=======
ጉዳያችን
=======
ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሃገር፣ቀደምት የመንግስት ስሪት ያላት፣ሕግ ስጋዊ እና ሕግ መንፈሳዊ ከራሷ አልፎ ለዓለም ሕግ አስተዋጽኦ ያደረገች ጥንታዊት ምድር። ይህች ታላቅ ሃገር ስሟ ገንኖ እና ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረችበት አንዱ እና ዋናው ምሰሷዋ የንጉሥ ዘውድ ምልክት ያላት ሃገር ስለሆነች ነው።ይህንን ምሰሶዋን፣ የህዝብ ብሶት አስታኮ የኢትዮጵያ ህዝብ (አሁንም ገና በቂ ምርምር ቢያስፈልግም) በ1966 ዓም አፍርሷል።ይህንን የኢትዮጵያ ምልክት በማፍረስ ሥራ ላይ በአንድም በሌላም የተሳተፉ የእኛ ታላላቆች የምሰሶው መኖር ቢያንስ አደጉ በሚባሉ ሃገሮች እንዳለው ለምልክት ማስቀመጥ እና በአስቸጋሪ ጊዜ ለችግር ፈቺነት ቢቀመጥ ኖሮ እያሉ የሚያወሩት ለብቻቸው ወይንም ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንጂ በጥናት አቅርበው ምሰሶውን የማፍረሱ ፋይዳ ኢትዮጵያን እንዴት እንደጎዳ ሽንጣቸውን ገትረው ለመከራከር ብዙ ሲሽኮረመሙ ይታያል።
የእኔ ትውልድም የዘውድ ምልክት በተለይ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ የሚነግረውም ሆነ የነገረው የለም።የወታደራዊው መንግስት፣የህወሃትኢሃዴግ መንግስት እና አሁን ያለው የጽንፍመር መንግስትም ሁሉም ዘውድ እና ንጉስ ሲባል እንድንሸማቀቅ አድርገው ሲሰሩን ኖረዋል። አሁን ዓይን የመግለጫ ጊዜ ነው።እንደ ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የነፃነቷ እና የአንድነቷ ምልክት ሆኖ የኖረውን የዘውድ ምልክት አፍርሳ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ተንከራታለች።ይባስ ብላ ባለፉት ነገሥታት ሃውልት ሥርም ልጆቿ ቆመው ስለሃገራቸው፣ስለየጥቁር ህዝብ ነጻነት እና ስለየሰውልጆች ሰላም ሲሉ በውሃ ጥም እና በረሃብ ተንከራተው ያመጡትን የነጻነት ፋና እንዳይዘክሩ በጥይት በመሃል አዲስ አበባ እየተገደሉ ነው።ለእዚህ አብነት የሚሆነው የ127ኛው የዓድዋ በዓል በትናንትናው ዕለት የካቲት 23፣2015 ዓም ለማክበር በምንሊክ አደባባይ በተሰበሰበው ሰላማዊ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ላይ የተወረወረው አስለቃሽ ጋዝ አንዱ አብነት ነው።የኢትዮጵያ ጠላቶች አይደለም የኢትዮጵያ አንዱ ምሰሶ እና ምልክት ዘውዱን የነገስታቱን ሃውልስ ስር ስትቆም ይደነግጣሉ። መድኃኒቱ የዘውድ ምልክትህን መመለስ እና ሙሉ መብትህን ማሳየት ነው።
እንዴት ይመለስ? ችግሮች የሉበትም ወይ? ሌላ ክፍፍል አይፈጥርም ወይ? ለምን የአማራ ክልል? አሁን ያለውም ሆነ መጪው ሕገ መንግስቱ እንዴት ነው የሚደግፈው? እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአዕምሯችሁ እንደሚነሳ አስባለሁ። ወደ እያንዳንዱ ምላሽ ከመሄዴ በፊት ኢትዮጵያ ለምን በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ስትሆን ሁሌ መሻገር ያቅታታል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ መቅደም ይገባዋል።
የዘመናዊ ትምሕርት ቀመስ ነን የሚሉ ምሑራን ሁሉ ይህ ጥያቄ ሲነሳ ወድያው ከአፋችሁ ነጥቀው የሚያነሱት የተቋም አለመኖር ነው። ሃገራችን ተቋም አልገነባችም ይሏችኋል። ተቋም ማለት የአውሮፓ እና አሜሪካ ዲግሪ ላላቸው ምሑራኖቻችን ዘንድ መሃል ከተማ ቢሮ ያለው የጸዳ ህንጻ እና ከረቫት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚርመሰመሱበት፣በመላዋ ሃገሪቱ ቅርንጫፍ ያለው ወዘተ ይታያቸዋል።የእዚህ ዓይነት ተቋም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መንደር የገባ እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመንደሩ የሚያውቀው ዓይነት መዋቅር ሲያማትሩ ይታያሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የገነባችው ከቤተመንግስቱ እስከ የገበሬ ቤት ድረስ የደረሱ ተቋማት እንዳሏት የአውሮፓ እና አሜሪካ ዩንቨርስቲ መጽሓፎች ላይ ስለሌሉ አያውቋቸውም። ኢትዮጵያ ግን በክርስትናም ሆነ የእስልምና የእምነት ተቋማቷ ሃገሩን በየጊዜው ካስተዳደሯ መንግስታት መዋቅር እና ተቋም በላይ ህዝቡን ይዘው ዘመናት ተሻግረዋል። ከእነኝህ በተጨማሪ እና ምናልባትም በመንግስት ስሪት ታሪኳ ዘመናትን ያሻገራት ምሰሶዋ ግን የዘውድ ምልክቷ ነው።
የዘውድ ምልክት የሃገር ምሰሶ ለመሆኑ ከኢትዮጵያ ታሪክ የበለጠ ማስረጃ ለማሰባሰብ መድከም ባያስፈልግም ምሑራኖቻችን ዓይናቸውን ገልጠው ያስተማሯቸውን የአውሮፓ ሃገራን የዘውድ ምልክት እና ንጉሶች ዛሬም መኖራቸው ለግድግዳ ጌጥ ሳይሆን ሃገር መንታ መንገድ ላይ ስትቆም የዘውድ ምልክቱ ተቋማዊ ሚና ጠቃሚ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው ጃፓን፣እንግሊዝ፣ዴንማርክ፣ኖርዌይ፣ስዊድን፣ቤልጅየምን ጨምሮ በዓለም ላይ ወደ 43 ሃገሮች የዘውድ ምልክታቸውን ዛሬም ሳይጥሉ በዲሞክራሲያዊ የመንግስት ስሪት ውስጥ ሃገራቸውን እያበለጸጉ ነው።ኢትዮጵያ ከእነኝህ ሁሉ ሃገሮች በታሪክም፣በጥንታዊነትም ሆነ በመንፈሳዊ ሃብቶች ሁሉ በብዙ እጥፍ ትበልጣለች።የዘውድ ምልክቷን ግን አፍርሳ ጥላለች።
የመሽኮርመም ጊዜ ያብቃ!
የኢትዮጵያ ነገሥታት በዝባዥ፣ኋላ ቀር አስተሳሰብ እየተባልክ ያደክ ወጣት ይሄው ዛሬ የነግስታቱን በዘመናቸው የነበራቸውን የሥልጣኔ ጥግ፣የሕግ አክባሪነት፣ለሰው ልጅ ያላቸው ዋጋ እና ለአምላካቸው ያላቸው ፍቅር አሁን የጽንፍ መንገድ እየተከተሉ ሰው በቁም ከሚሰቅሉት፣ሕግ ምን እንደሆነ ከማያውቁ እና ለሆዳቸው ሃገራቸውን ከሸጡ ቡድኖች ጋር እያነጻጸርክ መፍረድ ነው። ዛሬ የምንሊክ ሃውልት ፊት እንዳትቆም ያደረጉህን ለመርታት ፍቱን መድሓኒቱ ዘውዱን እመልሳለሁ፣ንጉሴንም አነግሳለሁ ብለህ ፖለቲካውን መስቀል ብቻ ነው። ይህንን ደግሞ ለእልህ እና ለብሽሽቅ ሳይሆን የሃገር ምሰሶ ስለሆነ ከልብህ ታግለህ ምሰሶውን አቁመው። ይህ ለአንዳዶች የእብደት መንገድ ይመስላቸዋል።ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ አናቱ ላይ ስለዘውድ ክፉ የሚያወራ ጎጆ ለተሰራበት ሰው የእብደት መንገድ ሊመስለው ይችላል።ነገር ግን ሀውልቱን የፈራውን በአካል ስጋና ደም አልብሰህ ንጉሥ ሾመህ ነው ሥርዓት የምታስይዘው። በእዚህ ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቀድም ብዬ ለመግለጥ ሞክርያለሁ። አሁን እያንዳንዱን ለመለስ እሞክራለሁ።
አሁን ባለችው ነባራዊ ሁኔታ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ከአሁኑ እና ከሚመጡት ሕገ መንግስቶች አንጻርስ እንዴት ይታያል?
አሁን ያለንበት የብልጽግና የጽንፍ ኃይሎች ኢትዮጵያን በሚያውኩበት እና ፈጽሞ ለማጥፋት በተነሱበት ጊዜ ይህ የዘውድ ጉዳይ ትልቅ ዕድል እና አጋጣሚ ሆኖለታል ማለት ይቻላል። ከፖለቲካው ዐውድ አንጻር ስንበለከት በተለይ አማራ እየተባለ እየተሰደደ፣እየተገደለ እና የዐድዋ በዓልን ለማክበር ከሃውልቱ ስር ለመቆም ያልተፈቀደለት የኅብረተሰብ ክፍል በኩራት ይዞት የሚነሳው ታላቅ ፖለቲካዊ ኃይል ዘውዱን በቦታው መመለስ ነው።
ለኢትዮጵያ የዘውድ ምልክት የመንግስት ስሪት ጉዳይ አይደለም።የከበረ የባሕላችን መገለጫም ነው። ይህ የእኔ ባሕል አይደለም የሚል መብቱ ነው።ቢያንስ ግን አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ለአማራ ማኅበረሰብ የዘውድ ሥርዓቱ እና ንጉስ መኖሩ የባሕሉ መገለጫ ነው።ለኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ባሕሉ እንደሆነ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓት የባሕሉ መገለጫ ነው። አባ ገዳ ለኦሮሞ ባህላዊ መሪው እንደሆነ እና በክልሉ አስተዳደርም ሆነ በመንግስት ሥርዓት ውስጥ እንደማይገባ ሁሉ፣ ንጉስም ለአማራ ማኅበረሰብ በክልሉም ሆነ በመንግስት አስተዳደር ጣልቃ የማይገባ የባሕል መሪው፣መካሪው እና የቅርስ ባለ አደራው ነው። አሁን ሃውልት አይደለም እራሱን ንጉሡን ነው የማምጣት ተልዕኮ መሆን ያለበት። ይህ ትግል ይጠይቃል።ነገር ግን ህዝብ ሁሉ በአንድ ልብ ተስማምቶ የሰራውን ዓለሙ ቢቃወም እና ቢጮሕ የሚመጣ አንዳች ነገር የለም።
ከሕገ መንግስት አንጻር ለገዳ የተፈቀደ ባሕል ለአማራ ክልል የዘውድ እና የንጉስ ባሕላዊ ቅርስ የሚከልክል ህግ የለም።እያንዳንዱ ክልል የራሱን ባሕል የማበልጸግ፣የማሳደግ እና የመጠቀም ሙሉ መብት አለው።ይህ ህግ ደግሞ በአሁኑ ሕገመንግስት ብቻ ሳይሆን በመጪ መንግስታት ሕገመንግስት ላይም የማይሻር ነባራዊ ሕግ ነው።ስለሆነም የአማራ ክልል ይህንን የባሕላዊ ቅርስ ባለአደራ ንጉሱን እና የዘውድ ምልክቱን ከእነ ሙሉ ክብሩ የመመለስ ሙሉ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ መብት አለው።
ከኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ አንጻር ይህ ለእራሱ ለአማራ ክልልም ክፍፍል አይፈጥርም ወይ?
በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ የጎንደር፣የሸዋ፣የወሎ፣የትግራይ እና የጎጃም ንጉስ የሚሉ ታሪኮች አሳልፈናል። እነኝህ ታሪኮች እያሉም ኢትዮጵያ የዘውድ ምሰሶዋ አስፈላጊ እንደሆነ በማወቋ ይዛው ኖራ ህልውናዋን አስጠብቃለች።አሁን ባለንበት ዘመን ዋናው እና አስፈላጊው የዘውድ ምልክቱን የአማራው ማኅበረሰብ በአንድ ድምጽ ቆሞ ባሕላዊ መገለጫዬ የቅርሴ ባለአደራ ነው ብሎ መነሳት እና ማስከበር ነው እንጂ አሁን በእጁ ያለው እና በ1966 ዓም ያፈረስነው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የዘውድ ምክር ቤት ከመካከላቸው የሚመጥን ሰው የማዘጋጀት ሥራ ከመስራት በቀላሉ መጀመር ይቻላል። ዋናው ጽንሰ ሃሳቡን ይዞ መነሳት እና ለእዚህም በቂ የፖለቲካ፣የሞራል፣የስነ ልቦና እና የብቁ አደረጃጀት መገለጫ አድርጎ መጠቀሙ ነው አስፈላጊው ጉዳይ። ይህንን ደግሞ የብልጽግና አማራ ክልል የአሁን መሪዎች ቢቀበሉት እና ባሕላዊ ዕሴታችን ነው ብለው የበታኝ ኃይሎች የሚብከነከኑበትን ቁልፍ ጉዳይ ይዘው ወደ ፊት በመምጣት ቢጠቀሙበት እራሳቸው ይከብራሉ፣ታሪክ ይሰራሉ፣ከሕዝብም ከበሬታ ያገኛሉ። ሆኖም ግን እንደ ባለፉት ግማሽ ክፍለዘመናት እየተሽኮረመሙ ከታሹ ህዝብ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ ቅርሱን እና ባሕሉን ለመጠበቅ መንቀሳቀስ እና ያለፉ ንጉሥ ሃውልት ስር ልቁም ሳይሆን እራሱን ንጉሡን ይዤ መጣሁ ወደ የሚል የላቀ የፖለቲካ ልዕልና መሻገር እና ምህዋሩን መዘወር መቻል አለበት።
ስለሆነም የዘውድ ምልክቱን እና ንጉሱን ከእነሙሉ ክብሩ በአማራ ክልል በቤተመንግስት መሰየሙ እና ማክበሩ የክልሉን የኖረ ባሕላዊ ዕሴት እና አንድነት ብቻ ሳይሆን ነገ የቀረው የኢትዮጵያ ክፍልም ምልክት እና መሰባሰብያ ሁነኛ የነበረ ዕሴት ፍለጋ ሲባዝን አንዱ አጋዥ እና የቀውጢ ጊዜ ምሰሶ እንደሚሆን አያጠራጥርም። አሁን ግን የአማራ ክልል ለሕልውናውም ሆነ ለውስጣዊ አንድነቱ ከገጠር እስከከተማ ለማጠናክር እንዲሁም ለፖለቲካ ልዕልና እና የሞራል ዕሴት በግርግር የወደቀውን የዘውድ ምልክቱን ማንሳት እና ወደ ቦታው የመመለስ ታሪካዊ አደራ ከፊቱ ተደቅኗል።
መደምደምያው
ኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓቷን በማዘመን እና የፓርላማ ሥርዓት አድርጋ መቀጠል ካልቻለች ላለፉት ግማሽ ክ/ዘመን የደረሰባት መንከራተት እንደሚደርስባት ቀድመው በ1966 ዓም የተናገሩ ምሑራን ነበሩ። ከእነኝህ ውስጥ ቀዳሚው ደራሲ እና ዲፕሎማት ሓዲስ ዓለማየሁ ነበሩ። እኝህ የፍቅር እስከ መቃብር፣የልምዣት እና ሌሎች መጻሕፍት ደራሲ እና የኢትዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ሓዲስ ዓለማየሁ የ1953 ዓም የእነጀነራል መንግስቱ ንዋይ እንቅስቃሴ እና የ1966 ዓም የኢትዮጵያ አብዮት ሲቀጣጠል በኢትዮጵያ የሚመጡት መንግስታት ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀድመው ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ይሄውም ''ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?'' በተሰኘው መጽሓፋቸው ላይ ኢትዮጵያ የዘውድ ምልክቷን ካፈረሰች የሚገጥማትን ፈተና ዘርዝረው አስቀምተዋል።ዛሬ የሚገባው ካለ እና ጊዜው አሁን መሆኑ ለተረዳ፣እንዲሁም ይህንን በሙሉ ልብ ይዞ ሊነሳ ከሚገባ ውስጥ ባሕሉ እና የቅርስ ባላደራ እና መገለጫው የአማራ ክልል ከወደቀበት አቧራውን አራግፎ ቢያነሳው እራሱንም ኢትዮጵያንም ይጠቅማል።የንጉስ ሃውልት ሥር አይደለም እራሱን ንጉሡን ነው የማመጣው ብሎ መነሳት የህልውናው ማጥበቅያ ሁነኛ ፖለቲካ ነው። ፖለቲካው ደግሞ ባለዐራት ጎማ ነው። ወደኋላም ያስኬዳል የኢትዮጵያ ታሪክ የዘውድ ታሪክ ነው እና እንዲሁም አሁን ላይ በታኝን ይመታበታል፣በዓለም አቀፍ ግንኙነት ይናኝበታል፣በመጨረሻም ለመጪ የሃገር ህልውና መሰረት ያጠብቅበታል።የዘውድ ጉዳይ ያለው የፈጣሪ ኃይል እና ከኢትዮጵያ ነፃነት እና ኃይል ጋር ያለውን ቁርኝት በተመለከተ በራሱ ሌላ አጀንዳ ነው። ይህም ግን የሚናቅ ጉዳይ አይደለም። ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ሰላም አጥታ የተንከራተተች ሃገር እና አሁንም ድረስ የዘውድ ምልክታቸው ከስልጣኔያቸው ጋር ያልተጋጨባቸውን ሃገሮች ለአብነት መመልከት ነው። የመጨረሻው መጨረሻ በአፍሪካ ያሉ መንግስታት የፌድራል ክልሎቻቸው ዘውድ እና ንጉሥ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ክብር ይሰጣቸዋል።ለምሳሌ በዑጋንዳ ማዕከላዊ ክፍል የቡጋንዳ ግዛት ንጉሥ አላት።በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችም በናሙናነት ማንሳት ይቻላል። በኢትዮጵያ አማራ ክልል የዘውድ ቅርሱን መልሶ የመጠበቅ ሙሉ ሕገመንግስታዊ መብት የማይሸራረፍ እና ማንንም እንዲገሰው መብት ሊሰጠው የማይችል ነው።
==============////===========
No comments:
Post a Comment