ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 22, 2020

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግስት ለጣና ሐይቅ እንቦጭ አረም አደጋ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶታል? ጣና እየታዘበ ነው።

የእንቦጭ አረም ነቀላ በጣና ሐይቅ ዙርያ 

ጉዳያችን ልዩ 
በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።እነርሱም - 

>> የፌድራል መንግስት የጣና ሐይቅ የአረም ብክለትን በተመለከተ ምን እየሰራ ነው?
>> የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጉዳይ፣
>> የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የማስፈፀም አቅም ከአፍሪካውያን ጋር ሲነፃፀር 
*********

የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጉዳይ 

በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ግዙፍ አደጋ ከጋረጠው ቀዳሚ የአካባቢ ጥበቃ አደጋ ውስጥ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም አንዱ ነው።ሐይቅ እንክብካቤ ከተነፈገው ይጠፋል።የሐረማያ ሐይቅ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነውን መመልከቱ በቂ ነው።በሐረማያ ሐይቅ ላይ አደጋ እንደተጋረጠ የጥናት ውጤቶች ከዓመታት በፊት ለመንግስት እንዲያውቀው አድርገው ነበር።ሆኖም ግን የተወስደ እርምጃ ካለመኖሩ እና የተደረጉ ጥረቶችም ከዘገዩ በኃላ በመደረጋቸው አሁን ላለበት አደጋ ተጋልጧል።ኢትዮጵያ ካሏት ሃይቆች ውስጥ የሐዋሳ ሐይቅ፣የጣና ሐይቅ፣የዝዋይ ሐይቅ እና ሌሎችም ውስጥ የሐረማያ ሐይቅ ወደ ድርቀት ተቀይሮ፣ዛሬ ድካሙ ሁሉ ሐይቁን ወደነበረበት እንዴት እንመልሰው? የሚል ነው።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 9/1987 ራሱን ችሎ በፌደራል የመንግስት መስሪያቤትነት የተመሰረተ ነው።መስርያቤቱ ''ዘላቂ የአካባቢና የደን አያያዝ፣ ልማትና አጠቃቀምን በማረጋገጥ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን የገነባች መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ሆና ማየት'' የሚል ርዕይ ያለው ሲሆን  ከተልኮው ውስጥ ደግሞ ''ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን  ለመገንባት የሚያስችሉ የአካባቢ ጥበቃና የደን ሃብት አያያዝ፣ ልማትና አጠቃቀም ለዛላቂ ልማትና ለድህነት ቅነሣ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የአካባቢ ሥርዓቶችን ማዘጋጀትና ተፈፃሚነታቸዉን ማረጋገጥ'' የሚል ይገኝበታል።

ከመስርያቤቱ  ስልጣን እና ተግባር ውስጥ ደግሞ  ''የሀገሪቱን የአካባቢና የደን እንዲሁም ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በሚመለከት ዘገባን በየወቅቱ እያዘጋጀ ያሰራጫል፣'' የሚል ይገኝበታል። በተጨማሪም መስሪያ ቤቱ የአካባቢ ፖሊሲና ህጎችን፣ የተፈጥሮ ሃብት ስነህይወታዊ ስርዓቶችን የሚያስጠብቁ ደረጃዎን በማውጣት፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን በመከታተል እና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት ሀገሪቱ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በስራ ላይ መዋላቸውን ከትትል የማድረግ ስልጣን እና ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የማስፈፀም አቅም ከአፍሪካውያን ጋር ሲነፃፀር 

ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከጎረበቶቻችን ጀምሮ ቀድመውን የሄዱት እና በእኛ ሀገር ፖሊሲ እና መመርያ ወጥቶለታል ቢባል በቂ ግንዛቤ በሕዝቡ ዘንድም ሆነ የማስፈፀም ስልጣን ከክልል እስከ ፌድራል በተገቢ ደረጃ የሌለው የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት በመንግስትም ሆነ በግል ሚድያዎች ድምፁ አይሰማም።ኢትዮጵያ ግን በዓለም ላይ በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጠቁት አገሮች ውስጥ ነች።በእርግጥ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ አላት።ሆኖም ግን በአገር ውስጥ የሚሰሩ ልማቶች እና አዳዲስ የንግድ ፈቃዶች በአግባቡ እና ደረጃውን በጠበቀ ደረጃ የአካባቢ ተፅኖ ግምገማ (Environmental Impact Assessment -EIA) በምን ያህል ጥብቅ በሆነ መንገድ ይደረጋል? መልሱን በዘርፉ ላይ ላሉት እተወዋለሁ።ሆኖም ግን አንድ ነገር ማለት ይችላል።እስካሁን በኢትዮጵያ ለሚደረጉ አዳዲስ የፕሮጀክት ፍቃዶች ያጨቃጨቁ ፕሮጀክቶች አልተሰሙም።በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደ ኬንያ፣ዑጋንዳ እና ታንዛንያ የፕሮጀክት ፍቃድ ከአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት ማግኘት ከባንክ የንግድ ሥራ ዕቅድ (Business Plan) አቅርቦ ብድር ከመጠየቅ በላይ አስጨናቂ የሚሆንበት ምክንያት አለ።ለእዚህ ምክንያቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፖሊሲ እና መመርያ በአግባቡ ስለሚተገበር እና መስርያቤቶቹ የማስፈፀም አቅማቸው በሕግ ከለላ ጥብቅ በመሆኑ  እና ባለሙያዎቹም የሚጠቀሙት ዝርዝር መመርያ በአግባቡ ሥራ ላይ ስለሚያውሉት ነው።


በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ በተመለከተ ያሉት ችግሮች አራት ናቸው።እነርሱም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለው ግንዛቤ በሕዝቡ ዘንድ ዝቅተኛ መሆን፣ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በአግባቡ ገብቶ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ አለመሰጠቱ እና የሚመለከተው መስርያቤትም የማስፈፀም አቅም ማነስ እና በቂ የሰው ኃይል አለመኖር ነው።የማስፈፀም አቅም ሲነሳ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የከለከላቸው ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ፓርላማ ካልሆነ ማንም እንደፈለገ ሊወስንባቸው የማይችልበት አሰራር የዘረጉ የአፍሪካ አገሮች መኖራቸውን ማስገንዘቡ አንዱ ማሳያ ነው።በዑጋንዳ ከአስር ዓመት በፊት በዋና ከተማዋ ካምፓላ በነበረ ረግረግ ውሃማ ቦታ ደልድሎ ለጎልፍ መጫወቻ ለማድረግ የከተማው ምክር ቤት  ፈቅዶ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤት በመከልከሉ ጉዳዩ እስከ ፓርላማ ደርሶ የወራት ክርክር ተደርጎበት ፓርላማው ቦታው እንዳይነካ  የወሰነበትን ጉዳይ የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ያስታውሳል።የአፍሪካ አገሮች የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤቶች  ምን ያህል የማስፈፀም አቅም እንዳላቸው በእዚህ መገንዘብ ይቻላል።በነገራችን ላይ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤቶች የተፈጥሮ ሃብትን ብቻ ሳይሆን የድምፅ ብክለት በተመለከተ መግለጫ የሚያወጡ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤቶች ያሉባት አህጉር ነች አፍሪካ።ከአፍሪካዎች የምንወስደው ብዙ ልምድ አለ።ችግሩ ግን በአንዳንድ ጉዳዮች በጣም መራመዳቸውን አለመስማታችን ነው። ኢትዮጵያ የምትሻልባቸው ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የአፍሪካ አገሮች ቀድመው የሄዱበት ዘርፎችን መለየት ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤት በጣና ሐይቅ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በተመለከተ የዓማራ ክልል ቅርንጫፍ መስርያቤቱ ከሚሰጠው አንዳንድ መግለጫዎች ባለፈ ለእዚህ ዓይነት ግዙፍ አደጋ ምን እየሰራ እንደሆነ ግልጥ አይደለም።ከመስርያቤቱ ባለፈስ የፌድራል መንግስት ምን እያደረገ ነው?

የፌድራል መንግስት የጣና ሐይቅ የአረም ብክለትን በተመለከተ ምን እየሰራ ነው?

የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በጣና ሐይቅ ላይ የተፈጠረውን አረም (ይሄው ወደ ሶስት ዓመት ሆኖታል) ተከታታይ የትግበራ እና ክትትል ሪፖርት ሲያወጣም ሆነ ችግሩን ለመፍታት የመሪነት ሚና ሲወጣ አይታይም።በእርግጥ መስርያ ቤቱ በእየክልሎች መዋቅር አለው።በክልል ደረጃ ብቻ የማይፈታ ችግር ግን ብሔራዊ መፍትሄ ይፈልጋል።አሁን ባለው ሁኔታ የጣና ሐይቅ አረም ችግርን ለመፍታት ሲዋትቱ የሚታዩት፣የእነርሱ ብቻ አደጋ ይመስል የአካባቢው ነዋሪዎች እና ግለሰቦች ናቸው።ጉዳዩ ግን ብሔራዊ ጉዳይ ነው።አሁን ባለንበት ዘመን የጣና ሐይቅ ችግር የመላዋ ኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን እስከ ግብፅ እና ሱዳን ድረስ ያለውን ስነ-ምሕዳር ላይ ሁሉ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

የጣና ሀይቅ አረም በተመለከተ በርካታ ብጥስጣሽ ዜናዎች ሰምተናል።ገበሬዎች እና ተማሪዎች ውሃው እስከ አንገታቸው ድረስ እየዋጣቸው በጥንታዊ አሰራር መንገድ አረሙን ስነቅሉ የማኅበራዊ ሚድያው እያዳነቀ የአንድ ሰሞን ርዕስ ሆኗል።አንድ ጊዜ ደግሞ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመቶ ሺህ ዶላር እንዳዋጡ ተነገረ።ሌላ ጊዜ ደግሞ አረሙን የሚያጠፋ መድሃኒት በምርምር ተገኘ ተባለ፣አዲስ ማሽንም ተፈበረከ፣እገሌ የተባሉ ባለሀብት አዲስ ማሽን አስረከቡ ተባለ።ሆኖም ግን የዛሬ ሦስት ዓመት የሐይቁ 50 ሺህ ሄክታር በአረሙ መሸፈኑ እንደተነገረ ሁሉ (ሪፖርተር፣ጁላይ 12/2017 ዓም እኤአ) ዛሬም አረሙ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ግንቦት 14/2012 ዓም ባስተላለፈው ዘገባ የጣና ሐይቅ እንቦጭ አረም መባባሱን እና ሰፊ ቦታ እያካለለ መሆኑን ዘግቧል።በአሁኑ ሰዓት ችግሩን ያባባሰው ደግሞ ከእዚህ በፊት ያቅሙን አረሙን ለማጥፋት  የሚጥረው ሕዝብ (ብዙ ለውጥ ባያመጣም) በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምንም ማድረግ ባለመቻሉ ነው።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጉዳዩን አስመልክተው ችግሩን ለመፍታት በምርምር የተደገፈ ሥራ ይሰራል ማለታቸው ይታወሳል።አሁን ጉዳዩ ምን ላይ ደረሰ? ይህ ብሔራዊ አደጋ በየትኛው የብሔራዊ መስርያቤት እየተማራ ነው።ችግሩ በዓማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ብቻ እንደማይፈታ ግልጥ ነው።የፌድራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት የማስተባበር ሥራ መስራት የለበትም ወይ? ለተወካዮች ምክር ቤት ችግሩን እና ችግሩን ለመፍታት የተወሰዱ ተግባራት እና ግምገማ ቀርቦ ለውይይት ቀርቧል ወይ? የመረጃ ክፍተቱ ትልቅ ነው። ችግሩ ብሔራዊ እስከሆነ ድረስ ብሔራዊ መፍትሄ ይፈልጋል።

በእርግጥ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ ስራው ከፍተኛ በጀት እና የሰው ኃይል ይጠይቃል።ሆኖም ግን የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ዓለምአቀፋዊ ከመሆናቸው አንፃር ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች አገራት የእዚህ ዓይነቱን ችግር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመፍታት የሚሰሩ ስራዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ወደኃላ እንደማይሉ ይታወቃል።የጣና ሐይቅ በተመለከተ ያለው መሰረታዊ ችግር ለመፍትሄው የሚንቀሳቀስ ማዕከላዊ አስተባባሪ ከፌድራል መንግስት አለመኖሩ ነው።ይህ በራሱ ትልቅ ስብራት ነው። ግለሰቦች ከአሜሪካ እስከ ጎንደር ጥረት ሲያደርጉ እንቅስቃሴውን በማዕከልነት ሰብስቦ የሚሰራ የፌድራል ቢሮ እንዴት አይኖርም? የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አልፎ አልፎ በዓማራ ክልል ቢሮው ከሚላቸው አንዳንድ ጉዳዮች ውጪ ከፌድራል መንግስት ጋር በመሆን ዘላቂ የመፍትሄ ዕቅድም ሆነ የተግባር ክትትል ሪፖርቱ በድረገፁም ላይ አላስቀመጠም።

ባጠቃላይ የጣና ሐይቅ እምቦጭ ዓረም ጉዳይ የፌድራል መንግስት በኃላፊነት ሊሰራቸው ከሚገባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባት ያለበት እንጂ ለክልል የሚተው ጉዳይ አይደለም።ችግሩን በአንድ ወቅት ከማንሳት ባለፈ እስካሁን ምን እንደተደረገ፣ ምን እንዳልተደረገ እና ጉዳዩን በማዕከል የሚያስተባብረው መስርያቤት ማን እንደሆነ ለማወቅ ሳይቀር ለሕዝብ እንግዳ ጉዳይ ሆኗል።ይህ አሳዛኝ ጉዳይ ነው።በተለያየ ቦታዎች የሚደረጉ ጥረቶችን በማዕከልነት አምጥቶ መስራት እንዴት እንዳልተቻለ በራሱ ጋራ ያጋባል።በኢትዮጵያ የዛፍ መትከል ጥሩ ተግባር ከአለፈው ዓመት ጀምሮ እያየን ነው።ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ሥራ በእዚህ ዓመትም እንደሚቀጥል ይታወቃል።ይህ በራሱ መልካም ተግባር ሆኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ስነ-ምሕዳር ከመመለስ ጎን ለጎን ያለውን መጠበቅም ሊዘነጋ አይገባውም።ጣና እየታዘበ ነው።


ጌታቸው በቀለ 

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...