ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 9, 2018

ሰሚ ያጣው የአማራ ዘርን የማፅዳት እኩይ ተግባር ፍትሃዊ የተባለ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል። Ignorance of Ethnic cleansing on Amhara nationality in Ethiopia can follow a new unrest in the country.

ጉዳያችን / Gudayachn
ግንቦት 1/2010 ዓም (ሜይ 10/2018)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ :- 

  •  አማራ በመባል ብቻ የተባረሩ ኢትዮያውያን ላይ የተሰራ ዜና በኢትዮያ ቴሌቭዥን (ቪድዮ)፣
  • ባህር ዳር የሚገኘው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ቴሌቭዥን ዘገባ (ቪድዮ) ፣
  • የአሜሪካ ራድዮ ጣብያ ዘገባ (ኦድዮ) እና 
  • የቀበሌ ሊቀመንበር ሰዎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ለቀው እንዲወጡ ያዘዘበት ደብዳቤ ቅጅ ተያይዟል። 

በኢትዮጵያ አማራ በመሆናቸው ብቻ ከሁለት ትውልድ በላይ የኖሩበትን ቀዬ ለቀው እንዲባረሩ የተደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ከጉርዳፈርዳ እስከ ኢልባቦር፣ ከሐረር እስከ ጅጅጋ፣ከቤንሻንጉል እስከ ሰሜን ጎንደር ወልቃይት አማራ ናችሁ ተብለው በአደባባይ እየተነገራቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተመፅዋች ሲሆኑ፣የከተማ ጎዳና ተዳዳሪ ሲሆኑ እና እርጉዞች ሳይቀሩ ጫካ እየወለዱ የሚቀምሱት እያጡ ሲሞቱ የኢትዮጵያ ሕግም ሆነ በሔራዊ እየተባለ የሚነገርለት የጦር ሰራዊት እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ አንዳች ነገር ሲያደርግ አልታየም።

ችግሩ ከአቶ መለስ ዘመን ጀምሮ ከፓርላማ እስከ ወረዳ ስብሰባ፣ከኢቲቪ እስከ ኢሳት ቴሌቭዥን ከአሜሪካ እስከ ጀርመን ራድዮ ሁሉም በተመሳሳይ የደረሰውን የዘር ማፅዳት እኩይ ተግባር ዘግበውታል።ሆኖም ግን የአራት ኪሎ ባለስልጣናት አንዳች እርምጃ ሲወስዱ አልታየም።ይልቁንም በህዝባዊ አመፅ ወቅት ስለጠፋ ንብረት በእየመድረኩ በዲስኩር ሲያደምቁ ማየት ተለምዷል።ጉዳዩ አሁን እጅግ የመረረ ደረጃ ደርሷል።በተለይ ታች ያለው ሕዝብ ዘንድ የመጨረሻ የሚባል ደረጃ እንደደረሰ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። የአማራ ተወላጆች እንደ ቤንሻንጉል ከመሳሰሉት ቦታዎች ሲባረሩ ጉዳዩ የሃይማኖት ጥላቻ መነሻ እንደሆነ እየታየም ነው።የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸው ብቻ እንዳሰደዳቸው ብዙ መረጃዎች መጥቀስ ይቻላል።በክልል ስልጣን ላይ የሚገኙት የፅንፈኛ እምነት አራማጅ ከሆኑ የመጀመርያ ኢላማቸው አማራ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ላይ ነው።

የአማራ ተወላጆች ከቀያቸው እንዲወጡ ተደረጉ የሚል ዜና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ሲወራ እንደ አንድ ቀላል ዜና የዜናው አንባቢውም ሆነ ሰሚው እንደ ቀላል ጉዳይ ሰምቶ ከንፈር የሚመጠውም ሆነ እንዳልሰማ የሚያልፈው እኩል የጆሮ ጠገብ አይነት ዜና ሆኗል።ሆኖም ግን እታች ያለው የተጎዳው ሕዝብ መሃል የፈጠረው ምሬት እና በቀላሉ የማይሽር የማኅበራዊ ቀውስ ነገ ለምትኖረው ኢትዮያ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ለሚኖር ማናቸው የጦርነት አደጋ ቅርብ ነው።አንድ ሕዝብ ህገ መንግሥቱም፣ሠራዊቱም መገናኛ ብዙሃኑም፣የሃይማኖት አካላትም ሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በዘሩ ብቻ ተለይቶ መጠቃቱ እያወቁ ዝም ካሉት በመጨረሻ ''በችግር ጊዜ ከወንድም በላይ ነች'' የሚላትን ጠብመንዣውን ይዞ ይነሳል።በእዚህ መሃል የሚወጣ መሪ ደግሞ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ ማንንም እየጠረገ የሚያስኬድ የብሶት ማስታገሻ አቅም ይኖረዋል።

የአማራ ተወላጅ በኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክም ሆነ የነፃነት ትግል ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የወደቀ የተነሳ፣ በቅኝ ገዢ ኃይሎች በተለየ መጠቃት አለበት ተብሎ አዋጅ የወጣበት ሕዝብ ለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።ፋሽሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን በዋናነት በትኩረት የሰራው ተግባር ቢኖር የጎሳ ልዩነት ለመፍጠር መሞከር ነበር።

ለማጠቃለል ከእዚህ በታች የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ኢሳት ቴሌቭዥን፣የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ አገልግሎት እና ባህርዳር የሚገኘው ክልላዊ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሁሉም በአማራነት ሰዎች እየተለዩ መባረራቸውን በማስረጃ እያስደገፉ ዜናውን አቅርበዋል።ሆኖም ግን መፍትሄ የሚሰጥ አካል የለም።ይህ መፍትሄ የማጣት ችግር ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን መንገላታት የሚመለከተው ስደተኞቹን የሚቀበለው የባህርዳር ከተማ ህዝብን ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣኖች ጨምሮ የሚጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ አላደረጉም።ይህ ሁሉ ሲደመር ፍትሃዊ ያለውን ጦርነት ሕዝቡ በማናቸውም ሰዓት ቢያውጅ ድንገት ደራሽ ሊባል አይችልም። ለሁሉም መፍትሄው ግን አሁንም በሕግ እና በሥርዓት የምትመራ ኢትዮጵያን ማምጣት የግድ አስፈላጊ ነው።ይህ ማለት ከእዚህ በፊት ለተገፉት ካሳ ሰጥቶ መልሶ ማስፈር እና ሕዝብ በማባረር የተሳተፉትን ለፍርድ ማቅረብ ሁሉ ይጨምራል።
ከእዚህ በታች አማራ በመባል ብቻ የተባረሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የዜና ማሰራጫዎች የተላለፉ ዜናዎች በናሙናነት ተመልከቱ።
Ethiopian National Television report on Amhara Nationality Ethnic cleansing in Ethiopia (video)
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ግንቦት 8/2018 እኤአ ያስተላለፈው

Amhara Mass Medea report on Amhara cleansing report from Bahir Dar city

ባህርዳር ከተማ የሚገኘው የአማራ ክልል መንግስት  ቴሌቭዥን በግንቦት 7/2018 እኤአ ያስተላለፈው 


Voice of America Amharic service report  on Amhara cleansing on May 2,2018
የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ግንቦት 2/2018 እኤአ የዘገበው 

ESAT  News on Amhara nationality ethnic cleansing (report from Washington DC)
ኢሳት ቴሌቭዥን ከሁለት ዓመት በፊት የዘገበው 



አማራ በመሆናቸው ብቻ ለቀው እንዲወጡ በቀበሌ ሊቀመንበር መጋቢት 10/2010 ዓም የበሎ ዴዴሣ  ቀበሌ መስተዳደር ዴዴሣ የተለጠፈ ደብዳቤ
Benishangule local authority public notice on Amhara nationality to leave their permanent place with in the region. The Federal government did not take any action for such ethnic cleansing public notice.

የበሎ ዴዴሣ  ቀበሌ መስተዳደር
ዴዴሣ

ቀን 16/7/2010 ዓም 

ማሳሰቢያ:_ ለበሎ ዴዴሣ  የአማራ ነዋሪዎች በሙሉ

ይኸውም የአማራ ተወላጆች ለሆናችሁ በሙሉ እስከ መጋቢት 30/7/2010 ዓም ድረስ ወይም እስከ ሚያዝያ 10/8/2010 ዓም ሀብታችሁን ሆነ ንብረታችሁን ሸጣችሁ ሆነ አርዳችሁ  የማትወጡ ከሆነ   ግን  በሕግ ተገዳችሁ  እየታሰራችሁ  ወዳችሁ ሳይሆን  በግድ  ተገዳችሁ  በህግ የምትወጡ መሆኑን  እስከተሰጠው  ጊዜ ገደብ  ካልወጣችሁ  በሚደርስባችሁ ችግር  የቀበሌው መስተዳደር ተጠያቂ አለመሆኑን  በዚህ ደብዳቤ መግለፃችን  እናስታውቃለን

ምንጭ : - ጌታቸው መታፈርያ 




ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...