ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 11, 2023

ጥያቄው እየመገብን ስናሳድግ የኖርነው ወደፊትም ማሳደግ የምንፈልገው የቱን ነው? የሚለው ነው። መጪው የኢትዮጵያ ዕጣም የሚወሰነው በእዚሁ ነው።



==========
ጉዳያችን ምጥን
==========

አባት እና ልጅ ዛፍ ስር ተቀምጠው ያወራሉ። ከዛፉ ስር ሁለት ድንቢጦች ጥሬ ይለቅማሉ። ከሁለቱ ድንቢጦች ፈንጠር ያለች ሌላ ድንቢጥ (እናት ድንቢጥ) ያገኘችውን አንዴ ለራሷ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሁለቱ ድንቢጦች እያመጣች እንዲበሉ ፊታቸው ታስቀምጣለች።ከሁለቱ ድንቢጦች ውስጥ አንዱ ተንኮለኛ ነው። ሦስተኛዋ ድንቢጥ እያመጣች ከሁለቱ ድንቢጦች ፊት የምትጥለውን ተንኮለኛው ድንቢጥ ሌላውን እየኮረኮመ ቀድሞ ይበላል። ሌላኛው አለምብላቱን የምታይ እናት ድንቢጥ ደግሞ ነገሩን እንደዋዛ አይታ ተመልሳ ሌላ ጥሬ ለማምጣት ትሄዳለች። አሁንም ግን መልሳ የምታመጣውን የሚበላው ተንኮለኛው ድንቢጥ ነው።

አባት እና ልጅ የድንቢጦቹን ድርጊት ይመለከታሉ። ልጅ በድንቢጦቹ ድርጊት እያየ ይስቃል።አባት ነገሩን በአንክሮ ይመለከታል። ከቆይታ በኋላ አባት ልጃቸውን፣ሰማህ ልጄ! እነኝህ ሁለት ድንቢጦች በእኛ ውስጥ ያሉ ሃሳቦች ምሳሌ ናቸው።ሁለቱ ድንቢጦች እንደ ባላንጣ ለሚበሉት እንደሚሻሙ ሁሉ በውስጣችንም ያለው ሃሳብ እንዲሁ እርስ በርሱ ይዋጋል። የእዚህ የውስጣችን ሀሳብ የመጣላት እና አንዱ አሸንፎ የመውጣቱ ፋይዳ የወደፊት እኛነታችንን ብቻ ሳይሆን በዙርያችን ያሉትንም ዕጣ ሁሉ ይወስናል።ጥሬውን የሚነጥቀው በውስጣችን ያለው የክፉ፣የጎሰኝነት፣ሌላውን የማጥላላት ምሳሌ ነው።የዋሁ እና ገሩ ድንቢጥ ደግሞ የመልካም፣ለሌላው የማሰብ፣ከጎጥ ይልቅ የሁላችን ኢትዮጵያ የሚለው ሀሳብ ምሳሌ ነው። በማለት አባት የድንቢጦቹን ምሳሌነት አፍታተው ነግረው የልጃቸውን ትኩረት ሳቡት። ልጅ ግን ጠየቀ፣ አባዬ ግን ከሁለቱ ሃሳቦች ማን ያሸንፋል? በማለት ጠየቀ።አባት መለሱ የበለጠ እየመገብን ያሳደግነው ያሸንፋል።የዘረኝነት፣የጎጥ እና የክፉውን ሀሳብ እየመገብን ካፋፋነው እርሷ ያሸንፋል።ኢትዮጵያ ለሁሉም፣ጎጠኝነት ይጥፋ፣እርስ በርስ አንጠፋፋ የሚለውን ሀሳብ እየመገብን ካሳደግነው ደግሞ እርሱ ያሸንፋል በማለት መለሱለት።

በኢትዮጵያ በህወሃት/ኢህአዴግ እና ኦነግ የተተከለው የጎሳ ፖለቲካ ትውልድ በክሎ ዛሬ ላይ በአማራ ብሔርተኝነት አገንግኖ ወጥቶ የኦሮሞንም ሆነ የትግራይን ብሄርተኝነት ወይንም የጎሳ ፖለቲካ የሚገዳደርበት ደረጃ ደርሷል።እዚህ ላይ ምንም ያህል ቢሽሞነሞን፣ ምንም ያህል የሌላው የበደል መጠን ጥግ ማለፍ ያስነሳው ቢሆን፣ምንም ያህል መድረሻው ኢትዮጵያዊነት ነው ቢባል፣ የአማራ ክልል የተነሳው እንቅስቃሴ ምድቡ ከብሄርተኝነት እንቅስቃሴ የሚመደብ ነው።ይህንን የሚያራምዱትም የሚክዱት አይደለም። እዚህ ላይ የብዙዎቻችን ለኢትዮጵያ ያለን ምኞትና ሕልም ግን ከየትም ጥግ፣ምንም ዓይነት መልኩን ቀይሮ ይምጣ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አደገኛ የመርዝ ብልቃጥ መሆኑን አይቀይረውም።

ሩቅ የማያይ የዛሬው አይገባውም።ዛሬ የሚሆነውን እያየ ይህ ኢትዮጵያን ወዴት ነው የሚወስዳት ብሎ ማማተር ያልቻለ ከአፍንጫ እስከ ከንፈር ድረስ ብቻ የማሰብ የተሰናከለ አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያን ስናስባት የት እንድትደርስ የምናስብላትን መድረሻ እያሰብን ካልሄድን የፊት፣የፊትን እያዩ የመሄድ አደገኛ መንገድ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ሆነ ኢትዮጵያን ፈጽሞ አይጠቅምም።የኢትዮጵያ መጪ ዘመን የሚወሰነው እየመገብን ባሳደግነው ድንቢጥ ይወሰናል።

አሁንም ጥያቄው እየመገብን ስናሳድግ የኖርነው ወደፊትም ማሳደግ የምንፈልገው የቱን ነው? የሚለው ነው። መጪው የኢትዮጵያ ዕጣም የሚወሰነው በእዚሁ ነው።ለችግር መፍትሄ ተመሳሳይ ችግር በመድገም አይፈታም።በተቃራኒው በመሄድ ነው ማሸነፍ የሚቻለው። በሌላው በኩል ያለ ጎጠኝነት ጎዳን ተብሎ በተመሳሳይ መንገድ በመሄድ ለጊዜው ስሜትን ያረካ፣ንዴትን ያበርድ ካልሆነ በቀር ዘለቄታዊ መፍትሄ ለሀገር አይሰጥም።ከጎሰኝነት በተቃራኒው በፍጹም ኢትዮጵያዊነት መንገድ በመሄድ እና ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያ ከልብ በመነጨ የፍቅር ስሜት በመሄድ እና ለእዚህም እስከ የህይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል ሀገር ይቆማል።ስለሆነም ስንመግብ የኖርነውን አውቀን፣ወደፊት ለመመገብ የምናስበውን ከአሁኑ በምናቅደው ልክ የነገዋ ኢትዮጵያ ትታወቃለች። መሬት ላይ ያለው ትልቁ የአብዛኛው ህዝብ እውነት ዛሬም የጋራ የሆነች እና ከጎሰኝነት የተጣላች ከፍቅር የታረቀች፣ሁሉንም ወገኔ የምትል ኢትዮጵያን ማየት ነው።
================////===========

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...