ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, June 26, 2018

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሁለት ወደ አንድ ሲኖዶስ እንድትመለስ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ምእመናን ማድረግ እና አለማድረግ ያሉባቸው ጉዳዮች

ጉዳያችን/ Gudayachn
ሰኔ 20/2010 ዓም (ጁን 27/2018 ዓም)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ተከፍሎ፣በመንበራቸው የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ እና ሊቃነ ጳጳሳት ከሀገረ ስብከታቸው ተሰደው በውጭ ሀገር እየኖሩ እንደሆነ ይታወቃል።የቅዱስ ሲኖዶስ በሀገር ቤት እና በውጭ መኖር የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ብቻ ሳይሆን የተፈታተነው፣የምእመናንን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት በእጅጉ ጎድቶታል።ምዕመናን በተለያየ ፍረጃ ሳብያ እርስ በርስ ተቃቅረዋል።በተለይ ይህ ሁኔታ ፖለቲካዊ ቃና እየተሰጠው በርካቶች በሌሉበት ፖለቲካ እየተፈረጁ ከቤተሰባቸው ጭምር ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገር ውስጥ እና ውጭ በሚል መከፈል የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጤናማ ግንኙነትን አዛብቶ ቆይቷል።ለእዚህም አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት አዛብቶ ቆይቷል።ለምሳሌ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን እና በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚገኙ የበርካታ ሀገሮች አብያተ ክርስቲያናት ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ከውጭ ወይንስ ከሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ጋር መሆን አለበት? የሚለው ጥያቄ አንፃር ከፍተኛ ውዝግብ ሲፈጠር ቆይቷል። በእዚህም ሳብያ ጉዳዩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ግንኙነት አንፃር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በነበራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንፃርም የእራሱን የሆነ ጥላ እንዳጠላ የሚታወቅ ነው።ከእዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኃላ በቅርቡ ምናልባትም በሳምንታት ውስጥ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለእርቅ እንደሚገናኙ መሰማቱ ይታወቃል።በእዚህ የእርቅ ሂደት ላይ የምእመናን ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለው ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው።

ምእመናን ማድረግ የሌለባቸው 
  • በአባቶች እና በሊቃውንት ጉባኤ መታየት የሚገባቸው የሥርዓት (ቀኖና) ሂደቶች ላይ አባቶችን ተክቶ ሃሳብ በመስጠት ሌላ ንትርክ አለመፍጠር፣
  • የቅዱስ ሲኖዶስ በሁለት መከፈል ሂደት ላይ ዛሬ እያነሱ (ቢያንስ የእርቅ ሂደቱ እስኪያልቅ ድረስ) የታሪክ ንትርክ አለመፍጠር፣
  • በውጭም ሆነ በሀገር ቤት የሚገኙ አባቶችን የአንዳቸውንም እያነሱ የመደገፍ እና የማጥላላት ፅሁፎች አለመፃፍ እና 
  • ማናቸውም ልዩነቶችን የሚያሳዩ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ንግግር፣ፅሁፍ እና አገላለጦችን ፈፅሞ ከመጠቀም መቆጠብ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ምእመናን ማድረግ የሚገባቸው  
  • አባቶች በምንም አይነት መልኩ የአሁኑን የእርቅ ዕድል እንዳያልፍ እንዲያደርጉ ደጋግሞ ማሳሰብ፣
  • የእርቅ ሂደቱ እንዲሳካ እና ምንም አይነት ከእርቅ ያለፈ ጉዳይ ምእመናን መስማት እንደማይፈልጉ አበክረው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለብፁዓን አባቶች በቃል፣በፅሁፍ እና ፔቲሽን በማዘጋጀት ጭምር ማሳሰብ እና 
  • ለእርቅ ሂደቱ የሚያስፈልገውን የሞራል እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ምእመናን እንዲያግዙ የተከፈቱ የፌስ ቡክ ገፅ እና የፔትሽን ማስፈንጠርያዎች ለእርቁ በጎ እሳቤ ይዘው በተነሱ ምእመናን ተከፍተው ሥራ ላይ ውለዋል።ምእመናን ይህንኑ አውቀው የፌስ ቡክ ገፁን ''ላይክ'' በማለት እና ፔቲሺኑን በመፈረም እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ።በእዚህም መሰረት  
የተከፈተው የፈስ ቡክ ገፅ ማስፈንጠርያ ለመክፈት የፌስ ቡክ ገፅ የሚለውን በመጫን መክፈት ሲችሉ፣ የፐቲሽኑ ማስፈንጠርያ ለመክፈት ደግሞ ፔትሽን የሚለውን በመጫን መክፈት ይቻላል።  

ባጠቃላይ ይህ ወቅት ወሳኝ ተግባራት የሚከወንበት እና የሁሉም ትኩረት በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና የአባቶች እርቅ ጉዳይ ከሁሉም በቀደመ መልኩ የምእመናን ተሳትፎ በእርቁ ሂደት ላይ የሚኖራቸው ድጋፍ መጎልበት እና አባቶች ከእርቅ ውጭ ምንም አይነት አማራጭ አለመኖሩን ደግሞ ማሳሰብ ባጠቃላይ ከሁሉም የሚጠበቅ የጋራ ተግባር ነው።
አበው ፀልዩ (የይልማ ኃይሉ) መዝሙር ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: