ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, December 31, 2019

የአዲስ አበባ ከተማ - የከተማዋን ነዋሪ ስነ-ልቦና ፣ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕከልነትን ታሳቢ ያደረገ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋታል።


ጉዳያችን  GUDAYACHN  
ታህሳስ 21/2012 ዓም (ዴሰምበር 31/2019 ዓም)

የአራዳ ዘበኛ  

አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያውን የፖሊስ ሥራ ያስተዋወቀች ከተማ ነች።ዘመኑ 1901 ዓም ነበር አዲስ አበባ የመጀመርያውን የፖሊስ ሰራዊት ጥንስስ የአራዳ ዘበኛ በሚል ስም ያደራጀችው።የኢትዮጵያ የፖሊስ ሰራዊት ታሪክ ጥንስስም እዚህ ላይ ይጀምራል።በወቅቱ ንጉሰ ነገስት ምንሊክ የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ፖሊስ የአራዳ ዘበኛ በሚል ለሕዝቡ ሲያስተዋውቁ ያወጡት አዋጅ እንዲህ የሚል እንደነበር ጳውሎስ ኞኞ 'አጤ ምንሊክ' በተሰኘው መፅሐፉ ላይ ጠቅሶታል።


ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ
ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሄር
ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ

አዋጅ!
ለሊት ሌባ እንዳይበዛ፣ ቀን አነባብሮ እንዳያነሳ፣ በተረፈ ክፉን ነገር ሁሉ የሚጠብቅ ዘበኛ ብናቆም ሁሉም ዘበኛ ነኝ እያለ እንዳይዝ ቁጥር እና ባንዲራ ያለበት በራስ ላይ የሚደረግ ምልክት አበጅቻለሁ። ያንን ምልክት ያደረገ ዘበኛ ቢይዝህ መያዝ ነው እንጂ ይህን ጥሰህ የተጣላህ ሰው ትቀጣለህ።
ሚያዝያ ፳፱ ቀን ፲፱፻፩ አመተ ምህረት አዲስ አበባ ከተማ። ይላል።

የአራዳ ዘበኛ ኮፍያው ላይ 'የምስጢር ዘበኛ' የሚል ፅሁፍም ነበረው።

የአራዳ ዘበኛ እስከ 1928 ዓም ጣልያን ኢትዮጵያን እስኪወር ድረስ ዘለቀ።ጣልያን ከኢትዮጵያ ተባሮ ከወጣ ከ1934 ዓም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖሊስ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተለት።ሰራዊቱ በአዋጅ ቁጥር 6/1934 በወቅቱ ስሙ አባዲና ፣የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ መመስረት ጋር ተከትሎ የፖሊስ ሥራ ሳይንሳዊ በሆነ መልክ የሚሰሩ መኮንኖች ሰራዊቱን መቀላቀል ጀመሩ።

የፖሊስ ሰራዊት የህዝብን ፀጥታ የማስከበር ሥራ እስከ 1967 ዓም ድረስ የሚያስከብርበት የተለያየ መንገድ ይጠቀም ነበር።ለምሳሌ የሚሊሻ ታጣቂዎች ከፖሊስ ጋር እንዲሰሩ ማድረግ፣አውጣጭኝ በሚል ሕብረተሰቡን ሰብስቦ በአንድ አካባቢ ሰብስቦ ወንጀል እንዲጋለጥ ከማድረግ ጀምሮ እስከ ፖሊስ እና ርምጃው የሚል ጋዜጣ እና የራድዮ ፕሮግራም እያደገ መጣ።እስከ 1967 ዓም ድረስ የፖሊስ ሰራዊት ሥራ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተከበረ ሙያ ነበር። ፖሊስ የሆነ ሰውም የማይዋሽ፣በሕዝቡም ውስጥ የተሻለ ተሰሚነት ነበረው።ከ1967 ዓም ለውጥ በኃላ በከፍተኛ የፖሊስ ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ወደ ማዕከላዊ ምርመራ ተሳቡ የቀሩት ወደ ደርግ የምድር ጦር እና የፖሊስ ሰራዊት መኮንኖች ውስጥ ሲዋቀር የፖሊስ ኃይሉም የሰለጠነ የሰው ኃይል ተዳከመ።ደርግ የህዝቡን መብት ለማፈን የፖሊስ ኃይሉ በቂ ስላልነበር የፖሊስን ሥራ የአብዮት ጠባቂ እና የደህንነት ክፍሉ አፋኝ ቡድን ወሰደው።በመቀጠል ፖሊስ ለትንንሽ የሌብነት ስራዎች ወይንም የፖለቲካ ጉዳይ የለባቸውም ለሚባሉ ወንጀሎች ብቻ የሚፈለግ ሆነ።

በ1983 ዓም ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ በአራዳ ዘበኛ ጥንስስ የተጀመረው የፖሊስ ሥራ በየክልሉ እንዲከፋፈል ተፈረደበት።የፖሊስ ኃይሉ በክልሎች ደረጃ ሲዋቀር የፖሊስ ማሰልጠኛዎችም በየክልሉ የመክፈት ሥራ ቢይታይም በጥራት እና በደረጃ ግን ዘመኑን የተከተለ ሳይሆን በቂ ስልጠና የሌለው ፖሊስ ሰራዊቱን መቀላቀል ጀመረ።

አዲስ አበባ የራሷ ፖሊስ ኃይል ለምን ተነፈገች?

በዘመነ ደርግ አዲስ አበባ በአብዮት ጥበቃ ስር ብትሆንም የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የሸዋ ፖሊስ ዋና መስርያ ቤቱን ከካሳንቺስ ወረድ ብሎ የሚገኘውን ህንፃ ተከራይቶ ይሰራ ነበር።በዘመነ ኢህአዴግ ግን የአዲስ አበባ ፖሊስ ደካማ ሆኖ እንዲደራጅ ከመደረጉም በላይ የፈድራል ፖሊስ ከፍ ተደርጎ እንዲደራጅ ተደረገ።በእዚህ ሳብያ ዘመናዊነት የሚታይባት አዲስ አበባ የከተሜ ማዕረግ ያለው ፖሊስ እንዳማራት ዓመታት ነጎዱ።የኢትዮጵያ ፖሊስ በአባዲና ኮሌጅ በጀመረው አሰለጣጠን መንገድ ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን የኮምፕዩተር እና ኢንተርኔት ዘመን በሚመጥን መልኩ በብዛት እና በጥራት ማሰልጠን  ይጠበቃል።

ከ2010 ዓም  የለውጥ ሂደት በኃላ የአዲስ አበባ የራሷ ፖሊስ የማግኘት መብት አሁንም አልተከበረም።ሌላው ቀርቶ ከእዚህ ለውጥ በፊትም ሆነ ከለውጡ በኃላ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን ክልሎች የራሳቸው የፖሊስ ኃይል እንደሚኖራቸው  የተጠቀሰውን መብትም ሳይቀር አዲስ አበባ ላይ ሲደርስ ታግቷል።ይህ ደግሞ አዲስ አበባ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብቱ ማዕከል እንደመሆኗ መንግሥታት አዲስ አበባን በቀጥታ በሚመሩት የፀጥታ ኃይል ስር የማድረግ ፅኑ ፍላጎት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ - የከተማዋን ነዋሪ ስነ-ልቦና ፣ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕከልነትን ታሳቢ ያደረገ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋታል።

የፖሊስ ኃይል አባል አካባቢውን በደንብ የሚያውቅ መሆኑ ብዙ ጥቅም አለው።በመጀመርያ ደረጃ የህዝቡን ስነ ልቦና፣ማኅበራዊ ሕግ  እና አስተሳሰብ የሚረዳ የፖሊስ ኃይል የሚያደርገውን የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን የችግር አፈታት መንገዱም አካባቢውን ከማያውቅ በተሻለ መንገድ ሕዝብ የማገልገል አቅም ይኖረዋል።

ከእዚህ አንፃር የአዲስ አበባን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ አዲስ አበባ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የተለየ ባህሪ እንዳላት እንመለከታለን።አዲስ አበባ በመጀመርያ ደረጃ ሕብረ ብሔራዊ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ነች።የብሔር ፖለቲካ አንግቦ የሚመጣ ኃይል ለአዲስ አበባ የተናቀ ሥራ ነው።ፖሊስን አዲስ አበባ የምታውቀው ከአራዳ ዘበኛ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሌሎች በጎሳ ዓይን ሲመለከቷት ለአዲስ አበቤ ግን ፖሊስ ፖሊስ ነው።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከህብረ ብሔር ከተማነቷ በላይ በዓለም ላይ ከኒውዮርክ እና ጀኔቫ ቀጥሎ  ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የሚገኝባት  ከተማ ነች።የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአንድ መቶ አምስት በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻው መነሻው አዲስ አበባ ነች።በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ካለቪዛ የመግባት ፍቃድ  መስጠቷን ተከትሎ ያለውን ሁኔታ ሁሉ ስንቃኝ አዲስ አበባ በምን ያህል ደረጃ ከአዲስ አበባ ጋር የተናበበ የፖሊስ ኃይል  እንደሚያስፈልግ መረዳት ይቻላል።ሌላው ቀርቶ አሁን በአዲስ አበባ የሚያዙት ሌቦች ከአዲስ አበባ የመጡ ብቻ ሳይሆን ከኬንያ እና ታንዛንያ ጭምር የመጡ ወንጀለኞች እየታዩ ነው።ይህ ማለት በየትኛውም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣብያ ቢያንስ በእንግሊዝኛ በበቂ ሁኔታ ቃል ሊቀበል የሚችል የፖሊስ መኮንን ያስፈልጋል ማለት ነው።

ባጠቃላይ የአዲስ አበባ የራሷ ፖሊስ የመኖሩ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።የፒያሳ ልጆችን ፀባይ፣የቄራ ልጆችን ብሽሽቅ፣ የጉለሌ ልጆችን ዱላ፣የቦሌ ልጆችን አስተዳደግ፣የቀጨኔ ልጆችን አስተሳሰብ የሚረዳ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋታል። ከእዚህ ውጪ በክልል ሰልጥኖ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ የፖሊስ ኃይል የአዲስ አበባን ስነልቦና የማይረዳ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ልጅ በሙሉ የክልል ሰው የሚንቁ መስሎ የሚታየው እና በንግግር እና ሃሳብ ሊግባባ የማይችል ፖሊስ በአዲስ አበባ ላይ ማሰማራት በመንግስት እና በአዲስ አበባ ሕዝብ መሃል ያለውን ግንኙነት የሚያበላሽ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ የፀጥታ ሁኔታዋ እንዳይበላሽ ያሰጋል። አሁንም ለመድገም የአዲስ አበባ ከተማ - የከተማዋን ነዋሪ ስነ-ልቦና ፣ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕከልነትን ታሳቢ ያደረገ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋታል።

አዲስ አበባ Addis Ababa City - New Flower of Ethiopia (ቪድዮ)



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...