- ከሽብርተኛው ሂዝቦላ ጎን የሚሰለፍ ሚናውን ከአሁኑ ይለይ።ኢትዮጵያን ያለ እና ኢትዮጵያ ለሁሉም እኩል ትሆናለች የሚል የሽብር ቡድኑን ለመፋለም ይነሳ!
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
የራሱን ሕግ የሚበላ መንግስት
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የመንግስት ስሪቱን በሚዘውረው ብልጽግና ጎሳን መሰረት ያላደረገ ፓርቲ መሆኑን ቢናገርም፣በሕወሃት/ኢሃዴግ ከተቀመረው የጎሳ አደረጃጀት ያልራቀ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ክልሎች ለመረን የለሽ እና ህግ አልባ ባለስልጣናት ስር እንዲወድቁ እና ህዝብ ለመረረ ፈተና እንዲወድቅ ያደረገ ፓርቲ ሆኗል። ለእዚህ ማሳያው እሩቅ ሳንሄድ በወልቂጤ በቅርቡ ውሃ ለመጠየቅ በወጣው ህዝብ ላይ የክልሉ ልዩ ኃይል በከፈተው ተኩስ የሰው ህይወት ቢጠፋም፣ ጠያቂ የሕግ አካልም ሆነ ጠያቂ የመንግስት ክፍል እስካሁን ወደ አደባባይ እንዲቀርብ አልተደረገም። ይህንን ተከትሎ በወልቂጤ ከሰባት ቀን በላይ ህዝብ በቤት የመቀመጥ አድማ ሲያደርግ ጉዳዩን እና ችግሩ ላይ የተነፈሰ አንድም የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ እስካሁን እኔ አላየሁም፣ አልሰማሁም። የመንግስት መገናኛ ብዙኃንን በሚከፍለው ቀረጥ የሚያስተዳድረው ግን ይሄው ህዝብ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።
አሁን ያለው ሃገራዊ ሁኔታ ለመግለጽ የተለያዩ መስኮችን በፈርጅ በፈርጁ ማቅረብ ይፈልጋል። ሆኖም ግን ከሁሉም ፈርጆች ውስጥ የሕግ ጉዳይ ብቻ ብንመለከት ብልጽግና እጅግ የተዘባረቀ እና አለባብሶ የማለፍ ሂደት ላይ እንደተጠመደ ለማወቅ በጣም ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ከህወሃት ጋር የተደረገውን ስምምነት ሂደት እና ሰሞኑን የኦሮምያ ክልል ለሸኔ እያቀረበ ያለው የእንደራደር ጥሪ መመልከት በቂ ነው። ህወሃት በኢትዮጵያ የተወካዮች ምክርቤት በሽብርተኝነት ፈርጆት ሳለ መንግስት ከምክር ቤቱ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር ሳያደርግ ማለትም ቢያንስ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጦ ምክር ቤቱ የሽብርተኝነቱ ፍረጃ አይነሳም ግን ውይይት መንግስት ያድርግ የሚል ይሁንታም ሳያገኝ የሄደበት ስምምነት አሁን መልሶ ለራሱ ለትግራይ ህዝብም ሌላ ትርምስ፣ለቀጠናውም ሆነ ለኢትዮጵያ ያልረጋ የሰላም ከባቢያዊ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህ ዛሬ ስንመለከተው ቀላል ይመስላል።ከመንግስታዊ መርህ እና ህግ ጉዳይ ግን የአካሄድ ጥያቄ አለበት ብቻ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። በእርግጥ የሃገር ሰላም ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ከእዚህ አንጻር የታየ ነው የሚል ምክንያት የሚሰጡ አሉ። ሆኖም ግን የአንድ ሰዓት ስብሰባ የተወካዮች ምክር ቤት አድርጎ በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ሰጥቶበት ያልሄደበት ጉዳይ ላይ ይህንን ያህል እርቀት ተሄዶም ዛሬም ግልጽነት የጎደለው የተድበሰበሰ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ አሁንም መልሰን የመርህ እና የህግ ጉዳዩ እንድናይ ያስገድደናል።
የሰሞኑ የኦሮምያ ጨፌ ምክር ቤት ከሸኔ ጋር ልነጋገር ብሎ ያወጣው መግለጫ ደግሞ በራሱ ሌላ የሕግ ጥሰት አለበት። በመጀመርያ ደረጃ ሸኔን ሽብርተኛ ያለው የፌድራል ተወካዮች ምክርቤት እንጂ የክልል ምክር ቤት አይደለም። ስለሆነም የክልል ምክርቤት በምን ስልጣኑ ነው ከሸኔ ጋር ለመደራደር መግለጫ የማውጣት ስልጣን ያለው? እነኝህ ሁሉ ሁኔታዎች ብዙ የሕግ ጥያቄዎች ያስነሳሉ። ሕግ ስትጠፋ ደግሞ ፍትሃዊነት ያጣ መንግስታዊ አሰራር ደግሞ መዘዙ የትዬለሌ ነው።አሁን በአጭሩ እየታየ ያለው መንግስት እራሱ ያወጣውን ሕግ የሚቆረጥም መሆኑ ነው። እንደእዚህ ዓይነቱ እና ሌሎች የመንግስት የተዘባረቀ እና የራሱን ህግ የመቆርጠም አካሄድ ይሆን እንዴ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊን ከስራ ያስለቀቃቸው? ችግሩ የህግ እና መርህ ጥሰቶቹ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድም ይዘውትና ትተውት የሚሄዱት አደጋ መኖሩ ነው ክፋቱ።ጥያቄው የራስን ሕግ እየቆረጠመ የሚሄድ መንግስት ምን ያህል ሊጓዝ ይችላል የሚለው ነው?
በኦሮምያ ክልል እየተፈጠረ ያለው ስብስብ የ''ሂዝቦላ'' ሽብር ቡድን ግልባጭ ስብስብ ይመስላል።
የህወሃት መንግስት ወደ መቀሌ ሸሽቶ ከሄደ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ያደረገው የጎሳ ፖለቲካ ይቀራል።ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባት ኢትዮጵያ ትመጣለች በሚል ነበር የለውጥ ሂደቱን የደገፈው። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥም በኢትዮጵያ ከትግራይ ቀጥሎ የኦሮምያ ክልል የኢትዮጵያን ሰላም በመንሳት እና የግጭት እና የህዝብ ሰቆቃ የየዕለቱ ተግባር የሆነበት ክልል የለም።በኦሮምያ ክልል የጽንፍ አቋም እንዲበቅል ካደረገው የጀዋር ቡድን ጀምሮ እስከ የኦነግ የጽንፍ ክፍል ድረስ ሁሉም ወደ ክልሉ ገብቶ ከክልል ልዩ ኃይል እስከ የቀበሌ ስልጣን ድረስ ለመቆጣጠር ችሏል። ይህም ሆኖ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ይህንን የጽንፍ ኃይል የሚቃወም ነገር ግን በእጅጉ እየተገፋ ያለ የኦሮምያ ክልል ተወላጅ እና በፌድራል ደረጃ ያለ ባለስልጣንም ብዙ ነው።
በኦሮምያ ክልል እየተፈጠረ ያለው ስብስብ የ ሂዝቦላ ሽብር ቡድን ግልባጭ ስብስብ ነው። የእዚህ የሽብር ቡድን አደረጃጀት ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ አደረጃጀት አለው።ሂዝቦላ በፍልስጤም ምድር ይብቀል እንጂ በሊባኖስ የፖለቲካ፣ምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ህይወት ውስጥ እንዴት ሰርጾ እየገባ ለመንቀል ያልቻሉት ቅንቅን እንደሆነ ያለፈውን የሊባኖስ የቅርብ ታሪክ ላይ ቡድኑ ምን ያህል ተጽዕኖ እየፈጠረ የሽብር ሥራ እየሰራ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ሂዝቦላ በሊባኖስ ውስጥ ትምህርት ቤቶች፣መስጊዶች፣ሆስፒታሎች እና የትራንስፖርት ኩባንያዎች ሁሉ ስለከፈተ በሊባኖስ ህዝብ ህይወት ውስጥ ገብቶ ምስኪኑን ህዝብ ለመንዳት እየሞከረ ነው። ከእዚህ ባለፈ ደግሞ በሊባኖስ መንግስት ውስጥ ሂዝቦላን የማይደግፉ ያላቸውን አስገድሏል፣አሰድዷል እንዲሁም በቤተሰባቸው ላይ ሳይቀር ጥቃት ፈጽሟል።
በኦሮምያ ክልል በክልሉ አስተዳደር፣ምክርቤት፣ልዩ ኃይል እና የእምነት ተቋማት ሳይቀር እንደአሜባ እየተስፋፋ ያለው የጽንፍ ኃይል ልክ እንደ ሄዝቦላ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃንን በወለጋ እና በሌሎች ቦታዎች ፈጅቷል፣ንብረት አቃጥሏል፣ዘርፏል። ይህ ጥቃት ወደ ከተሞች ሲመጣ በከፍተኛ የሙስና ዘረፋ ላይ ተዘፍቆ በሚልዮን የሚቆጠር ሃብት ለማንቀሳቀስ ሲሞክር ይታያል።አሁን የጽንፍ ኃይሉ ከልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ እስከ ታች ያለ የቀበሌ ሊቀመንበር መለየት ባልተቻለበት መንገድ ክልሉን በሂዝቦላ አደረጃጀት ለመምራት እየተንቀሳቀሰ ነው። የእዚህ ሂዝቦላዊ ንቅናቄ አንዱ መገለጫ የትዕዛዝ መስመሩም ሆነ የሴራ ሃሳብ አመንጪዎቹ አንድ ቦታ ላይ የተሰበሰቡ ሲሆን የተለያዩ ሴራዎችን በመጎንጎን ኢትዮጵያን ለማመስ እና ተጽዕኗቸው ውስጥ ለማስገባት ይሞክራሉ። ይህ ሂዝቦላዊ እንቅስቃሴ ህዝብ እንዲገዛለት የተለያዩ የማስፈራርያ አጀንዳዎች ይፈበርካል።አጀንዳዎቹ እንደማያዋጡ ቢያውቅም የሚፈልገው ኢትዮጵያውያንን ማሸበር ስለሆነ ሰላም ለመንሳት ይሞክራል። ለምሳሌ በቅርቡ በአዲስ አበባ የኦሮምያ መዝሙር ይዘመር አጀንዳ እና በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ ከእዚሁ በኦሮምያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው እና እንደ አሜባ በፌድራል መንግስት ውስጥም ሰርጎ ገብቶ ሂዝቦላዊ አደረጃጀት ከያዘው ''ቲንክ ታንክ '' ቡድን የመነጨ ሃሳብ እና በልዩ ኃይሉ እና በገንዘብም ሲደገፍ የነበረ ነው።
በኦሮምያ የበቀለው ሂዝቦላዊ መዋቅር የመንግስትን ፖሊሲ ሁሉ ለማንቀሳቀስ ሲሞክር ብቻ ሳይሆን ሲሰራ በግልጽ እየታየ ነው።ከህወሃት ጋር የተደረገው ስምምነት ምንም እንኳን የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አሜሪካ ሰር ነው እንዳሉት ከዋሽንግተን ይምጣ እንጂ በኦሮምያ ያለው የሂዝቦላዊ እንቅስቃሴ ሃሳብ አመንጪዎች ከህወሃት ጋር በጓሮ መነጋገር የጀመሩት ቀድመው ነው።ለሂዝቦላዊ ስር በኦሮምያም ሆነ በፌድራል መንግስት ስር መስደድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያሳዩት ቅጥ ያጣ ቸልተኝነት እና ስሱ የሆነ ዓይን አንዱ እና ዋና ምክንያት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሸኔ ጉዳይ በወለጋ ጫካዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኦሮምያ ክልል ሙሉ መዋቅር እና ልዩ ኃይል ውስጥ እንዲሁም በፌድራል መንግስት መዋቅር ውስጥ እንደሆነ በግልጽ አያውቁም ማለት ሞኝነት ነው። ሆኖም ግን ጉዳዩ ገፍቶ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የተወሰዱ እርምጃዎች አልተሰሙም። ይልቁንም የሂዝቦላ እንቅስቃሴ ሰሜን ሸዋ ላይ ልዩ ኃይል እያለ ያሰለፋቸውን አስቁሞ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡትን የሚያግድ፣ ሰሞኑን ደግሞ ሸገር ከተማ ተብሎ በተሰየመው የአዲስ አበባ ዙርያ ባሉ ነዋሮዎች ላይ የማፈናቀል ሥራ እየሰራ ነው። በሽገር ዙርያ ያሉት ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ ያሉት አማራ በመሆናቸው መሆኑን ለአንከር ሚድያ እና ኢሳት የገለጹበት መንገድ ሁሉ የሂዝቦላ ግልባጭ እንቅስቃሴ ፋሽሽታዊ ሥራ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ለማጠቃለል ኢትዮጵያን የሚያምሱ የሕግ ጥሰት የታየባቸው የመንግስት የራሱን ሕግ የመቆርጠም መዘዝ እና የሂዝቦላ ግልባጭ የሆነው በኦሮምያ ክልል እና በፌድራል መንግስት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የጎሳ ለበስ ግን ፍጹም ፋሺሽታዊ እንቅስቃሴ ዋና ግቡ ኢትዮጵያን በበለጠ አተራምሶ በሆነ የመንግስት ቅርጽ ሁሉንም ክልልሎች ለመዋጥ ነው።ይህ ዓላማው ደግሞ በሌሎቹ የብልጽግና አባል ክልሎች በደንብ ታውቋል።ለእዚህም ነው ሰሞኑን የአማራ ክልል ያወጣው መግለጫ ከአፋር እስከ ደቡብ ክልል፣ከሱማሌ እስከ ጋምቤላ ክልል በውስጥ አዋቂ እንደተዘገበው በጣም ትክክል ነው በሚል የተስማሙበት። ምክንያት የሂዝቦላ ግልባጭ በመጀመርያ ሊውጣቸው የፈለገው እንደርሱን እንደሆነ ገብቷቸዋል።መፍትሔው አንድ እና አንድ ነው።ከሽብርተኛው ሂዝቦላ ጎን የሚሰለፍ ሚናውን ከአሁኑ ይለይ።ኢትዮጵያን ያለ እና ኢትዮጵያ ለሁሉም እኩል ትሆናለች የሚል የሽብር ቡድኑን ለመፋለም ይነሳ!
============//////=========።
No comments:
Post a Comment