ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, January 1, 2020

መንግስት በግልፅ ተነጋግሮ ካላረመው ኢትዮጵያ ከባድ የፀጥታ አደጋ ያሰጋታል

ጉዳያችን GUDAYACHN   
ታሕሳስ 22/2012 ዓም (ጃንዋሪ 1/2019 ዓም)

'ሳይቃጠል በቅጠል' የምትለው የኢትዮጵያውያን አባባል ትልቅ ትምህርት አላት።ቅጠል እራሱ ተቀጣጣይ ነው።እሳት ሲቀጣጠል በቅጠል ላጥፋው ብትል አትችልም።ምክንያቱም እሳቱ እራሱ ሊያጠፋው የመጣውን ቅጠል ይበላዋል።ሳይቃጠል ገና በትንሽ ጭስ ላይ እያለ ግን በቅጠል ብትመታው ያለው ፍንጥርጣሪ እሳት ተበታትኖ ይጠፋና ትልቅ የእሳት አደጋ ሳያስከትል እና ነፋስ እያግለበለበ ሳያቀጣጥለው የመጥፋት ዕድል አለው። 

የኢትዮጵያ ወቅታዊው ፖለቲካ በቅንነት ኢትዮጵያን ወደተሻለ መንገድ ለማሻገር የሚተጉ የመኖራቸውን ያህል የተለመደውን የሴራ ፖለቲካ እያውጠነጠኑ ያደፈጡ ኃይሎችም አሉ።የሴራ ፖለቲካው ደግሞ በራሱ በመንግስት የቢሮክራሲ መዋቅር ውስጥ የተተበተበ እና በጎሳ መር ድርጅቶች ላይ ሁሉ ማድራቱ ነው አደጋው።ስለሆነም በኢትዮጵያ ወሳኝ በሆኑ መንግስታዊ ድርጅቶች ላይ ሁሉ የቅርፅ እና የዓይነት መልክ እያመጣ ኢትዮጵያዊ ቃናውን እያሳጣው እንዳይሄድ እያንዳንዱን መዋቅር መልሶ መላልሶ መፈተሽ እና አላስኬድ ያለውን አሰራር እና ፖሊሲ ሁሉ መከለስ ያስፈልጋል።

አሁን ላለው የኢትዮጵያ በር ላይ የፀጥታ አደጋ ውስጥ የሚጠቀሰው አንዱ የክልሎች ልዩ ኃይል ጉዳይ ነው።አንዲት አገር አገር የሚያሰኛት እንደ አገር የጋራ ተቋማት ሲኖሯት ነው።በተለይ ቁልፍ የሆኑት መንግስታዊ  ተቋማት ለምሳሌ የጦር ኃይል እና የፀጥታ ኃይሉ በአገሪቱ ካሉት ክፍሎች ለአንዱ ባላዳላ መልክ ሁሉንም ባማከለ እና የገንዘብ ምንጩም በአገሪቱ የጋራ ሀብት የሚተዳደር ካልሆነ እጅግ አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ አመላካች ነው።

በኢትዮጵያ ከ1967 ዓም ወዲህ ባሳለፍናቸው ሁለት የአምባገነን መንግሥታት ታሪክ ለአምባገነንነት ዋና ምሰሶ ሆነው ያገለገሉት በተለይ ለፖለቲካ ስልጣኑ ሶስቱ ምሰሶዎች ናቸው።እነርሱም የወታደራዊ፣ደህንነት እና የኢኮኖሚ አውታር ናቸው። ከእነኝህ ውስጥ የወታደራዊውን ጉዳይ ብንመለከት በደርግ ዘመን ከጎሳ የፀዳ ወታደራዊ ኃይል ቢኖረውም በውስጡ ግን የስልጣን ወንበሩን የሚያስጠብቁ ''ቅልብ ጦር'' የሚባል በኮ/ል መንግስቱ የሚታዘዙ አስፈሪ የሰራዊት ኃይል ነበሩ።ይህ ጦር ከሌላው የኢትዮጵያ ጦር የተለየ ሆኖ እንዲወጣ ሲደረግ ዋና ዓላማው የሚቃወሙትን ሁሉ በኃይል ለመስበር ነው። በዘመነ ህወሓት-ኢህአዴግም ''አግአዚ'' የሚባል ጦር ነበር።ይህ የጦር ኃይል ከቅልብ ጦር የሚለየው በአንድ ጎሳ የተፈረጀ እና እንደተባለውም ለይስሙላ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ አባላት ቢኖሩትም ከስያሜው ጀምሮ  እስከ ማዕከላዊ ማዘዣው ድረስ ከአንድ ጎሳ ጋር የተመደበ ይልቁንም ይህ ሰራዊት የሚሰራው የጭካኔ ሥራ ሁሉ ከጎሳው ተግባር ጋር እየተገናኘ የሄደበት ታሪክ የተስተናገደበት ሁኔታ ነበር።

የአሁኑ አስፈሪ ሁኔታ ምንድነው?

ያለፈ የታሪክ ስህተት ለአሁኑ አስተማሪ ነው።ደርግን የቅልብ ጦር ጭካኔ ስልጣኑን አልጠበቀለትም።ህወሓትም የአጋዚ ጦር አላዳናትም።የሁለቱም ጦር አባላት የት እንዳሉ አይታወቅም።ምናልባት የአጋዚ ጦር አሁንም አለ ይሆናል።ነገር ግን እያረጀ ከመሄድ እና ወደ የግል ህይወቱ ከመግባት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም።ከእነኝህ ሁሉ ተምሮ ዛሬን ማስተካከል ተገቢ ነው። 

በኢትዮጵያ በክልሎች ያለው የልዩ ኃይል ብዛት፣የስልጠናው ዓይነት እና እየታጠቀ ያለው የጦር መሳርያ አይነት ሁሉ ስንመለከት እና በፍጥነት መታረም ካልቻለ ከደርግም ሆነ ከህወሓት የባሰ አደጋ ለኢትዮጵያ አያስከትልም ማለት ሞኝነት ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች አንዳንዴ የሚገርሙኝ ትልቁን አደጋ ላይ ሲጮሁ እና መንግስት እንዲታረም ሲጮሁ አለመታየታቸው ነው። በትንሹ ጉዳይ ደግሞ ከሚገባው በላይ አጋኖ በማቅረብ ለመጠላለፍያነት ሲደክሙበት ይታያሉ። ከእዚህ የክልሎች ኃይል እያፈረጠሙ መሄድ በላይ ለኢትዮጵያ ውስጣዊ የፀጥታ ችግር የከፋ ጉዳይ ምን አለ? 

በተለየ ሁኔታ በአሁኑ ሰዓት የክልል ልዩ ኃይል ጡንቻ ማፈርጠም በእየክልሉ እንደቀጠለ ነው።በቅርቡ  ካልተሳሳትኩ በሰላም ሚኒስቴር አቅራቢነት የተወካዮች ምክር ቤት የክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ የሚፈቱበትን ሁኔታ ላይ መነጋገሩ ተነግሮ ነበር።ሆኖም ጉዳዩ መልሶ የት እንደደረሰ አልተሰማም። በትግራይ ቁጥሩ የማይታወቅ የክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አለ።በዓማራም በተመሳሳይ መልክ እንዲሁ ክልሉ በመንግስት ጦር ሳይሆን በልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ነው ፀጥታውን የሚያስከብረው።በኦሮምያም እንዲሁ የክልሉ ልዩ ኃይል አሁን በከፍተኛ በጀት እየተደጎመ የ28ኛ እና 29ኛ ዙር ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ማስመረቁ ሰሞኑን ተነግሯል።

የክልል የጦር ኃይል በተመለከተ ሁሉም ክልል ወደራሱ የአገር መልክ እየሄደ ያለ ይመስል እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት የስልጠና እሽቅድምድም ላይ ያለም ይመስላል። በመጀመርያ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል ስልጠና ከዋናው የኢትዮጵያ ጦር ኃይል የስልጠና እና የትጥቅ ደረጃ ጋር እንዲገዳደር ተደርጎ መሰልጠኑ ምን ዓይነት አገራዊ ርዕይ ነው? የክልል ልዩ ኃይል የስልጠና ዓይነቱ ጣርያ የት ላይ ይቆማል? ለምሳሌ ወደፊት ታንከኛ፣አየር ኃይል እያሉ ላለማሰልጠናቸው ምን ዋስትና አለ? ሰሞኑን በኦሮምያ የታየው የክልሉ ልዩ ኃይል ከኢትዮጵያ የምድር ጦር ኃይል እኩል የሰለጠነ እንደሆነ ከእንቅስቃሴው መመልከት ይቻላል።በተለያዩ አስተሳሰቦች በምትናጠው የኦሮምያ ክልል ውስጥ የብሔራዊ ጦሩ ሚና ምን ሊሆን ነው? ብሎ አለመጠየቅ ምን ዓይነት የፖለቲካ እብደት ነው? ቀድሞ ክልሎች ትንንሽ የፀጥታ ጉዳዮችን እንዲፈቱ ከበድ ያለ ሲያጋጥማቸው በቶሎ ማዕከላዊ መንግስት የፌድራል ጦር ኃይል እንዲልክ እንዲጠይቁ ተደርገው ነበር የተሰሩት።አሁን ግን የስልጠናው ገደብም ሆነ የሚይዙት የጦር መሳርያ አይነት መጠን የሚታወቅ አይመስልም። 

ሰሞኑን በተመረቁት የኦሮምያ ልዩ ኃይል ስልጠና ምረቃት ላይ በአዋሽ ቢሾለ በመገኘት የመረቁት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሲናገሩ  "የልዩ ኃይሉ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የተገኘውን ድል ማስቀጠል ነው" ብለዋል።ምክትል ፕሬዝደንቱ በተጨማሪም የልዩ ኃይሉ ተልዕኮ የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ከማስጠበቅ በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እና መብት ማረጋገጥ የተጣለበት ሃላፊነት ነው ብለዋል። ልዩ ኃይሉ የአንድ ብሔርን ጥቅም እና መብት ማስጠበቅ የተጣለበት ኃላፊነት የሚለው አባባል እንደአገር የማሰብ የጋራ ርዕይ አይደለም።ይሄው ሰራዊት ግን ነገ በአዲስ አበባ ውስጥ ግባ ሲባል ለአዲስ አበቤ መብት ሳይሆን ለጎሳው መብት ለማስከበር እንደሆነ አቶ ሽመልስ ዛሬ ላይ ቆመው በግልጥ እየነገሩን ነው። ይህ ሁኔታ ነው የጎሳ ግጭት የሚያመጣው።የእኔ የሚለው ሰራዊት ያጣ ሕዝብ ወደ ጎሳው ልዩ ኃይል እንዲያማትር ሊያደርገው ነው።መንግስት ማለት ሁሉን በእኩል የሚዳኝ እንጂ የአንዱ አባት የሌላው እንጀራ አባት ሊሆን አይገባም።

ባጠቃላይ ከእዚህ በፊት የኦሮምያ ልዩ ኃይል በሱማሌ ክልል ላይ፣የሱማሌ ልዩ ኃይል በኦሮምያ ክልል ላይ እንዲሁም የኦሮምያ ልዩ ኃይል በሰሜን ሸዋ የዓማራ አዋሳኝ ክልሎች ላይ ያደረሱት ግጭት እና የሰው ሕይወት መጥፋት ይታወቃል። ይህ የክልል ልዩ ኃይል የኢትዮጵያ መጪ ዘመን አደጋ ነው።መንግስት ቁልፍ ከሆኑ አካላት ውስጥ አንዱ የሆነውን የወታደራዊ እና የደህንነት  አካሉን በአግባቡ በማዕከላዊነት መያዝ ይገባዋል። ፌዴራሊዝም አሰራር አለው።ክልሎች የፀጥታ ኃይል ይኖራቸዋል ቢባል የምድር ጦር ያህል ሰራዊት ያሰለጥናሉ ማለት ፈፅሞ ሊሆን አይችልም። መጪው ምርጫ ስርዓት ሊይዝ የሚችለው ክልሎች ያላቸው የልዩ ኃይል በሙሉ ፈርሶ ወደ አንድ ብሔራዊ ዕዝ ሲገባ እና በክልሎች የሚኖረው የፀጥታ ኃይል በፖሊስ አደረጃጀች ደረጃ ከተቀመጠ ብቻ ነው።ይህ ካልሆነ እያንዳንዱ ክልል የልዩ ኃይሉን በምድር ጦር ደረጃ የማሰልጠን እሽቅድምድም ውስጥ የማይገባበት ምንም ሁኔታ የለም። ከሰሞኑ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ስልጠና የተመለከቱ የሱማሌ፣የዓማራ፣የአዲሷ ሲዳማ፣ቤንሻንጉል ወዘተ ክልሎች ሁሉ የልዩ ኃይል ስልጠና በጀት መጨመር ላይ ይሮጣሉ።ይህ ደግሞ ልማቱን ያቀጭጫል።ነገሩ ሲገፋ ነገ የውጭ ኃይሎች በጎን በልማት ስም እየገቡ የአንዳንድ ክልሎች ልዩ ኃይል ስልጠና በጀት ማዕከላዊ መንግስት ባላወቀው መንገድ አይደጉምም ማለት አይቻልም።ክልሎች የወታደራዊ ኃይላቸው ጉልበት ሲፈረጥም ደግሞ የሌሎች ክልሎች ወሰን ጋር ግፍያ ውስጥ ይገባሉ። መዘዙ ብዙ ነው።እየተሄደ ያለው ሁሉ የማዕከላዊ መንግስትን አቅም እያደከሙ በግርግር የክልሎች ጉልበት እንዲጠነክር የሚያደርግ ሂደት ነው። ይህ ማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የማዕከላዊ ስልጣን እየተሸረሸረ በጎጥ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መጪ ዕድል የመወሰን አደጋ አለው ማለት ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግስት ከልቡ ከምርጫው በፊት አንድ አይነት ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።   

                                        በቅርቡ የተመረቀው የኦሮምያ ልዩ ኃይል በከፊል (ፎቶ =ፋና)
ጉዳያችን / Gudayachn
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።