ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, February 26, 2023

ሦስት ሳምንት ያልሞላት አራስ እናትን ቤት በግሪደር አፍርሶ በከተማ ዙርያ ከተማ ልመሰርት ነው ያለው የኦሮምያ ክልል ፕሮጀክት፣እውን የከተማ ፕሮጀክት መስፈርት ያሟላል?

የኦሮምያ ክልል በሸገር ፕሮጀክት ስም የአዲስ አበባ ዙርያ ነዋሪዎችን ቤት ሲያፈርስ
ፎቶ ቢቢሲ አማርኛ።

===========
  • ስሜት ፕሮጀክት አይሆንም።ቂምም ልማት አይሆንም። ምኞትም ውጤት ሆኖ አያውቅም።
  • በዓለም ላይ በዋና ከተማ ዙርያ ከተማ ልገነባ ነው የሚል ፈላስፋ እስካሁን አልተሰማም።የእዚህ ዓይነት ፕሮጀክት በመሰረታዊ የከተማነት መርሕ (Basic Principle of Urbanization) ላይም አይታወቅም።
  • አዲስ አበባን የፈጠራት የነገስታቱ ነጋሪት እና አዋጅ ሳይሆን የንግድ እና እንዱስትሪ መስፋፋት ነው።

በእዚህ ጽሁፍ ስር የሚከተሉትን ርዕሶች ያገኛሉ 
  • በዋና ከተማ ዙርያ ከዋና ከተማ የተነጠለ ሌላ ከተማ?
  • የሸዋ ኦሮሞን ለመግፋት ውስጣዊ ዓላማ የያዘው የሸገር የከተማ ፕሮጀክት፣
  • የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የሸገርን ፕሮጀክት በሶስት ምክንያቶች አይደግፉትም።
  • በሸገር ፕሮጀክት ስም መሬታቸውን የተነጠቁት አሳዛኝ ዜጎች ቢቢሲ እንደዘገበው ታሪክ
===========
=========
ጉዳያችን ልዩ
=========


በዋና ከተማ ዙርያ ከዋና ከተማ የተነጠለ ሌላ ከተማ?

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ስድስት ከተሞችን በማጣመር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 የወረዳ አስተዳደሮችን በማዋቀር  ሸገር ከተማ እገነባለሁ የሚለው የኦሮምያ ክልል ፕሮጀክት በርካታ ጥያቄዎች በውስጡ ይዟል። ከተማ ጥሩ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለማልማት እፈልጋለሁ ያለ የማንንም አልሚ እንቅፋት መሆን አይፈልግም።ስለሆነም የሸገር ከተማ ለማልማት እፈልጋለሁ ያለው የኦሮምያ ክልልን በማልማቱ የሚቃወመው የለም። ምንም ይሁን ምን ዛሬ የለማው ነገ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ሃብት ስለሆነ ማልማት በራሱ ችግር ሊሆን አይችልም። ችግር የሚሆነው የልማቱ ግብ ነገ ህዝብ የሚያስታርቅ ነው የሚያጣላ? የሚለው ነው።ከተማነት በባህሪው ህዝብ የሚያስታርቅ ነው።ከተማነት በቋንቋ እና በጎሳ መታጠር እና ማጠር አይደለም።ከተማነት ከሃገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰቦች የሚንሸራሸሩበት አንዱ ስለሁሉም፣ሁሉም ስለአንዱ የሚያስብበት ድንበር የለሽ የአኗኗር ዘይቤ የተላበሰ የቅርቡንም ሆነ የሩቁን እየተቀበለ ከአካባቢው ጋር አስማምቶ የሚያኖር ቦታ ነው።

በዓለም ላይ ሀገሮች በዕቅድ ከተማ ይገነባሉ።በአፍሪካም ይህንን የሚያደርጉ አሉ።ለምሳሌ በናይጄርያ የሌጎስን ከተማ በአቡጃ አዲስ ከተማ የመገንባት ሥራ ሊጠቀስ ይችላል። አቡጃ ግን በሌጎስ ከተማ ዙርያ በከተማ ዙርያ ከተማ ተደርጋ አልተገነባችም። በአቡጃ እና ሌጎስ ከተማ መሃል የ715 ኪሜ እርቀት አለ።በዓለም ላይ በዋና ከተማ ዙርያ ከተማ ልገነባ ነው የሚል ፈላስፋ እስካሁን አልተሰማም።የእዚህ ዓይነት ፕሮጀክት በመሰረታዊ የከተማነት መርሕ (Basic Principle of Urbanization) ላይም የለም አይታወቅም። ከተሞች በህዝብ ብዛት አሰፋፈር ይመሰረታሉ።ለህዝቡ መስፈር ምክንያት ከሚሆኑት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ምጣኔ ሃብታዊ ምክንያት ነው።ምጣኔ ሃብታዊ ምክንያቶቹ ደግሞ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ናቸው። በንግድ እና ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ንግድ እስከ ግማሽ ድረስ የሚንቀሳቀስባት የምትባለው አዲስ አበባ ዙርይ የሚመሰረተው ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር ምን ዓይነት የንግድ ግንኙነት ይኖረዋል? ከአምስት ሚልዮን በላይ የሆነ ህዝብ የያዘ ከተማ የከበበ ሌላ ከተማ ምን ዓይነት ነው? ከተሞች ሲሰፉ የሚቀመጥላቸው ሕግ እና አሳሪ ማኅበራዊ ግንኙነት ይዘው አይደለም። በራሳቸው መስተጋብራዊ፣ታሪካዊ እና ትውልዳዊ የባሕል ውርርስ እንዲሁ በነጻነት የሚያድጉ እና የሚሰፉ ናቸው።ይህ ነው የከተሞች ባህሪ። የኦሮምያ ክልል ከአምስት ሚልዮን በላይ ሕዝብ የከበበ በዋና ከተማ ላይ ሌላ ዋና ከተማ የመፍጠር ፍልስፍና ከመሰረታዊ የከተሞች እድገት አንጻርም የተቃረነ ነው። እየተፈለገ ያለው የጎሳ ፖለቲካ የሚያቀነቅነው ክልል ጎሳ አልባ የሆኑ ግን ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያቀነቅኑ የከተሞችን የፍልስፍና ጥግ በጎሳዊ አስተሳሰብ ለመቅረጽ የሚሞክር ፖለቲካዊ ግብ ያለው ነው። ማኅበራዊ ሳይንስ በፖለቲከኞች ቢሮ ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ በቀላሉ የሚዘወር የሚመስላቸው የኦሮምያ ክልል አማካሪ ምሁራን በዘርፉ ያላቸው ደካማ ዕውቀት ከማስደንገጥ አልፎ ጤንነታቸው በራሱ አሳሳቢ አይደለም ማለት አይቻልም።

የሸዋ ኦሮሞን ለመግፋት ውስጣዊ ዓላማ የያዘው የሸገር የከተማ ፕሮጀክት


የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የሸገርን ፕሮጀክት በሶስት ምክንያቶች አይደግፉትም።

የኦሮምያ ክልል የሸገር የከተማ ፕሮጀክት በሸዋ ኦሮሞ ላይ የተጫነ የግድ ፕሮጀክት ነው።ፕሮጀክቱን ከአባገዳዎች፣እስከ የአዲስ አበባ ዙርያ ነዋሪ የኦሮምያ ተወላጆች፣ከገበሬ እስከ ሰራተኛ ተቃውሞታል። ተቃውሟቸውንም በሺህ የሚቆጠሩ የሸዋ ኦሮሞዎች ሰልፍ በመውጣት ተቃውመውታል። ይህንንም ኢሳትን ጨምሮ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ዜና ዘጋቢዎች ዘግበውታል።ይህም ሆኖ ግን ዛሬ አቶ ሽመልስ ፕሮጀክቱ በሕዝብ ተቀባይ የሆነ ይመስል ዛሬ አባ ዱላ እና አብረዋቸው ያሉትን በዙርያቸው ሰብስበው ከተማው ተመሰረተ ብለዋል። የሸዋ ኦሮሞዎች የሸገርን ፕሮጀክት በሶስት ምክንያቶች አይደግፉትም።ይሄውም 

1ኛ/ የመሬታቸውን ዋጋ በፍጥነት ስላወረደው።

በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ ባለይዞታ የሸዋ ኦሮሞዎች የመሬታቸው ውድነት እና ተፈላጊነት አንዱ ምክንያት ከአዲስ አበባ ጋር ያላቸው ቁርኝት ነበር።አዲስ አበባ ጋር በመጠጋት በራሱ የመሬቱ ዋጋ ተፈላጊ ያደርገዋል።አዲስ አበባ እየሰፋ ሲሄድ የእነርሱም ቦታ መጠቃለሉ ስለማይቀር ቦታቸው አይደለም ለመሸጥ ለመከራየት ሳይቀር ዋጋው እየጨመረ ስለሚሄድ ለልጆቻቸው ሳይቀር ቅርስ ሆኖ ነበር የኖረው። የአቶ ሽመልስ 'አላዋቂ ሳሚ' ዓይነት ምክር ግን በዛሬዋ የሸገር ከተማ ምስረታ ብቻ የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ዙርያ ያለው የመሬታቸው ተፈላጊነት ወርዶ ማደሩ ስለሚታወቅ ይህ ፕሮጀክት ሲሳይ ሳይሆን ችግር ሆኗል።

2ኛ/ ፕሮጀክቱ ከሸዋ ውጭ ያሉ ኦሮሞዎችን በአዲስ አበባ ዙርያ ለማስፈር ያለመ እና ሥራ የጀመረ በመሆኑ።

የሸገር ፕሮጀክት አንዱ የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ያስቆጣበት ምክንያት ከእዚህ በፊት በአቶ ለማ መገርሳ ተፈጽሟል የተባለው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከሸዋ ውጭ የሆኑ የኦሮሞ ማኅበረሰብ የማስፈር ሥራን በሸገር ፕሮጀክት ለመቀጠል በመታሰቡ እና ይህም በሚልዮን የሚቆጠሩ በኢትዮጵያዊነታቸው ጥብቅ ናቸው የሚባሉትን የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በኦነግ ደጋፊ ከሸዋ ውጭ በሚመጡ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች የመተካት ዓላም መያዙን ስለሚረዱ ነው። በእዚህም ሳብያ በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ቀስ በቀስ ይዞታቸውን እየለቀቁ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው።

3ኛ/ አዲስ አበባ ይፈጸም የነበረ ጉዳይ በመቶ ኪሎ ሜትሮች እርቀት እንዲጓዙ ስላደረገ።

በአዲስ አበባ ዙርያ የነበሩ ነዋሪዎች የመሰረታዊ አገልግሎት የመንግስት የቢሮ አገልግሎት ያገኙ የነበረው በቅርባቸው ካለው የአዲስ አበባ አስተዳደር የነበረ ሲሆን አሁን እንደ ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ሱልልታ ኤር ሞጆ የመሳሰሉት ከተሞች የአስተዳደር አገልግሎትም ሆነ ሌሎች ተዛማች አገልግሎቶችን ለማግኘት ቅርባቸው ወዳለው ወደ አዲስ አበባ እንዳይመጡ አዲሱ የሸገር ፕሮጀክት ስለሚያግዳቸው እጅግ እሩቅ ወደ ሆኑ አዋሳኝ የኦሮምያ ክልል ለመሄድ ይገደዳሉ። በእዚህም ነዋሪዎቹ በጎሳ ፖለቲካዊ የከተማ ምስረታ ፕሮጀክት ምን ያህል እንደተጎዱ የሚያውቁት እነርሱ ናቸው።

ለማጠቃለል የሸገር ፕሮጀክት በትክክል እንደ የኦሮምያ ክልል አገላለጽ ''የስማርት ከተማ'' እንመሰርታለን የሚለውን አባባል የክልሉን ሃብት ሙሉ በሙል ቅንጡ ከተማ መገንባት ላይ ለማዋል ካልታሰበ በቀር በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ሃገሮችም ቢሆን በዋና ከተማ ዙርያ ሌላ ከተማ እንገነባለን የሚል ቅዠት ውስጥ አልገቡም። የኦሮምያ ክልል ይህ ፕሮጀክት ለከፍተኛ የሙስና እና የሃገር ሃብት መባከን ብቻ ውሎ ጥቂት ቅምጥል ባለስልጣናት ኪሳቸውን የሚያደልቡበት ፕሮጀክት ሆኖ ልክ የኦሮምያ የኢኮኖሚ አብዮት ሲባል እንደነበረው እና አሁን የት እንዳለ የማይታወቀው ፕሮጀክት ሁሉ መቀለጃ እንዳይሆን ያሰጋል። ኢትዮጵያ የበላው ሲሄድ የሚበላው ሲመጣ የሚኖርባት ሃገር መሆኗ ያሳዝናል።ይህ ጉዳይ ዐይን ባወጣ አምባገነንነት እና የጎሳ ፖለቲካ ተሸፍኖ የሃገር ሃብት እንዲሁ ሲባክን ማየት አሳዛኝ ነው።ፕሮጀክቱ ፖለቲካው ግርግር እና ከአዲስ አበባ ጋር መነታረክያ አጀንዳን በሸገር ከተማ ስም ተቋማዊ የኦሮምያ ክልል ዲፓርትመንት ከመክፈት ባለፈ እና የሸገር ከተሞች የተባሉትን ዋና ዋና መንገዶች በመቀባባት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ የሸገር ፕሮጀክት ትርፍ የሚሆነው የባለስልጣናቱ ኪስ መድለብ ብቻ እና ብቻ ነው። 

የመጨረሻው መጨረሻ ማሳረግያ ዓረፍተነገሬ ግን ሃገር ኢንዱስትሪ ሳትገነባ ቅምጥል ስማርት ከተማ ለመገንባት ስትጋጋጥ ማየት ምን ያህል አላዋቂነት ነው? ስማርት ከተማ ውስጥ በእንዱስትሪ ያላመረተ፣እርሻ ያላረሰ ዝም ብሎ ከተማ እየተደረደረለት ጥፍሩን እያጸዳ እንዲኖር ነው? እንዱስትሪ እና ንግድ ከተማን ይፈጥራል። አዲስ አበባን የፈጠራት የነገስታቱ ነጋሪት እና አዋጅ ሳይሆን የንግድ እና እንዱስትሪ መስፋፋት ነው።የኦሮምያ ሸገር ፕሮጀክት የፕሮጀክትነት ትንሹን መስፈርትም አያሟላም።ፕሮጀክት ሕዝብ ካልተውያየበት እና ካልተስማማበት በትሪልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢፈስበት አይሳካም።ቢሳካም ዕድሜ የለውም። አዬ! አለማውቅ ደጉ።በምኞት ፈረስ አስጋልቦ እንደ አቶ ሽመልስ ጥቁር መነጸር አድርጎ በንግግር ማሳመር መጎማለል ሲያመጣ ይገርማል! 

ከእዚህ በታች በሸገር ፕሮጀክት ስም ሦስት ሳምንት ያልሞላት አራስ እናትን ቤት በግሪደር ከማፍረስ ጀምሮ በሌሎች ዜጎች ላይ የደረሰውን ግፍ ቢቢሲ አማርኛ የዘገበውን ሙሉ ዘገባ ይመልከቱ።

 

ከሰሞኑ ቤቷ የፈረሰባት የ20 ቀኗ አራስ እና የሸገር ከተማ ነዋሪዎች እሮሮ


ቢቢሲ አማርኛ
25 የካቲት 2023
==========
“የቤቱን ጣሪያ ከቤት ሳልወጣ በላዬ ላይ አፈረሱት። ቆርቆሮውን ቤት ውስጥ ሳለሁ ነው የሚነቅሉት። ዕቃ ለመሸከፍም ጊዜ የለም” ይህንን የተናገረችው ከሰሞኑ በሱልልታ አካባቢ መኖሪያ ቤቷ የፈረሰባት እስከዳር ናት።

ለደኅንነቷ ሲባል ትክክለኛ ስሟ የማይገለጸው እስከዳር ከተገላገለች 20 ቀኗ ነው። የአራስ ጀርባዋም አልጠናም።

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሱልልታ ለሁለት ዓመት የኖረችበት ቤት ሕገወጥ ነው ተብሎ በፀጥታ ኃይሎች የካቲት 16/2015 ዓ.ም. ፈርሶባት ዘመድ ላይ ወድቃለች።

ከሰሞኑ እየተካሄደ ካለው መጠነ ሰፊ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ከገለጸው የቤት ፈረሳ ጋር ተያይዞ ያለ ምንም ማስጠንቂያ፣ ምትክ ሳይሰጣት ቤቷ ፈርሶ “ዘመድ ላይ ወድቄያለሁ ብላለች።”

ቤት ፈረሳው የተካሄደው ትናንት የካቲት 16/2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት መሆኑን የምትናገረው እስከዳር በወቅቱም የተሰማት ድንጋጤ ቃላት አይገልጻውም ብላለች።

በእስከዳር አገላለጽ ጠመንጃ ታጥቀው የመጡ ግብረ ኃይሎች በዚህች ዕለት መጥተው የውጪውን አጥር በር ነቃቀሉ። ከዚያም ወደ ዋናው ቤት መጥተው ጣሪያውን ካፈራረሱ በኋላ ዕቃዋን ይዛ እንድትወጣ ተነገራት።

“እቃችንን እንድናወጣ ነግረውን ይሄዱና ዶዘር ይዘው በመመለስ ያርሱታል” ትላለች።

ልጇን ይዛ ከቤት አልወጣም ብላ የነበረ ቢሆንም፣ ተለምና ወደ ግቢው እንድትወጣ በኋላም በዛፍ ጥላ ስር ተጠልላ “አሻፈረኝ አልወጣም ብዬ የነበረ ቢሆንም ተለምኜ ወጣሁ” ትላለች።

አፍራሾቹ መሳሪያ ታጥቀው እና አቀባብለው በግራ እና በቀኝ ቆመው ነበር ብትልም አልወጣም ለማለት “ስለደነገጥኩ አልፈራሁም” ብለላች።

ቤቷ ከፈረሰ በኋላ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና “ፈጣሪ ይድረስ ነው የሚባለው” ስትል ከቢቢሲ ጋር በስልክ በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ስድስት ከተሞችን በማጣመር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 የወረዳ አስተዳደሮችን በማዋቀር በተመሠረተችው ሸገር ከተማ ሱልልታ ልዩ ስሙ ቃርዮ ነዋሪ ናት።

ቤቷን ከአርሶ አደር ላይ መሬት ከገዛ ግለሰብ የገዛችው እስከዳር ውል ተፈራርማ ብትገዛውም ካርታ የለውም።

በሁለት ክፍሏ ቤት ከአራስ ልጇ በተጨማሪ ነፍሰ ጡር እህቷ ከባሏ ጋር አብረው ይኖሩ ነበር።

ስትገዛው ሁለት ክፍል ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ማዕድ ቤትም ጨምረውበታል።

ከሰሞኑ አስተዳደሩ ሕገወጥ ግንባታ በሚል እንደ እስከዳር ያሉ በርካቶች ለረጅም ዓመታት የኖሩበት ቤት ፈርሶባቸዋል።

“ለአስራ አምስት ዓመት የኖርንበት ቤት ፈረሰብን”

በአዲስ አበባ የካ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በኦሮሚያ ክልል፣ በሸገር ከተማ ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ሱልልታ ኤር ሞጆ፣ ገላን ሰፋ ያለ የቤት ፈረሳ እየተካሄደ እንደሆነ አቶ ተስፋዬ ገመቹ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ የፈረሱ ቤቶችም ከተሰሩ ከ15 እስከ 20 ዓመታትም የቆዩ መሆናቸውም ተገልጿል።

ቢቢሲም በሱልልታ ለአስራ አምስት ዓመት የኖሩና ከሰሞኑ ቤታቸው የፈረሰባቸውን ወይዘሮ አስቴር በሚያናግርበት ወቅት እያለቀሱ እና ሳግ ድምጻቸውን እየቆራረጠው “እኛ እንደ ኢትዮጵያዊ አልተቆጠርንም” ብለዋል።

እስከዳርም ሆነ ወይዘሮ አስቴር ቤታቸው ተለይቶ እንደፈረሰ ገልጸው፣ ማስጠንቀቂያም ሆነ ስለደረሰባቸው ችግር ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት አካል የለም ይላሉ።

አስራ አምስት ዓመት በዚህ ስፍራ እንደኖሩ የሚናገሩት ወ/ሮ አስቴር በመቶ ሺህ ብሮች (አምስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) ያለቻቸውን ጥሪት አሟጠው ቤቱን እንደገዙት ያስረዳሉ። የመብራት አገልግሎት ካስገቡም አንድ ወር ደፍኗል።

ንግግራቸው በእንባ እየተቆራረጠ፣ የአካል ጉዳተኛ መሆናቸውን እየተናገሩ፣ ጥዋት ማታ እያለቀሱ እንደሚውሉም በሐዘን ተሰብረው ተናግረዋል።

ወይዘሮ አስቴር ጥሪታቸውን ያሟጠጡበት እና ለዚህን ያህል ዓመታት የኖሩበት ቤት እንዲህ ፈርሶ ሜዳ ላይ ሲወድቁ የተሰማቸው ስሜት “ውሻ እንኳን ክብር አለው” በሚል ነው የገለጹት።

ወይዘሮ አስቴር ሁለት ክፍል ያረፈበትን 200 ካሬ ሜትር ቦታ የገዙት ከአርሶ አደር ሲሆን እርሳቸውም ሌሎች ክፍሎች ጨምረውባቸዋል።

በሱልልታ አካባቢ ቤቶች መፍረስ ከጀመሩ 20 ቀናት አካባቢ እንደሆነ የምትናገረው እስከዳር የሚፈርሱ ቤቶች የኤክስ ምልክት በሰማያዊ ቀለም አንደተደረገባቸው ታስረዳለች። የእሷም ቤት ምልክት ቢኖረው ምክንያቱን ያስረዳቸው አካል ወይም መቼ እንደሚፈርስ የገለጸላቸው እንደሌለ ነው የምትናገረው።

አንዳንድ ቤቶች ከዚህ ቀደም ምልክት ተደርጎባቸው ለዓመታት ሳይፈርሱ እና ነዋሪዎቹም ሳይወጡ ስለቆዩ ነገሩ ግልጽ አልነበረም ትላለች።

“ቤታችን የፈረሰበትን ምክንያት አልተነገረንም” በማለት የሚናገሩት ሁለቱም ግለሰቦች ገንዘብም እንዲከፍሉ የተጠየቁ እና ገንዘብም በቀበሌ ከፍለው ከመጡ በኋላም እንደፈረሰ ያስረዳሉ።

ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች በብሔራቸው ምክንያት ኢላማ ተደርጎ ቤታቸው እንደፈረሰ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ኢሰመጉም እነዚህ ቅሬታዎች እንደደረሱት አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

ይህንን ለማጣራት ወደ ሸገር ከተማ ከንቲባ በተደጋጋሚ ብንደውል ልናገኛቸው ስላልቻልን ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

ከቤት ፈረሳ ጋር ተያይዞ ደረሱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች

ኢሰመጉ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከቤት ፈረሳ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የካቲት 15/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በፈረሳዎቹ ወቅት ከመንግሥት በኩል ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ መኖሩን የጠቆመው መግለጫው በዚህም የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል ብሏል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በፀጥታ ኃይሎች እና ቤቶቻቸው በሚፈርሱባቸው ነዋሪዎች መካከል ውጥረቶች መፈጠራቸውን መግለጫው ጠቅሶ፣ ቁጥራቸው ያልተጠቀሱ ሰዎችም ስለመታሰራቸው ኢሰመጉ መረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ብሏል።

በለገጣፎ፣ ለገዳዲ አርባ አራት ማዞሪያ ኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ለአስራ አምስት ዓመታት የኖሩት አቶ ሁሴን ከሰሞኑ በነበረው ውጥረት አንዲት ነፍሰ ጡር በጥይት ተመትታ ምኒልክ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በርካታ ወጣቶች መታፈሳቸውን፣ መታሰራቸውን እና ድብደባ መፈጸሙንም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ሁሴን ለአስራ አምስት ዓመታት የኖሩበት ቤታቸው የፈረሰው የካቲት 11/2015 ዓ.ም. ነው። የእሳቸው ቤት በፈረሰበት ወቅት በተጨማሪ የ700 አባወራዎች ቤት ፈርሷል።

እሳቸውም በአካባቢው እንዳሉት ነዋሪዎች ትንሽ ቤት ያላትን 200 ካሬ ሜትር ከአርሶ አደር ላይ በ105 ሺህ ብር በውል ተፈራርመው የገዙት በ2000 ዓ.ም ነበር። በዓመታትም ውስጥ ቤቱን አስፋፍተው የሚከራዩ ቤቶችም ሰርተዋል።

በአካባቢው ለዓመታት ሲኖሩ የልማት አዋጥተዋል እንዲሁም ነዋሪ ናችሁ በሚል ዕውቅና ተሰጥቶን ጤና መድንም አውጡ ተብለናል ይላሉ።

“መብራት እና ውሃ በልማት ከፍለን ሊገባልን ትንሽ ቀን ነበር የቀረው” የሚሉት አቶ ሁሴን የአካባቢው ነዋሪ አንድ ሚሊዮን 400 ሺህ ብር መክፈሉን ገልጸው፣ ሕጋዊ ማህተም ያለው ደረሰኝ እንደያዙም ይናገራሉ። መብራት ኃይል ተሂዶም ተከፍሎ ሰሞኑን መብራት ሊቀጠል ጫፍ ደርሶ እንደነበርም ነው ለቢቢሲ የገለጹት።

ከአንድ ወር በፊት የአካባቢው አመራሮች ሰብስበዋቸው ባዶ ቤቶች የሌቦች መሰብሰቢያ እንዳይሆኑ ሊያፈርሷቸው መሆኑን እንደገለጹላቸው እና በእነዚህም ቤቶች ላይ ምልክት መደረግ መጀመሩን ያስረዳሉ።

ሆኖም አቶ ሁሴን እንደሚናገሩት ባዶ ቤቶቹን አፍርሰው ሲጨርሱ ሌሎችንም ማፍረስ እንደጀመሩ እና ለዚህም ተግባር ፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ የአካባቢው ወጣት እና ልዩ ኃይል በጋራ ተጣምረው እየሰሩ ነው ብለዋል።

ቤት ማፍረሱም ጋር ተያይዞ ሕዝቡ ሲወጣ በጥይት የተመቱ ሰዎች አሉ ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች በር እየተገነጠለ፣ እስከ 40 ሺህ ብር አንዲከፍሉ የተጠየቁ አሉ ሲሉም ይወቅሳሉ።

በአካባቢያቸው የነበረ መስጊድ ጭምር በአፍራሽ ግብረ ኃይል ጣራው ተነቅሏል ብለዋል። “መስጊዱ ፈርሷል፣ ቁርዓኑ ተበታትኗል” ሲሉም በቁጭት ይናገራሉ።

“አንፈልጋችሁም ውጡ እየተባልን ነው” ይላሉ።

“ባለቤቴ ከወለደች ገና ሁለት ወሯ ነው” የሚሉት አቶ ሁሴን በአሁኑ ወቅት ከሁለት ልጆቻው ጋር ዘመድ ላይ ወድቀዋል።

“የምሄድበት ሁሉ ተምታቶብኛል” ብለዋል።

“መውደቂያ የለንም”

“ለዓመታት ያፈራነው ንብረት በአስር ደቂቃ ውስጥ ወድሞ፤ አሁን ደግሞ በዚህ የኑሮ ውድነት፣ ቤት ኪራይ አዲስ አበባ ላይ ጣሪያ በነካበት ሰዓት የት እንገባለን? መውደቂያ የለንም። ልጆቻችን ትምህርት ቤት ውሰዱ እያሉን ነው። የት እንውሰዳቸው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

አቶ ሁሴን ልጆቻቸውን ይዘው ዘመድ ቤት ቢጠጉም፣ በአርባ አራት ማዞሪያ ለአስራ አምስት ዓመታት የኖሩት ሌላኛው የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሰይድ ሦስቱን ልጆቻቸውን ወደ ክፍለ ሃገር ልከዋል።

በአሰሪና ሠራተኛ አገናኝነት የሚተዳደሩት አቶ ሰይድ በአንድ ሺህ ብር ትንሽ ቤት ተከራይተው እቃቸውን በሸራ ውጭ ላይ አስቀምጠው ነው ያሉት።

አብዛኛው ነዋሪ በየእምነት ተቋማቱ ተጠግቶ፣ አፈር ላይ የተኙ፣ እቃቸው ውጭ ተበትኖ ያሉ፣ እዚህም እዚያም የወደቁ፣ በዘመድ አዝማዱ የተጠለሉ ሲሆን ቤተሰብ የሌላቸው ደግሞ ሜዳ ላይ ወድቀው “በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ናቸው” ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ እቃቸውን እየጫኑ ወደ ወደ የመጡበት እየሄዱ ሲሆን ደብረ ብርሃን መጠለያም የገቡ እንዳሉ አቶ ሰይድ ያስረዳሉ። እቃቸውን ጭነው ወደተለያዩ ክልሎች ለመሄድ መኪናዎች ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ይጠይቃሉ ብለዋል።

እስከዳር መኪና ተኮናትራ መራ ቤቴ አካባቢ ለማቅናት ያሰበች ሲሆን፣ አቶ ሰይድ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መቶች ጉባኤው አቶ ተስፋዬም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ በጣም የሚያሳስብ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

በላስቲክ ዳስ ሰርተው የሚኖሩ፣ ተጨማሪ ጉዳት እየደረሰባቸው እና ለሌሎች አደጋዎች እየተጋለጡ መሆኑንም በመጥቀስ “ሕግን ማስከበር ተገቢ ቢሆንም ሰብዓዊነት ሊሰማን ይገባል” ይላሉ።

አብዛኞቹም ነዋሪዎች የፈረሰባቸው ቤት ከ15 ዓመት በላይ የኖሩበት እንደሆነ ገልጸው “መጀመሪያ ላይ ሕገወጥ ናቸውም ከተባሉ በእንጭጩ (ከመነሻው) መቅጨት ይቻል ነበር” ሲሉም ያስረዳሉ።

አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት “በአካባቢው ያለው ነዋሪ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ሰፍቶ፣ ትምህርት ቤት ልጆቻቸው እየተማሩ፣ ጥሪታቸውን አሟጠው የሰሩት ቤት ፈርሶ እሱን እንዲያጡ ተደርጎ፣ በዚህ ሁኔታ ሕግን ማስከበር ተገቢነት አለው ወይ የሚል ጥያቄን እንድንጠይቅ ነው የሚያደርገን።”

“ፈረሳው ወጥነት የሌለው አሰራር ታይቶበታል”

ኢሰመጉ ከቤት ፈረሳ ጋር ተያይዞ ባወጣው መግለጫ አንዳንዶቹ የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ፣ ሕጋዊ ቤቶችም ጭምር የፈረሱበት መሆኑን አስፍሯል።

በተጨማሪም አንዳንድ ቤቶች ደግሞ የመብራት እና የውሀ አገልግሎት የመንግሥት ተቋማት ያስገቡላቸው እና ይህ በሚደረግበት ወቅት ምንም አይነት የሕጋዊነት ጥያቄ ያልተነሳባቸው፣ አንዳንዶቹ የፈረሱ ቤቶች ከተሰሩ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ያሳለፉ ናቸው ብሏል።

እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች የፈረሳ ድርጊቱ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄን እያስነሱ ነው ብሏል።

ሕጋዊ የሆነ ካርታ ያላቸው ሳይቀሩ፣ ሳይት ፕላን ያላቸው ቤቶችም እንደፈረሱ አቤቱታዎች እንደረሷቸው፣ እንዲሁም አንዳንዶቹ ሕገወጥ ቤት ገንብተው ያልፈረሱባቸው ቤቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት አቶ ተስፋዬ፣ ወጥነት የሌለው አሰራር መሆኑን ያሰባሰቧቸውን መረጃዎች ዋቢ አድርገውም ይናገራሉ።

በስፋት እየተፈጸመ ነው በተባለው ፈረሳ አንዳንዶቹ ከጫካ ፕሮጀክት ጋር፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሸገር ከተማነት ጋር ስለመያያዙ አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ።

እስካሁን ምን ያህል ቤቶች ናቸው የፈረሱት? በዚህስ ምን ያህል ሰዎች ተጎዱ ስለሚለው ጥልቅ ምርመራ እንደሚያደርጉና በቅርቡም ይፋ ይሆናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ምክንያቶች ቤቶች የሚፈርሱ ቢሆንም አሁን በስፋት እየተደረገ መሆኑን ከደረሷቸው መረጃዎች ተረድተዋል።

የደረሱ አቤቱታዎችን ለመርመር ኢሰመጉ ሦስት መርማሪዎች እና አንድ አሽከርካሪ ወደ ሰበታ ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ የላከ ሲሆን አራቱም ሠራተኞቹ ለእስር መዳረጋቸውን አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል።

ባልደረቦቹ በገላን ጉዳ ፖሊስ መምሪያ ለስምንት ቀናት ያህል ታስረው በዋስ ቢለቀቁም ጉዳዩ እልባት አላገኘም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች የከፉ እንደሆኑም በርካቶች ሪፖርት ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ።

መንግሥት ቀድመን ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል ቢልም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለቢቢሲም ሆነ ለኢሰመጉ እንደተናገሩት ይህ ተፈጻሚ አልሆነም ይላሉ።

ማስረጃዎችን መመርመር ቢገባም አንዳንድ ሁኔታዎች ግን ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጠ አመላካች መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ይጠቅሳሉ።

ለምሳሌ ያህልም ቤቷ የፈረሰባትን አራስ ሴት ዋቢ አድርገው “በምንም መልኩ ማስጠንቀቂያም እንኳን ተሰጥቶ ቢሆን መጠበቅ ይገባ ነበር። አንድ አራስ ወልዳ ተኝታ ብዙ ድጋፍ ሊደረግላት በሚገባበት ወቅት በላይዋ ላይ ቤት ሲፈርስ ትንሽ የሰብዓዊነት ጥያቄ ያስነሳል” ይላሉ።

ሆኖም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ስለሚባለው ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ድምዳሜ ላይ አልደረስንም ብለዋል።

ያለው ፈረሳ ወጥ አይደለም የሚያሰኙ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት አቶ ተስፋዬ ከሌሎች ቦታዎች ተፈናቅለው መጥተው ቦታ የተሰጣቸው ግለሰቦች እንዳሉ፣ ሕገወጥ ቤቶች ተብለው ያልፈረሱ እንዳሉም ይጠቅሳሉ።

“ወጥ አሰራር የሚኖረን ከሆነ እነዚህን ሰዎች ከማፈናቀላችን በፊት ምንድን ነው ልናደርግላቸው የሚገባው?” የሚለው መመለስ አለበት በማለት፣ እንደ መንግሥት የትኛውንም ማኅበረሰብ በተመሳሳይ ዐይን ማየት እንዳለበትም ያስረዳሉ።

“ሕግን ብቻ ማክበር ተገቢ ቢሆንም፣ እንደ ሁኔታው ግን ሰብዓዊነትንም ልናካሂድ ይገባል” ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ።

አክለውም “እነዚህም ዜጎች ናቸው። ከዚህም ይሁን ከዚያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው። በዝቅተኛ ኑሮም ላይ ያለ ይሁን ከፍተኛ ኑሮ ላይ ያለ፣ የትኛውም ብሔር ይሁን የትኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ግልጋሎት ነው ማግኘት ያለበት” ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አርብ የካቲት 17/2015 ዓ.ም. ባናገራቸው ወቅት ገብርኤል የሚባልና ዶሮ እርባታ፣ ቻይና አካባቢም በርካታ ቤቶች እየፈረሱ እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬም የፈረሳ ሂደቱ እንደቀጠለ መረጃዎች ደርሰውናል ብለዋል።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ ማንም ሰው ለእራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደኅንነት በቂ በሚሆን የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት አንዳለው እና ይህም መብት መጠለያን እንደሚጨምር ይደነግጋል።

ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች እና መፍትሄዎች

ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ከቀረቡለት አቤቱታዎች በመነሳት ሊደረጉ የሚገባቸውን መፍትሄዎች እና ጥንቃቄዎች በሰሞኑ መግለጫው አካቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በሚገኙ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የቤት ፈረሳዎች ተገቢውን የህግ ሥነ-ሥርዓት የተከተሉ እንዲሆኑ እና በምንም አይነት ከቤት እና ከመሬት አስገድዶ የማፈናቀል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ
መንግሥት የቤት ፈረሳ እንቅስቃሴዎችን በሚያደርግበት ወቅት ሕጋዊ የሆኑ ቤቶችን ከማፍረስ እንዲቆጠብ
ሕጋዊ አይደሉም የሚባሉ ቤቶችም ቢሆኑ ቤት መስራት በሚጀመርበት ወቅት ማስቆም የሚቻልበት ሁኔታ ማመቻቸት
ከረጅም ዓመታት በኋላ የሚደረጉ ፈረሳዎች ሰብዓዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ በመሆናቸው የቤት ፈረሳ እንቅስቃሴው ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ለሚፈርሱ ቤቶች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥ
በቤት ፈረሳዎች ወቅት የሚስተዋሉ ከመንግሥት በኩል ተመጣጣኝ ያልሆኑ የኃይል አጠቃቀሞች በአስቸኳይ እንዲቆሙ
ከቤት ፈረሳ እንቅስቃሴዎቹ ጋር ተያይዞ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቤቶች በሚፈርሱበት ወቅት ለነዋሪዎች በቂ ጊዜ በመስጠት ቅድሚያ እንዲያሳውቁ
ንብረታቸውን ለማውጣት በቂ ጊዜ እንዲሰጡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለወደሙ ንብረቶች ግን መንግሥት ተገቢውን ካሳ እንዲሰጥ እንዲሁም ይህንን ሕገ-ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በሕግ እንዲጠይቅ
በአካባቢ ላይ የሚኖሩ እና ቤቶቻቸው የሚፈርስባቸውን ሰዎች ጋር ውይይት በማድረግ አካታች የሆነ ዘላቂ መፍትሄን ማምጣትን አካቷል።
በአካባቢው የሚኖረው አብዛኛው ነዋሪ ዝቅተኛ ኑሮ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሁሴን በበኩላቸው መውደቂያ የሌላቸው እና የዕለት ጉርስም መሸፈን የማይችሉ በመሆናቸው የቤቶች ፈረሳ ሊገታ ይገባል ይላሉ።

ከዚያ በተጨማሪም ቤታቸው ለፈረሰባቸው እና ለተፈናቀሉት “መቋቋሚያ እና መጠለያ ይሰጠን” ሲሉም ይጠይቃሉ።

*ለደኅንነታቸው ሲባል ያናገራቸውን ነዋሪዎች ትክክለኛ ስም አልተጠቀምንም።
============/////==============

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...