ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 11, 2018

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰኘ አዲስ ንቅናቄ ባህርዳር ላይ ተመስርቷል።የንቅናቄው እድሎች እና ፈተናዎች ምንድናቸው?


የንቅናቄው ምስረታ ላይ የተገኘው ሕዝብ 

ጉዳያችን/ Gudayachn 
ሰኔ 3/2010 ዓም (ጁን 10/2018 ዓም)

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መስራች ጉባኤውን ለሁለት ቀናት ያህል ሰኔ 2 እና 3/2010 ዓም በባህር ዳር ከተማ  አካሂዷል።በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት ጀነራር ተፈራ ማሞን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የተገኙ ሲሆን የንቅናቄውን አመራሮችም ይፋ ሆነዋል።በእዚህም መሰረት አመራሮቹ የሚከተሉት መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። እነርሱም : -
1-ዶር ደሳለኝ ጫኔ-ሊቀመንበር
2-አቶ በለጠ ሞላ-ምክትል ሊቀመንበር
3-አቶ ጋሻው መርሻ-የድርጅት ጉዳይ 
4-አቶ መልካሙ ሹምየ-የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ
5-አቶ ተመስገን ተሰማ-የማኅበራዊ ጉዳይ ሀላፊ
6-አቶ ዳምጠው ተሰማ -የውጭ ጉዳይ ሀላፊ
7-አቶ ካሱ ኃይሉ -የኢኮኖሚ ጉዳይ ሀላፊ
8-አቶ ክርሥቲያን ታደለ-የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ
9-ወ/ሪት መሰረት አስማማው-ሴቶች ጉዳይ ሀላፊ
10-አቶ የሱፍ ኢብራሄም-የጥናትና ስትራቴጂ ጉዳይ ሀላፊ
11-አቶ ጥበበ ሰይፈ-የህግ ጉዳይ ሀላፊ
12-አቶ ተሰማ ካሳሁን-የወጣቶች ጉዳይ ሀላፊ
13-አቶ ዳንኤል አበባው -የፋይናንስ ጉዳይ ሀላፊ
14-አቶ በለጠ ካሳ-የፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ

የጉባኤው መርህ '' ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፣አንድ አማራ ለሁሉም አማራ'' የሚል መሆኑ በመርሐግብሩ መክፈቻ ላይ ተነግሯል።በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በንግግራቸው ላይ  እስካሁን አማራው ያልተደራጀበት ምክንያት ውስጥ ችግሩ ይሻሻላል ከሚል ተስፋ እና በብሔር መደራጀት ለሀገር አንድነት አደጋ አለው ከሚል መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም ግን ሁሉ ነገር ከልክ በማለፉ ለመደራጀት መወሰኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ዶ/ር ደሳለኝ ንግግራቸውን በመቀጠል  በቀጣይ የስራ ዕቅዳቸው ውስጥ የሚከተሉት ተግባራት እንዲከናወኑ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።እነርሱም: -
  • አማራውን የሚጎዳ አከላለሎች እንዲስተካከል መስራት፣ 
  • በሕገ መንግስቱ ውስጥ የአማራ ሕዝብ የሚጎዱ አንቀፆች እንዲከለሱ መታገል፣ 
  • በሌላ ክልል የሚኖረው የአማራ ተወላጅ መብት እንዲከበር ማድረግ፣ 
  • ከወንድም የኦሮሞ እና ሌሎች ብሔሮች ጋር በህበረት መስራት፣
  • ብአዴን በትክክል እንዲሰራ መታገል እና በውስጡ ያሉት የንቅናቄው ደጋፊ እንዲሆኑ ማድረግ፣
  • በተለያዩ ቦታዎች ለታሰሩት እና ንብረታቸው ለተነጠቁ ሁሉ ካሳ እንዲሰጥ መታገል እና 
  • በኢትዮጵያ የሚኖሩ ማናቸው የፖለቲካ ሂደት  አማራው የሚሳተፍበት መንገድ ማመቻቸት እና ከሌላው ዜጋ እኩል ለስልጣን ማብቃት የሚሉት በንግግራቸው ውስጥ ከጠቀሷቸው ውስጥ ናቸው።

የንቅናቄው እድሎች እና ፈተናዎች

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በአሁኗ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር መመስረቱን ይዞ ለንቅናቄውም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያመጣው ዕድል እና ፈተናዎች አሉት።ከሁሉ በፊት ግን ንቅናቄው የተመሰረተበት ምክንያትን ከዳር ሆኖ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚመለከት ተመልካች ሶስት ምክንያቶች ለመመስረቱ ማስቀመጥ ይችላል።የመጀመርያው ምክንያት የህወሓት ፅንፈኛ እና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በአማራው ላይ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የተሰራው የጭቆና ተግባር አንዱ ሲሆን፣በሁለተኛ ደረጃ ብአዴን-ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአማራው ስም እየነገደ የሰራው ሸፍጥ እና ሶስተኛው ምክንያት ከደቡብ እስከ ምስራቅ፣ከምዕራብ እስከ መሃል ኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች አማራ እየተባሉ መፈናቀላቸው እና ለሚፈናቀሉትም በቂ እርዳታ የሚያደርግም ሆነ በአፈናቃዮቹም ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱ የእዚህ አይነት ንቅናቄ እንዲመሰረት ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል።
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የንቅናቄው ሊቀመንበር 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የሚናቅ ጉልበት ይኖረዋል ብሎ መገመት አይቻልም።ለእዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ።እነርሱም ህወሓት የትግራይ ብሔርተኝነትን እያስኬደበት ያለው ጉልበት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ብዙዎችን ወደ መረረ ትግል ስሜት ውስጥ ማስገባቱ አንዱ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ አማራ እየተባሉ ለአመታት ከኖሩበት ቦታ እየተፈናቀሉ ሲሰደዱ እና ለልመና ሲዳረጉ ተገቢው ወቅታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ ነው።በተለይ በማፈናቀሉ ሂደት ውስጥ ከኦሮምኛ በስተቀር  አማርኛ ፈፅመው የማይችሉ በቷልዳችሁ አማራ ናችሁ ተብለው የተሰደዱ በርካቶች አሁንም በመጠለያ ቦታ ወይንም በከተሞች ውስጥ እየተንከራተቱ ይገኛሉ።እነኝህ ሁለት ሁኔታዎች የአማራ ብሔርተኝነትን እያፋፋሙት ይምጡ እንጂ ትልቁ እና ዋናው ጉዳይ ግን ህወሓት ሰራሹ የጎሳ ፈድራሊዝም አደረጃጀት እና ህገ መንግስቱ የአማራውን ሕዝብ በሚያጠቃው መልኩ የተሰሩ ናቸው የሚለው መሪ ሃሳብ ነው።በሽግግር መንግስቱ ወቅትም ሆነ ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ ሌላው ተወክሎ አማራው ግን አልተወከለም የሚለው አባባል አሁንም ድረስ ጎልቶ እየተነገረ ነው።የህወሓት ውጤት ብአዴን ስሙን የቀየረው ቆይቶ መሆኑ ይታወቃል።ስለሆነም ጉዳዩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መፍትሄ ከሚሹት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የአማራው ጉዳይ መሆኑን መካድ አይቻልም።እዚህ ላይ የአማራ ጉዳይ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገው ህወሓት እራሱ የአማራ ጉዳይ የሚል አጀንዳ በማነፈስቶውም ሆነ በተግባሩ ግፍ በመስራት ጉዳዩ እራሱን ወደ አጀንዳነት እንዲቀየር ስላስገደደ ነው።

ይህ ንቅናቄ መልካም እድሎች አሉት።ከእነኝህ እድሎች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል። እነርሱም:  -
  • ብአዴን ውስጥ ያሉ በደሉን ለሚረዱ ወገኖች አዲስ ጉልበት ይዘው የመውጣት ዕድል አላቸው፣
  • የፈድራል አደረጃጀቱን ለማዋቀር ተፅኖ የመፍጠር አቅም አለው፣
  • በእየቦታው አማራ በሚል ስም ለሚፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን አፋጣኝ የሕግም ሆነ የማቴርያል ድጋፍ እንዲደርስ የማስተባበር አቅም ይኖረዋል፣
  • በፌድራል ደረጃ የሚደርሱ በደሎችን በጥናት በማስደገፍ ለፌድራል መንግስት በማሳሰብ እንዲስተካከል ተፅኖ ለመፍጠር ይችላል፣
  • የክልሉ ተወላጆች በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ ገንዘባቸውን፣እውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን በመሰዋት ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የማድረግ ዕድል ይኖራል።

የሚሉት ለንቅናቄው የወደፊት እድሎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።ከእዚህ በተለየ ግን ንቅናቄው ከእድሎች በተለየ ፈተናዎችም ይኖሩበታል።

የንቅናቄው ፈተናዎች

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከሚኖሩበት ፈተናዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው። እነርሱም -
  • የከረረ ብሔርተኝነት ያላቸው ወደ አመራሩ ከመጡ ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ የመቸገር ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፣
  • በህወሓት ሰርገው እንዲገቡ የሚደረጉ ግለሰቦች የሚፈጥሩት አሉታዊ ስዕል በንቅናቄው ላይ የሚሰጠው መልካም ያልሆነ ስዕል እና ከሌሎች ብሔሮች ጋር ለማጋጨት የሚደረጉ ሙከራዎች፣
  • እራሱን በቶሎ ወደ ኢትዮጵያዊ ንቅናቄ ካልቀየረ በከረረ ብሔርተኝነት ስሜት የተመሰጡ አባላቱን ወደ ሃገራዊ አጀንዳ ባለቤትነት ለመቀየር የመቸገር ሁኔታ መፈጠር።የእዚህ አይነቱ ችግር አሁን ህወሓት እራሱ ገጥሞት የሚገኘው ችግር ነው።መግብያ ሲዘጋጅ መውጫው አብሮ መታየት አለበት።
  • በተሰሩ ግፎች እና ጥፋቶች ላይ ከሚገባው በላይ በመዘከር የይቅርታ እና የአንድነት መንገዶች እንዲከፈቱ ማድረግ ካልቻለ አማራን ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ደረጃ ወደ አደገኛ መንገድ የመሄድ አዝማምያ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ባጠቃላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ብአደንን ልገዳደር ወይንም ሊጠቀልል ባህርዳር ላይ ተመስርቷል።በሂደቱ የብአዴን አመራርም ሆነ ለውጥ ፈላጊው ክፍል ይህንን ንቅናቄ እንደስጋት እንደማያየው መገመት ይቻላል።ብአዴን ብዙ ጊዜ በውስጡ ባሉ ስውር እጆች በህወሓት ፍላጎት ሲነዱ ተመልክቷል።ስለሆነም ንቅናቄው ከብአዴን በኩል የጎላ ተግዳሮት ሊገጥመው ይችላል ብሎ ቢያንስ ለጊዜው ይኖራል ተብሎ አይገመትም።በሌላ በኩል ንቅናቄ እንጂ ፓርቲ ስላልሆነ የሚያቅፈው መልከአ ምድራዊም ሆነ የህዝብ ብዛት ቀላል የሚባል ስላልሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ሂደት ላይ የእራሱ አሻራ ይዞ ሊመጣ ይችላል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን መጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሕበረ ብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ወይንስ በብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመራል? ወይንስ ሁለቱም በእየፊናቸው ተደራጅተው ለውድድር ይቀርባሉ? እዚህ ላይ ግን ኦፌኮን ኦህዴድን፣አብን ደግሞ ብአደንን ለመገዳደር ከቆሙ ሌላ የፖለቲካ መሰነጣጠቅ እንዳይፈጠር ያሰጋል።ከእዚህ ያልቅ ግን ድርጅቶች ውሕደት ፈጥረው የሁሉም መብት የሚከበርባት ኢትዮጵያን እንዲያሳዩን የምድሪቱ ፍጥረታት በሙሉ የምንመኘው ቀዳሚ ምኞታችን ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: