ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 2, 2018

በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የገዛችውን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ልታስባርክ ነው።የሶስት ቀናት ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤም አዘጋጅታለች።

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 25/2010 ዓም (ሜይ 4/2018 ዓም)

በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከስድስት ወራት በፊት ከፍተኛ ውድድር ከተካሄደበት ጨረታ በኃላ በእግዚአብሔር ፈቃድ  ህንፃ ቤተ ክርስቲያን መግዛቷ ይታወቃል።ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ቀድሞም በቤተ ክርስቲያንነት ኖርዌይ ስትጠቀምበት የነበረ ሲሆን ህንፃው በ1900 ዓም እ ኤ አ የተመሰረተ እና  በአሁኑ ሰዓት ህንፃው  ውስጣዊ ክፍሎቹ ላይ አንዳንድ መጠነኛ የፅዳት እና የጥገና ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በመሆኑም የህንፃው የውስጥ ክፍል ፀድቶ እና ተስተካክሎ ግንቦት 11/2010 ዓም (ሜይ 19፣ 2018 ዓም) ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚባረክ ለማወቅ ተችሏል። 

ከእዚህ በተጨማሪ የቅዳሴ ቤቱን ቡራኬ አስታካ ቤተክርስቲያኒቱ የሶስት ቀናት ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤም  አዘጋጅታለች። ስለሆነም ጉባኤው ከዓርብ ግንቦት 10 እስከ ግንቦት 12/2010 ዓም (ሜይ 18 እስከ 20/2018 ዓም) የሚቆይ ሲሆን ቅዳሜ ግንቦት 11 (ሜይ 19) የቤተ ክርስቲያን ቡራኬ በብፁዓን ጳጳሳት እንደሚከናወን እና እሁድ ቅዳሴ እና በዓለ ንግሥ እንደሚኖር ለማወቅ ተችሏል። በቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ ላይ እስካሁን አቡነ ሚካኤል እና አቡነ ኤልያስ የሚገኙ ሲሆን መንበራቸው ኦስሎ ላይ የሆነው አቡነ ሕርያቆስ የኖርዌይ፣ኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአቡነ ኤልያስ ልዩ ረዳት ከብፁዓን አባቶች ጳጳሳት ጋር በቡራኬው ላይ የሚገኙ እና አባቶችን በሀገረ ስብከታቸው የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።(ስለ አቡነ ሕርያቆስ የቀደሙ አገልግሎቶች ለማንበብ ይህንን ይጫኑ)።

በቤተ ክርስቲያኒቱ ቡራኬ ክብረ በዓል ላይ ከብፁዓን ጳጳሳት በተጨማሪ መላከ ሕይወት ቀሲስ ጌጡን እና ዘማሪ ይልማ ኃይሉን ጨምሮ ሰባክያነ ወንጌል እና ካህናት እንዲሁም ከልዩ ልዩ የአውሮፓ እና ኖርዌይ ክፍል የሚመጡ ምዕመናን እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዘንድሮ ዓመት ብቻ በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ አራት ሀገሮች ማለትም እንግሊዝ፣ጀርማን፣ኖርዌይ እና ግሪክ የእራሷን ህንፃ ቤተክርስቲያን ገዝታለች።

ከእዚህ በታች የኦስሎ ኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የተገዛው ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በእዚህ ሳምንት ስያፀዱ የሚያሳዩ ፎቶዎች ይመልከቱ።


ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ከዋና የኦስሎ ከተማ እንብርት በቅርብ እርቀት የሚገኝ ሲሆን የተሰራው በ1900 ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነበር። 

 የቤተ ክርስቲያኑን የውስጥ ክፍል ምዕመናን በፅዳት ላይ ሚያዝያ 23/2010 ዓም (ፎቶ ጉዳያችን)
አቡነ ሕርያቆስ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ፅዳት እና እድሳት ሲከታተሉ ሚያዝያ 23/2010 ዓም (ፎቶ ጉዳያችን)





ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: