ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, January 3, 2020

ኢቢሲ ከብርሃን ባንክ ጋር ፈጠረ የተባለው ስምምነት መንግስትን የሚያሳማ እና በባንኮች መካከል ያለውን ጤናማ ውድድር የሚያበላሽ እንግዳ ስምምነት ነው።

የኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዋና መስርያ ቤት 

ጉዳያችን / Gudayachn
ታህሳስ 24/2012 ዓም (ጃንዋሪ 3/2020 ዓም)
===============
ዛሬ ዓርብ ታሕሳስ 24/2012 ዓም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዜና ላይ ኢቢሲ (የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን) ከብርሃን  ባንክ ጋር  ስምምነት ፈጠሩ የሚለው ዜና ሲጀምር እንዲህ በማለት ይጀምራል -
'' የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ብርሃን ባንክ የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል'' ካለ በኃላ ዜናው በመቀጠል ''የጠበቀ ግንኙነቱን ለማጠናከር የመግባብያ ስምምነት ተፈራርመዋል'' ይላል ዜናው። ዜናው ላይ የብርሃን ባንክ ባለስልጣናት እና የኢቢሲ ኃላፊዎች ሳቅ በሳቅ ሆነው ስለምን እንደተዋዋሉ ሳይነግሩን ተስማሙ የሚለው ደጋግሞ ሲነገር በዜናው ላይ ይታያል።

የኢቢሲ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር  ንጉሴ  ምትኩ በእዚሁ በስምምነቱ  ዜና  ላይ ብርሃን ባንክን ሲገልጡ ''ባጭር ጊዜ ተመስርቶ ስኬታማ እንደሆነ እኔም በነበረኝ ምልከታ ምስክር ለመሆን ችያለሁ ብዬ አስባለሁ'' ብለው ሲናገሩ  ዜናው ያሳያል።በሌላ በኩል የብርሃን ባንክ ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም መስፍን ''ከኢቢሲ ጋር ያደረግነው ስምምነት የብርሃን ባንክን ቪዝብሊቲ ከፍ የሚያደርግ ነው'' ብለዋል።

ስህተት 1 
ነፃ የውድድር ሜዳ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያሳያል 

የባንክ ኢንዱስትሪው በኢትዮያ ከአስራ አምስት ያላነሱ ባንኮች የያዘ እና ውድድር ላይ የሚገኝ ነው።የግሎቹ ባንኮች እርስ በርስ ከፍተኛ ውድድር ላይ ናቸው።ለመንግስትም ተገቢውን ግብር ያስገባሉ።መንግስት ደግሞ በተቀበለው ግብር መልሶ የማኅበራዊ እና የመሰረተ ልማት አገልግሎት ይሰጣቸዋል።መንግስት ለሁሉም ባንኮች እኩል አገልግሎት ሊሰጥ ነው የሚገባው። መንግስት ማለት አንዱ እጁ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ነው። ኢቢሲ በተናጥል ከአንድ የግል ባንክ ጋር የዕድሜ ልክ የመስለ ስምምነት አደረገ ተብሎ መቅርቡ መንግስት በባንኮች ውድድር ውስጥ አንዱን ደግፎ የመቆም ያህል ያስቆጥረዋል።በዛሬው የስምምነት ዜና መግቢያ ላይ ኢቲቪ የብርሃን ባንክ እና ኢቲቪ አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል የሚል ዓረፍተ ነገር ተጠቅሟል።ምንድነው አብረው ሲሰሩ የቆዩት? በምን መስፈርት? ድንገት ተዋደዱ? የህዝብ ሀብት የሆነ ድርጅት እንደፈለገ ከፈለገው የግል ድርጅት ያውም ከፍተኛ ውድድር በሚታይበት ቁልፉ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ ከሆነ ከአንዱ ተወዳዳሪ ባንክ ጋር  በተናጥል አብሬ እየሰራሁ ነበር ሲል ምን ማለቱ ነው?ይህን እኔ አይደለሁም የምጠይቀው የውድድር ሕጉ እራሱ የሚጠይቀው ሞራላዊ ጥያቄ ነው።


ስህተት 2 
የመንግስት ሚድያ ሥራ አስኪያጅ ከተወዳዳሪ ባንኮች ውስጥ የሚያደንቀውና የማያደንቀውን ባንክ ሚድያውን ወክሎ መናገር የለበትም 

መንግስታዊ ድርጅቶች  ያውም ቁልፍ የሆነው ሁሉንም እኩል እንዲያገለግል የሚጠበቅበት የመንግስት ልሳን ኢቢሲ ሥራ አስኪያጅ ስለ አንዱ የግል ባንክ በምልከታ በሚል ከግል ባንኮች ውስጥ አንዱን ነጥለው ከላይ እንደተጠቀሰው ''ስኬታማ'' ነው የሚል ቃል መናገር የለባቸውም።እዚህ ላይ የብርሃን ባንክ ስኬታማ ነው አይደለም የሚል ክርክር እየገባሁ አይደለም።ኢቢሲ ማለት ያለበት በዘገባው ሚዛናዊ ዘገባ አቅርቦ ወይንም የባንኩ ባለስልጣን ያሉትን ጠቅሶ ማለት ይችላል።በምልከታ ግን ስኬታማ ነው ስለዚህ ስምምነት አደረግን ማለት ተገቢ አይደለም።በሁሉም ባንኮች ግብር የሚተዳዳር   ኢቢሲ አንዱን ነጥሎ በምልከታ ስኬታማ እንዴት ሊለው ይችላል? ይህ በራሱ የመንግስት ሚድያን ተጠቅሞ  ያልተከፈለ ማስታወቂያ ነው።የግል ስሜት እና ግንኙነት ሌላ ነገር ነው።የህዝብ ንብረትን እኩል ለሁሉም ተወዳዳሪ ባንኮች  ክፍት ማድረግ ሌላ ነገር ነው።


ስህተት 3
የመንግስት ሚድያ የአንዱ ባንክ የመታየት አቅም ከሌላው ጎልቶ እንዲወጣ የመስራት መብት የለውም 

ከዜናው ለመረዳት እንደሚቻለው ብርሃን ባንክ በእዚህ ስምምነት ተጠቅሞ እንደ የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጁ ገለጣ ባንኩ የበለጠ ''ቪዚብልቲውን'' (ጎልቶ የመታየት አቅሙን) ከፍ እንደሚያደርግ ተገልጧል።በመጀመርያ ደረጃ  ኢቢሲ በምን መስፈርት ተጠቅሞ ነው  ከሌሎች ባንኮች በተለየ ከብርሃን ጋር የተዋዋለው? በሥራ አስኪያጁ ምልከታ? ወይንስ በቦርድ አባላቱ ውሳኔ? ግልጥ አይደለም።መንግስታዊ የመገናኛ አውታር ያውም በመንግስታዊነቱም ሆነ በግዙፍነቱ ትልቁ ኢቢሲ ስምምነት ከማድረጉ በፊት ሌሎች ባንኮችን አወዳድሯል? ወይንስ ጨረታ አውጥቷል? ደግሞስ የሕዝብ ንብረት የሆነው  ኢቢሲ የህዝብ ሀብት የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዴት ይህንን ውል አላደረገም።ምናልባት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር  ይህንን ስምምነት ቢያደርግ መንግስታዊ ወይንም የህዝብ ሀብት ከመሆኑ አንፃር ይህ ጥያቄ አይነሳም ነበር። ብርሃን ባንክም ከግል ሚድያ ጋር ይህንን ስምምነት ቢያደርግ ጥያቄው አይነሳም።ምናልባት የግል ሚድያው ሥራ አስኪያጅ  ብርሃን ባንክን በምልከታዬ (ኦዲት ሪፖርቱን ሳይጠቅሱ) ስኬታማ ነው እያሉ ቢናገሩ ኖሮ ቅሬታ አያስነሳም ነበር። የህዝብ ሀብት ኢቢሲ የግል ስምምነት በሚመስል መልኩ ከተወዳዳሪ ባንኮች አንዱን ''ቪዚብልቲው'' ከፍ እንዲል ሊሰራ ነው የሚል ቀልድ መሰል  ንግግር  ባልሰማን ነበር።

ለማጠቃለል 

ከላይ ለማስረዳት እንደተሞክረው የባንኮች የውድድር ሜዳ ላይ መንግስታዊ ሚድያ ያውም ግዙፉ ሚድያ በምንም መስፈርት አንዱን ባንክ ነጥሎ አብሬው እሮጣለሁ ተወዳዳሪዎቹን እንዲቀድም እረዳዋለሁ መሰል ሥራ ውስጥ እንዲገባ የንግድ ሕጉም፣የመንግስት አሰራርም ሆነ ሞራላዊ ሁኔታዎች አይፈቅዱለትም።ቢያንስ ይህ ስምምነት ሲደረግ ኢቢሲ የሄደበት ለሁሉም ባንኮችም ሆነ ሚድያ ግልጥ የሆነ ሂደት ካለ ያሳይ።ከእዚህ ውጪ ግን ምንም አይነት አሰራር ያለ አይመስለኝም። በውድድር ዓለም ውስጥ የመንግስት ድርጅቶች በተለይ ቁልፍ የሆኑት ለምሳሌ መንግስታዊ ሚድያ (ሁሉንም ኢትዮጵያ የመሸፈን አቅም ስላላቸው)፣ የውሃ እና ፍሳሽ፣መብራት፣ቴሌ የመሳሰሉት በውድድር ዓለም ባሉ የግል ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ካለምንም  ሕጋዊ ሂደት አንዱን እጅ ይዘው ከፍ ሊያደርጉ፣ሌላውን ደግሞ ችላ ሊሉ አይችሉም። እነኝህ መንግስታዊ አካላት ለሁሉም እኩል የማገልገል ግዴታ አለባቸው።ምክንያት - ከሁሉም በሚሰበሰብ ቀረጥ የሚተዳደሩ ናቸው እና መንግስትን ያሳሙታል።ይህንን ሁኔታ ከንግድ ሕጉ አንፃር እና ከመንግስታዊ ድርጅቶች መመርያ አንፃር ሌሎች አጣቅሰው ብዙ ሊሉበት እንደሚችል እገምታለሁ።


የመጨረሻው መጨረሻ ግን ለብዙ ዓመት በማኅበራዊ ሚድያ የጠየኩት EBC በእንግሊዝኛ ብቻ ሳይሆን በቴሌቭዥን ላይ ስፅፍ በአገሪቱ ፊደል ''ኢቢሲ'' ብሎ ይፃፍ የሚለውን ጥያቄ ለአንድ ሺኛ ጊዜ እጠይቃለሁ።ይህ ለመላው ዓለም የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳይ ከልጆች ሳይቀር አዕምሮ የማይጠፋ ያደርገዋል።ፊደል እንደሌለን የእንግሊዝኛ ፊደል ብቻ ማድረግ ያለማወቅ ደረጃ ነው።በአማርኛ እያወሩ ኢቢሲ ብሎ አለመፃፍ ጤነኛ አስተሳሰብ አይደለም።አንድ ቀንም ይህ ጉዳይ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ የሚከፈትበት ጉዳይ መሆን አለበት።




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...