ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 30, 2018

የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ጠላት የህወሓት አዛውንት መሪዎች ናቸው

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ : -

  • አዛውንቶቹ የሴራ ፖለቲካ ባለቤቶች የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለዩባቸው ሁለት መንገዶች እና 
  • የጀብሃ ዘፋኝ በኃላ ሻብያን ሸሽታ በስደት ባለፈው ሳምንት ያረፈችው ፀሐይ ባራኪ (ፀሐይቱ) በጆሲ ኢን ዘ ሃውስ የተቀናበረው ዜማ (ኦድዮ) ያገኛሉ።

ጉዳያችን / Gudayachn 
ግንቦት 23/2010 ዓም (ሜይ 31/2018 ዓም)

ነሐሴ 18፣2004 ዓም ፍኖተ ነፃነት በተሰኘው ጋዜጣ በዳሰሳ ዓምድ ስር በዞን ዘጠኝ ፀሐፊዎች የቀረበው ፅሁፍ ላይ የህወሓት አነሳስን ስገልጥ የሕወሓት ወላጅ ከሆነው  መስራች አባላት አንዱ ከሆኑት አረጋዊ በርኸ The Origin of The Tigray People’s Liberation Front በሚለው ጥናታቸው ላይ ያሰፈሩትን መነሻ ያደርጋል።አቶ አረጋዊ በእዚሁ ፅሁፋቸው ህወሓት አፈጣጠሩ ሲጀምር መጀመሪያ ትግራዋይ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ሕብረት ተብሎ እንደተፈጠረ ይነግሩናል፡፡ የህብረቱ አባላት ከሆኑት ውስጥ መለስ፣ ተክሌ እና አባይ ፀሃዬ የዩንቨርስቲ ተማሪዎቹን ማኅበር  አርታኤ ቡድን ይመሩ ነበር፡፡ የኅብረቱ ዋነኛ ዓላማ ለትግራይ ሕዝቦች ፖለቲካዊ ንቃት ማጎናፀፍ ብቻ ስለነበር፣ ከዚያ የተሻለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችል በሚል “ማህበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ” (ማገብት) ተወለደ፡፡ ማገብት  የህወሓት ወላጅ አባት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ማገብት ህወሓት ከመመስረቱ በፊት ከኅግሓኤ (ሕዝባዊ ግምባር ሓርነት ኤርትራ) ጋር የሥራ ግንኙነት መስርቶ ነበር፡፡ (ስሙም ከዚያው የተገኘ ይመስላል፡፡) መለስ ከህወሓት፣ ጥቂት ቀደምት አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ መጽሐፍት እንደሚተርኩት መለስ ዜናዊ እና አቦይ ስብሓት የህወሓት መስራቾች ሳይሆኑ፣ ከተመሰረተ ጥቂት ወራት በኋላ ትግሉን የተቀላቀሉ መሆናቸውን A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975- 1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ አረጋዊ በርኸ ጽፈዋል፡፡

አዛውንቶቹ የሴራ ፖለቲካ ባለቤቶች የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለዩባቸው ሁለት መንገዶች 

ህወሓት ከተመሰረተ በኃላ የመጀመርያ የጅራፍ በትሩን ያሳረፈው የኢድዩ እና የፊውዳል ርዝራዦች ናችሁ እያለ የትግራይ አዛውንቶችን እና እናቶችን ወደ ማጎርያ ከመላክ እስከ ግድያ እና ለስደት የዳረገ ድርጅት ነው።በእዚህም ሳብያ ላለፉት አርባ ዓመታት ሙሉ የትግራይ አንድ ትውልድ ጨርሶ በህወሓት ቅኝት ብቻ የተቃኘ አንድ ትውልድ ፈጥሯል። ይህ በህወሓት ቅኝት የተፈጠረው ትውልድ የተቀረፀበት አንዱ እና ዋነኛው ባሕሪ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ትግራይን እና የትግራይ ተወላጆችን በጠላትነት እንደሚመለከት አድርጎ መሳል እና የዐማራ ተወላጅ ዋነኛ ጠላት ነው የሚል ትርክት በማስቀመጥ (በ1967 ዓም ባወጣው ማነፈስቶ ላይ እንዳስቀመጠው) ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አባቶቹ ተፈጅተው የተረፈው ትውልድ ሌላውን ኢትዮጵያዊ የሚፈራ አድርጎ ቀርፆታል።

ይህ ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንዲፈራ ተደርጎ የተቀረፀው ትውልድ የፍራቻ እና የማራራቅ ስራው የሚሰራው እና የሚቀመመው በአዛውንቶቹ የህወሓት አመራር ነው። ላለፉት አርባ ዓመታት በተንኮል እና የሴራ ፖለቲካ የተካኑት አዛውንት የህወሓት አመራሮች ላለፉት አርባ አመታት ውስጥ የመጣውን ትውልድ ስሜቱን ከወጣትነቱ ጀምሮ የመጠቀሙባቸው ሁለት መንገዶች በማስደንበር እና በማጋጨት ነው።የማስደንበር ስራው የሚከናወነው ተከታታይ የፕሮፓጋንዳ ሥራ በስብሰባዎች፣በፅሁፎቻቸው እና በመገናኛ ብዙሃን ሲሆን።ተደጋግሞ በመናገር ብዛት ይህንን ትውልድ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የትግራይ ጠላት እንደሆነ ይህንን ጠላት ካሉት ለመታደግ ደግሞ የህወሓት አዛውንቶቹ አመራር ብቸኛ ጠባቂዎቻቸው እንደሆኑ እንዲሰማቸው አእምሯቸውን የመቆጣጠር ሥራ ለአመታት ሲሰሩ ኖረዋል።


ከማስደንበር ስራው በተጨማሪ የህወሓት አዛውንት አመራሮች የትግራይ ሕዝብ የመጨረሻ ምሽጋቸው እና ምሰሷቸው መሆኑን በማመን የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ግልጥ የሆነ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል።  እነኝህ ግጭቶች ለአዛውንቱ አመራር ሆን ተብለው የሚፈጠሩ እና የትግራይ ሕዝብ ሁል ጊዜ ሰግቶ እንዲኖር የሚያደርግበት አይነተኛ መሳርያ ሆነው አገልግለውታል። ለእዚህ አብነት የሚሆኑትን ምሳሌዎች ማንሳት ይቻላል።በ1997 ዓም ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ህወሓት ''ኢንተርሃምዌ'' የምትለዋን ቃል የተጠቀመበት በመጀመርያ ደረጃ የትግራይን ሕዝብ ለማስደንበርያነት ነው።በቀጣይ ቀናትም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የጎረቤት ፀብ ሳይቀር ስም እየጠቀሰ በመገናኛ ብዙሃን መጠቀስ የማይገባው ፀያፍ ዜናዎችን ሲሰራ ሰንብቷል። በቅርቡ ደግሞ በወልዲያ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተሞች የተደረጉ በእግር ኳስ ጫወታ ሳብያ የተፈጠሩ ግጭቶች ብዙ ሰው የሚያስበው በጫወታው መሃል የተነሱ ግጭቶች አድርጎ እንጂ ከጀርባ የትግራይን ሕዝብ ለማስደንበር የሴራ ፖለቲከኞች አዛውንት የህወሓት አመራሮችን ፈፅሞ አላሰባቸውም።ሆኖም ግን በወልዲያ በፒክ አፕ መኪና ተጭነው ጫወታው ከመደረጉ በፊት ከተማዋን እየዞሩ ጠብ የሚጭር ቃላት የሚያወጡ ወጣቶችን ከትግራይ ይዞ መጥቶ ከዋዜማ ጀምሮ ሕዝቡን ለፀብ ያዘጋጁ እነማን ናቸው? በአዲስ አበባው የወልዋሎ የአዲግራት ዩንቨርስቲ ቡድን ጋር የተፈጠሩ ፀቦች ተራ ግጭቶች ናቸው? እስከ ዳኛውን መልበሻ ክፍል ድረስ እየመጡ ከጫወታው በፊት የተደረጉ ነገር የመቆስቆስ ስራዎች በኃላም አሰልጣኙ በቀዳሚነት የተሳተፈበት ግጭት ሜዳ ላይ ብቻ በተፈጠረ የስሜት መጋል የተከሰተ ከሆነ ጥሩ ነው።ሆኖም ግን ቅንብሩ አይመስልም።ከእዚህ በተለየ ህወሓት የማስደንበር ሌላ ተግባሩን የሚፈፅመው እንደ የግል ንብረቱ የሚመለከተውን የትግራይ ሕዝብ በድንገት ከቦታችሁ ተነስታችሁ ለቃችሁ ወደ ትግራይ ኑ! እያለ ከጎንደር እስከ ደቡብ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን በሚስጥር የሚያውቀው ሊከሰት የሚችል ግጭት አለ የሚል የተሳሳተ መልዕክት እየላከ የማስደንበር ተግባር መፈፀሙን ባለፉት ሁለት ዓመታት የታዘብነው ጉዳይ ነው።እዚህ ላይ በውጭ ሀገር የሚገኙ የትግራይ ልማት ማኅበራት አመራር የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ተመሳሳይ የማስደንበር እና የማጋጨት ሥራ በትግራይ ተወላጆች ላይ እንደሚሰሩ የአደባባይ ምስጢር መሆኑን ሳንዘነጋ ነው።

ይህንን ሁሉ የግጭት እና የማስደነበር ሥራ ሲሰራ አስተሳሰቡን በአዛውንቶቹ የተንኮል መረብ ቁጥጥር ስር የወደቀው ሌላው የትግራይ ተወላጅ ነገሮችን አጢኖ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተባብሮ ከመስራት ይልቅ በትግራይ ልማት ማኅበር በኩል የመጣ ብጣሽ ወረቀት መልዕክት ማመኑ ምን ያህል በሚገባ እያገናዘበ እንዳልሆነ እና በአዛውንቶቹ የሚሰራበትን ተንኮል እንዳላየ ሲያልፈው ይታያል።ይህ ግብ ውሎ አድሮ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ማወቁ ነው ቁምነገሩ።አንዳንዶች ህወሓት ባይመጣ ኖሮ ትግራይ ከተሞቿ ፎቅ ሊኖራቸው እንደማይችል ያስባሉ።ሆኖም ግን ሃያ ሰባት ዓመት ማለት ቀላል ጊዜ አይደለም።እነ ሐዋሳ፣ሻሸመኔ እና አዳማ ከተሞች ያደጉት በጊዜ ሂደት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ህወሓት ባይመጣም አሁን ትግራይ ያለው ልማት እንደሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ቢያንስ የመሰረተ ልማት እና የከተሞች መስፋት አይደርሳትም ብሎ ማሰብ አይቻልም።የህወሓት አዛውንቶች ኖሩም አልኖሩም ትግራይ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመልማት ሂደቷ አይቆምም።አንዳንዶች የትግራይ ተወላጆች ህወሓት ቤተ መንግስት ከሌለ ትግራይ ልማት የማታይ አድርገው የሚያስቡ አሉ።ሆኖም የሕግ የበላይነት እና እኩል ተጠቃሚነት ጋር ዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ከተስተካከለ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ይልቁንም ከታሰበው በላይ የማደግ እድሉ ትልቅ ነው።የህወሓት አዛውንት መሪዎች ግን አሁንም የትግራይን ሕዝብ ሊያሞኙ ይሞክራሉ።

የተንኮል ፖለቲካ ባለቤቶች አዛውንቶቹ ገለል ማለት አለባቸው

ህወሓት ከሁለት ዓመት በፊት መደበኛ ስብሰባውን ሲያደርግ አዛውንቶቹን አመራሮች ለማስወገድ እና ለውጥ ለማምጣት (ምን አይነት ለውጥ እንዳሰቡ አልታወቀም) ወጣቶቹ እና ጎልማሶቹ ከፍተኛ ርብርብ አድርገው ነበር።ሆኖም የአዛውንቱ ክፍል አሁንም በድንገት ደርሶ ወንበሩን ያዘው።በእዚህም አቶ አባይ ወልዱ የመጨረሻ ድምፅ የተሰጠባቸው በአስረኛ ደረጃ የተመረጡ ቢሆኑም ወደላይ መጥተው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን ከወልቃይት እስከ ወልድያ የትግራይን ሕዝብ ከቀረው ወንድሙ ጋር በድንበር አጋጭተው ገበያም እንዳይደራረስ እያደረጉት ነው።አንድ አመራር ለሕዝቡ የሚያስብ ከሆነ ዘለቄታ የህዝብ ግንኙነት ላይ እንጂ ጊዜያዊ  ግንኙነት ላይ ብቻ ሊያልም አይችልም። የህወሓት አዛውንት አመራሮች ግን የነበረውን የህዝብ ግንኙነት ሲያደበዝዙ ሲታይ የትግራይ ሕዝብ ዋና ጠላት ይሄ የአዛውንቶቹ አመራር መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

ባጠቃላይ ለትግራይ ሕዝብ ቀዳሚ ጠላቱ የህወሓት አዛውንት አመራሮች መሆናቸውን ማወቅ አለበት።ሕዝቡን የሚወድ አመራር  ሕዝቡን ከህዝብ አያጋጭም።ይልቁንም ለዘለቄታ አብሮ የሚኖርበትን መንገድ ሲፈልግ ይታያል።በህወሓት አዛውንቶች እና አፈቀላጤዎቻቸው ዘንድ የሚታየው ግን ከእዚህ የተለየ ነው።በመድረክ ንግግሮቻቸው የሚያቃቅር እና ሁሉን ነገር በኃይል እንዲፈታ ሲነግሩት ይሰማሉ።በመጋጨት እንጀራ እንደሚገኝ ይመክሩታል።እነርሱ በመጡበት መንገድ ብቻ መፍትሄ እንዳለ በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ላይ ተቀምጠው ይመክሩታል።ስልጣን ላይ ከወጡ ሩብ ክፍለ ዘመን እንዳለፈ እና በእነኝህ ዘመናት ውስጥ በርካታ ነገሮች መቀየሩን እረስተውታል።በተጨማሪም ከእነርሱ ውጭ ህዝቡ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዙለታል። ይህ ሁሉ ግን ተራ ፈጠራ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ ሲኖር ያለፉት ሃይ ሰባት አመታት የመጀመርያው አይደለም።አሁን ያለው መፍትሄ አንድ ነው።ይሄውም ለዘመናት በላዩ ላይ ሆነው ያረጃ የማርክስ ርዕዮት የጫኑበትን  የአዛውንቶች አመራር ላይ መነሳት እና ከሁሉም ሕዝብ ጋር አብሮ የሚያኖር አመራር ማምጣት እና እራሱን ከሴራ ፖለቲካ ነፃ ማውጣት አለበት። ለእዚህም ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው።

 ባለፈው ሳምንት ከእዚህ ዓለም በ79 ዓመቷ በሞት የተለየችው  የፀሐይቱ (ፀሐይ ባራኪ) ዜማ (ኦድዮ)
(ፀሐይ ባራኪ ለጀብሃ  ዜማዎች ታዜም እንደነበር እና በኃላ ነገር አለሙን ትታ በተቀመጠችበት በ1983 ዓም ሻብያ አስመራን ሲቆጣጠር በሱዳን በኩል ወደ ኔዘርላንድ ተሰዳ ባለፈው ሳምንት ሕይወቷ እስካለፈ ድረስ በስደት ኖራለች። ፀሐይ ባራኪን የአሁኑ ትውልድ አናውቃትም።ምናልባት ባለፈው ሳምንት እረፍቷ ሲሰማ በተነገረው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅናት የአሁኑ ትውልድ አካሎች ብዙ ነን።ፀሐይ በ1960ዎቹ በአዲስ አበባ ከአንጋፋ ዘፋኞች ጋር ሙዚቃዎቿ ይሰሙ እንደነበር ይነገራል።)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...