ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, February 12, 2020

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ድምፅ የሚሰማባቸው ሰፈሮች ወቅታዊ ገፅታ

ጉዳያችን/ Gudayachn
የካቲት 5፣2012 ዓም (ፈብሯሪ 13/2020 ዓም)
================
በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ በሚከተሉት ርዕሶች ስር ፅሁፎች ያገኛሉ። እነርሱም - 

- የካቲት ወር በ1909 ዓም ፣
-  የካቲት ወር በ2012 ዓም፣
- ኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች፣
ብልፅግና  ፓርቲ የጀዋርን ቡድን የማቅጠን ሂደቱን  አጠናክሮ በግልጥም በስውርም ቀጥሏል፣
የብልፅግና ፓርቲ የገጠመው ትልቁ ተግዳሮት ፣
-  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ፀጥታ ወሳኝ ጉዳይ ነው፣
እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ሰውን የማያፍሩት የህወሓት አመራሮች ጉዳይ፣
ቴዲ አፍሮ በመጪው ሳምንት በመስቀል አደባባይ
 ===============================
የካቲት ወር በ1909 ዓም

በ1909 ዓም የዳግማዊ ምንሊክ ሴት ልጅ ንግስት ዘውዲቱ በየካቲት 4 ቀን ዘውድ ደፉ።በእዚሁ ዓመት ራስ ተፈሪ የንግስትቱ ሞግዚትና አልጋ ወራሽ እንዲሆኑ ተሾሙ።የንግሥት ዘውዲቱ ወደ ንግስና መምጣት በልጅ ኢያሱ ዘመን የነበረው ሹክቻ እና ብጥብጥ የሚቆምበት በመሆኑ ህዝቡ መደሰቱ ይነገራል።ከንግስት ዘውዲቱ ንግስና በኃላም የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በአንፃሩ የተረጋጋ መልክ ቢያሳይም በመሬት ባላባቱ የጦር አበጋዞች እና ትምህርት ቀመስ በሆኑ ወጣት የሹማምንቱ ልጆች መሃል ልዩነት ፈጥሮ ነበር።በወቅቱ በዘመናዊ ትምህርት የተሻሉ የነበሩት እና የውጪውን ዓለም በተለይ ስለ አውሮፓ ስልጣኔ የተሻለ ግንዛቤ የነበራቸው የቀድሞው ራስ ተፈሪ (የኃላው ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ) ይደገፉ የነበሩት በወቅቱ በነበሩ ጥቂት ዘመናዊ ትምህርት ቀመስ ወጣቶች  ሲሆኑ እነኝህ ወጣቶች ንግስት ዘውዲቱ ከነገሱም በኃላ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያስጨንቃቸው ነበር።

በወቅቱ የሚጨነቁት ወጣቶች ዋና ምክንያታቸው 20ኛው ክፍለዘመን ከመግባቱ ጋር በአውሮፓ የነበረውን እንቅስቃሴ ከሌላው ባላባት በተሻለ ማወቃቸው ነበር።በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ያለው የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አመጣጥ በአድዋ እንደነበረው ዓይነት አይደለም።በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ዓለም ተቀይሯል።ወቅቱን የመጠነ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የሚጠይቅ እና ለእዚህም የመሬት ባለቤት በመሆን እና አገሬን እወዳለሁ ብሎ በመፎከር ብቻ የሚገኝ ሳይሆን ዘመናዊ ትምህርት እንደሚያስፈልግ ያውቁ ስለነበር የንግሥት ዘውዲቱ መምጣት ብቻ ኢትዮጵያን የ20ኛውን ክ/ዘመንን እንደማያሻግራት ገብቷቸዋል።ስለሆነም ከንግስት ዘውዲቱ ንግስና ቀን ጀምሮ የራስ ተፈሪ ቡድን ራስ ተፈሪ ኢትዮጵያን እንዲመሩ ለማድረግ ጥረታቸውን ቀጠሉ።

የካቲት ወር በ2012 ዓም

የየካቲት ወር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድምፅ የሚሰማበት ወር ነው።2012 ዓም ከገባ ስድስተኛ ወር ሆነ።ከየካቲት ወር  ቀደም ብሎ በነበሩት ወራት ከሶስት ያላነሱ የአደባባይ የህዝብ በዓላት እና የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ስብሰባ የመንግስት የፀጥታ አካልንም ሆነ ሕዝብን በተወጠረ ስሜት የያዘ ጉዳይ ነበር።በተለይ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት የውስጥ ወይንም የውጭ ያልታወቀ ኃይል አንዳች አደጋ እንዳይፈጥር ማስጨነቁ አልቀረም።ይህንንም ተከትሎ ነው የዘንድሮው የመሪዎች ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ጥበቃው በሄሊኮፍተር በታገዙ ኮማንዶዎች ጭምር መሆኑን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በዜና ላይ ሳይቀር ሁሉ ሲያሳይ ነበር።ትልቁ ቁምነገር ግን ስብሰባው በሰላም ተፈፅሟል።

በዘንድሮው የካቲት ላይ ሆነን ከመቶ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ የተጨነቁት ወጣት ምሑራን ተመሳሳይ ስሜት ዛሬም ይታያል።ኢትዮጵያ በወሳኝ የ21ኛው ክ/ዘመን በብቃት የመሻገር እና ያለመሻገር ድልድይ ላይ ትገኛለች።ጊዜው ወሳኝ ለመሆኑ ከእኔ አባባል በላይ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፓርላማ ቀርበው እንደተናገሩት ''ጊዜው የሞትሽረት ወቅት'' መሆኑን ተናግረዋል።ይህ ማለት ከሩቅ ተመልካች ብቻ ሳይሆን እራሱ መንግስትም ያመነው ነው ማለት ነው።

ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች 

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ክ/ዘመን በርዕዮተ ዓለም ስትንገላታ ነው የኖረችው።የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በአገር ውስጥ ፖለቲካ ብቻ የተያዘ አይደለም።የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሂደት በጉጉት ከሚጠብቁት ውስጥ ዓለም ዓቀፍ ቱጃር ኩባንያዎች ናቸው።እነኝህ ኩባንያዎች ከቻይና ጋር በአፍሪካ ቅርምት የድርሻቸውን የገበያ ድርሻ ለመውሰድ በከፍተኛ ጉጉት ላይ ናቸው።የግሉን የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሳደግ ላይ ከቻይና እስከ ኒውዮርክ ያሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነው።ነገር ግን መጠኑ በምን ያህል ይሁን?መንግስት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ በምን ያህል ደረጃ ራሱን ከምጣኔ ሃብቱ ማርቅ አለበት? የግል ዘርፉንስ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው ወይንስ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቅድምይ ሊሰጣቸው የሚገባው? በሚሉት ዙርያ ጥያቄዎች መነሳታቸው  የሂደቱን ወሳኝ አፈፃፀም  ይወስነዋል።

የውጪ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጉረፍ በተለይ በቁልፉ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ለምሳሌ እንደ ባንክ፣ቴሌ እና የኃይል ማመንጫ ዘርፍ  መምጣት በራሱ መጥፎ ነው የሚል አመለካከት የመኖሩን ያህል መምጣታቸው ተገቢ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። ይህንን ክርክር ለጊዜው እናቆየው እና ጉዳዩ ግን በኢትዮጵያ መጪ ፖለቲካ ላይ የውጪው በተለይ የምዕራባውያን  የድጋፍ ዋና መሰረት ከጅኦ-ፖለቲካው በተጨማሪ ይሄው  የኢትዮጵያን የገበያ እና ጥሬ ዕቃ የማግኘት ጉጉት  የአገሪቱን መጪ ፖለቲካንም እንደሚወዘወዝ መገንዘብ ይገባል።

ብልፅግና  ፓርቲ የጀዋር ቡድንን የማቅጠን ሂደቱን  አጠናክሮ በግልጥም በስውርም ቀጥሏል።

ጀዋር በአንድ ቀጭን መንገድ መሄድ ጀምሮ መንገዱ መሃል ላይ ሲደርስ የኃላ በር በኃይል ሲዘጋ ዘወር ብሎ የተደናገጠ እና ያለው አማራጭ የፊቱ ምን እንደሚሆን ሳያውቅ የሚሄድ ሰው ይመስላል።ብዙ ስልት አውቃለሁ የሚል ብቻ ሳይሆን በአንድ ወቅት የዕድምያቸውን አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲንገላቱ የኖሩት አቶ አንዳርጋቸውን ስልት አለዎት ወይ? እያለ መመፃደቅ ደረጃ የደረሰው ጀዋር አሁን የአሜሪካ ዜግነቱን ለመተው አመልክቶ አዲስ አበባ ላይ ያንን ስንቀው የነበረውን ኢትዮጵያዊነት ስጡኝ እያለ እየተማፀነ ነው።

የምርጫ ቦርድም የካቲት 2/2012 ዓም ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳይ በፃፈው ደብዳቤ ጀዋር ዜግነት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁ ለማወቅ ተችሏል።በሌላ በኩል የጀዋር ቡድን እና የብልፅግና ቡድን በኦሮምያ ውስጥ ከፍተኛ ፍጥጫ ላይ መሆናቸው ግልጥ ሆኗል።በእዚህም ምክንያት ብልፅግና የአመራር ሚናውን ቢይዝም በወረዳ እና በዞን ደረጃ እንዲሁም በሌላው ቢሮክራሲ ውስጥ የጀዋር ቡድን የሚደግፉ ፅንፈኞች  ላይ ርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።ርምጃው በያዝነው ወር በበለጠ እንደሚጠናከር ይጠበቃል። በእዚህ ሂደት ብልፅግና ቀድሞ የሰራቸው ስራዎች የጀዋርን አከርካሪ ብቻ ሳይሆን ጥርሱን ያነቃነቀ ሥራ ሰርቷል።ይሄውም በታች ደረጃ ያሉትን የእርሱ አድናቂዎች በተለያየ የስራ እና የብድር ዕድል እየሰጡ ከጀዋር የመለየቱ ሂደት በብዙ ቦታ ተሳክቷል።ለምሳሌ በአምቦ ውጥረት ለመፍጠር የሚሞክሩ ወጣቶች ላይ መንግስት  በቀጥታ ማሰር መጀመሩ እና በትናንትናው እለትም በጅማ ጀዋር ሊያደርግ ያሰበው ስብሰባ ህዝቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ፎቶ ይዞ በመውጣቱ  ከፍተኛ መሸማቀቅ በጀዋር ላይ ደርሷል። ይህ ብቻ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከጅማ በተጨማሪ የቦረና እና ባሌ የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ልብም በድማቅ ንግግራቸው እና በልማት ፕሮጀክቶች መግዛት ችሏል።በእዚህም ጀዋር ከፍተኛ ክስራት ደርሶባታል። በእዚህ አይነት ጊዜ ላይ ጀዋር የለመዳት አንድ አይነት አካሄድ አለ።እርሱም እየተነነበት ያለውን የደጋፊ ኃይል ለማንቃት አንድ የማንቂያ እና የመሞከርያ ጉዳይ አንስቶ አንድ አይነት ግጭት ለመፍጠር እንደሚያስብ  እና አለሁ ለማለት እንደሚፈልግ የታወቀ ነው።ባለፈው ተከበብኩ የሚለውን ጉዳይ ለግጭት የተጠቀመበት ለእንደዚህ ዓይነት የመሞከር ሥራ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል።የጀዋርን መኖር እንደ መጠባበቂያ ኃይል የሚመለከቱት ሶስተኛ ረድፈኞች በሌላ በኩል የጀዋርን ደጋፊ መሳሳት ተከትለው ራሳቸውን ወደ መቅበር እያዘነበሉ እንደሆነ ይታያል።

የብልፅግና ፓርቲ የገጠመው ትልቁ ተግዳሮት

ኢህአዴግ በመፍረሱ (መፍረስ የሚለው በራሱ ፈርሷል ወይንስ? የሚል ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) የማይደሰት የለም።አንዱ እና ዋናው ጥላቻ አደረጃጀቱ በጎሳ ላይ መሆኑ ሲሆን ብልፅግና ቢያንስ እንደ ሱማሌ፣አፋር እና ቤንሻንጉል ያሉ ክልሎችን ፖሊሲ አውጪው አካል ውስጥ መግባታቸው እንጂ አሁንም ብልፅግና አደረጃጀቱ ከኢህአዴግ የጎሳ አደረጃጀት ለመውጣት የሚውተረተር  ምንልባት ከምርጫው በኃላ የሚሳካለት ሊሆን ይችላል።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን የብልፅግና ፓርቲ መሰረታዊ እና ትልቁ ተግዳሮት ከፍተኛ የአድርባይነት እና የአቅም ችግር ያለባቸውን የኢህአዴግ ካድሬ እና አመራር ይዞ ለመሄድ የሚያደርገው ደካማ አካሄድ ዋጋ እንዳያስከፍለው ያስፈራል።ብልፅግና በአዲስ አካሄድ ነው የምሄደው ካለ አቅም ያላቸው እና ከነበረው የአድርባይነት ባህል የለሉበት አዲስ የሰው ኃይል ማካተት እና ወደ አመራር ማምጣት እንጂ የነበረውን አድር ባይ ካድሬ አስራ ሰባት ቀን አይደለም ከዛ በላይ ቢሰለጥንም የተሻለ መንገድ ከማምጣት ይልቅ ወደ ኃላ እንዳይጎተት ያስፈራል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ፀጥታ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ ላይ የሚመጡ ለውጦች በሙሉ ማዕከል የሚያደርጉት የፖለቲካውን አውድ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ በተለይ የሃይማንቱን አውድም ጭምር ነው።በተለይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው የምከተላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዋናዋ የፖለቲካ ስሜት ማብረጃ ስትሆን ኖራለች።ይህ የደርግ መንግስትም ሆነ የህወሓት መራሹ መንግስት ሲመጣ  በስጋት የሚመለከታት  እና በሚፈልገው መልክ ለመቆጣጠር በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሰዋል።በአሁኑ ጊዜም የኦዴፓ እና የፅንፍ አካል ተጠግተው ከእዚህ በፊት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የማዳከም ሥራ ሲሰሩ የነበሩ እንደ እነ ቀሲስ በላይ ያሉትን በገንዘብ በማባበል ቤተክርስቲያንቱን ለመክፈል ከሁለት አካላት  ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑ ይሰማል።እነርሱም የመጀመርያው ከፅንፈኛው የጀዋር ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ከፅንፈኛ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ነው።ሁለቱም አካላት የምታከኩት ሃይምኖትን ይምሰል እንጂ ግቡ ፖለቲካዊ እና ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚደረግ ትልቁ አጀንዳ አካል ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ በመንግስት በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈፀመውን ጉዳይ በቀላሉ እየተመለከተው ነው።የደህንነት መስርያቤቱም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ለመክፈል የሚደረገው ሙከራ ትልቁ እና ቀዳሚው የኢትዮጵያ የፀጥታ ጉዳይ እንደሆነ ያሰቡበት አይመስልም። አጀንዳው አገርን የመክፈል እንጂ ቤተክርስቲያኗን ብቻ አይደለም።ከጀርባ የሚንቀሳቀሰው የበጀት እና ሃይማኖቱ የማይመለከታቸው የሰው ኃይል ሁሉ የሚያሳየው ጉዳዩ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን አገራዊም መሆኑን ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ድንገተኛ ስብሰባ ለመጪው ሰኞ ጠርቷል።የስብሰባው ዋና አጀንዳ በወቅታዊው በቤተክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳት ላይ እና በተለይ በኦሮምያ ቤተ ክህነት በሚል በቀሲስ በላይ የሚመራው ቡድን ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ ቀኖናዊ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ሰውን የማያፍሩት የህወሓት አመራሮች ጉዳይ  

በቅዱስ መፅሐፍ የሚገኝ አንድን ሰው ክርስቶስ እራሱ ሲጠቅሰው ''ሰውን የማያፍር፣እግዚአብሔርን የማይፈራ'' አንድ ሰው ነበር በማለት ነው።አንድ ሰው እግዚአብሔርን ባያፍር የሰፈሩን ሰዎች ያፍራል።ሰውን ባያፍር እግዚአብሔርን ይፈራል።ሲሆን ሁለቱም ቢሆን ጥሩ ነበር።የህወሓት አመራር ግን ሁለቱንም አጥተውታል። በከዘራ እና በሰው እየተደገፉ የሚሄዱት ፣አቶ ኃይለማርያም  በአንድ ወቅት ሲመራቸው ''እንደ ጆፌ አሞራ ቢሮዬ ቁጭ ብዬ ይዞረኛል'' ያሏቸው አቦይ ስብሐት ሲሆን አክሱም ፅዮን ተቀምጠው ካልሆነ ወደ አድዋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጥግ ይዘው ዳዊት በመድገሚያቸው  እና የህወሃትን አመራር በመምከርያቸው ጊዜ በአገር አማን መቀሌ ላይ ዛሬም ክላሽ ወጣቱን እያስያዙ ሲፎክሩ ማየት ያስገርማል። ኢትዮጵያን ከባንክ እስከ ግድብ ፕሮጀክት፣ከስኩአር ፕሮጀክት እስከ የኮንትሮባንድ መዳኒት ማስመታት ድረስ ከዝያም በላይ ከ11 ቢልዮን ዶላር በላይ ግጠው ወስደውባት እና ራቁቷን ቆማ ዛሬም ሰውን ሳያፍሩ፣እግዚአብሔርን ሳይፈሩ የካቲት 11 በዓል ለመጨፈር የህወሓት አመራር እየተዘጋጀ ነው።መቸም ረስተነው ይሆናል እንጂ ህወሓት በዓሏን ዱባይ ላይ ሁሉ ድል አድርጋ በድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሳ እንደነበር መቸም አይረሳም መቀሌ ላይ የውሃ ፕሮጀክቱ ገንዘብ ተበልቶ ዱባይ ላይ ውስኪ ሲወራረድ ነበር። በ21ኛው ክ/ዘመን ሕዝቡን ለስራ ከማስነሳት ይልቅ ወንድምህን ግደል ብሎ ያውም አንድ እግራቸው መቃብር በገባ አዛውንት ሲቀሰቀስ መመልከት ምንኛ ያሳዝናል።ህወሓት የካቲት 11 ለማክበር ምን ዓይነት ሞራል አላት? ቢያንስ ራሱ  ተራው የህወሓት ታጋዮች የተነሱበት የመነሻ መፈክርን የአሁኖቹ የህወሓት አመራሮች አንግበውታል? የኤፈርትን ገንዘብ በማን እጅ ነው? የትግራይ ከተሞች ንፁህ ውሃ ማግኘት ተስኗቸው የኤፈርት ብር ኝን በማን እጅ ነው? የካቲት 11 ሲከበር በየትኛው የሞራል ልዕልና ነው?

ቴዲ አፍሮ በመጪው ሳምንት በመስቀል አደባባይ  

ኪነ ጥበብ ኢትዮጵያዊነትን በተለይ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ትውልዱን ለማስተማር ምን ያህል ሰርቷል? ቢባል ይህንን ያህል የጎላ ሥራ አልታየም ማለቱ ይቀላል። የኢትዮጵያን ነገር ትቶ ያልተወው ቴዎድሮስ ካሳሁን ግን በትውልዱ ውስጥ ኢትዮጵያን ለማጉላት ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ቴዲ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በመስቀል አደባባይ ለሕዝብ ስራዎቹን ያቀርባል።በእዚህ ላይ ብዙ ባልልም፣ቴዲ የፍቅር ጉዞ ብሎ ገና በጧቱ ትውልዱን ለመምከር ሥራ ሲጀምር እነ ጀዋር በከፈቱበት የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ ተሰናክሎ ነበር።ዛሬ ጀዋር የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ስጡኝ እያለ በሚለምንበት ሰዓት ቴዲ ኢትዮጵያ የሚለውን ዜማ በመስቀል አደባባይ ጮክ ብሎ በመጪው ሳምንት መጨረሻ ያዜማል።ግሩም ነው። ኢትዮጵያ!

=====================//////================


የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ! ቪድዮ 




ጉዳያችን / Gudayachn



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...