እንደነበሩ የሚያሳይ ጉዳይ አንስቼ ጽሑፌን አበቃለሁ። በንጉሱ ዘመን የፓርላማ አባላቱ ጥያቄ ያነሳሉ። ጉዳዩ በእርዳታ የሚመጣ ገንዘብ ለትምህርት ቤት መስርያ የዋለ ይህንን ያህል ገንዘብ ነው ገንዘቡ ከዓለም ባንክ የተገኘ ነው የሚል ሪፖርት የገንዘብ ሚኒስትሩ ያቀርባሉ። የገንዘቡ መጠን እና በእዚያንጊዜ በእየጠቅላይ ግዛታቸው የተሰራው የትምህርት ቤት ብዛትና ወጪ ከነከናቸው።አባላቱ ከንክኗቸው አልቀሩም።ወደ ንጉሱ ጋር ቀጠሮ አስይዘው ገብተው እንዴት ይህንን ያህል ገንዘብ ወጣ ይለናል የገንዘብ ሚኒስትሩ ስናስበው ይህንን ያህል አይሆንም የሚል ክርክር ይዘው ነው የቀረቡት። ንጉሱም የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስትሩን ጠርተው የፓርላማ አባላቱ እያንዳንዱ የተሰሩትን ትምህርት ቤቶች በእየ ጠቅላይ ግዛቱ እየዞሩ እንዲያዩና የተሰራበትን ዋጋ ደምረው እንዲያመጡ ወጪ እንዲመደብ ያደርጋሉ።በእዚህ መሰረት የፓርላማ አባላቱ በእየጠቅላይ ግዛቱ እየዞሩ እያንዳንዱ ትምሕርትቤት የተሰራበትን ወጪ ደምረው ሲመጡ ወጪው ከተባለው በላይ ሆኖባቸው ወደንጉሱ ጋር ገብተው ጉዳዩን በማስረጃ መረዳታቸውንና የጠመኔና የቦርድ ሌሎች ወጪዎችን ሁሉ ተጨማሪ ወጪ እንደነበሩ ያረጋግጣሉ። ይህንን የሚያውቁ በፊልም ጭምር የተናገሩት ማስረጃ አለ። ዛሬ የእኛ ፓርላማ የት ነው ያለው? እንጠይቅ። በቀጣይ ሦስት ዓመታት የትልቅ ሃገርን ታሪካዊ ፓርላማ ዐውድ ቀሩና አሳዩን። ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ማለት ነው። ውለታ ዋሉላት!
======================//////==========

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...