ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, February 1, 2020

መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ የተለያዩ ''ሴናርዮዎች'' በሚል ርዕስ በኖርዌይ የኢትዮጵያውያን መድረክ አዘጋጅነት በኦስሎ የተደረገው ስብሰባ ይዘት


     ዶ/ር ተክሉ አባተ  


       ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥር 23/2012 ዓም (ፌብርዋሪ 1/2020 ዓም)

- ''በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባብዛኛው የሚታየው የጥቅም አክራሪነት እንጂ የብሔር አክራሪነት ማለት አይቻልም'' በካይሮ፣ግብፅ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ አሶሼት ፕሮፌሰር  ዶ/ር ተክሉ አባተ 

=======================
ዛሬ የካቲት 1/2012 ዓም በኦስሎ፣ኖርዌይ የሚገኘው የኢትዮጵያን የጋራ መድረክ በኦስሎ ''አንቲ ራሲስት'' የስብሰባ አዳራሽ መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ሴናርዮዎች በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መርሃግብር ላይ በስካይፕ ከካይሮ፣ግብፅ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ አሶሸት ፕሮፌሰር ተክሉ አባተ እና ከኖርዌይ የኢዜማ ድጋፍ ሰጪ ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

በመጀመርያ መጪውን ምርጫ አስመልክተው ዘርዘር ባለ መልክ ሃሳባቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ተክሉ አባተ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ መሰረት  ሰኔ 4 ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ስማቸው ቅደም ተከተል ዕጣ ያወጣሉ፣ነሐሴ 10 የምርጫ ማድረጊያ ቀን ይሆናል፣ነሐሴ 10 እና 11 ውጤት ይለጠፋል፣ነሐሴ 11-15 በክልል ደረጃ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል፣ነሐሴ 11-20 አጠቃላይ የምርጫው ውጤት ይገለጣል ካሉ በኃላ አከራካሪ ጉዳዮች ያሏቸውን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል።

አከራካሪ ጉዳዮች 

በአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ በማንሳት በኢትዮጵያ ምርጫ መደረግ አለበት ወይንስ የለበትም? ብለው የሚጠይቁ መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ በመቀጠል እርሳቸው የሚያነሷቸውን ተጨባጭ ማስረጃዎች እንደሚከተለው  ዘርዝረዋል። እነርሱም -

1) ሰላማዊ እና የተሳካ ምርጫ ለማድረግ የሚያስቸግሩ ነባራዊ ሆነታዎች አሉ።ዛሬም ሕፃናት በሰሜን ጎንደር ታፍነው ተወስደው  አደጋ ደርሶባቸዋል፣ምዕራብ ወለጋ ብንወስድ ጦርነት አለ፣አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰው ወጥቶ ለመመለስ ስጋት ላይ ነው።

2)የጥቅም አክራሪነት ሰፍኗል።እኔ የብሔር አክራሪነት አልለውም።የጥቅም አክራሪነት ነው የተስፋፋው።ሰዎች የጥቅም ፍላጎታቸውን በብሄር አክራሪነት ለመሸፈን እየሞከሩ ነው። በአማራም በኦሮሞም ብንመለከት ያለው የጥቅም አክራሪነት ነው። ይህ የጥቅም አክራሪነት ደግሞ ለሽምግልናም አስቸጋሪ ነው።ስለሆነም ለምርጫው አንዱ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

3) የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ድረስ እንደፈለጉ ተዟዙረው ስብሰባ ማዘጋጀት አልቻሉም።ለምሳሌ በቅርቡ ኢዜማ በጎንደር እና በባሕርዳር ያደረጋቸው ስብሰባዎች ላይ የደረሱትን መመልከት ይቻላል። እነኝህን ስብሰባዎች የሚያውኩ ሰዎች ይህንን  የሚያደርጉ ሰዎች ለአማራ ሕዝብ አስበው  ነው ብዬ ማሰብ አልችልም የጥቅም ጉዳይ ነው።

4) በርግጥ የተወሰኑ በብሄር ስሜት የተነሱ አሉ።ሁሉም በጥቅም ብቻ ነው ማለት አይቻልም።እነኝህ ደግሞ ተጠቂ ነን የሚል ስሜት ያላቸው ግን የራሳቸውን ብሔር በሌላው ላይ ለመጫን የሚፈልጉ ናቸው።በተለይ በትምህርት ደረጃ ዝቅ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ብሔርህ ተነካ በሚል ይቀሰቅሱታል።

5)የፓርቲዎች መብዛት ሌላው ችግር ነው።በአሁኑ ጊዜ ከ110 በላይ ፓርቲዎች አሉ።አብዛኛው ብሔር ተኮር ነው። ጥቂት በኢትዮጵያ ላይ የሚሰሩ አሉ። ይህ ማለት የምርጫ ቅስቀሳውን ብቻ ስናስብ በራሱ ጉድዩን አስፈሪ (''ናይት ሜር'') ያደርገዋል። ካሉ በኃላ ዶ/ር ተክሉ ምርጫው እነኝህን ተግዳሮቶች አልፎ ምርጫው ጊዜ ላይ ቢደርስ የሚከተሉትን ''ሰነርዮዎች'' ማስቀመጥ እንደሚቻል ዘርዝረዋል።

ምርጫው ከላይ የተገለፁትን ተግዳሮቶች አልፎ መደረግ ደረጃ ቢደርስ

1) ታዛቢዎችን የማዋከብ እና የማስፈራራት ሥራ በብሄር ድርጅት ደጋፊዎች አይኖርም ማለት አይቻልም።በቅርቡ በሲዳማ የክልል ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ላይ በታዛቢዎች ላይ የተደረገውን እንደምሳሌ ማስታወስ ይቻላል።

2) የክልል ፓርቲዎች ህዝቡ የክልሉን ፓርቲ ብቻ እንዲመርጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕዝቡን ሊያስገድዱት ይችላሉ።

3) የምርጫው ቆጠራ በራሱ ደረጃውን በጠበቀ መልክ ላይደረግ የመቻል ዕድል ሊገጥመው ይችላል።

4) ከሁሉ የከፋው ደግሞ ምርጫው ውጤት ሲነገር ውጤቱን አንቀበልም የሚሉ ክፍሎች ሊነሱ ይችላሉ።

5) በምርጫው ውጤት ብሔር ተኮር ድርጅቶች ሊያሸንፉ ይችላሉ። ይህ በራሱ የሚፈጥረው የፖለቲካ ውጥረት ይኖራል።ምክንያቱም የክልል መንግሥታት  ከአሁኑ በባሰ የመጠንከር ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል።ይህ ማለት የማዕከላዊ መንግስትን ስልጣን በባሰ መልኩ ይሸረሽራል። ምናልባት በአዲስ አበባ ደረጃ ካየን በቀዳሚነት ኢዜማ እና ባልደራስ በከፍተኛ ደረጃ  ፉክክር የሚያሳዩበት ቦታ ሊሆን ይቻላል።በሶስተኛ ደረጃ ብልፅግና ፓርቲ ሊከተል ይችላል።
እዚህ ላይ በክልል ደረጃ የብሔር ድርጅቶች አብላጫውን ያዙ ማለት አራት ኪሎ ሲመጡ የሚኖረውን የእርስ በርስ መገፋፋት አስቡት።ምክንያቱም አሁን የሚመጡት የህዝብ ድምፅ ይዘናል በሚል ስለሆነ ከፍተኛ መፈታተግ ይኖራል ይህ በራሱ ለአገር የሚፈጥረው ጉዳት አለ ያሉት ዶ/ር ተክሉ ምርጫው በርግጥ ቢደረግም ሆነ ባይደረግ የራሱ የሆነ አደጋ ''ሪስክ'' ሊኖረው ይችላል ካሉ በኃላ የምርጫው ሂደትም ሆነ እርሱን ተከትሎ የሚመጣው አሳሳቢ ጉዳይ መነሻ ያሏቸውን ጠቅሰዋል።

ከምርጫው ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ችግሮች መነሻ ምክንያቶች 

1) ፓርቲዎች ለሚናገሩት ንግግር ኃላፊነት መውሰድ አለመቻል እና ለተሳሳተ አነጋገራቸውም የሚጠይቃቸው አካል አለመኖሩ፣

2) የመንግስት ሕግ የማስከበር ፍላጎት እና አቅም (አንዳንዶች አቅም አለው የሚሉ አሉ ግን አቅሙን እስካሁን አላሳየንም) በበቂ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ አለማሳየቱ፣

3)ፈታኝ የኑሮ ውድነት፣ሥራ አጥ ወጣት መብዛቱ፣ይህ በራሱ ጀብደኞች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።በቀላል ብር የሚደለሉ እና ለብጥብጥ  የሚገዙ ወጣቶች መብዛት አስከትሏል።

4) በአሁኑ ጊዜ ያለው ወጣት በዘመነ ህወሓት የኖረው ወጣት በራሱ በከፍተኛ ደረጃ የሞራል ድቀት ያደገ ወጣት መሆኑ፣

5) የህዝቡ የፖለቲካ ንቃት ደረጃ አለማደግ።አብዛኛው ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚፈልግ ቢሆንም 5% የማይሆኑ ጥቂቶች የሚፈጥሩት የነውጥ ሥራ ብዙሃኑ በቀላሉ እንዲጠቃ አድርጎታል ካሉ በኃላ ዶ/ር ተክሉ ምን አደረግ አለበት? የሚል ጥይቄ አንስተው የሚከተለውን የመፍትሄ ነጥቦች ዘርዝረዋል።

ምን ማድረግ ይገባል?

1) የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀነባበረ የስነ ልቦና ዘመቻ ተደርጎበታል።ስለሆነም አሁንም በቂ የፖለቲካ ንቃት ያስፈልገዋል።ስለሆነም ፖለቲካ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ለሕዝብ  አሁንም መንገር ይገባል።ፖለቲካ ማለት ከዳቦ ከውሃ ጋር የሚገናኝ እና ቀጥታ ተፅኖ የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑን ለሕዝብ በሚገባ መንገር ያስፈልጋል።ይህንንም በሚድያ፣በብሎግ ሳይቀር ለሕዝብ መንገር ያስፈልጋል።በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህንን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

2) የውይይት መድረኮችን ማብዛት ያስፈልጋል።ለምሳሌ ዛሬ የተሰበሰብንበት የኢትዮጵያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ የመሰሉ ድርጅቶች በሌሎች አገሮችም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

3) ኢትዮጵያውያን መድረኮችን ማብዛትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማጠናከር፣

4)መከባበር አስፈላጊ ነው።የብሔር ድርጅቶች የኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን፣የኢትዮጵያዊ ድርጅቶች የብሔር ድርጅቶችን መነቃቀፍ ሳይሆን የተሻለ ፖሊሲ ላይ  መሆናቸውን የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ለብሄር ድርጅቶች ማሳየት እና በብልጫ ልቆ መገኘት እንጂ በመናቅ እና በመዘላለፍ መሆን የለበትም፣

5) በውጭ የሚኖረው ማኅበረሰብ በምርጫው ላይ የራሱ ሚና እንዳለ ማመን ያስፈልጋል።ለምሳሌ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚደግፈውን የፖለቲካ ፓርቲ የማስተዋወቅ ድርሻውን መወጣት አለበት።በማለት በካይሮ፣ግብፅ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ አሶሸት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክሉ አባተ ገለጣቸውን አጠናቀዋል።

በመቀጠል ዶ/ር ሙሉ ዓለም አዳም በኖርዌይ የኢዜማ ድጋፍ ሰጪ ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ አባል በዶክተር ተክሉ የቀረበውን ማብራርያ አወድሰው በኢትዮጵያ የግለሰቦች ሚናንም በደንብ ማሰብ እንዳለብን አሳስበዋል።በእዚህም መሰረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያላቸውን ተፅኖ እንዳለ ሆኖ ምርጫውን በተመለከተ በእዚህ ሁኔታ እስከ ምርጫው  ድረስ በተለመደው አካሄድ ይሄዳል? ወይንስ እርሱ እንደሚለው ወደለመድነው የሥርዓት ማስከበር ሥራ ይገባል የሚለው ሁኔታዎችን ሊቀይራቸው እንደሚችል  ገልጠዋል። ከእዚህ በመቀጠል ዶ/ር ሙሉዓለም ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ስብስቦች መጠናከር እንዳለባቸው ገልጠው፣ ባለፈው ሳምንት በኦስሎ የተደረገው የኢትዮጵያዊነት ስብሰባ አንዱ ማሳያ እንደሆነ እና ኢትዮጵያውያን የበለጠ የእዚህ አይነት ስብስቦች ላይ በመገኘት አገራዊ ግዴታቸውን መወጣት አስፈላጊ መሆኑ ላይ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በስብሰባው መደምደምያ ላይ ከተሳታፊዎች የተነሳው ጥያቄ ኢትዮጵያ በእዚህ በብሄር ፖለቲካ በምትታመስበት ጊዜ የሃይማኖት አባቶች እና  መምህራን የት ናቸው? ለምን ሕዝብ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ አይመክሩም? ካህናትም እስከ ማውገዝ የሚደርስ ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ይህንንም አስመልክቶ ዶ/ር ተክሉ ሲመልሱ ችግሩ መኖሩን ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በአገርቤት ሕዝብ በብሄር መከፋፈል እንደሌለበት የሚመክሩ ለምሳሌ የ24 ሰዓት የቴሌቭዥን ስርጭት የጀመረው የማኅበረቅዱሳን ቴሌቭዥን በሰፊው የማስተማር ሥራ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በእዚህ የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ስብሰባ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቂ ባለመሆኑ የጋራ መድረኩ በዕለቱ የተያዘውን የጋራ መድረኩን ሪፖርት እና የአዳዲስ አስተባባሪዎች ምርጫ ለማድረግ አለመቻሉ ተገልጦ።ኢትዮጵያውያን ለወደፊቱም በጋራ ሻይ እና ቡና ሲጠጡ ለብቻቸው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመከራከር የእዚህ አይነቱን መድረክ ቢጠቀሙበት ጠቃሚ እንደሆነ ሃሳብ ተሰጥቶ የዕለቱ ስብሰባ ተፈፅሟል።



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: