ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, January 29, 2020

የጎሳቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ከሚሮጡ እና ስልታዊ የእርስ በርስ መመጋገብ ከሚያሳዩት የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ የፅንፍ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንታደጋት!

ኢትዮጵያውያን እጃችንን በእጃችን እንዳንቆርጥ ልንጠነቀቅ ይገባል።

ጉዳያችን/ Gudayachn
ጥር 20/2012 ዓም (ጃንዋሪ 29/2020 ዓም)

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመር ዙርያ ግርግር ለመፍጠር ሲሞከር ይታያል።ግርግር ለመፍጠር የሚሞክሩት ደግሞ የዳበረ የፖለቲካ ዕውቀትም ሆነ ቅንነት የራቃቸው ሁሉ  መሆናቸው ነው አስቀያሚው መልኩ።መጪው የፖለቲካ መድረክ በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ ማዕከላዊ መንግስትን ሳይቀር ሥራ አላሰራ የሚል ጉዳይ ነው።አጀንዳዎች በየቀኑ የፈለፈላሉ፣የዋሁን ሕዝብ ለመቀስቀስ ይሞከራል።የመጨረሻ ግቡ ግን ጥቂቶች በጀርባ የሸረቡትን ሴራ ወደ መሃል አምጥቶ የእራሱን ጎሳ የበላይ የሚሆንበት መንገድ ላይ ብቻ የማውጠንጠን ብቸኛ ግብ ያለው እኩይ ሥራ ሆኖ ይታያል።የጎሳ ፖለቲከኞች  ይህንን ፖለቲካቸውን የሚጠቀሙት ለስልት እስከ ቤተ መንግስት መግቢያ ድረስ ብቻ እንጂ፣አይደለም ጎሳቸውን የራሳቸውን ቤተሰብ በስልጣን ከመጣባቸው  በጎሳቸው ስም እየፎከሩ ከማረድ የማይመለሱ ለመሆናቸው ብዙ ሺህ ጊዜ ቢነገርም የገባው ያለ አይመስልም።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ግርግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ሁሉ ዋና ግባቸው የግላቸው የስልጣን  ጥም እና ሀብት የማካበት ብቻ እና ብቻ ግብ ነው። ከእዚህ ውጪ አንዳች ነገር አይፈይዱም።ለእዚህ ደግሞ ማስረጃው በዓለማችን ጎሳቸውን እና የዘር ሃረጋቸውን እየመዘዙ ዓለምን በደም የዘፈቁት የእነናዚ እና ፋሺሽትን ታሪክ መመልከት ነው።ሁሉም ሲነሱ ለስልትነት እና ወደ የሚለኩሱት  ጦርነት የሚገባ ሕዝብ ለማግኘት በጎሳ ስም ጠሩት።ቀጥለው ግን  በስሙ ወጥተው ቆልቁል ማየት ከጀመሩ በኃላ  መልሰው ያረዱት የራሳቸው ጎሳችን ያሉትን ነው።

በመጀመርያ ደረጃ በትክክለኛ  ለሕዝብ ቆምያለሁ የሚል ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ የሚነሳው  በውስጡ ከሚፈጠር የጠነከረ ህዝብን የመውደድ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር እና ለሕዝብ አብዝቶ የማሰብ ሰውነት የታደለ ሰው ደግሞ ሊያስብ የሚገባው ቢያንስ እንደ አገር ከሚኖርበት አገሬ ለሚለው ሕዝብ በሙሉ ሳይለያይ ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ ለሰው ዘር በሙሉ ነው። የእዚህ ዓይነት ሰውነት ሳይላበሱ ለመንደሬ ቆምያለሁ ሌላውን ደግሞ በመርገጥ የበላይ ስሆን የፖለቲካ ትግሉ በድል ተደመደመ ማለት ነው ብለው የሚያስቡ ደካሞች የመጨረሻ መጨረሻ እንደሌለው አለማወቃቸው በራሱ አስገራሚ ነው።

የኢትዮጵይ የፖለቲካ ሜዳ ለማጥለቅለቅ የሚፈልጉ  የጎሳ አቀንቃኞች ሁሉ ስለ ጎሳ እኩልነት ሳይሆን የእነርሱ ጎሳ የበላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ሰላም እንደምትሆን ይሰብኩናል። እነርሱ ልቦና ውስጥ የበቀለው  የጎሳ አስተሳሰብ እንዴት በሌላው ላይ እንደሚሰርፅ ሲያወጡ እና ሲያወርዱ መሽቶ ይነጋል።በኢትዮጵያ የአንዱ ጎሳ ሰው ተነስቶ አንዱን ሲበድል ሊታይ ይችላል።ብዙዎችም ይህ ደርሶባቸዋል። ላለፉት 27 ዓመታትም ይህ አይኑን አፍጥጦ ታይቷል።ችግሩ አለ።አሁንም በብሮክራሲ ደረጃ የፅንፍ ጎሰኞች በመግባታቸው ይታያል። ይህ ማለት ግን አጠቃላይ የአንድ ጎሳ ሕዝብ ሁሉ አስተሳሰብ አይደለም። ይህ ችግር ደግሞ የሚፈታው ለችግሩ ተቃራኒ የአብሮነት ፖለቲካ በማራመድ እንጂ ተመሳሳይ የጥላቻ ፖለቲካ በማራመድ አይፈታም። 

ብዙ ሰው  የበለጠ ተበደልኩ ባይ ነው።ብዙ ሰው ወደ መሃል መጥቶ የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ውጪ መጨራረስ እንደሆነ የመረዳት አቅሙ ደክሟል። ስለሆነም የጎሳውን የበላይነት በማረጋገጥ ብቻ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያመጣ ይመስለዋል።ከመቶ ዓመት በላይ ያሳለፈው  የፈረንሳይ አብዮት ያነሳቸው መሰረታዊ የሰው ልጅ ጥያቄዎች ውስጥ  -እኩልነት የሚለው አስተሳሰብ ተንቆ የእኔ ጎሳ የበላይ እንዲሆን መታገል አለብኝ በሚል አስተሳሰብ የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ፅንፈኞች  በየፊናቸው ማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ወደ መሃል ይምጣ እና በርሱ መመራት አለብን የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አስተሳሰብም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ላይ ዘመቻ መክፈት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። ይህንን የሚያደርጉ አካላት ያልተረዱት ጉዳያ ቢኖር የጎሳ ፖለቲካ ከእዚህ በላይ ከተለጠጠ እሳቱ ማቆምያ እንደሌለው ነው።ለነገሩ እሳቱ ሲነሳ እነርሱ ለክረምት ሽርሽር አውሮፓ እና አሜሪካ ናቸው።

 የእነኝህ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚፈጠር አንድ ግርግር በጋራ ለመፍጠር ስልታዊ መመጋገብ ማሳየታቸው ነው።ሁሉም ተነስተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ወይንም በኢትዮጵያ ጉዳይ የአንድነት ፖለቲካ የሚያራምዱት ላይ ዘመቻ ለመክፈት የሚፈጥሩት ግንባር ነው።በእዚህም የተለያዩ አጀንዳዎች በመፈልፈል እና ያንን በማራገብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት የምያገነቅኑ ኃይሎችን ሥራ እንዳይሰሩ ማወክ ነው።የማዋከቡን ሥራ ደግሞ በማድረግ ረብ የለሽ የህዝብ ጆሮ ለመሳብ ይጠቀሙበታል።በእዚህም ዋና ግባቸውን ከህዝብ ደብቀው ጉዳያቸው ፊት ለፊት የሚታየውን  ወቅታዊ አጀንዳ ላይ የእነርሱ ወገን የሚጠቅምበት የፖለቲካ አጀንዳ ሽምያ ላይ በየሚድያቸው ሲያራግቡ መዋል  ስራቸው ሆኗል።በእዚህም ህዝብን ከመንግስት ጋር ማጣላት፣በመንግስት ውስጥ የተሰገሰጉ የእነርሱ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችን ሽፋን መስጠት እና የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠበቅ እና ከጎሳ ፖለቲካ የፀዳ አስተሳሰብ የያዙትን በምያነሱት አጀንዳ እያስታከኩ  መምታት ስራቸው ሆኗል። ይህንን እኩይ ተግባር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ሁል ጊዜ ግርግር በመፍጠር የህዝብ ስነ ልቦና እንዳይረጋጋ ማድረግ አንዱ እና ተቀዳሚ ስራቸው ሆኗል።

ለማጠቃለል ወቅቱ የሰከነ አስተሳሰብ፣የኢትዮጵያን መጪ ዕድል ለማጨለም የሚንቀሳቀሰውን በዓማራ፣በኦሮሞ እና በትግራይ ውስጥ የሚታየውን  የእኔ ጎሳ የበላይ ይሁን መሰል እንቅስቃሴ በአንክሮ መመልከት የሚገባበት ጊዜ ነው።በመሰረቱ የጎሳ ፖለቲካ የዲሞክራሲ ፀር ነው ።የጎሳ ፖለቲካ ምክንያታዊነት የሌለው እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ እና ብቸኛ አስተሳሰብ በሆነው የእኔ ጎሳ ከሆነ ፃድቅ፣የእገሌ ከሆነ ኃጢአተኛ እያለ የመፈረጅ፣የማሰብ፣የመመራመር እና የምክንያታዊነት ድሃ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ በልምምጥ እና በማግባባት ብቻ የማይገፋበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ማምረር፣መቃወም እና መታገል ያስፈልጋል።ይህንን የምቃወመው፣የሚታገለው እና የሚጠላው ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን ያኖራትም ይህ የአብዛኛው ሕዝብ ፖለቲካ የአንዱ በአንዱ ላይ የመጫን ሳይሆን የእኩልነት ጥያቄ ስለሆነ ነው። ይህ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ግራ የተጋባ እስኪመስል ድረስ ዝምታው አስጠቅቶታል። በዓማራ፣ኦሮሞ እና ትግራይ ውስጥ የመሸጉ የጎሳቸውን የበላይነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያን እናሳድጋለን ለሚሉ በሙሉ የምንላቸው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይሄውም እባካችሁ ኢትዮጵያ እጇን በእጇ እንድትቆርጥ አታድርጉ።ለእኩልነት እንጂ የጎሳችሁ የበላይነት እንዲሰራ በመስበክ አታደንቁሩን። ኢትዮጵያ የሁሉም እንድትሆን የሚሰሩ ኢንጂ   የጎሳቸው የበላይነት እንዲኖር ለሚሰብኩን የትኛውም ዓይነት አደረጃጀች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እጅን በእጅ ከመቁረጥ አይለይም።


የጥቁር  አልማዝ በጃኖ ባንድ 





ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: