ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 4, 2018

በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ያለው ልዩነት ዜሮ ካልሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ያሰጋናል። (Expectation - Actual= 0)።(የጉዳያችን ማሳሰቢያ)

ጉዳያችን / Gudayacn
ሚያዝያ 26/2010 ዓም (May 4/2018 ዓም)
---------------------------------
ከላይ የተሰጠው  ርዕስ የተጋነነ የሚመስለው ካለ እንዳልተጋነነ ቢረዳው ደስ ይለኛል።ይህ የግል አስተያየቴ ነው።አጉል ትንቢት ግን አይደለም።ዶ/ር ዓብይ  በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ደርሶ የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥረት የረገበ የመሰለው በአጭር ዕይታ ተስፋ ከንግግራቸው ብዙዎች በመሰነቃቸው ነው።ይህ ተስፋ እና እንዲሆን የሚጠበቀው እና የሚሆነው መካከል ልዩነት ከተፈጠረ ከፍተኛ አደጋ እስከ እርስ በርስ ጦርነት የሚያስነሳ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ  ሁኔታ በኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል።ዶ/ር ዓብይ በፍጥነት እየተዘዋወሩ ንግግር ማድረጋቸው፣ሕዝብ ብሶቱን ሲናገር ማድመጥ በእራሱ የፈጠረው በጎ ተፅኖ አለ። ይህ ተፅኖ ግን በጣም ጊዜያዊ እንጂ ዘለቂታዊ አይደለም።ዘለቂታ የሚሆነው በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ያለው ልዩነት ዜሮ ከሆነ ብቻ ነው (Expectation - Actual= 0)

ችግሩ 
====
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሕግ አስፈፃሚው በህወሓት ስር፣ሕግ አውጭው በተከፋፈለ ሁኔታ እና የተፅኖ መጠናቸው ያልለየው ዶ/ር ዓብይ ደግሞ የትኛው ጋር እንደሆነ የማስፈፀም አቅማቸው ገና አልታየም። ይህ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ይመስለኛል።ዶ/ር ዓብይ በጎ ህሊና አሳይተዋል።ኢትዮጵያ እንዴት ብትሄድ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።በልካም  ነው።ይህ ማለት ሕዝብ ከመንግስት የሚፈልገውን የለውጥ ፍላጎት አፅንተውታል ማለት ነው። አሁን ችግሩ በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ልዩነት በታየ ቁጥር ባልተጠበቀ መልኩ ግጭት ሊፈጠር ይችላል።የሚጠበቀው  ለውጥ እንዳይደረግ በዋናነት ያለው እንቅፋት አሁንም የሴራ ፖለቲካ የተለያየ የጥቅም ፍላጎት ያላቸው አካሎችን የማነሳሳት እና ቅራኔዎችን የማስፋት ተግባር በአናንድ ፅንፈኛ የህወሓት አካላት እየተፈፀመ ስለሆነ ነው።

መፍትሄው
======
ለኢትዮጵያ መጪ መፍትሄ ዋናው እና ዋናው ዋስትና ሁሉንም አካል ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ወደ መመስረት ሂደት መግባት እና መጪ የምርጫ ሁኔታን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት አሁን ያለውን የሲቪልም ሆነ የወታደራዊ መዋቅር ማፈራረስ ሳያስፈልግ ሆኖም ግን አሰራሩም ሆነ የሰው ኃይሉ በጎሳ  ላይ የተመሰረተ ግንኙነቱን ማጥፋት እና ኢትዮጵያዊ አቅሙን መገንባት ማለት ነው።ሁሉን ያሳተፈ ሽግግር መንግስት ለመመስረት ዶ/ር አብይ አሁኑኑ መስራት ያለባቸው ሰባት  ዋነኛ ተግባራት የሚመስሉኝ እነኝህ ይመሳሉኛል። እነርሱም
1ኛ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በፍጥነት ማንሳት፣
2ኛ) የሽብርተኝነት ሕጉን መሻር፣
3ኛ) ሁሉን ያሳተፈ የሽግግር ምክር ቤት መመስረት እና ፍኖተ ካርታውን፣እቅዱን በግልጥ ማስቀመጥ፣
4ኛ) የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መስጠት፣
5ኛ) የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን በሙሉ መፍታት ።
6ኛ) የሕግ የበላይነት ብቻ እና ብቻ የእያንዳንዳንዱ ግለሰብ ዋስትና መሆኑን በሚገባ ማሳየት ይህንንም ተከትሎ በግል፣በሕቡ እየተደራጁ ሕዝቡን የሚያስፈራሩ የህወሓት ፅንፈኛ ክፍሎችን የሚገታ ሕግ ማውጣት እና አሰራሩም ግልጥ ማድረግ፣
7ኛ) የሲቪክ ድርጅቶች፣የሙያ ማኅበራት እና ዜጎች የመደራጀት መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ
የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ማጠቃለያ 
=======
ለማጠቃለል አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ ያልቆረጡ ፅንፈኛ የህወሓት አካላት ወደ ለውጥ የሚሄደውን የለውጥ ኃይል የመገዳደር እጅግ አደገኛ አካሄድ እያሳዩ ነው።ይህ ሁኔታ ዶ/ር ዓብይን የሚያስወቅስ አድርገው በማሰብ በጣም የብልጣብልጥነት ሥራ እየሰሩ እንዳሉ ለአድናቂዎች በመንገር እጅግ ወደ አደገኛ መንገድ ሕዝቡን እና ኢትዮጵያን እየመሯት ነው።ግጭቶች በእየቦታው እየፈነዱ ነው፣ምጣኔ ሃብቱ መንኮታኮቱን ቀጥሏል።የስራ አጡ ብዛት ጨምሯል፣የህዝብ ቁጥር እያደገ ነው፣የጎሳ ቁርሾው ለውጥ ካጣ ሊባባስ ይችላል፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግጭትም ሊያስከትል ይችላል።ስለሆነም ሕዝብ ከሚጠብቀው ለውጥ ያነሰ ሳይሆን ከጠበቀው በላይ በመሄድ ብቻ ነው ሀገር ማረጋጋት የሚቻለው።
ዶ/ር  ዐብይ ያላቸው አንድ ምርጫ ብቻ ነው።ለውጡን ሕዝብ በሚጠብቀው መጠን ወይንም ከጠበቀው በላይ እንዲሄድ ማድረግ ካልቻሉ የችግሩ ፈጣሪዎችን በግልጥ ለሕዝብ መንገር።ከእዚህ ባነሰ ችግር የሆነውን የኢትዮጵያን ጉዳይ ነካክተው መተው አደጋ አለው።ቆሻሻ ከነካኩት የበለጠ ይሸታል።ከነካኩ ማስተካከል ይፈልጋል።ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ልትቀጥል አትችልም።ለውጡ በዘገየ ቁጥር ወደ እርስ በርስ ጦርነት የማምራት አደጋው ይጨምራል። ይህ ተራ ግምት አይደለም።ከግምት በላይ ነው።ለለውጡ ህወሓት ከልብ፣ከልብ ቢያስብበት እና ከለውጥ ያነሰ ነገር ሁሉ የበለጠ አደጋ መሆኑን ከልብ ማመን አሁንም በጣም ይጠበቅበታል።ልመናም ጭምር ነው። ይህንን የምለው የሚመጣው አደጋ ከአሁኑ የከፋ መሆኑን በእርግጠኝነት ማወቅ ስለሚቻል ነው።''ሰይጣንን አንድ ቀን ቢገለጥ ኖሮ ሰው ሁሉ ልመንን ይል ነበር'' እንዳሉት አባት ለለውጥ ካለመዘጋጀት የተነሳ ወደፊት የሚመጣው አደጋ እጅግ የከፋ ነው።ዛሬ ግን በፍጥነት ወደ ቀና ለውጥ መምጣት ብልህነት ነው። ዶ/ር ዓብይም ከእዚህ በኃላ ምንም ደቂቃ ባያጠፉ እና ፍፁም የሆነው ለውጥ ሁሉን ያሳተፈ አካል ምስረታ ላይ ዋስትናው ላይ አሁኑኑ ሥራ ወደመጀመር ቢሄዱ ጥሩ ነው።



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...