ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, December 16, 2019

የኢትዮጵያ የመንግስት ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዜና ይዘት ስብጥር ጉዳይ ካልተስተካከለ ለአገር አንድነት አደጋ አለው (ጉዳያችን ሃሳብ)

ጉዳያችን / Gudayachn
ታኅሳስ 6/2012 ዓም (ዴሰምበር 16/2019 ዓም)

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ላይ የራሳቸውን አሻራ በአጭር እና በረጅም ጊዜ ማስቀመጣቸው የማይካድ ሀቅ ነው።ጥያቄው ግን የመገናኛ ብዙሃኑ ተፅኖ በምን ያህል መጠን እየሄደ ነው? ተፅኖው አዎንታዊ ነው ወይንስ አዎንታዊ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ከስር ከስር እየተከታተለ የሚያጠና አካል አለመኖሩ ጉዳት አለው።የሚከታተለ እና ሪፖርቱን ለሕዝብ የሚያቀርብ አካል አለመኖሩ ግን የመገናኛ ብዙኃኑን አዎንታውም ሆነ አሉታዊ ተፅኖ ከመፍጠር ግን የሚገታቸው አይደለም። እዚህ ላይ መንግሥታዊው የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲን አልዘነጋሁትም።ይህ ድርጅት ግን ብዙውን ጊዜ ከፖሊሲ እና መመርያ አንፃር የመገናኛ ብዙሃንን ከመከታተል ባለፈ ጠለቅ ያለ ጥናት አስጠንቶ ለሕዝብ ሲያቀርብ አልገጠመኝም።

በአሁኑ ወቅት ያለው ዜና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ምን ይመስላል?


የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከ2010 ዓም የኢህአዴግ የለውጥ ጅማሬ በፊት ከነበሩበት አቀራረብ በብዙ ተቀይረዋል።ከተቀየሩበት መንገድ አንዱ በተቻለ የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል ይነካል ያሉትን ዜና ለማካተት ጥረት አለ።ለምሳሌ በቀድሞ ጊዜ ከነበረው የደረቀ ፕሮፓጋንዳ አሁን በቴክኒክም ሆነ በአቀራረ የተሻለ ሁኔታ አለ።ለምሳሌ ቀድሞ ከአራት ኪሎ ብቻ ለሚወጡ  ምናልባት የፓርላማውን መክፈቻ ብቻ ያውም ከስንት አንዴ በመንግስት ከታዘዙ ብቻ የቀጥታ ስርጭት ይሸፍኑ የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን አሁን በበርካታ ክንውኖች ላይ የቀጥታ ስርጭት ያሳያሉ።በሌላ በኩል የዜና ዝግጅቶች በተመሳሳይ ሰዓት በቀጥታ በማኅበራዊ ሚድያ መታየታቸው እና በዩቱብ መጫናቸው ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ግን ካለምንም መቆራረጥ እና በዕለቱ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ አለ።ይህም ሆኖ ግን የዜና ሽፋኞቹ  በክልል የታጠሩ እና አንዱ ስለሌላው በሚገባ እንዲያውቅ የሚያደርግ አይደለም።


 የኢትዮጵያ የመንግስት ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዜና ይዘት ስብጥር ጉዳይ ካልተስተካከለ ለአገር አንድነት አደጋ አለው

በእዚህ አነስተኛ ፅሁፍ ለማንሳት የምሞክረው  ዋናው ጉዳይ የመንግስት ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዜና ይዘት መላው ኢትዮጵያን የካለለ አለመሆኑ በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ የሚፈጥረው አደገኛ የመለያየት ጥፋት ይኖራል።ለእዚህ መነሻዬ የተጠና መረጃ ኖሮኝ አይደለም።ነገር ከራሴ ምልከታ ነው።ምልከታው ግን ትክክል እንደሆነ እና የአደጋው ውጤት በራሱ ከገመትኩትም በላይ ሊሆን ይችላል።

የዜና ስብጥሩ ችግሩ እና መፍትሄው 


ስለአንድ የጋራ አገር የተለያየ መረጃ የደረሰው ትውልድ ነገ ይጣላል።ለዛሬው  የወጣቶች በዩንቨርስቲ ግቢ ውስጥ ፀብ አንዱ መነሻ ትናንት የተሰጠው የመገናኛ ብዙሃን በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ መረጃ መሰጠቱ ነው።በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በአማርኛ፣ኦሮምኛ፣ትግርኛ፣ሱማልኛ፣አፋርኛ የሚተላለፉ ዜና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ይደርሰዋል? ለምሳሌ ሁሉም ዜና በተለያየ ልሳን ሲያቀርቡ ቀዳሚ የሚያደርጉት በመንግስት ቀዳሚ የሆነውን ዜና ለምሳሌ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወይንም የተወካዮች ምክርቤት የተደረገ እና ሌላም ዜና በተመሳሳይ መልክ ያቀርባሉ።ይህ ተገቢ ነው የዕለቱ ቀዳሚ አጀንዳ ለሁሉም ልሳን ዜና መቅረቡ ተገቢ ነው። 


የመረጃ ክፍተቱ የሚመጣው ግን እዚህ ላይ አይደለም።ወደ ክልሎቹ ስመጣ ነው ችግሩ። የአማርኛ ልሳን ዜና ላይ ስለ አዲስ አበባ እና ከክልሎችም በጣም ተመርጠው የጎሉ የተባሉት ይቀርባሉ።በኦሮምኛ ልሳን የሚነበበው ደግሞ በቀዳሚ የመንግስት የዕለቱን ዜና ካወራ በኃላ በዝርዝር ወደ ኦሮምያ ክልል ያሉ ዜናዎች ያወራል። የትግርኛውም፣የሱማለውም ሆነ የአፋሩ ተመሳሳይ እንደ አማርኛው፣ኦሮምኛው እና ትግርኛው በዝርዝር ስለክልላቸው የሚዘግቡትን ያህል የአማርኛው ስለ አዲስ አበባ ያለውን ዝርዝር ለኦሮምኛው ልሳን አድማጭ አይነግሩትም፣የአማርኛው ዜና ላይም በዕለቱ አምቦ ከተማ ምን እንደተደረገ ከኦሮምኛው ወስዶ ለአማርኛ ልሳን ሰሚው አያወራም።ሁሉም ላይ የሚታየው ችግር ይህ ነው።ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት አንዳቸው ከአንዳቸው በእየእለቱ ዜና አይቀያየሩም።ስለ ኦሮምያ ክልል መረጃ ለማግኘት ከአማርኛው ዜና አጠናቃሪ በተሻለ የኦሮምኛ ክፍሉ የልሳኑ ተናጋሪ  በመሆኑ የበለጠ ዝርዝር መረጃ የማግኘት ዕድል አለው።በሌላውም እንዲሁ ነው። ሁሉም በየራሱ ልሳን ያጠናቀረውን ዜና ያቀርባል እንጂ የሌላውን ዝርዝር ገብቶበት ለሌላው አይነግረውም።በእዚህም አዲስ አበቤ በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ስለምትገኘው አዳማ (ናዝሬት) መረጃ ያጥረዋል።የአዳማ ነዋሪም ስለ ባህርዳር ለማወቅ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ልያስስ ነው ለእዛውም የልሳን ማወቅ እና አለማወቅ ካልገደበው። በጠገላብጦሽም ብናየው ተመሳሳይ ነው። 


ይህ ጉዳይ ደግሞ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት በአንድ አገር በሚኖር ሕዝብ መሃከል ፈጥሯል።ይህ የመረጃ ክፍተት ደግሞ ፖለቲካውን፣ማኅበራዊ  ኑሮውን እና ምጣኔ ሃብቱን ሳይቀር በአጭር እና በረጅም ጊዜ ይጎዳዋል።ጉዳቱ ደግሞ በአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን በረጅም ጊዜ አገር የሚለያይ እና የተለያየ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ የመፍጠር አደጋ አለው።

 የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዋናውን ብሔራዊ ዜና በጋራ ካዘጋጁ በኃላ የአማርኛው ልሳን ከኦሮምኛው እና ትግርኛው ልሳን ያሉትን ዜናዎች  አስተርጉሞ በዝርዝር ስለ ኦሮምያ ክልል ትግራይ ክልል እና ሌሎችም ያሉትን ዝርዝር ጉዳዮች በዜና እንዲያቀርብ እንፈልጋለን። የአፋር፣የሱማለውም ሆነ የሌላው እንዲሁ የአማርኛ ዜናዎች የያዙትን የዕለቱን ይዘት  በዝርዝር ተርጉመው ለአድማጮቻቸው ማስደመጥ አለባቸው።ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው።ባህርዳር ያለው ስለ ደምቢዶሎ ውሎ ማወቅ ይፈልጋል።አሳይታ ያለው ስለሞያሌ ውሎ ማወቅ ይፈልጋል።አዲስ አበቤ ስለ ዶሎ መና ያለው የአንዲት መንደር መንገድ ጠረጋ ዜናም ቢሆን መስማት ይፈልጋል።ከዜናው ትንሽነት እና ትልቅነት አይደለም ጉዳዩ። ሕዝብ የሚተነትንበት የራሱ አይን አለው።አንዱ ስለአንዱ በዝርዝር ካወቀ ችግሩንም ሆነ ጉዳቱን፣ደስታውንም ሆነ ሀዘኑን ይረዳል።በመረዳት ብቻ አይቆምም ርዳታ ሲፈልግ ይደርስለታል።አሁን ያለውሁኔታ ግን ሁሉም እንደ ጋሪ ፈረስ በየልሳኑ የምቀለውን  የአካባቢውን ዜና እያቀረበ ሌላው ሳይሰማው እንደ ጋሪ ፈረስ ሕዝብ በእየአካባቢው እንዲያስብ የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው። እዚህ ላይ ሁሉም ዜና በየልሳኑ የተወሰነ ስለሌላው አያወራም እያልኩ አይደለም።ጥልቀት ያንሰዋል።ጫፍ ጫፉን ነው የምትንነግሩን፣ባለ ልሳኑ የሚያወራውን ዜና ያህል የጠለቀ ዝርዝር እኩል እንወቅ እያልን ነው። በእርግጥ በአንድ የዜና ሽፋን ጊዜ ሁሉን መሸፈን አይቻል ይሆናል።ነገር ግን ሁለት አማራጭ አለ። አንዱ በእየለቱ ሁሉም በልሳኑ የሌላው ልሳን ያዘጋጀው ዜና ላይ ጉልህ የሆኑትን ከሁሉም ክልሎች የማቅረብ ግድታ ቢገባ የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ከዋና የዜና እወጃ በተለየ በሳምንት ሁለት ወይንም ቢያንስ አንድ ቀን ሰፊ የክልሎች ዜና በስፋት ሁሉም የዜና እወጃ በልሳኑ በጥልቀት እንዲዘግብ እና ዘገባው ደግሞ ሁሉንም ክልሎች የሳምንት ዜና  የሸፈነ እንዲሆን ማድረግ ነው።የመረጃ ክፍተቱ የሚፈጥረው አደጋ ይታየን።

ለማተቃለለ ይህ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።በነገራችን ላይ  ህዝቡ የቪኦኤ እና ዶቼቬሌ ራድዮን የሚከታተለው የተለየ ነገር ሆኖ አይደለም።የዜና ሽፋናቸው አብዛኛውን ክልል ስለምሸፍን ነው።መረጃዎች ከባህር ማዶ ሲመጡ ደግሞ ከውጭ አገር ማሰራጫው ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በራሱ የጠራ አይደለም። የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ይህንን ቢያስቡበት ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን  በ1955 ዓም ሲከፈት (ቪድዮ )



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...