ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, June 2, 2018

ወደፊት ለመራመድ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ዝግጅት ማድረግ ይገባናል።ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኦስሎ፣ኖርዌይ ያደረጉት ንግግር (የጉዳያችን ልዩ ሪፖርታዥ)


ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ኦስሎ ግንቦት 25፣2010 ዓም (ፎቶ ጉዳያችን)


ጉዳያችን/ Gudayachn
ግንቦት 25/2010 ዓም (ጁን 2/2018 ዓም)

በእዚህ ሪፖርት ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተካተዋል። እነርሱም : - 

  • በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያሉብን ችግሮች ምንድናቸው?
  • የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዴት መጣ?
  • የ1983 ዓም የብሔር ፖለቲካ ዋነኛ ስህተት ምንድነው?
  • የለማ ቡድን (ዶ/ር ዓብይ) የለውጥ ዕድል በተመለከተ እንዴት እንሂድ?
  • የእነ ለማ ቡድን (ዶ/ር ዓብይ) የለውጥ ኃይል ከሌሎች ሀገሮች ምን መማር አለበት?
  • ሀገር ክትፎ አይደለም 


የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ  እና አቶ ኦኬሎ በአካል እና  የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በስካይፕ የተገኙበት በርካታ ኢትዮጵያዊ ከኖርዌይ ልዩ ልዩ ከተሞች (ኦስሎን ጨምሮ)፣ከስዊድን፣እንግሊዝ እና ሌሎች የአውሮፓ ከተሞች የታደሙበት ስብሰባ ዛሬ ግንቦት 25/2010 ዓም ኦስሎ ከተማ ተደርጎ ነበር።በስብሰባው መክፈቻ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አጭር የምስጋና ንግግር ካደረጉ በኃላ የዝግጅቱ አስተባባሪ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ አቶ ይበልጣል የመክፈቻ ንግግር፣ በኖርዋይ የአርበኞች ግንቦት 7 ወክለው አቶ ደባሱ ንግግር ካሰሙ በኃላ ግጥም በአማርኛ ወ/ሮ አፎምያ፣ እንዲሁም ግጥም በእንግሊዝኛ አቶ ልዑል አቅርበዋል።በመቀጠል የዕለቱ ዋና ተናጋሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ንግግር አሰምተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዛሬው የኦስሎ ንግግራቸው መግብያ ላይ ባለፈው ዋሽንግተን ላይ ያደረጉትን ንግግር እንደማይደግሙ ነገር ግን እዛ ላይ ያልተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ በቀልድ አዋዝተው ከገለጡ በኃላ ንግግራቸውን ጀምረዋል።በንግግራቸው ላይ የተነሱትን ነጥቦች ከእዚህ በታች በርእስ ከፍዬ አቀርባለሁ።እዚህ ላይ ርዕሶቹ ለአንባቢ የትኩረት ነጥቦች እንዲረዳ ርዕሶቹን የሰጠሁት እኔ ነኝ።ንግግራቸው በርእስ ሳይከፈል በወጥነት የቀረበ ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያሉብን ችግሮች ምንድናቸው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የንግግራቸው መግብያ ያደርጉት በፖለቲካው መድረክ ለዘመናት የኖሩ ችግሮቻችንን ሲገልጡ በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች አስቀምጠዋቸዋል።እነርሱም የመንፈስ ችግር፣ ለኢትዮጵያ ከእኔ ሌላ የሚያውቅ የለም ማለት እና የሌላውን አለመስማት ችግሮች ዋና ዋና እንደሆኑ አብራርተዋል።የመንፈስ ችግር ያሉት ላለፉት አርባ አመታት የኖረው ከፍተኛ የመጠራጠር እና ሁሉንም በበጎ አለማየት መሆኑን አብራርተው ይህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሳይቀር ዝም ብሎ የመጠርጠር መንፈስ መኖሩን ነገር ግን በእዚህ መንፈስ መያዝ እራሱ ወደ አደገኛ ሁኔታ እንዳይመራ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።ይህንን ሲገልጡት ቃል በቃል  " መጠርጠርን አርት አድርገነዋል" ስለሆነም ከእዚህ የመንፈስ ችግር መውጣት አስፈላጊ ነው።ይህንን ስል ሁሉ ነገር አበቃ ተስተካከለ እያልኩ አይደለም።ሆኖም ግን በጥንቃቄ እያየን የምንሄደው መሆን እንዳለበት ከገለጡ በኃላ በአሁኑ ጊዜ አነጋገራችንም መቀየር አለበት ህወሓት እና ኢህአዴግ እያልን ነው የምናወራው ምክንያቱም ለለውጥ የተነሳ ከመካከላቸውም ስላለ ብለዋል።

ሁለተኛው እና ሶስተኛው ችግር  እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል የሚለው እና የሌላውን አለመስማት ፖለቲካችን መነሻው ከ1966 ዓም የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አብራርተው በዛን ጊዜ ወጣት በነበርንበት ወቅት ኢትዮጵያ የእራሷን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ግን ከውጭ የመጣ ርዕዮት የተጫነባት አንዱ ምክንያት እኔ ያሰብኩት ብቻ ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚል ስሜት ነበር።በእዚህም በርካታ ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎቻችንን አጥተናል።ይህ አደገኛ ስሜት ክፋቱ የተለየ ሃሳብ የሚያስበውን በሙሉ በጠላትነት መፈረጁ ነው። ይህ በ1983 ዓም የነበረው ለውጥም በተመሳሳይ መልኩ ደግሞታል ብለዋል። እነኝህ ሶስቱ ችግሮች ለመጀመርያው አብዮት መክሸፍ ምክንያት መሆናቸውን ያብራሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የብሔር ፖለቲካ አነሳስ ታሪካዊ ዳራ ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል።

የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዴት መጣ?

የመጀመርያው ለውጥ ወቅት የውጭ ርዕዮት ዓለምን እንደ አመለካከት ወስዶ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የመጫን ስህተት አንዱ እና ዋናው የክሽፈት ፖለቲካችን መሆኑን ከገለጡ በኃላ የብሔር ፖለቲካ እንዴት እንደ ርዕዮት ዓለም ራሱን ችሎ ብቅ እንዳለ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል።
    " የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ በመጀመርያ በርዮት ዓለምነት የወጣ አስተሳሰብ አልነበረም።
       ያኔ የብሔር ፖለቲካ የታሰበው በታክቲክ ደረጃ ነበር።በታክቲክ ደረጃ የታሰበው የብሔር 
       ፖለቲካ እራሱን ችሎ ከምር አደረጉት እና በርዮት ዓለምነት ብቅ ያለው በ1983 ዓም ነው።"

የ1983 ዓም የብሔር ፖለቲካ ዋነኛ ስህተት ምንድነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በታክቲክነት ይነሳ የነበረው የብሔር ፖለቲካ ከምር ሆኖ በ1983 ዓም ራሱን ችሎ በርዮት ዓለምነት ሲቀርብ የአንድ የተለየ ኅብረተሰብን ጥቅም ለይቶ መቆም ያለውን አደገኛነት ከግንዛቤ አላስገባም ብለዋል።አንድን ኅብረተሰብ በብሔርም ሆነ በሌላ ለይቶ ለመብቱ መቆም በእራሱ የሚያመጣው ጉድለት ሲያብራሩ ግለሰብ፣ቤተሰብ እና የወል ስብስቦች የእየራሳቸው ፍላጎቶች ኖሯቸው ሳለ የብሔር ፖለቲካ ግን የሁሉንም የተለያየ ፍላጎት ጨፍልቆ እኔ የማውቅላችሁን ፍላጎት ውሰዱ የሚል ነው ብለዋል። ይህንንም በምሳሌነት ሲያስረዱ በወል ስብስብ ውስጥ ለምሳሌ የክርስትና እና የሙስሊም ወገኖቻችን የእየራሳቸው ፍላጎት አላቸው፣ሙስሊሙ ክርስቲያኑ አምልኮ ውስጥ አይገባም፣ክርስቲያኑም ሙስሊሙ ውስጥ እንዲሁ አይገባም።የወል ስብስብን ፍላጎት ጨፍልቆ እኔ በማውቅልህ መንገድ ሂድ ማለት አይቻልም።ምክንያቱም ሀገር እና ፖለቲካን ስታስብ ሁል ጊዜ ሁሉንም የወል ስብስቦች የሚያረካ መሆን አለበት።አንዱን በብሄር ወይንም በሌላ መልክ ነጥሎ ለመጥቀም የሚያስበው የብሔር ፖለቲካ አንዱ እና ዋናው ስህተቱ አሁን ድረስ ሀገራችን ችግር ላይ የጣላት ምክንያትም ፖለቲካ (መንግስት) ለወል ስብስቦች መብት ብቻ ለመቆም የመሞከሩ አባዜ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በንግግራቸው አስረግጠው አብራርተዋል።

ከእዚሁ የብሔር ፖለቲካ ለአንድ የወል ማኅበረሰብ ጥቅም ከመቆሙ አንፃር በመጨረሻ ውድቀቱ ላይ ቆምኩለት የሚለውን የወል ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ የሚለውን የራሱን ማኅበረሰብ መጨረሻ ላይ መብላቱ ነው አስከፊው ሁኔታ ብለዋል።

የለማ ቡድን (ዶ/ር ዓብይ) የለውጥ ዕድል በተመለከተ እንዴት እንሂድ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከላይ የተሰጠውን የለማ ቡድን ወይንም የዶ/ር ዓብይ የለውጥ ዕድል በሚል በቀጥታ ርዕስ አይስጡት እንጂ የአሁኑን የሀገር ቤት ለውጥ አስመልክተው ሲናገሩ ሶስተኛው ዕድል በሚል ገልጠውታል።ማንም ሀገር ለለውጥ ሶስት ጊዜ ዕድል ያገኘ ሀገር የለም ካሉ በኃላ "የአሁኑን ዕድል ኢትዮጵያ ካበላሸች እና ካበላሸን እንደ ሀገር ልንቀጥል የምንችልበት ሁኔታ ያሰጋል" ብለዋል። ዓቢይ ከሰማይ የመጣ አድርጋችሁ አትዩ በትግሉ ሂደት የመጣ ነው።አንዳንድ ወገኖች ሲያታልሉን ነው ምናምን እያሉ ያወራሉ።ቀደም ብዬ እንዳልኩት መጠርጠር አርት አድርገን ይዘነዋል።እነ ዓብይ የመጡበትን ሂደት እናስታውስ ከመመረጣቸው በፊት ማን ይመረጣል እያልን እንደነበር አስታውሰው በሂደቱ ግን እነዓብይ እንዳሸነፉ በግልጥ እንደታየ አስታውሰዋል።ስለሆነም አሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ " የለውጥ ኃይሎችን (እነዶ/ር ዓብይን ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ እስከ ሄዱ ድረስ እንደግፋቸዋለን።የምያደናቅፉትንም መታገል አለብን" ብለዋል።

የእነ ለማ ቡድን (ዶ/ር ዓብይ) የለውጥ ኃይል ከሌሎች ሀገሮች ምን መማር አለበት?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ እነዶ/ር ዓብይ በፖለቲካ አሸንፈዋል።ህወሓትም በፖለቲካ ተሸንፏል ካሉ በኃላ ሆኖም ግን ህወሓት በወታደሩ ዙርያ እና በዝርፍያ የደለበ ሀብት በመያዝ አሁንም አሉ ብለዋል።ስለሆነም የለውጥ ኃይሉ ይህንን ማወቅ እንዳለበት እና ከእዚህ አንፃር አካሄዱን መቃኘት እንዳለበት አሳስበው ለአብነት የግብፅን እና የደቡብ አፍሪካን የቅርብ ታሪክ ጠቁመዋል።የግብፅ አብዮት ሲነሳ እና ሙርሲ የሙባረክን ኃይል ከጣለ በኃላ የሀገሪቱን ሀብት 50% የያዘው የግብፅ ጦር ኃይል ህዝቡ የዕለት ዳቦ እንዳያገኝ በማድረግ ሕዝብ ሙርሲ ላይ እንዲነሳ እና የሙባረክ ሰዎች ተመልሰው እንዲመጡ ማድረጉን ገልጠዋል።በተመሳሳይ መልኩ ከነጭ የአፓርታይድ ወገን ሁኔታው እንደማያስኬድ የተመለከተው ዲክለርክ ለለውጥ ሲነሳ የተፈጠረውን የመቀልበስ ሂደት በምሳሌነት አሳይተዋል።ስለሆነም አሁን በኢትዮጵያ ያለው የለውጥ ኃይል (የለማ ቡድን) ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልክ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገር ክትፎ አይደለም 

በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገልጠው ለውጡን እኛ ካላመጣነው የሚል የስልጣን ጥማት የለንም።እኛ መድረስ አለብን የምንለው ዜጎች አሽከር ሳይሆን የእኔ የሚሉት ሀገር ባለቤት እንዲሆኑ ነው ካሉ በኃላ ንግግራቸውን ሲደመድሙ እንዲህ ብለዋል : -
      " ሀገር ክትፎ አይደለም።ሀገር ሁላችን ባለቤት የምንሆንባት ደረጃ መድረሷን ማረጋገጥ አንዱ ግባችን ነው ከአሁን በኃላ ተመልሶ የወያኔ ኃይል ስልጣን ላይ እንዳይመጣ ማድረግ ዋና ስራችን መሆን አለበት።ለእዚህም በአካሄድ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብዬ እንደተቀስኩላችሁ በመንፈስ ዝግጅትም ሊኖረን ይገባል።በ1966 እንደነበረው የእኔ ብቻ ሃሳብ ትክክል ነው የሚል ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለብንም።ስለኢትዮጵያ መጨነቅ የእኛ ብቻ ሥራ ነው ብለን አናምንም የዓብይም የሁሉም እኩል ኃላፊነት ነው።ከእነ ዓብይም ሆነ ከሌሎች ሀገር ለመገንባት ከሚቆሙት ጋር ሁሉ መቆም አለብን ከትጥቅ ትግል ጋር እና ከተቃዋሚነት ጋር አልቆረብንም" ብለዋል።




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: