ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 2, 2023

በአማራ ክልል የተነሳው አለመረጋጋትን በፍትሐዊ እና ርቱዕ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማድረግ የሚገባቸው ሦስት ተግባራት።
=========
ጉዳያችን
=========

ያለመተማመኑ መናር 

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ደቡብ ጎንደር፣ጎጃምና ሰሜን ወሎ የፋኖ ታጣቂ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭቶች መፈጠራቸውና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለሰዓታት የተራዘመ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተሰምቷል። ይህ ድንገት ደራሽ ጉዳይ አይደለም።የእዚህ ዓይነት ህዝባዊ እንቅስቃሴ በድንገት ሊፈጠር እንደሚችል በተለያየ ጊዜ በኦሮምያ ክልል የተፈጸሙት ዘርን መሰረት ያደረጉ ማፈናቀሎች፣የክልሉ ባለስልጣናት ከኦነግ ሸኔ ጋር እየተናበቡ የፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት ብቻ ሳይሆን ትዕቢት የተሞሉ ንግግሮች ሁሉ ሲሰሙ አንድ ቀን የህዝብ ቁጣ እንደሚያስገነፍል የሚጠበቅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በተለየ መልኩ በኦሮምያ ክልል በሚሆነው እና በሌሎች ተለዋዋጭ ጉዳዮች ሳብያ በተለየ መልኩ የአማራ ክልል ነዋሪ የነበረ እምነቱ ተሸርሽሯል። ይህ መሸርሸር ደግሞ ከህወሓት ጋር በፕሪቶርያ ከተደረገው ስምምነት ተከትሎ በርካታ ጉዳዮች ብዥታ ፈጥረዋል። በእዚህ ያለመተማመን እና የጥርጣሬ ስሜት ውስጥ የክልል ልዩ ኃይሎች እና ሌሎች ኢመደበኛ ታጣቂዎች ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ሲመጣ ያለመተማመኑን ደረጃ በእጅጉ አናረው።

ይህ ዛሬ የተፈጠረው ሊፈጠር እንደሚችል የዛሬ አምስት ዓመት ግንቦት 1/2010 ዓም ጉዳያችን ላይ ''ሰሚ ያጣው የአማራ ዘርን የማፅዳት እኩይ ተግባር ፍትሃዊ የተባለ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል።'' በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ መመልከት ለጊዜው በቂ ነው።አሁን እየሆነ ያለው ባጭሩ ድንገት ደራሽ አይደለም።


 ህዝባዊ እንቅስቃሴው ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ነው ወይንስ ኢትዮጵያን የሚል እንቅስቃሴ ነው?

አንዳንዶች የአማራ ክልል ምንም ዓይነት የብሔር እንቅስቃሴ መነሻውን ቢያደርግም፣''አማራ ሁሌ ለኢትዮጵያ የቆመ ነው፣ኢትዮጵያን አይከዳም '' የሚል የተለመደ አነጋገር በተለይ ከአማራ ክልል ተወላጆችም ሆነ ከደቡብ ኢትዮጵያውያን የሚሰሙ አነጋገሮች ናቸው። ሆኖም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በራሱ በእንቅስቃሴው ባሕሪ፣ አነሳስ እና የወደፊት አቅጣጫ እንጂ አንዱ ክልል የተለየ ቅዱስ እና ምንም ዓይነት የአክራሪ ብሔርተኞች መነሃርያ የማይሆን ሌላው ደግሞ የተለከፈ ብቻ የሚለው አካሄድ አያስኬድም። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከመነሳቱ በፊት በጀርመን የናዚ ዓይነት የከፋ መንግስት ይነሳል ብሎ ቢያንስ በእዚያ ደረጃ የጠበቀ የጀርመን ህዝብም ሆነ የውጭ መንግስታት እንዳልነበሩ ታሪክን በትንሹ በማገላበጥ መረዳት ይቻላል።  ይህ ማለት የአማራ ክልል እንቅስቃሴ ፍጹም ብሔርተኛ እና በአደገኛ ኃይሎች እጅ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ገባ ለማለት አሁን በህዝባዊ እንቅስቃሴ ደረጃ ከመሆን አልፎ አመራሩ ነጥሮ ስላልወጣ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት የማይቻል ቢሆንም እንቅስቃሴው ግን በምንም የመጠለፉ አደጋ ግን መቼም ሆነ መቼ የለም ለማለት አይቻልም። ለእዚህ አብነት የሚሆነው እና ማነጻጸርያ የሚሆነው በሰኔ 3፣2010 ዓም ''የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰኘ አዲስ ንቅናቄ ባህርዳር ላይ ተመስርቷል።የንቅናቄው እድሎች እና ፈተናዎች ምንድናቸው?'' በሚል የቀረበው ጽሑፍ ስር ድርጅቱ ሊገጥሙት ከሚችሉት ዕድሎችና ፈተናዎች ውስጥ ፈተናዎች በሚለው ስር የሚከተሉት ተዘርዝረው ነበር።እነርሱም ፡ 
 • የከረረ ብሔርተኝነት ያላቸው ወደ አመራሩ ከመጡ ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ የመቸገር ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፣
 • በህወሓት ሰርገው እንዲገቡ የሚደረጉ ግለሰቦች የሚፈጥሩት አሉታዊ ስዕል በንቅናቄው ላይ የሚሰጠው መልካም ያልሆነ ስዕል እና ከሌሎች ብሔሮች ጋር ለማጋጨት የሚደረጉ ሙከራዎች፣
 • እራሱን በቶሎ ወደ ኢትዮጵያዊ ንቅናቄ ካልቀየረ በከረረ ብሔርተኝነት ስሜት የተመሰጡ አባላቱን ወደ ሃገራዊ አጀንዳ ባለቤትነት ለመቀየር የመቸገር ሁኔታ መፈጠር።የእዚህ አይነቱ ችግር አሁን ህወሓት እራሱ ገጥሞት የሚገኘው ችግር ነው።መግብያ ሲዘጋጅ መውጫው አብሮ መታየት አለበት።
 • በተሰሩ ግፎች እና ጥፋቶች ላይ ከሚገባው በላይ በመዘከር የይቅርታ እና የአንድነት መንገዶች እንዲከፈቱ ማድረግ ካልቻለ አማራን ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ደረጃ ወደ አደገኛ መንገድ የመሄድ አዝማምያ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል።የሚሉ ነበሩ።
አሁን ያለውን እንቅስቃሴ ከስሜት በተለየ በሚገባ ወዴት ሊሄድ ይችላል? ኢትዮጵያዊነት በተመለከተ ኢህአዴግ ውላጅ የሆነው ትውልድ ''አማራ ፊርስት '' የሚል ነው ወይንስ ''ኢትዮጵያ ፈርስት '' የሚል ነው? የሚለው አሁንም መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩን በኃይል ከመፍታት ይልቅ ማድረግ የሚገባቸው ሦስት ተግባራት።

በእዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለማንሳት እንደተሞከረው በዘመነ ኢህአዴግም ሆነ ባለፉት አምስት ዓመታት በጀዋር መሐመድ ''ስልጣን ይዘናል '' ከሚለው ጽሑፍ እስከ አቶ ሽመልስ ''ሰበርናቸው'' የመስቀል አደባባይ ንግግር፣ከመቶ ሺዎች የወለጋ እና የሸገር መፈናቀል እስከ ፍትሕ ያጡ የደቡብ እና ሱማልያ ክልል ነዋሪዎች ጭምር የብሶቱ ጣርያ ከመጠን ያለፈ ነው። ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም፣መከላከያም፣ብልጽግናም ካለምንም ማጉረምረ ሊውጡት የሚገባ እውነት ነው። ለእዚህ እውነት እዚህ ላይ መዘርዘር ጊዜ ማጥፋት ነው። አሁን ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ ለመተንተን የሚነሳ የመንግስት አካል መነሳት ያለበት ይህንን እውነት ከመቀበል ካልሆነ ቀጣይ የመፍትሄ ሂደቱ ሁሉ የተሳሳተ እና አለባብሶ የመሔድ ከንቱ ድካም ይሆናል። በመሆኑም ይህንን እውነት ጠቅላይ ሚንስትሩም አምነው እና ተቀብለው ወደ መፍትሔ መሄድ ተገቢ ነው። 

ወደ ሦስቱ የመፍትሄ መንገዶች ስንመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚከተሉትን ሦስት ተግባራት በፍጥነት መፈጸም አለባቸው። እነርሱም 

1) የመወቃቀሻ እና እውነቱን የማንጠርያ መድረክ ከአማራ ክልል እጅግ የተከበሩ ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣መከላከያ የኦሮምያ ክልል አመራሮች እና የፋኖ አመራሮች ጋር በፍጥነት መፍጠር።
 • መድረኩ ከውይይት በኋላ ለህዝብ መቅረብ ያለበት ለበለጠ ግጭት የማይዳርገው ክፍል ተለይቶ ነገር ግን ዋና ሃሳቡን ያልጣለ የመወቃቀሻ መድረኩ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራድዮ በቀጥታ መተላለፍ አለበት።
 • በመወቃቀሻ መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ እና በኦሮምያ ክልል ለሆነው ሁሉ ያሳዩት ለዘብተኝነት ላይ በግልጽ ይጠየቁ፣እርሳቸውም ከእዚህ በፊት ያልሰማናቸውን ጉዳዮች ጨምረው ለምላሽ ይዘጋጁ።ውይይቱ ስሜት የሚነካ እና ፍጹም ግልጽነት የታየበት መሆን አለበት።
 • ሀገር በሆነ ባልሆነው ወደ ግጭት እየገባች የትውልድ ሞት ከሚከተል ለእዚህ ዓይነት መወቃቀስ መዘጋጀት እና ስህተትን ውጦ ለነገ ስህተትን አስተካክሎና መተማመንን በምንም ወጪ ቢሆን ከፍሎ ሀገርን ማስቀጠል ግዴታ ነው። 
 • ስለሆነም ይህ የመወቃቀሻ መድረክ እጅግ በፈጠነ መንገድ ማድረግ ብዙ ችግሮችን ያስወግዳል።
2) በኦሮምያም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ አመራሮች በሙሉ እስከ መካከለኛ ድረስ ያሉትን ከባለሙያዎች ውጭ በሙሉ ከስልጣን ማንሳት እና አዲስ ከጎሳ ፖለቲካ አክራሪ የተሻለ አቋም ላይ ያሉትን መተካት።
 • አሁን በሁለቱም ክልል ያሉት አመራሮች በሴራ ሹክቻ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሙስና የተነከሩበት ደረጃ ማንም ወንጀለኛ የሚነዳቸው ስለሆኑ ያከረሩ የጸብና የግጭት መነሻ ናቸው።
 • በተለይ በኦሮምያ ክልል ያለው ከጎሳ ፖለቲካ መበስበስ አልፎ ፈጽሞ ለማንኛውም ኃይል ተገዢ ብቻ ሳይሆን የመሰረታዊ የኢትዮጵያ ዕይታቸው ከጥላቻ ባለፈ ወደ ፍጹም ፋሺሽታዊ መንገድ እየሄደ በመሆኑ 
 • በቀጣይ ኢትዮጵያ እንድትሄድበት ከሚፈለገው የአንድነት መንገድ አንጻር በሁለቱም ክልሎች ያሉ አመራሮች በብሄር ፖለቲካ የተደናበሩ ስለሆነ እና  
 • ወቅታዊ ችግሩን በአዲስ አሰራር በመቀየር ቁርጠኝነትን የማሳያ አንዱ መንገድ ስለሆነ።
3) የጎሳ ፖለቲካ የመጪዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ እንዳልሆነ እና እስከዛሬ የነበረው በህወሓትና ኦነግ የተተረኩት የውሸት ትርክቶች ጉዳይ ምዕራፍ ለመዝጋት ግልጽ፣አሳማኝና ተግባራዊ ስራ መንግስት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጽ ብቻ ሳይሆን በቁርጠኝነት የማሳያቸው ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን መጥቷል።
 • እዚህ ላይ ህገመንግስቱ ላይ ያሉት መሰረታዊ ችግሮች ማስተካካል። ሀገር በጦርነት ከሚታመስ ህገመንግስትን በማረም ማስተካከል ተገቢ ነው።
 • በአማራ ላይ፣በኦሮሞ ላይ እና ሌሎችም ላይ ያሉ ጸብ ጫሪ ትርክቶች በወንጀለኝነት የሚያስጠይቁ ማድረግ፣
 • የአኖሌን ሃውልት ከማፍረስ ማናቸውም የጎሳ ቀስቃሽ ንግግር ያደረገ እና የጻፈ በፍጥነት በህግ መቅጣጥ
 • ዲጂታል ጎሳ አልባ መታወቂያ ከታቀደው ጊዜ በፈጠነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ
 • የክልሎች አከላለል ጎሳን መሰረት ያደረገ እንዳይሆን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ። እዚህ ላይ በፍጥነት የሚለው ቃል የምጠቀመው ዘመን በማርዘም ችግር ከማባባስ ይልቅ በተግባራዊነቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ሀገር ማቆም ከሁሉ የተሻለው አማራጭ መሆኑ ቢያንስ ያለፉት አምስት ዓመታት አስተማሪ ስለሆነ ነው።
ለማጠቃለል 

የአማራ ክልል ህዝብ በግልጽ መወቃቀስ የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ለጋራ ሕግ አብሮ እንዲቆም ማድረግ ይቻላል። ለእዚህ አንዱ ማስረጃ ክልሉ ካለው ማኅበራዊ ባሕል አንጻር ህግ የማክበር ባሕሉ እጅግ የጠነከረ ነው።እስኪያምንህ ይዘገያል።ካመነህ አብሮ ይዘልቃል።አይቶ አይቶ ካላመነ በቃኝ ብሎ ይነሳል። ያላየበትን መንገድ በቅንነት እና በእንባ ጭምር ስታስረዳው መልሶ ይሰማሃል። አንዴ ከሰማህ በኋላ መልሰህ ስትዋሽ ካገኘህ ግን  ነገሩ አበቃ ማለት ነው። አሁን ያለበት ደረጃ መንግስት ስህተቱን አምኖ ለማስተካከል እድል እንዲሰጠው የማሳመን እና ለገባው ቃል ተግባራዊ እንዲያደርግ እድል ያለበት ጊዜ ነው። አሁን የተፈጠረው መከራ ብቻ አይደለም።ለተሰራው ስህተት ማረምያ፣የጎሳ ኃይሎችን ማስታገሻ አድርጎ ወደ መልካም ሀገራዊ ዕድል መቀየርም ይቻላል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሀገር ገልብጠን፣ ነፍጥ ከመነቅነቅና መከላከያን ከመበተን መለስ ያለ ንግግር እና ስህተትን የማረም ሂደት አያስፈልግም የሚሉ እነ''በለው'' ባዮች አይነሱም ማለት አይደለም። ሆኖም ህዝብ በግልጽ ይመንበት፣ከደም መፋሰስ ይልቅ ስህተትን በማረምና ሀገራዊ አቅጣጫን ከማስተካከል መለስ ያሉ ካልበተን አናርፍም ለሚሉ እራሱ ህዝብ ምላሽ ይሰጣል።ከእዚህ በተረፈ ግን በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ ችግር በወታደር ኃይል ለመፍታት መሞከር አይቻልም።ጦርነት ውስጣዊ ስሜት እና ለመሞት እርግጠኛ የሆነ የስሜት ደረጃ ይፈልጋል።መከላከያ ደግሞ ከአማራ ክልል ጋር የሚያደርገው ጦርነት ፈጽሞ ምክንያታዊ አለመሆኑን ይረዳል። በመሆኑም በሙሉ ስነልቦና አይዋጋም። ይህ ማለት ግን መከላክያ ላይ የሚሆነውን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቀበላል ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የመንግስት ኢፍትሃዊ አካሄድ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት መሆኑን ስለሚያውቅ መንግስት በይቅርታ እና በማስተካከል ሥራ እንዲጀምር፣በፋኖ ታጣቂ በኩልም በመከላከያ ላይ ምንም ዓይነት ግጭት እንዳይፈጠር በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን አንጥሮ በማቅረብ ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ በቅንነት መነሳት ይገባል።ከኢትዮጵያ መታወክ አይደለም ዜጎቿ ጠላቷቿም በሚገባ ቢያስቡት አይጠቀሙም።

==================//////===========No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...