ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, May 27, 2018

የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈድሬሽን ደንብ በሕዝብ የማይስተካከልበት ምን ምክንያት አለ? (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayacn
ግንቦት 20/2010 ዓም (ሜይ 28/2018 ዓም)


የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን ሕግ በራሱ መከለስ እንዳለበት በእዚህ ሳምንት መጨረሻ የተነሳው ጉዳይ በእራሱ አመላካች ነው። የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን የሚጋብዛቸውን እንግዶች የፖለቲካ ተሳትፎ የጎላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሕጉ ይከለክል ከነበረ (የሕጉን ትክክለኛ ቅጅ ስላላገኘሁት ሆኖም ከእዚህ በፊት በሚጋበዙ እንግዶች ዙርያ የተነሱ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ) ይህ ሕግ አሁን ላይ ይሰራል ወይ? ብሎ የመጠየቂያ ጌዜው አሁን ነው ማለት ነው።ሕግ ከወቅቱ ጋር እየታየ ይስተካከላል፣ ይከለሳል።ወሳኙ ጠቅላላ ጉባኤው ነው።ምናልባት ይህ ሕግ የውስጥ ንዑስ ሕግ እንጂ ፈድሬሽኑ በአሜሪካ ሕግ የሚመዘገብበት ዋናው ሕግ አንቀፅ ውስጥ ስለማይሆን የውስጥ ደንቡን ተከትሎ መስተካከል ይችላል ማለት ነው።


በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ብሎ የወጣው ሕግ የፖለቲካ ተሳትፎን እያጤነ ይለይ ከነበረ በወቅቱ አስፈላጊ ነበር ቢባልም ሃሳቡ ግን ትክክል ነው ማለት አይደለም።ስፖርት በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ አስተሳሰብ ክብደት እና ቅለት እየታየ ተጋባዥ እንግዳ መጋበዝ በእራሱ የአዲሱን ወጣት የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያቀጭጭ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የስፖርትን አምስቱን መሰረታዊ መርሆዎች ጋር  ላለመጣጣሙ  እማኝ ማቅረብ አይቻልም።የቀደሙ የኢትዮጵያ መሪዎች አፄ ኃይለስላሴም ሆኑ ኮለኔል መንግስቱ በስፖርት በዓላት ላይ እየተገኙ ወጣቶችን ያበረታቱ ነበር።ይህ ተፈጥሯዊ አሰራር ነው።አንድ ሰው በፖለቲካ መስመሩ ብቻ የኢትዮጵያን የጋራ ዕሴት በተቃረነ መልኩ እስካልቆመ ድረስ የስፖርት በዓሎች ላይ በክብር እንግድነት የመገኘት መብቱ ሊገሰስ አይገባም።

ስለሆነም የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፈድሬሽን አሁን ላይ ሆኖ እራሱን ሲመለከተው  ያለፈው ሕጉ ችግር ነበረበት  ማለት ነው። በእርግጥ በወቅቱ ለነበሩት የፖለቲካ ትኩሳቶች ላለመንገላታት  ጠቅመው ይሆናል።በአንድ ወቅት ከነበረ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተዛመደ መልክ የወጣ ሕግ ግን ሁል ጊዜ ትክክል ነው ማለት አይቻልም።አሁን አዲስ ትውልድ መጥቷል።ዘመን እየነጎደ ነው።ልዩነት ከማስፋት የማጥበብ አስፈላጊነት ላይ የሚያጠነጥኑ አስተሳሰቦች እና ኢትዮጵያዊነት  በልዩነት አንድነት የሚለው አስተሳሰብ ከመቼውም ጊዜ የጎሳ አስተሳሰብን መተካት እንዳለበት ከፍ ያለ እምነት በሕዝብ ዘንድ ይንፀባረቃል።ይሄው ሃሳብ ደግሞ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይም እየተስተጋባ ነው።


እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ስለ ሕጉ እያወራን ያለው ዛሬ ዶክተር ዓብይ ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ለሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፈድሬሽን ዳላስ ላይ በሚደረገው የዘንድሮ  በዓል ላይ እንድገኝ ፍቀዱልኝ ብለው የመጠየቃቸው  ምክንያት ስለሆነ  እና ይህንን ለመርዳት መውጫ የመፈለግ መላ አይደለም።ይልቁን ጥያቄው በእራሱ የሕጉን መከለስ አስፈላጊነት አመላከተ እንጂ።ሲሆን ክስተት ሳይፈጠር ቀድሞ መጪውን አስቦ ሕግ ማስተካከል ተገቢ ነበር።ሆኖም ሁል ጊዜ ይህ አይሳካም እና ክስተቱ የሕጉ መስተካከል አስፈላጊነትን አሳየ ማለቱ ይቀላል።


ጠቅላይ ሚንሰተር ዶ/ር ዐብይ ዘንድሮ በሚደረገው የሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ እግር ኳስ ውድድር ላይ መገኘት በሚለው ሀሳብ ሰዎች የተለያየ ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል::ይህ ማለት መከፋፈል ማለት አይደለም::የተለያዩ ሀሳቦች ከማንሸራሸር ያለፈ ስም አይሰጠውም::ሀገራዊ ለውጥ በግለሰቦች ልቦና ተመላልሶ በህብረተሰብ ውስጥ አድጎ የሚተገበር ድርጊት ነው::የስፖርት ፌድሬሽኖቹ ህግ በተመለከተ ዶ/ር ዐብይ መጋበዝ ላይ አሳሪ አይመስለኝም::አሳሪ ስላልሆነም ነው አንዳንድ ግለሰቦች ላይ አከራካሪ ሲሆን የነበረው:: አሳሪ ሕግ ሆኖ ቢሆን ኖሮ አንቀፅ ጠቅሶ ይቆም ነበር።ከእዚህ በፊት በነበሩ ሂደቶች ግን (የብርቱካን ሜደቅሳ ማስታወስ ይቻላል) የሕጉን ትርጉም ለማስረዳት የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ ሳይቀር ሲያወያይ ነበር።ምክንያቱም አንዳንዶቹ ግለሰቦች የምከለከሉበት የፖለቲካ አስተሳሰባቸው መሰረት ማድረጉ ያልተዋጠላቸው በርካታ ወገኖች ስለነበሩ ነው። ይህ በእራሱ ክፉ ነገር አይደለም።ለንትርክም አይጋብዝም።ሆኖም ግን ሕግ በረጅም ጊዜም የሚያረጅ ከመሆኑ አንፃር ትናንት የነበረው አሰራር ዛሬ ላይ የትናንቱን አይነት ጥያቄ ይዞ መጥቷል።ባለቤቱ ሕዝብ ደግሞ እንዲስተካከል የምፈልገው ሕግ በሙሉ ሕግ ሆኖ ይኖራል።ይህ በዲሞክራሲያዊ አሰራሮች ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች ሁሉ የሚከተሉት ነው።


ዶ/ር ዐብይ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ባምንም::ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ እስከ ውጭ ነዋሪ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድረስ የጎላ ተቃውሞ ካለመኖሩ አንጻር እና የእርሱ በበዓሉ ላይ መገኘት ከሀገራዊ ፋይዳ አንጻር የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ ፌድሬሽኖቹ ቢፈቅዱ ትልቅ ጥቅም አለው:: ከእዚህ አትራፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ነች:: አንዳንዶች የአሜሪካ ምክር ቤት ወደ ሕግ መውሰኛው የመራውን የሰብዓዊ መብት ሕግ ለማስቀየር ነው እና ሌሎች መላ ምቶችን ይሰጣሉ። ይህ ግን ከእዚህ ጋር አይገናኝም።ሕጉ እንዲፀድቅ የሚጠይቅ ሕዝብ ነው እንጂ መንግስት አይደለም።ከእዚህ ይልቅ በርካታ ሕዝብ በስታድዮሙ መታደሙ የኢትዮጵያዊነት አመክንዮ በምን ያህል በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ለአሜሪካኖችም ሆነ ለእራሳችን የምንገልጥበት መልካም አጋጣሚ ነው። ይህ ካልተፈቀደ ዶ/ር ዓብይ የጎሳ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ጋር ሄደው ንግግር ያድርጉ? በነገራችን ላይ ቀላል የማይባል በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠር በውጭ የተወለደ እና በጉዲ ፈቻ የመጣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አለ:: ይህ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት የጠማው የሌላ ሀገር ዜጎች በሀገራቸው የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ሲሳተፉ÷የመሪዎቻቸው ርዕይ በአደባባይ ሲያዳምጡ በቅናት እና በቁጭት የሚኖሩ ናቸው::ስለሆነም የፖለቲካ ሜዳውንም ሆነ እንዲህ አንዳንዴ እንደ ዶ/ር ዐብይ አይነት ሰዎች ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ ቢሰሙ በውስጣቸው የሚሰንቁት በጎ ነገር ቀላል አይደለም::ስለሆነም የእዚህ ዐይነት መድረክ ምን ማለት እንደሆነ ካልተረዳን ከባድ ነው::

ይህ ማለት ሕጉን ለማስተካከልም ሆነ ዶ/ር ዓብይን በአሜሪካም ሆነ አውሮፓ የሚደረጉት የስፖርት ፈድሬሽን ጫወታዎች  ላይ እንዲገኙ ፔትሽን ሕዝብ ማሰባሰብ ይችላል።በፔትሺኑ አማካይነት በልዩ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት የጎሳ ፖለቲካን ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ያዞሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር በክብር እንግድነት መጥራቱ ምንም የሚያመጣው ጉዳት የለውም።በብሔራዊ ደረጃ የተጎዳውን ኢትዮጵያዊነት በእዚህ ደረጃ በማንሳት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በአንድነት መኖር የበለጠ ነው ብሎ መስበኩ ብቻ ያመጣው ስነ ልቦናዊ ልዕልና በእራሱ በክብር እንግድነት ያስጋብዛል።

ለማጠቃለል  የስፖርት ፈድሬሽኑ ለውሳኔው ከተቸገረ በቀላሉ በኦንላይን ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥበት ፔቲሽን ክፍት አድርጎ ማስወሰን ይችላል።የእዚህ አይነት ሃሳቦች ሲነሱ የምንደናገጥ እና የምንሰጋ እንደምንኖር አስባለሁ።ምክንያቱም ለውጥ መኖር በእራሱ የሚያጠፋ መስሎ ማሰብ ተፈጥሯዊ ስጋት ነው።ሆኖም ግን የሚያስደነግጥ ጉዳይ የለውም።ለውጡ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ግን የስፖርት ፈድሬሽኑ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ አመላካች ነው።የእዚህ አይነቱን የለውጥ ሂደት ዛሬ ባይደረግ ነገም የማይቀር ነው። ለማጠቃለል የሰላሳምስተኛውን የኢትዮጵያውያን ስፖርት ውድድር በዳላስ ማስታወቂያ  በድምፅ የሰራው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በማኅበራዊ ድረ ገፁ ላይ የዶ/ር ዓብይ በበዓሉ ለመታደም መጠየቅን አስመልክቶ የፃፈውን በመጥቀስ ፅሁፌን እገታልሁ። ዓለምነህ እንዲህ ይላል ህዝባቸውን ለማግኘት ፍቀዱልኝ ልገኝ ብለው መጠየቃቸው  (ዶ/ር ዓብይን ነው) በዜግነታችን የሚያከብረን እኩል ተነጋግሮን ተደማምጦን መፍትሄ ለማበጀት የሚሻ መሪ አያደርገውምን "

የዘንድሮው በዓል ማስታወቂያ ቪድዮ 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...