ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, January 31, 2013

''ሃገሬ ስንት ነች?'' (ከ ጉርዳፈርዳ ወረዳ ለተባረሩ በ ሺህ ለሚቆጠሩ ስዱዳን መታሰቢያ )

ማሳሰቢያ:- ይህ ፅሁፍ አምና ድርጊቱ(በ ደቡብ ክልል ማጂ ዞን በጉርዳፈርዳ ወረዳ ለ ዘመናት የኖሩ ኢትዮጵያውያን በግድ ማፈናቀል) እንደተፈፀመ(መጋቢት 30/2004 ዓ.ም.)  የተፃፈ ፅሁፍ ነበር። ብዙዎች በ ዜናነት ከማተት ባለፈ በተገቢው ያህል አልተናገሩለትም።ጉዳዩ ግን የመላው ኢትዮጵያውን በ አንድቦታ የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብቱን ስለሚንድ ከ እርሱ ጋር ተያያዥ የሆኖ ሕጎችን በሙሉ ስለሚያፈርሳቸው ከ ሕግ እና ከ ፖለቲካ ጥያቄ በዘለለ ለመመልከት የሚያስገድድ ነው።በትናንትናው እለት ጥር 23/2005 ዓም ጉዳዩ እንደገና አለም አቀፍ ዜና ሆኖ ቀርቧል።የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት በ ምክርቤት ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲናገሩ ''ማንም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ቦታ የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብት አለው'' የሚለውን የ ህገመንግስቱን አንቀፅ ከመጥቀስ ይልቅ በደምሳሳው ''መሬቱን የ ደቡብ ክልል ነው የጠየቀው ፣ጉዳዩን ማራገቡ ማናችንንም አይጠቅምም'' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህን በሚናገሩበት ሰዓት ግን በ ሺ የሚቆጠሩ ከ አካባቢው ለዘመናት የኖሩ ነዋሪዎች ''የተሰራብንን ግፍ መንግስት ይመልከትልን'' ብለው ለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት እያሉ ነበር። 

''ሃገሬ ስንት ነች?'' አቤል ጥያቄ 
አቤል ይባላል ደቡብ ኢትዮጵያ ከ ማጂ ዞን ጉርዳፋርዳ ወረዳ ተወልዶ ያደገ ከወረዳዋ በተለየ ሌላ ሀገር ያለ የማይመስለው የ አስራ ሁለት ዓመት ልጅ ነው።ደስተኛ ህይወቱን የመንደሩ ነዋሪ ሁሉ ይመሰክርለታል። ዛሬ ግን የደስታ ድባቡ ጠፍቶ በ ሃዘን የተዋጠ ልጅ ለመሆኑ በቂ ምክንያት ነበረው።
አቤልን የ መንደሩ ነዋሪ በጋራ ያወጣለት ስም አለ። ' ሮጦ የማይደክመው ' የሚል።ቀኑ ሙሉ ይሮጥበት የነበረው ሜዳ ዛሬ ወፍ ዝር አይልበትም ህዝቡ ንብረቱን ትቶ መሄድ ከጀመረ ወር ሊሞላው ነው። አቤል
ከ አራት የእድሜ አቻዎቹ ጋር ስለ ሰሞኑ ጉድ በ ልጅነት እግሩ ለ አምስት ሰዓት ያህል ቆሞ ካወራ በኋላ እንኳን ለ አንድ ደቂቃ ያወራ አልመስልህ ብሎት ስለመሸበት ብቻ ወደ ቤቱ ሄደ እንጂ ቤቱ አስጠልቶታል ። አሁን ግን መሸበት እናም እንዳቀረቀረ ወደ ቤቱ አመራ።

ማታ አባቱ የነገረው ነገር አሁንም እውነትነቱ አልገባ አለው። አባቱ ብቻ አደለም በ አስር ሺ የሚቆጠር ህዝብ ''በቶሎ ሃገሩን ለቃችሁ ውጡ!'' ተብለው ሰማይ ምድሩ ተደፍቶባቸው አይቷል።
አባት የ መንግስት ትዛዝ ገርሞታል ፣ደንቆታል፣ከ ሁሉ ያስለቀሰው ለ ብዙ ዓመት ያስቀደስበት ልጆቹን ሁሉ ክርስትና ያስነሳባት የ ቤተክርስትያኑ ጉዳይ ነው።'' ከ መድሃኔ ዓለም ታቦተ-ሕግ ርቀን ከ ክርስቶስም ሳንሆን ከ ለፋንበትም ንብረት ሳንሆን ሁለት ወር 'ሁዳዴ ' ፆመን ሳንገድፍ ስደተኛ ሆን ማለት ነው ?''ይልና ቀጥሎ ''ምን አይነት ሰዎች ምን አይነት ስብሰባ አርገው ከቀዬአችን ሊያስወጡን ወሰኑ አንተ? ምን አጠፋን? ሕግ ይሄን ያክል ተናቀ?መንግስት ምንም ግፍ ያልተፈፀመ ይመስል በ ራድዮና ቴሌቪዥኑ አለመናገሩ ምን ማለት ነው? '' ይላል።ለ አቤል ግን ''ምን አይነት ሰዎች ምን አይነት ስብሰባ አርገው ከቀዬአችን ሊያስወጡን ወሰኑ? ምን አጠፋን? ሕግ ይሄን ያክል ተናቀ? መንግስት ምንም ግፍ ያልተፈፀመ ይመስል በ ራድዮና ቴሌቪዥኑ አለመናገሩ ምን ማለት ነው? '' ሲል አባቱ ማታ የተናገረው ንግግር ጆሮው ላይ ይደውልበታል ።አባቱ ድሮ ' መንግስት' የሚለው ቃል በጣም ያከብር የነበረ መሆኑን ያስታውሳል። አባቱ ብቻ አደለም።የ ስነ -ዜጋ ትምህርት መምህሩ ስለ አንድ መንግስት 'ኃላፊነትና ግዴታ' ብዙ አስረድተውታል።።የ መንግስትን ብቻ አደለም የ አንድ ዜጋን ግዴታና መብትም ነግረውታል። በ ስነ-ዜጋ ትምርት ፈተናም ላይ ሁል ጊዜ ከ ዘጠና በላይ በማግኘቱ ሁለት ጊዜ በመምህሩ መሸለሙን አይዘነጋውም።

ሰሞኑን ጎረቤቱ ሁሉ ተሰብስቦ የ ሚነጋገርበት ጉዳይ አንድ ብቻ ነው :-
''ውጡ ተባልን'' የሚል። አቤል ጎረቤቱ ስነጋገር ቀድም ብሎ ማውራት ልማዱ ነው ጎረቤቱ ቡና ላይ ''ሀገር ልቀቁ'' ስለተባለው ወሬ ሲሰማ ነጠቅ ያረግ ና ''ሊሆን አይችልም ......የ አንድ መንግስት ግዴታ .....ነው ። ህገ መንግስቱ አንቀጽ ....ላይ .....የሚል አለ'' ብሎ ከ ስነ ዜጋ ትምርት የተማረውን ሊያስረዳ ይሞክር ነበር። በ ልበ ሙሉነት። ጎረቤቱም ሆነ ወላጆቹ በመጀመርያ እሱ የነገራቸውን የ ህገ መንግስት አንቀፅ ከ ወረዳው ሹሞች ጋር ሲነጋገሩ ይጠቅሷት ነበር።ቆይቶ ግን ጥቅስ እና ተግባር መለያየቱ ገባቸው።
ዛሬ ግን ከ ቤተሰቡ አልፎ አቤልም ያ! የ ስነ- ዜጋ መምህሩ የነገሩት ሁሉ ውሸት መሆኑን የተረዳው የ መንግስት ወታደር አጎቱን ና አባቱን ቤተሰባቸውን ይዘው ከ ሌሎች በ ሺህ ከሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጋር ለቀው እንዲወጡ የሚገልፅ ደብዳቤ ለመላው የ ጉርዳፈርዳ ሰፋሪ ሕብረተሰብ ከታደለ በኋላ ነበር።
ታላቅ ወንድሙ የዛሬ ሰባት ዓመት የ ስምንት ዓመት ልጅ ሳለ-በ 1997 ዓም በነበረው የ 'ቅንጅት' ምርጫ ተብሎ በሚጠራው ጊዜ '' ስነ-ዜጋ ትምህርትና የ ገሃዱ ዓለም አልጣጣም አለኝ'' ብሎ ሲናገር ና አባቱን በጥያቄ ሲያጣድፍ የነበረ መሆኑ ዛሬ ይበልጥ ትዝ አለው። አቤል ተገረመ በ ልጅነት አናቱ ላይ ጉዳዩ ሁሉ ፈላበት።
ድንገት ተነሳና ወደ አባቱ ሄደ ቤተሰቡ የሚይዘው ግራ ገብቶታል።
አባት ያሉትን በሬዎች በተገኘው ዋጋ ለመሸጥ ይጣደፋል። ልጆች ፍራሽ ያስራሉ።
እናት በርጩማ ላይ ራሷን በ ሁለት መዳፍዋ ደግፋ ተንሰቅስቃ ታለቅሳለች። አቤል አባቱን ሊጠይቅ የነበረውን ጥያቄ ተወው። እንባው አቀረረ በ እንብርኩ ሆነና እናቴን ባፅናናት ብሎ ያሰበውን ቃላት መደርደር ጀመረ። ወድያው እንባውን ማቆም አቃተው። ቀጠለና :-


''እማ በቃሽ ስንት ቀን ታለቅሻለሽ? እኛ ልጆችሽ እስካለን ሁሉ ይተካል።ደግሞ ሌላ ምትክ ቦታ መንግስት ይሰጠን ይሆናል'' ብሎ ከመናገሩ
እናቱ 'እሳት ጎርሳ' ተነሳችና በቁጣ አየችው ልጅ መሆኑን የረሳች ይመላል ቀጠለችና
'' ካሁን በሁዋላ መንግስት መንግስት አትበል ከፊቴ.......
ከ አባትህ ጋር ከእዚህ ቦታ ስንመጣ አንድ ወፍ ዝር አይልም ነበር።
አባትህ ወደ እርሻ ሲሄድ ስንት ጊዜ ነብር የበላው ይሆን? እያልኩ ነፍስ እና ሥጋዬ ስትላቀቅ ከረምኩ?እመብርሃን ባማላጅነቷ ከለለችልኝ እንጂ......ተምርያለሁ ከምትሉት ከናንተ እኔው ደንቆሮዋ እሻላለሁ። መንግስት ለምንድነው ነፍስና ሥጋዬ እየተላቀቀ ካቀናሁት መሬት ና በፍቅር ከምኖርበት ሕዝብ የሚነጥለኝ? በል አስረዳኝ? የ እንጀራ ልጅ ነን እኛ ? ንገረኝ ያንተ ትምርት ለ እዚህ መልስ ካለው አሁን ንገረኝ? በላ? .......የዛሬ ሳምንት ለቀው የሄዱት እነ እማዋይሽ የት እንዳሉ ታውቃለህ? ከ መንግስት አድርሱን አቤት የምንለው በደል አለ ብለው ቢሄዱ የሚያናግራቸው ጠፍቶ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ግቢውን ከፍቶላቸው ሰርቶ የሚበላ እጃቸው ያዲሳባ ሕዝብ ለማኝ መሆናቸውን አሁን አባትህ ነገረኝ። እረፈው ! እናትህ ለማኝ ልትሆንልህ ነው!'' ለቅሶው ባሰባት።
ቤተሰቡ ንብረቱን እየሰበሰበ ሁሉም ጆሮውን ጣል አርጎ ይሰማ ነበርና ሁሉም ይህን አዲስ ግን ደግሞ ሌላ መከራ ሲሰማ ስራውን አቁሞ ማልቀስ ጀመረ። መንደሩ ሰሞኑን ለቅሶና 'ኡኡታ!' ለምዷል የለቅሶው ምክንያት ስለሚታወቅ ማንም አዲስ ነገር ተፈጠረ ብሎ አይመጣም። ወደ ምሽቱ ላይ ሁሉም ተሰብስቦ ለወጉ ያህል ቡና ተፈልቶ ''የናንተ መቼ ነው ውጡ የተባላችሁት? የናንተስ መቼ ነው?'' መባባል ልማድ ከሆነ ሰነበተ።

ECADF Ethiopian News
በሽፈራው ሽጉጤ ትዕዛዝ ከተፈናቀሉት የአማራ ብሄር ተወላጆች መካከል ጥቂቶቹ(ፎቶ ከ ECADF)


አቤል ግራ ገባው እናቱ ማፅናኛ የሚለው ቃላት ሁሉ ማለቃቸውን ሙሉ በሙሉ አወቀ። እናቱ ብዙ የምትበልጠው ነገር መኖሩ ዛሬ ገባው። ዛሬ በፊት ዳዊት መድገም ብቻ የምትችል ይመስለው ነበር። የእርሱ ስነ-ዜጋ ትምህርት ቢያንስ ዛሬ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ተረዳ።
''መንግስትና ሕዝብ......መንግስት ለ ዜጎቹ ያለበት ግዴታ......ዜግነት......የ ዜግነት መብቶች......ወዘተ'' የሚሉት የ ስነ-ዜጋ ትምርት ላይ ያሉ ቃላት በ አይኑ ላይ ተርመሰመሱበት።
ቀና ሲል አባቱ በፍቅር ሲመለከተው አየ። ለመጠየቅ ድፍረት አገኘ። የ አባቱ አይኖች እንደዚህ የሚያዩት ከሆነ የጠየቀው ሁሉ እንደምደረግለት ያውቀዋል። እና ጠየቀ

'' አባ'' አለ አቤል።
''ወየ ልጄ'' አለ አባት ተስፋ የቆረጠ ፊቱን ወደ ልጁ አዙሮ።
'' ስነ-ዜጋ ትምርት ላይ ትቸር መንግስት ለ ህዝቡ ያስባል፣ህዝብን ይንከባከባል ያሉን ውሸት ነው ማለት ነው?ማነው የ ስነ-ዜጋ ትምርት ደብተሬ ላይ የተፃፈውን ከ ደረሰብን ጋር የምያስታርቅልኝ ?'' አለው ሲፈራ ሲቸር።
አባት ለመልሱ ጊዜ አልወሰደበትም '' አንተው ነህ ልጄ አንተው ነህ! ስነ-ዜጋ ደብተርህ ላይ የተፃፈውን የሚያጣምሙትን የምታስተምር አንተው ነህ ልጄ ዓለም ይሄው ነች በ ዘረኞች፣በ ጥቅመኞች ፣ ህዝብን ከ ሕዝብ ጋር በ ማላተም ትርፍ ያገኙ በሚመስላቸው ሰዎች ተሞልታለች። ሆኖም ግን ፀረ-ዘረኞች፣ፀረ-ጥቅመኞች ና ህዝብን ከ ሕዝብ ጋር በሚያስማሙ ሃሳብ አፍላቂዎችና ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ከ አደጋ ድናለች በ እያንዳንዱ የ ህዝቦች አደጋ ውስጥ አንዳንድ የ አደጋ አምካኞችን እግዝያብሔር ፈጥሮላታል።ለምሳሌ በ አሜሪካ የ ባርያ ፍንገላ ውስጥ አብርሃም ሊንከንን፣ በ ናዚና ፋሺዝም ክፉ ተግባር ውስጥ እነ ዊንስተን ቸርችልን እየፈጠረ ሰዎችን አድኗል። ማን ያውቃል ደብተርህ ላይ የተፃፈውን ከ ገሃዱ ዓለም ጋር የምታስታርቀው አንተ የማትሆንበት ምን ምክንያት አለ? ንገረኝ ምን ምክንያት አለ? ከ ቂም በቀል ነፃ ልቦና ብቻ ይዘህ እደግልኝ ልጄ አይዞህ !'' አለ አባት ።


አቤል እንባውን አቅርሮ ዝም አለ።

አባት ቁጢጥ ብሎ ቁመቱን ከ ልጁ ቁመት ጋር አስተካከለና '' ልክ አደለም? ተሳሳትኩ ?'' አለ።
አቤል ራሱን ግራና ቀኝ በማወዛወዝ አለመሳሳቱን ገለፀ አሁን ግን እንባው መውረድ ጀምሮ ነበር። አባት ወደደረቱ አስጠጋውና ''ታድያ ለምን ታለቅሳለህ? እኔ አባትህ እያለሁ ክንዴን ሳልንተራስ አይርብህም፣ አይጠማህም ሁሉን ሰርቼ ነው ያገኛሁት የሰው ላብ አልወሰድኩ ሁሉን መልሼ አገኘዋለሁ!'' አለ።
አቤል '' ለ እዛ አደለም የማለቅሰው''
''ታድያ ሌላ ምን አዲስ ነገር መጣ የማላውቀው?''
አቤል ወደመሬት አቀርቅሮ ዝም አለ።
''ንገረኝ አይዞህ የኔ ጌታ ንገረኝ'' አባት ግራ ተጋባ።
'' ነገ ትምርት ቤት አልሄድም እነ ሰጠሄኝ፣እነ ግርማቸው ሁላችንም ባንድቀን መለያየታችን ነው ....ጓደኞቼን .....አስተማሪዬ ቲቸር አልማዝ.....ቲቸር አልማዝ አንድም ቀን ሲያለቅሱ አይቼ አልቅውቅም ነበር ትናንት ግን ውጡ ተብለናል ብለው መሬት አቀርቅረውሲያለቅሱ ነው የዋሉት......እህህህ '' አቤል ጧ ብሎ አለቀሰ።

አባት ለዚህ አይነቱ ነገር መልስ የለውም።ልጁን አቅፎ አብሮ ማልቀስ ጀመረ።በ ልጅነቱ ባንዲት ጀንበር ቀየውን ለቆ ብሄድ ለ አንድ ሕፃን ልጅ የሚፈጥረውን ስሜት አሁን ልብ ]አለው።አባትና ልጅ ተላቀሱ። በ መሃል አባትና ልጅን የለያያቸው የ መንግስት ታጣቂ ከ ቤት ገብቶ በጁ የያዘውን የ ስም ዝርዝር እያነበበ ''የናንተ ወረዳውን ለቃችሁ የምትወጡበት ቀን ነገ መሆኑን አውቃችኋል? '' ብሎ ሲደነፋና በ ቁጣ አይን ቤተሰቡን ስገላምጥ ነበር። ታጣቂው ቶሎ ከቤት መውጣቱ ነው አንጂ ትልቅ ፀብ ሊፈጠር የነበረ መሆኑ የ ቤቱ የ ዝምታ እና ሊገነፍል ያኮበኮበ የ ቁጣ መንፈስ ያስታውቃል።
////////////////--------------/////////////////////-----------------//////////////////////////----------------///////////
ይህ ከ ሆነ ከ ሳምንት በኋላ አቤል ና ቤተሰቡ የተገኙት አዲስ አበባ በ አንድ መጋዘን ውስጥ ከ ብዙ ከነርሱ መሰል ስዱዳን ጋር ነበር። አቤል አሁንም የ ስነ-ዜጋው ደብተር ላይ የተማራት ስነ-መንግስት ምራፍ ሶስት ላይ ያሉት ፅሁፎች ትዝ ብለውት እረፍት ነሱት። ቢቸግረው ያገኘውን ሰው ሁሉ መጠየቅ ጀመረ። ቆይቶ ግን አጎቱ ''ልጄ ደብተርህን በጉያህ አርገው! እንዳታስፈጄን '' ያለው ንግግር ዝም አንዲል አረጉት።
አቤልን አጎቱ ''ደብተርህን በጉያህ!እንዳታስፈጄን'' ያሉት ቀን አይረሳውም።ቀኑ የ አዲስ አበባ የ መጋቢት ወር ዝናብ መሬቷን ማራስ የጀመረበት ቀን ነበር።ድንገት ''ከ መንግስት የመጣን ነን መንግስት የወሰነውን ልናሳውቃችሁ ነው '' ያሉ ሰዎች ስደተኞቹ ወዳረፉበት መጋዘን መጥተው መንግስት ወደየ ክልላችሁ ግቡ በሏቸው ብሎናል'' ብለው ሲናገሩ ።

አቤል በንዴት ተነስቶ

'' ሃገሬ ስንት ነች? ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም? እስከ ዛሬ የኖርኩባት የኔ ሀገር አደለችም ? የተወለድኩት ጉርዳፋርዳ ነው። ሌላ ሀገር አላውቅ?'' አቤል በንባ የተሞሉ አይኖቹን ይዞ ፊቱን ከ ካድሬው ወደ አባቱ አዞረና ጥያቄውን ደገመው። በ አዳራሹ ውስጥ ያሉት ሁሉ ትንፋሻቸውን ውጠው ማዳመጥ ጀመሩ።አቤል ቀጠለ '' አባዬ ሃገረ ስንት ነች? ሀገራችሁ ግቡ የሚለን?''ብሎ ሲናገር አዳራሹ ለቅሶ በለቅሶ ሆነ።
ከለቅሶው ቀጥሎ ግን ጥያቄው ጎረፈ በተለይ በትምህርት ገፋ ያሉት ጥያቄ ሊያባራ አልቻለም።
''በ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ መኖርያውን ትቶ መሰደድ የ ሀገር አደጋ አደለም? ቀይመስቀል የት ነው? የ አደጋ ጊዜና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል መስርያበት በ 'ብአዴን ' ተተካ? ይህ ሰው ሰራሽ አደጋ አይደለም?'' ወዘተ ጥያቄ።

የ አቤልን የምታህል ከባድ ጥያቄ ግን አልተገኘችም የ ትውልዱ ጥያቄ ሆና ትኖራለችና።

'' ሃገሬ ስንት ነች? ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም? እስከ ዛሬ የኖርኩባት የኔ ሀገር አደለችም ?'' የምትለዋ ጥያቄ።

አዎን ሀገራችሁ ግቡ ባዮች ከ አቤል የከበደ ጥያቄ ይገኝላችሁ ይሆን ? ሀገራችን ኢትዮጵያ በናንተ አቆጣጠር ስንት ነች? አሁን የምንኖርባት ሀገራችን አደለችም? ምንጭ 
በ ጌታቸው በቀለ

ኦስሎ
የታሪኩ መነሻ የ አሜሪካ ድምፅ ራድዮን የ አማርኛው አገልግሎት በ መጋቢት / 2004 ዓም የዘገበውንና ከዚህ በታች የተያያዘውን ከፍተው ያዳምጡ።
http://www.voanews.com/templates/mediaDisplay.html?mediaPath=http://media.voanews.com/audio/AMH_aa_Farmers_dislocated_in_Southern_Ethiopia_Part_1-04April2012.Mp3&mediaContentID=፩፬፮፫፮፲፩፭


   

5 comments:

Anonymous said...

dear Getachew, 3 wendoch lijoch alugn.tarikun kanebebku behuwala aleqesku.lib yemineka tarik!

Ye HARER LIJ said...

HAGERE SINT NECH???
This must be every body's current question.
My three generation lived in Harer. I was born also in Harer.But now we are not autorized to work in Harere.
Please get me an ansewr for the perfect current Ethiopian question-
Is not Harer my country? wher is my country? can any body from so called EPRDF TO MY TOP QUESTION
HAGERE SINT NECH????????????????

Anonymous said...

I thought and I believe Hagerachin andit nat, and egziabeher yemimelekibat. I am an Ethiopian, Amhara and my wife is Ethiopian, Tigray: what answer should i give to my children if they ask me the name of our country, surely Ethiopia. Gin betam yamal, yikenekinal. Hagere sint nech? Andit nat bil idealist yasegnegn yihon? Ere befitsum ersua andit nech, yesew megegna yedingil marayam yeaserat hager. Ena ahun sint honish emama Ethiopia? Melishilin!!!

Anonymous said...

እኔንም አስለቀሰኝ። እጅግ አንጀቴን በላኝ። አምላክ ሆይ ኧረ በቃ በለን? ኧረ እነዚህን ሰዎች ወይ ልቦና ስጥልን ወይ አንሳልን። ኧረ ተፈተንን

Anonymous said...

Thank you for being a mouthpiece for the voiceless who are languishing under woyane ethnic fascists. http://vimeo.com/18242221 I donot think even the Italian fascists committed such crimes on the Ethiopian people like these home grown fascists.