ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ወደ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ደጋግማ የምትወስደው አንዱ ዓላማ ግድቡን በኃያላኑ ቁጥጥር ስር እንዲገባ ነው::ግብፅ አሁን ባለው ሁኔታ በግድቡ ላይ ምንም ዓይነት የቀጥታ ወታደራዊ ጥቃት በመፈፀም የምታተርፈው ነገር እንደሌለ ታውቃለች።ምክንያቱም ወታደራዊ ጥቃት የሚያስከትለው ብዙ ውጪ አለ።ይሄውም ሌሎች ኃይሎችን ከኢትዮጵያ ጎን ለማቆም ከመጋበዙ በላይ የአፍሪካውያን ጋር የምትገባው ፍጥጫ በራሱ የመገለል አደጋ ያስከትልባታል።በውሃው ጉዳይ ላይ ያላትን የወደፊት ድርድር በበለጠ አበላሽቶ የካሳ ጥያቄ ንትርክ ውስጥም ይከታታል።በሌላ በኩል አሁን ባለው ሁኔታ የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ የሚያምስ ሥራ መስራት ቀጠናውን ዙርያውን ለከበቡት የፅንፍ ኃይሎች ዕድል መስጠት መሆኑን ኃያላኑም ይረዳሉ።ስለሆነም ይህንን እርምጃዋን ቢያንስ አሁን አይደግፉላትም።ለምን? ቢባል ለቻይናም ሆነ ለአሜሪካ ዋነኛ የንግድ መተላለፍያ መስመር በእዚሁ አካባቢ ስለሚገኝ ሌላ ሊብያ እና ሶርያ ከመፍጠር የሚገኝ ትርፍ ለኃያላኑ የለም።በመሆኑም ብዙዎች እንደሚሉት የግብፅ አዋጪ መንገድ ከጀርባ ኢትዮጵያን ማዳከም ነው።የእዚህ ፅሁፍ መነሻ ግን ይህ አይደለም።ግብፅ ጉዳዩን ወደ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የመውሰዱ ጥረቷን ለምን ገፋችበት? በሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ላይ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ኃያላኑ እራሳቸው የሚፈሩት ትልቅ ጉዳይ በግድቡ ጉዳይ እርስ በርስ እንዳያጋጫቸው እና የተፅዕኖ የመፍጠር አቅሙን አንዱ ለብቻው ጠቅልሎ እንዳይወስድ ነው።በዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ከተጋጩ ደግሞ ግጭቱ ወደ የሚፈሩት የአፍሪካ ላይ ንጥቂያ ማደጉ አይቀርም::ይህ ደግሞ አንዳቸውም ሳይጠቀሙ አፍሪካውያን በሚጫወቱት ሁለት ካርድ ጠንክረው የመውጣት ወይንም የአንዱ ሙሉ ንብረት የመሆን ሁኔታ ይፈጠር እና መቶ ከመቶ የማጣት ዕጣ ለጊዜው በማን ላይ እንደሆነ ባልታወቀ አንዱ ሃያል ሀገር ላይ ይደርሳል።ይህ ማለት ቢያንስ አንዱ የሚያጣ ሃያል ሀገር የመሆን አደጋው ሁሉም ጋር እኩል ነው ማለት ነው።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1884 እስከ 1885 ዓም በበርሊን የተደረገው አፍሪካን የመቀራመት ኮንፍረንስ ዓላማ ይሄው ዓይነት ነበር።ሁላችንም ከምናጣው ተከፋፍለን ትንሽ ትንሽ ይድረሰን የሚል ዓላማ ነበረው።ኮንፍረንሱ እርስ በርስ ላለመጋጨትም የረዳ ነበር።የዓባይ ጉዳይም ይሄው ነው።በተናጥል ቢሄዱ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በመጨረሻ ተስማምተው ወይንም ኢትዮጵያ በዓላማዋ ፀንታ ጠንክራ ትወጣለች በእዚህም ሁሉም ያጡታል።ከእዚህ ይልቅ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ከመጣ ግን ሳይነጣጠቁ የድርሻቸውን ሚዛን እየጠበቁ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን እየተጠቀሙ ቢያንስ ኢትዮጵያ ጠንክራ እንዳትወጣ ግብፅም ከተፅዕኗቸው ውጪ ሳትሆን ለመጫወት ይመቻቸዋል::በእዚህ ሁሉ መንገድ ስንመለከተው ግብፅ ጉዳዩን ወደ የፀጥታው ምክር ቤት እንድትወስደው ከኋላ የሚጎተጉቱ የሉም ማለት አይቻልም::በሌላ አነጋገር "ጉዳዩን ለብቻዬ እንዳየው አታድርገኝ::ሁላችንም በተሰበሰብንበት ሳሎን ይዘኸው ና!" እንደማለት ነው::
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960 ተጀምሮ በ1968 ዓም የተፈፀመው እና ምርቃቱ ግን በ1971 ዓም የተከናወነው የአስዋን ግድብ፣ ግብፅ ከሰራች በኋላ በምዕራቡ ዓለምና በሩስያ መሃል ጦርነት ቀረሽ ፍጥጫ ነበር::የግብፁ የያኔው ፕሬዝዳንት ገማል ናስር ከሩስያ ጋር በመቆም፣ሩስያም በግልጥ ከግብፅ ጋር በመቆም የግድቡን ንብረትነት አረጋገጡ እንጂ የጦር መርከቦች ለውጊያ ተሰብቆባቸው ነበር።ሃያላኑ ያን ጊዜ እንዲህ መከፋፈላቸው የግድቡን ባለቤትነት ለግብፅ አስከበረ።
ኃያላኑ ከአስዋን ተምረው የኢትዮጵያን ግድብ ከኢትዮጵያም ከግብፅም ተፅዕኖ ወጥቶ እነርሱ የሚያሽከረክሩት እንዲሆን ዛሬ ከያኔው ተምረው የሚመክሩ አማካሪዎች የሏቸውም ማለት አይቻልም።ቁምነገሩ ኢትዮጵያም አካሄዱን ቀድማ የመረዳቷ ቁምነገር ነው።ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ግብፅም ብትሆን ብልህነቱ ቢኖራት በፍትሃዊ አጠቃቀሙ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምታ፣ኢትዮጵያም ቃል በገባችው መሰረት ግብፅን የሚጎዳ ነገር እንደማታደርግ እያሳየች ተባብረው መቀጠል ነው ያለባቸው።የግብፅ መንግስት ጃልጅልነት የሚታየውም እዚህ ላይ ነው።በድርድሩ ተስማምቶ የኃያላኑን መጎተት አቁሞ መጠቀም የተሻለ መንገድ ነው።ኢትዮጵያ እንድትዳከም ግድቡ በኃያላኑ የእጅ ዙር ተፅዕኖ ስር እንዲወድቅ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት ይዞ መሮጥ ለራሷ ለግብፅም በረጅም ጊዜ የሚያመጣው ጥቅም የለም።
የኃያላኑ እንደፈለጉ በተናጥል በግድቡ ጉዳይ ላይ እንዳይገቡ ሌላው ስጋት የሚሆነው የዓባይ ግድብ ጉዳይ በአፍሮ ዓረብ መሃል የተቀመጠ ወሳኝ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ ነው።የዓባይ ግድብ ጉዳይም ወደ አፍሮ አረብ ፍጥጫ አደጎ ኃያላኑ ወደ አንዱ በግልጥ አድልተው ቢቆሙ በአፍሪካም ሆነ በአረብ ሀገራት ያለው ጥቅማቸውን የሚያውክ ሁኔታ እንደሚፈጠር ያውቃሉ::ስለሆነም ነገሩ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እየተንከባለለ ቢቆይና አስፈላጊ ሲሆን ተጽዕኖ የሚያሳርፉበት ጉዳይ እንዲሆን ይፈልጋሉ::የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ስሌትም የኃያላኑም ዕሳቤ ይህ ነው የሚሆነው።አሜሪካም ሆነች ቻይና ለመጪው ዘመናቸው በአፍሪካ ሀብት ላይ ካልተንጠላጠሉ ኢንዱስትሪዎቻቸው በጥሬ ዕቃ ችግር እንደሚጎዱ ያውቃሉ።በቅርቡ ትራምፕ ወደ 9ሺህ የሚሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ከጀርመን እንደሚወጡ ሲናገሩ ያሉት ወደፊት ትኩረታቸው ወደ አፍሪካ እና እስያ እንደሆነ እና የአሜሪካ ወታደሮችም ለሁለቱ አህጉሮች እንደሚፈለጉ የሰጡት ፍንጭ የሃያላኑን መጪ አቅጣጫ አመላካች ነው።አፍሪካ ሲነሳ ደግሞ ኢትዮጵያ አለች።ኢትዮጵያ ስትነሳ የዓባይ ግድብ አለ።
በሌላ አንፃር ግን የግብፅ ወደተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መሮጥ በራሱ በተባበሩት መንግሥታት በኩልም ተቀባይነት አላገኘም። የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ በቅርቡ ያሉት፣ ሶስቱ ሀገሮች በራሳቸው መፍታት አለባቸው የሚል ነው::በመሰረቱ አንድ ጉዳይ ወደ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሚሔደው ቢያንስ በአህጉራዊ ድርጅቶች ታይቶ ነው::ግብፅ ይህ ጠፍቷት ሳይሆን አሁንም ከኋላ ሆነው "ይዘሽው ነይ!" የሚሏት የኃያሉን ቃል በማመን ነው::ግብፅ የዓባይ ግድብ ጉዳይ በሃያላኑ እጅ እንዲወድቅ እና ግጭት ተፈጥሮ በሰላም ማስከበር ስም በገላጋይነት ቢገቡ ሁሉ ምኞቷ ነው።በእዚህም ለዘለቄታው ኢትዮጵያ ተጠቅማ ጠንክራ ከምትወጣ ይልቅ እንድትዳከምላት ካላት የረጅም ጊዜ ዕቅድ አንፃር ነው።ስለሆነም አሜሪካ ብቻዋን እጇን እንድታስገባ ያደረገችው ጥረት ሁሉ በምትፈልገው መጠን ባለመሳካቱ አሁን ቢያንስ ሃያላኑ በቡድን በተፅኗቸው ስር እንዲገባ እንደ ገፀ በረከት ለመስጠት የጅራት ማወዛወዝ ሥራ እየሰራች ነው።ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነቷን እስከጠበቀች ድረስ ፈፅሞ አይሳካም።
ባጭሩ ግን የዓባይ ጉዳይ አሁን ኃያላኑን የሚያጋጭ ጉዳይ እንዳይሆን እና ምስራቅ አፍሪካን የሚያናጋ እንዳይሆን መጨነቅ አለ::ጭንቀቱ ኢትዮጵያ እንዳትጎዳ አይደለም::ሌላ ሊብያ እና የመን ከመጣ የንግድ ጥቅማቸው ይጎዳል::የአንዱ ኃያል በተናጠል ለመቆጣጠር ይንቀሳቀሳል፣ይህ ደግሞ ከባድ ግጭት ያመጣል::ዓባይ ግድብን ተቆጣጠርክ ማለት ግብፅ ላይ ቢያንስ በጎ ተፅኖ አለህ ማለት ነው።ግብፅ ላይ ተፅኖ አለህ ማለት የዓለም በርካታ የንግድ መስመር የሚንቀሳቀስበትን መተላለፍያ ላይ ተፅኖ አለህ ማለት ነው።ይህ ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ስታመነጭ የኤሌክትሪክ ሽያጭ በምትሰጣቸው አገሮች ላይ ሁሉ ተፅኖዋ ያድጋል።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን በአሁኑ ጊዜ ኤሌክትሪክ ማለት ከነዳጅ በላይ ነው።በቅርብ ዓመታት የዓለማችን ተሽከርካሪዎች በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ አየቀየሩም ማለት አይቻልም።ስለሆነም ለኢትዮጵያውያን የዓባይ ግድብ ጉዳይ የሞት እና የሽረት ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይገባል።
በመጨረሻ ግን የወቅቱን የዲፕሎማሲ መስመር በተመለከተ በእዚህ ሁሉ መሃል ግን የኢትዮጵያ አብራ ከግብፅ ጋር አለመጮህ ባንድ በኩል ጥሩ ይመስላል።አብረህ ስትጮህ እና ስትመላለስ ነገሩ እንዲጋጋል የሚፈልገው ወገን ይጠቀማል።ግብፅ አሁን ጉዳዩ የዓለም ፀጥታ አካል ነው ብላ ለማሳመን ነው የምትሞክረው።ስለሆነም ኢትዮጵያ አብራ ማዳመቅ አለመቻሏ ሳያበሳጫት አይቀርም።በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያ ቢያንስ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጥሩ አረብኛ የሚናገሩ እና የዲፕሎማሲው ልምድ ያላቸው ልዩ ልዑካን አባላት መርጣ ልካ ሃገራቱን በሚገባ ስለጉዳዩ መንገር እና በእየሃገራቱ ላሉት ሚድያዎች በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ መግለጫ መስጠት አለባት።ከአዲስ አበባ ከሚወጣ መግለጫ ይልቅ ይህ ብዙ ሥራ ሊሰራ ይችላል።
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment