ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, August 29, 2023

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

============
ጉዳያችን ምጥን
===========

ብራዚል፣ሩስያ፣ህንድና ደቡብ አፍሪካ በጥምረት የመሰረቱት ብሪክስን ለመቀላቀል ቬኒዝዌላ፣ኢንዶኔዥያና አልጀርያን ጨምሮ 23 ሀገሮች ያመለከቱ ቢሆንም በመጪው ጥር 1፣2024 ዓም እኤአ ጀምሮ ብሪክስ  የተቀበላቸው ሀገሮች ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገሮችን ብቻ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። እነርሱም ኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ኢራን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ሳውዳረብያ እና አርጀንቲናን ተቀብሏል።

ብሪክስ ኢትዮጵያን ከሳሃራ ሀገሮች በታች በብቸኝነት ሲመርጣት ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን ሳንጨምር ከሁለቱ አንዱ ማለትም ከግብጽ ጋር መርጧታል። ይህ የብሪክስ ኢትዮጵያን የመቀበል ጉዳይ አንዳንድ የምዕራብ ሀገሮችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገሮችም ለምሳሌ ናይጄርያ የመሳሰሉ ሀገሮች የተጽዕኖ አቅም በኢትዮጵያ በበለጠ ደረጃ ጥላ እንዳጠላበት በትልጽ ታይቷል። ጉዳዩ ኢትዮጵያ አሁን አሰላለፏ ከእነ ብራዚል፣ኢራን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬትና አርጀንቲና ጋር ያለው ጠንካራ የሚባል ኢኮኖሚ አንጻር ያላትን መጪ የማደግ አቅም፣የፈተናዎች የመቋቋም አቅምም፣ ለዓለም ካበረከተችው ታሪካዊ አስተዋጽኦ፣ወሳኝ እና ስልታዊ አቀማመጥ፣የተፈጥሮ ሃብት፣ከአፍሪካ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት እና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሁሉ ኢትዮጵያ ተመራጭ ሀገር አድርጓታል።

''ሠላሳ ሚልዮን ህዝብን በአራት ሚልዮን ህዝብ የምንቀይር ሞኝ አይደለንም ''

ሠላሳ ሚልዮን ህዝብን በአራት ሚልዮን ህዝብ የምንቀይር ሞኝ አይደለንም ያሉት በ1969 ዓም በኢትዮጵያ የሩስያው አምባሳደር ነበሩ። ለእዚህ ምላሻቸው መነሻው ደግሞ ሩስያ ሱማልያን ስታስታጥቅ ቆይታ ለምን ወደ ኢትዮጵያ ፊቷን በፍጥነት አዙራ የኢትዮጵያ አጋር ሆነች? የሚል ጥያቄ ሲጠየቁ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 30 ሚልዮን ሲሆን ሱማልያ 4 ሚልዮን ህዝብ ነበራት። ዛሬም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጀርያ ቀጥላ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ባለ 123 ሚልዮን ህዝብ መሆኗ ብቻ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያላት ተጽዕኖ በቀላሉ አይታይም። አንዳንዶች ብሪክስ ኤርትራ ካላት የጸረ ምዕራቡ አቋም አንጻር ለአባልነት ይጋብዛታል ብለው የሚያስቡ ነበሩ። ነገር ግን ጉዳዩ የ120 ሚልዮን ህዝብን የመምረጥ ስሌት ለብሪክስ አባላት ከባድ ሂሳብ አይደለም። 
 
ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የብሪክስ አባል ለመሆን ቢያስቡም የሩቅ ህልም ሆኖባቸዋል።

የብሪክስ አባል ሆኖ በቀጣይ ከምዕራብም ሆነ ከብሪክስ አባላት ጋር የልማት አጋርነትን ማጎልበት የብዙ አፍሪካ ሀገሮች ምኞት ነው። በእዚህም በኢትዮጵያ በብዙ በአዎንታዊ መልኩ ቀንተዋል። የናይጀርያ አንዳንድ ጋዜጦች መንደሪኑን ከዛፉ ለመቅጠፍ የዘለችው ጦጣ በዝላይ አለመድረሷን ስታውቅ ድሮም መንደሪኑ አይጣፍጥም ብላ ሳትቀምስ እንደሄደችው ዓይነት ነው። ናይጀርያ እንዴት አመልክታ አልገባችም ለሚለው አንዳንድ ምሁራን ምላሽ ለመስጠት ብሪክስ በቅርቡ ውጤቱ የሚታይ አይደለም በረጅም ጊዜ ነው የሚታየው የሚል ጽሑፍ በመጻፍ ምሁራኑን ለማጽናናት ሞክረዋል።

ከሳሃራ በታች ያሉ ሀገሮች ኢትዮጵያ ያላትን ያህል የምጣኔ ሃብት ነጻነት ስለሌላቸው ዘው ብለው ብሪክስ ውስጥ ቢገቡ በሚቀጥለው ቀን ከባንኮች እስከ ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ተቋም ድረስ የተያዙት በውጪ ኩባንያዎች በመሆኑ እንደፈለጉ የመወሰን አቅማቸው የሚታሰብ አይደለም። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በምንም መልኩ አሁንም በውጭ ብድር እና እርዳታ የታገዘ ቢሆንም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አንጻር በአንጻራዊ መልኩ የተሻለ የተጽዕኖ መቋቋም አቅም ይታይበታል። ከሁሉም ደግሞ ቀድሞ ከነበሩት ሦስት መንግስታትም ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያ አሁንም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አንጻር አንጻራዊ ነጻነት ያላት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፖሊሲ አውጪው የመወሰን አቅሙ የተሻለ ነው። የብሪክስ መስራቾችም በናይጀርያ እና በኢትዮጵያ መሃል ያለው የመወሰን የነበረ አቅም የገባቸው ይመስላል።

የብሪክስ አባል መሆን ማለት የምዕራብ ግንኙነትን ማራገፍ ማለት አይደለም።

ኢትዮጵያ ካለፉት ታሪኳ ልትማር ይገባል። ብሪክስም ይጠቅማታል፣ከምዕራቡ ጋርም ያላት ግንኙነት ይጠቅማታል።በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ብዙ ሀገሮች ከአንዱ ጎራ እየተጠቀለሉ ሲገቡ እንደህንድ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ገለልተኛ በሚል ድርጅት መስርታ የሁለቱንም የልማት ጥቅም በማግኘት ጊዜውን አልፋዋለች። ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገሮች ለምሳሌ ከህንድ እና ከደቡብ አፍሪካ አንጻርም ሲታይ የባህል እና የታሪክ ጋርዮሿ በራሱ ለልማስ ስኬት የሚያመጣው አዎንታዊ አስተዋጾ ቢኖረውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ተወላጆቿ የሚኖሩበት እና የቴክኖሎጂ ግንኙነቷም እየሰፋ የመጣው የምዕራቡ ግንኙነቷን ፈጽሞ ገለል ማድረግ አትችልም። አንዳንድ ምሁራን እና ሚድያዎች ጉዳዩን ከቀኝ ወደ ግራ የመዞር ያህል አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት ትንሽ ብስለት የጎደለው አካሄድ ትክክል አይደለም። በእርግጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ የመግባት ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ ጉዳዩ ከአንድ ጎራ ወደ ሌላ የመሄድ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የማደግ ተስፋዋን በአጋርነት ከቆሙት ጋር ሁሉ አብራ የምትሰራ መሆኗን በተግባር ማሳየት ነገር ግን የበለጠ የሚያግዟት ጋር ተባብራ መስራት አዋጪ መንገዷ ነው።

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና ከቀዳሚ ስድስት የዓለማችን ሀገሮች ጋር መመረጧ ዛሬም ደጋግመን እኛ እራሳችንን ያላወቅን፣ከሆኑ ዓመታት በኋላ እራሳችንን ዝቅ አድርገን የምናይ እኛ ማን ነን? ማን ነበርን? ዛሬስ የት ላይ ነን? ወደፊስ የምንሄደው? እራሳችንን ሳናውቅ ሌሎች ያወቁን ምናችንን ነው? ብለን ደግመን የመጠየቂያ ጊዜ አሁን ነው። ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ገደማ በዓለም ላይ ያላት የዲፕሎማሲ አቅም በተለይ ከንጉሱ ከስልጣን መውረድ በኋላ ደብዝዞ ኖሯል። በንጉሱ ዘመን ከተሰራው የኢትዮጵያን ማዕከልነት እና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ካጎሉት ውስጥ ጉልሁ እና አሁንም ድረስ ቀጣይ ፋና የሆነው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አሁን የአፍሪካ ሕብረት በአዲስ አበባ የመመስረቱ ጉዳይ ነበር።

የአፍሪካ ሕብረት ጉዳይ ኢትዮጵያን የግዙፍ አህጉራዊ ዲፕሎማሲ የማሳለጥ አቅሟን አሳድጎታል። ከአፍሪካ ሕብረት በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ከመሆኗ እና በምግብ እራሷን ያለመቻሏ ሁሉ ተደማምሮ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ መሪነት አቅም በእጅጉ ከመፈታተን አልፎ ትናንሽ ሀገሮች ከኋላዋ ተነስተው የተሻለ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተመልካች ሆናለች። ከእዚህ ሁሉ በኋላ ኢትዮጵያ ከእነብራዚል፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና አርጀንቲና ጋር ተጋፍታ ከሳሃራ በታች ካሉ ሀገሮች በሁሉም መስፈርቷ ያለፈውን እና የመጪ ተስፋዋንም ጭምር በሚገባ መርምረው የብሪክስ መስራች ሀገሮች ሲመርጧት ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግርማ በፍጥነት አሳድጎታል። ይህንን በብዙ ማስረጃዎች ማስረዳት ይቻላል።በእርግጠኝነት ማለት የሚቻለው ግን ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በርካታ ንግግሮች፣ውይይቶች፣አቅምን አግዝፎ የማቅረብ የተለያዩ ስልቶች እና የነበረ እና ዘላቂ ወዳጅነትን ለማጽናት የተደረጉ በርካታ የዲፕሎማሲ እና ሁለንተናዊ ጥረቶች እንደነበሩ ለመረዳት ከባድ አይደለም።

ለማጠቃለል፣ አሁን የእኛ ቦታ ከእነብራዚል፣አርጀንቲና እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር በእኩል ደረጃ መሆኑና ተፈላጊነታችን በእዚህ ደረጃ መናሩ ለእኛ አልታየን ከሆነ ለሌሎች መታየቱ ግልጽ ሆኗል። የእኛ እንደምንፈለገው ደረጃ መሆን ብቻ ሳይሆን እራሳችንን በምን ያህል የቀረንን ሞልተን በቶሎ ከመረጡንም ከተመረጡት ጋርም በፍጥነት አስተካክለን በፍጥነታቸው ልክ ለመሄድ ተዘጋጅተናል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ነው ቁም ነገሩ። የማደግ ተስፋችን ከፊታችን ቆሞ እኛ ግን በብሄር ፖለቲካ እና በመንደርተኝነት እየተቧደኑ ከሚገፉን እና ሀገር ከሚበትኑ ጋር ከቆምን ዛሬም ኢትዮጵያ የገጠማትን የማደግ ተስፋ መልሰን የምናጨልም ሆነን የመጪውንም ትውልድ ዕድል ዘጊዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። ኢትዮጵያ ከሁሉም አጋሮቿ ጋር አብራ እንድትለማ በውስጧ ጋሬጣ የሆኑ ሃሳቦች የሚዘሩባትን መጋፈጥ ብቸኛው አማራጭ ነው።
==================/////===============

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...