ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 17, 2023

ህገወጦቹ እና የጀርባ ያለው ኃይል የሚፈልጉት ህዝብ በቁጣ ሁከት እንዲያስነሳ እና ሃገር እንዲተራመስ በእዚህም የጽንፈኞቹ መንግስት መመስረት ነው።ምዕመናን በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋል።

አዳማ፣ ናዝሬት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን


በእዚህ ጽሑፍ ስር 
  • የህገወጡ ቡድንና የጀርባ ደጋፊው ኃይል ዋና ፍላጎት
  • በብልጽግና ውስጥ ያለው የችግሩ ሥር እና በሽመልስ የሚመራው ኦሮምያ ብልጽግና ውስጥ ያለው ሥር አሁን ይለያያል።
  • ምዕመናን በጥንቃቄ መሄድ ይገባናል።መንግስትም ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን የመወጣት ወሳኝ ጊዜ ደርሷል።

======
ጉዳያችን
======

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ በጵጵስና ከሚያገለግሉት ውስጥ ሦስቱ በህገወጥ መንገድ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ሳያውቁ ኢጲስ ቆጶስ መሾማቸው እና ይህንኑ ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስቱም ላይ የውግዘት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እያለ ክትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰበር ዜና በተላለፈው ዜና መሰረት ሦስቱም በሕገወጥ መንገድ የወጡት  እና ትናንት የካቲት 9 እና ዛሬ የካቲት 10/2015 ዓም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በቅዱስ ሲኖዶስ፣ህገወጦቹ ሦስቱ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣በሚኒስትር ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሓዘ ጥበብ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን እና የአነጋገሩ ሽማግሌዎች ጭምር በተገኙበት የተደረጉትን ንግግሮች ለህዝብ ተላልፈዋል።በእነኝህ ውይይቶች ላይ ማንም ህዝብ ሊፈርድ በሚችለው እና እራሳቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከእዚህ በፊት ከሰጡት መግለጫ በተለየ በእዚህ ውይይት ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ምንም ዓይነት የአካሄድም ሆነ የፍትሓዊነት ችግር እንደሌለ በአንደበታቸው ሲመሰክሩ ታይተዋል።

ከእዚህ በኋላ ዛሬ የካቲት 10/2015 ዓም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና ሥራአስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ እና ብጹዕ አቡነ አብርሓም ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በስምምነቱ መሰረት ሦስቱም እየሄዱ አለመሆናቸውንና በህገወጥነቱ ለመግፋት ማሰባቸውን የሚገልጽ መግለጫ መስጠታቸው እና ከእዚህ መግለጫ በኋላ ቤተክህነት በሚገኘው የቀድሞ ቤታቸው ውስጥ እንደገቡ በመግለጫቸው ገልጸዋል። 

የህገወጡ ቡድንና የጀርባ ደጋፊው ኃይል ዋና ፍላጎት

አሁን የህገወጡ ቡድን (የቀድሞ ሦስቱ ጳጳሳት) ተልዕኮ ግልጽ እየሆነ ነው።በኦሮምያ ክልል ህዝብ ሆ! ብሎ ይቀበለናል ያሉት ስሌት ተገላቢጦሽ ሆነባቸው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አዳራሽ በነበረው ውይይት ላይም ይህንኑ የህዝብ መነሳት እና በሄዱበት ሁሉ እንዳልተቀበላቸው ልክ ቤተክህነት ዱርዬ የገዛባቸው አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። ኦሮምያ ክልል ያሉ ሰብረው የገቡባቸው ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ህዝብ ቤተክርስቲያን መሄድ አቁሞ ቤቱ ተቀምጧል። በእዚህም ምክንያት አብያተ ክርስቲያናቱ ካለቅዳሴ ወና ሆነው የተቀመጡ ሲሆን በወለጋ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ አቡነ ናትናኤል ከእዚህ በፊት የቀደሱት ቅዳሴ በድምጽ ቅጂ እያቀረቡ የተቀደሰ ለማስመሰል ከቤት ያለውን ምዕመን ሊያታልሉ ሲሞክሩ ከቅዳሴ በኋላ በሞባይል ስልክ ያለው ዓለማዊ ሙዚቃ ሲገባ ሁሉ ተሰምቶ ቤተክርስቲያንን መዘባበቻ አድርገዋታል። 

በሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮምያ ክልል ይህንኑ የህገወጡን ቡድን ከማጀብ ጀምሮ በተለያዩ ሆቴሎች እየቀለበ ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር እንዲመክሩ የሚያመቻች አካል ሆኗል። የኦሮምያ ክልል በብዙ መልኩ ከማዕከላዊ መንግስት ፈጽሞ የተለየ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የሙስና ዝቅጠት ውስጥ የገቡት የጨፌ ምክርቤት አባላት ጭምር ግርግር በመፍጠርና የኦነግ ሸኔን ዓላማ በቢሮ ተቀምጠው አንድ በአንድ እያስፈጸሙ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት በኦሮምያ የሚኖረው ህዝብ ከኦነግ ሸኔ እኩል የኦሮምያ ልዩ ኃይልን ይፈራል፣ይጠላል። ይህ በእንዲህ እያለ የኦሮምያ ጨፌ የክልል ምክርቤት ለሸኔ የሰላም ጥሪ ማድረጉ ዛሬ ተሰምቷል።ሸኔ የሚሰራውን ሁሉ የኦሮምያ ክልል ልዩ ኃይል እየሰራው ነው። ዛሬ የኦሮምያ ክልል ጥሪ ያደረገው ለራሱ ነው ወይንስ ለሸኔ የሚለው በራሱ ጥያቄ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንጻር እየተንቀሳቀሱ ያሉት ህገወጥ የቀድሞ ጳጳሳትም ሆኑ እነርሱን አጅቦ የተነሳው የኦሮምያ ብልጽግና ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ብጥብጥ እንዲነሳ እና በእዚህ ሳብያ የኦሮምያ ክልል ከሸኔ ጋር ሆኖ አዲስ አበባን ለማጥቃት በእዚህ ትርምስ ከህወሃት ጋር ተመሳጥረው ኢትዮጵያን አተራምሶ የጽንፈኞቹን መንግስት ማቆም ነው።የቤተክርስቲያኒቱ ህገወጦች መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለይ የህገወጦቹን በሚደግፍ መልኩ የተናገሩት የብዙዎችን ቁጣ ቀስቅሷል። ነገሩ የፖለቲካ ጨዋታ ያለበት መሆኑ በትክክል ይሸታል። ከመግለጫቸው ብኋላ ግን የተቅላይ ሚኒስትሩ የለዘበ አቀራረብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በኩል ስህተት እንደሌለ በሰሞኑ የተለቀቁት የህገወጡ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያደረጉት ውይይት ላይ ተንጸባርቋል። ለእዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃሳብ መቀየር የታየባቸው ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።እነርሱም  
  •  የኦርቶዶክሱ ማኅበረሰብ ከሃገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሳየው ንቅናቄ
  • የክልል መሪዎች ከደህንነት ሚንስትር ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ስብሰባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ያለፈውን መግለጫ በብርቱ ስለተቃወሙ እና የህጋዊ ሲኖዶስ ህጋዊነት መንግስት ማክበር እንዳለበት በጥብቅ ትዕዛዝ ስላስተላለፉ እና
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩም እራሳቸው ከብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቤተመንግስት ያደረጉት ውይይት ላይ በአባቶች ላይ የሚጠቅሱት አንድም ነቁጥ ሳላላገኙ ይልቁንም በቃላቸው እንደተናገሩት ቤተክርስቲያን በቋንቋ አንጻር እየሰራች ያለውን ሥራ ከእዚህ በፊት የማያውቁትን ማወቃቸውን በመግለጻቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በብልጽግና ውስጥ ያለው የችግሩ ሥር እና በሽመልስ የሚመራው ኦሮምያ ብልጽግና ውስጥ ያለው ሥር አሁን ይለያያል።

አሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የገጠማት ችግር ሃይማኖታዊ ሳይሆን ዛሬ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ላይ አቡነ አብርሃም እንዳሉት ፖለቲካዊ ችግር ሆኗል። ስለሆነም ፖለቲካዊ ችግሮች በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በድፍኑ በሚታዩ የዘመቻ አስተያየቶች ደምድሞ ቁጭ የሚባልበት አይደለም። ጉዳዩ በተለያዩ ዕይታዎች ሲተነተኑ እና ተበትነው ሲቀርቡ ማድመጥ እና መመርመር ይገባል።አሁን በሚታየው ሁኔታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንጻር ያለው የብልጽግና አሰላለፍ እና የሽመልስ እና የኦሮምያ ክልል የጽንፈኛ ቡድን ከጀርባ ከባዕዳን ጋር ከሚያገናኙ አገናኝ መኮንኖች ጋር ያለው አሰላለፍ ይለያል። በብልጽግና በኩል አንዳንድ በእምነት የማይመስሏት ይህ የቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ አይተው ቤተክርስቲያንን መውጊያ አድርገው ለማቅረብ ቋምጠው ቀርበው ነበር። ብልጽግና ሲባል ግን ሥራ አስፈጻሚ አካሉ የአማራ ክልል፣የአፋር፣ሱማሌ፣ደቡብ እና ሌሎች ክልሎችን የያዘ በመሆኑ እና የሥራ አስፈጻሚው አካል ደግሞ የሕግ መከበር አስፈላጊ መሆኑ ላይ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህጋዊ ሲኖዶስ ማክበር ላይ የሰጡት አስተያየት እና የምዕመናን ከሃገር ውስጥ እስከውጭ መነሳት ብልጽግናም ነገሩን ቀለል አድርጎ ለማየት የሞከረበት ዕይታ ስህተት እንደነበር ብቻ ሳይሆን የመንግስት ለውጥ ሊያስነሳ የሚችል የህዝብ ማዕበል ሊነሳ የመቻሉ ሁኔታ ግልጽ በመሆኑ ከህገወጦቹ ጋር በመቆም ጉዳዩ እንደማይፈታ ግልጽ በመሆኑ በሽመልስ የሚመራው የኦሮምያ ብልጽግና ያህል ሌላው የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ቢያንስ የእነ ሽመልስ የድፍረት መንገድ መጨረሻው ሞት እንደሚሆን ግልጽ ሆኖለታል። ስለሆነም ከላይ የተሰጡት ምክንያቶች ሳብያ በብልጽግና ውስጥ ያለው የችግሩ ሥር እና በሽመልስ የሚመራዊ ብልጽግና ውስጥ ያለው ሥር አሁን ይለያያል። ይህንን ልዩነት አይቶ መሄድ በጅምላ ደምድሞ ከመሄድ (የቤተክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግር ፖለቲካዊ መሆኑን እስከተረዳን ድረስ) የስሩ መጠን የበዛበትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ ማወቅ ቢያንስ በፖለቲካ አቀራረብ ላይ ጠቃሚ ነው። 

ምዕመናን በጥንቃቄ መሄድ ይገባናል።መንግስትም ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን የመወጣት ወሳኝ ጊዜ ደርሷል።

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የህገወጥ ቡድኑ ተልዕኮም ሆነ ከጀርባ የሚዘውሩት ዋና ፍላጎት የህዝብ ስሜት አስነስቶ ያልተደራጀ እና በብስጭት የተነሳሳ ብጥብጥ ማስነሳት ነው። በእዚህም ሳብያ የጽንፈኛ መንግስት ለማቆም ከሸኔ እና ህወሃት ጋር በመሆን ለመመስረት ዕቅድ አለ። በእዚህም ለዘብተኛው የብልጽግና ቡድንን መምታት ይፈለጋል። ለእዚህ ደግሞ ሃይማኖት የህዝብ ስስ ብልት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን መተንኮስ ተፈልጓል። ስለሆነም ምዕመናን በቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች ላይ ያለውን ዕምነት ከእዚህ ቀደም እንደነበረው መተማመኑን እና ከጎናቸው መሆኑን አጽንቶ መቀጠል አለበት።የቤተክርስቲያን ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም። ስለሆነም ብጹአን አባቶች የቤተክርስቲያኒቱ የማይነኩ እና የሚነኩ ድንበሮችን ስለሚያውቁ ከየተለያዩ ቡድኖች ሃሳቦች በተለየ የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ መስማት መከተል ይገባል።

በሌላ በኩል መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።ቤተክርስቲያን እየተሰበረች በሕገወጦች ስትወረር ቆሞ የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ከሰባሪዎች ጋር አጅቦ እየገባ ንጹሃንን እየገደለ ህገወጦችን የማስገባት እኩይ ተግባር ባለፈው ሳምንታት በኦሮምያ ክልል ሲፈጸም ሰንብቷል።አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣አማካሪዎቻቸው እና ሽማግሌዎች በተገኙበት ስምምነት ከተደረገ በኃላ ህገወጡ ቡድን ሰጠ ተብሎ የተላለፈውን መግለጫ ተከትሎ የተከናወኑ የህግ ጥሰቶችን መንግስት ሕግ ማስከበር ካልቻለ፣ ህዝብ ህጉን ሊያስከብር መነሳቱ አይቀርም።ይህ ህግ የማስከበር ሂደት የመንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ጉዳይ ጋር አይገናኝም። ጉዳዩ ህጋዊ ሰውነት ያለው ከ70 ሚልዮን በላይ ምዕመን ተቋም የመጠበቅ እና ያለመጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነት ነው።ስለሆነም መንግስት ምስክር በሆነበት የህግ ጥሰት በዝምታ ከተመለከተ ብልጽግና ኢትዮጵያን በማፍረስ ሂደት ተሳታፊ ተደርጎ በታሪክም ሊያስጠይቀው ይችላል። 

ለማጠቃለል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያፈነገጡት ቡድኖችም ሆኑ ተባባሪዎች መመርያ የሚቀበሉት ከጽንፈኛ የሸኔ ቡድን ነው።ከሸኔ ባለፈም ለእዚህ ልዩነት ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ የሚንቀሳቀሱ ባዕዳን ካለምንም ጥርጥር እየደገፉ እንደሆነ ከሰሞኑ ለህገወጡ ቡድን በሃገር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ያዋጡት ዝርዝር ሰሞኑን በዘሓበሻ ሚድያ የተለቀቀውን ስንመለከት የባዕዳን እጅ በሃገራችን ነጋዴዎች በኩል ምን እየሰሩ እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጳጳሳት ጋር ያደረጉት ውይይ ላይ በእዚህ ጉዳይ እጃቸውን የከተቱ እነማን እንደሆኑ እነማን ኢትዮጵያን እንደሚወዱ እና ማን ሊያጠፉ እንደሚፈልጉ በሰሞኑ ሂደት ተመልክተናል ያሉት ይህንን የባዕዳን እጅ ጋር የተሞዳሞዱትን ነው ወይ? ማለት ይቻላል።በመሆኑም ምዕመናን በጥንቃቄ እና ለዘለቄታዊ መፍትሄ፣መንግስት ደግሞ ሕግ በማስከበር የማያወላውል አቋሙ ቀጥ ብሎ መሔድ ይጠበቅበታል።
======================////===========

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...