ጉዳያችን /Gudayachn
ጥር 2/2012 ዓም (ጃንዋሪ 11/2020 ዓም)
- በምዕራብ ወለጋ፣ መንግስት ከሸማቂዎች ጋር ግልጥ ጦርነት ላይ ነው። መንግስት በእዚሁ አካባቢ በሚያደርገው ሽፍቶችን የማጥራት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።በቅርቡ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ይመለሳል። ለእዚህም በሽፍቶቹ የተጎዳው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር እያደረገልን ነው - አቶ ታዬ ደንዳበኦሮምያ የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ
ከሳምንታት በፊት በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል የምትገኘው የደንቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በዩንቨርስቲው በተነሳ ግጭት ሳቢያ ተማሪው በራሱ ወደ ትውልድ ቀዬው ለመሄድ ሲነሳ የተወሰኑ የዓማራ ክልል ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ በጋምቤላ በኩል አድርገው ለመምጣት በትራንስፖርት ተሳፍረው ጉዞ ይጀምራሉ።ሆኖም ያሰቡት ሳይደርሱ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል 'ሱድ' የምትባል ቦታ ሲደርሱ ጎረምሶች መኪናውን አስቁመው 18 ተማሪዎችን ማለትም 14 ሴቶች እና 4 ወንዶችን አግተው ወደ ጫካ ይገባሉ።ከእነኝህ ውስጥ ተማሪ አስምራ ሹሜ የተባለችው ወጣት በድንገት አምልጣ በብዙ ፈተና እና መከራ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ዘመን ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር ተቀላቅላለች።
ተማሪ አስምራ ሹሜ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል እንዲህ ብላለች -
''አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ 'የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት' ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።
'ከታየሁ እኔም እገደላለሁ' ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታታላለን' አሉኝ።
ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም 'በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከልክሉናል' ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ 'የእነርሱ ነው ያዥው' ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። 'እንከታተላለን' ነው ያሉኝ።ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን 'መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ' እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።"
ቢቢሲ የታገቱት ተማሪዎች ወላጆችን አነጋግሮ እንደገለጠው የአንዷ ወላጅ ልጃቸው ከታገተች ከሰሙ ከአራት ሳምንታት በላይ መሆኑን እንደገልጡ ዘግቧል።ይህ በእንዲህ እያለ ጉዳዩን አስመልክቶ የኦሮምያ የፀጥታ ባለስልጣናት በቂ ምላሽ እንዳልሰጡ ነው የተሰማው። ከአንዲት ተማሪ የስልክ ንግግር በመነሳት የአጋቾቹ ዋና ፍላጎት አስመልክቶ ቢቢሲ እንደዘገበው አጋቾቹ ሕዝብ ልጆቻችንን ብሎ መንግስትን ሲያስጨንቅ መንግስት ከእኛ ጋር እንዲደራደር ያስገድደዋል የሚል ስሌት እንዳላቸው ይጠቅሳል።ጉዳዩ ግን ብሄራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ይሻል።የእገታ ጉዳይ የሽብር ተግባር ነው።ሽብር ደግሞ የአገር ውስጥ ሳይሆን አካባቢያዊም፣ዓለም አቀፋዊም የጋራ ችግር ነው።
በሌላ በኩል በምዕራብ ወለጋ፣ መንግስት ሕዝቡን ሲዘርፉ እና ሲያሰቃዩ ከነበሩ ሸማቂዎች ጋር ጋር ግልጥ ጦርነት ላይ እንዳለ በኦሮምያ የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ታዬ ደንዳ ለቪኦኤ ትናንት ጥር 1/2012 ዓም ገልጠዋል።እንደ እርሳቸው ገለጣ በምዕራብ ወለጋ መንግስት በሸማቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ያለው ሁሉም የሰላማዊ መንገድ ከተሞከረ በኃላ መሆኑን ካብራሩ በኃላ እስከዛሬ ሰላማዊውን ሕዝብ ሲጎዱ ምንም ያላለ ዛሬ በሽፍታ ላይ እርምጃ ሲወሰድ የሚናገር አንዳንድ ማኅበራዊ ሚድያ ዘገባዎች ትክክል አይደሉም ብለዋል።አቶ ታዬ ደንዳ በእዚሁ ማብራርያ መንግስት በእዚሁ አካባቢ በሚያደርገው ሽፍቶችን የማጥራት ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለና በቅርቡ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ይመለሳል ለእዚህም በሽፍቶቹ የተጎዳው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር እያደረገልን ነው ብለዋል።
ዘግይቶ የደረሰን ዜና
ዘግይቶ የደረሰን ዜና
ታግተው የነበሩ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስታወቀ
********************
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
********************
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ መለቀቃቸውን አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቀሪ 6 ተማሪዎች በእገታ ላይ መሆናቸውን በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠቱን ተናግረዋል ።
ምንጭ = የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment