ጉዳያችን / Gudayachn
ታሕሳስ 16/2012ዓም (ደሴምበር 26/2019 ዓም)
እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ታህሳስ 21/2019 ዓም ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ይዘው የወጡት የአንድ ሚኒ ባስ ላይ የተለጠፈ ፖስተር ጠቅሰው ከሞጣ መስጂድ የቃጠሎ አደጋ ጋር ለማገናኘት የሄዱበት ርቀት አስደንጋጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ኡስታዝ አሕመድ ጀበል በሚኒ ባስ የውጪ ክፍል ላይ ተለጥፎ ያነሱት ፎቶ እና እንደ ትልቅ ወንጀል ያብጠለጠሉበት ፖስተር ''የአባቶቻችንን ታሪክ እንደግማለን '' የሚለውን ፅሁፍ ነው።
በቅድምያ በየትኛውም ቦታ የሚደረግ የሃይማኖት ቦታ የማቃጠል፣የመግደል እና የመንቀፍ ተግባር የሚወገዝ ብቻ ሳይሆን፣ይህንን የፈፀሙም ሆነ እንዲፈፀም የረዱ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።በሞጣ መስጂድም ሆነ በባሌ፣ሐረር እና ሲዳማ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቃጠሎ ያደረሱ በሙሉ ለፍርድ መቅረብ እና ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት አለባቸው።ይህንን ኢትዮጵያውያን ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያኑ ከአደባባይ ንግግር እስከ ማኅበራዊ ሚድያ ደጋግሞ የገለጠው እና ሁላችንም የምንስማማበት ጉዳይ ነው።
ለእዚህ ፅሁፍ መነሻ ያደረገኝ አደገኛ አካሄድ ግን የሐይማኖት ቀዳሚ ሰዎች ወደ አክትቪዝም መግባት አደገኛ አካሄድ ነው። ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ በአንድ የሚኒባስ ታክሲ ውጪያዊ ክፍል ላይ የተመለከቱትን ''የአባቶቻችንን ታሪክ እንደግማለን'' የሚል ሌላ ቦታ የተፃፈ ጥቅስ ከሞጣ የመስጊድ ቃጠሎ ጋር አገናኝተው ለመቀስቀሻነት ሲጠቀሙ እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ተጠቅመዋል።እንዲህ ይነበባል -''"የአባቶቻችንን ታሪክ እንደግማለን" ሲሉ የቱን ታሪክ ሊደግሙ ነው ብለህ መቁጠር ብትጀምር ባለፈው አንድ ዓመት ዉስጥ ብቻ ብዙ መቁጠር ትችላለህ። ለምሳሌ ትናንት ምሽት በሞጣ ከተማ መስጂዶችን እና የሙስሊሞችን ንብረቶች አቃጥለው' ----' በማለት ያብራራሉ።
የአባቶቻችን ታሪክ መልካም የሆነውን የማንደግመበት ምክያት ምንድን ነው? የኢትዮጵያን ነፃነት ለመጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ፣ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ለማድረግ ከስነ ፅሁፍ እስከ ስነ ህንፃ የሰሩትን መልካም ሥራ፣ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ታቦትና ድንጋይ ተሸክመው ይቅር መባባላቸው እና ሌሎቹን የማንደግመብት ምክንያት ምንድነው? ኡስታዝ አህመዲን በኢትዮጵያ መስራች አባቶች ላይም ሆነ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና የተጫወቱትን አባቶች ሁሉ መስጂድ ያቃጠሉ ይመስል በፈስቡክ ያብጠለጠሉበት አግባብነት የሌለው አገላለጥ አደገኛ የታሪክ ትርክት ውስጥ እየገቡ እንደሆነ አመላካች ነው።አባቶቻችን የመሐመድን ቤተሰቦች ያስጠጉ፣ አስጠግተውም በእምነታቸው ላይ ተፅዕኖ ሳይፈጥሩ በሰላም ወደ መካ የላኩ የተከበሩ አባቶች የነበሩባት ምድር ነች ኢትዮጵያ። አባቶቻችን ከሸህ ሁሴን ጀብሪል ጋር ተመራርቀው የኖሩ፣ከአባጅፋር ጋር ተመካክረው የኖሩ አባቶች ናቸው ያሉን።ይህንን መልካም ተግባር መድገም ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው?
ኡስታዝ አሕመዲን የዛሬ ዓመት ገደማ ለ'ኢትዮ ቱብ' በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ኢትዮጵያን እስር ቤት ከመግባታቸው በፊት በደንብ እንደማያውቁ እና እስር ቤት ከገቡ በኃላ እንዳወቁ አብራርተው ነበር።በእርግጥ እርሳቸው መጅሊሱ አካባቢ ባሉ አለመግባባቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሄዱበት ጉዳይ እንዳለ ይሰማል።ይህ በራሱ ጉዳዩን በሚያውቁ ቢብራራ ይሻላል።ኡስታዝ አህመዲን ግን ከእስር ከተፈቱ በኃላስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያውቁታል ወይ? ካወቁትስ ቀረብ ብለው ተረድተውታል ወይ? ሙስሊም ከክርስቲያኑን ለማጋጨት ይህ ትውልድ ያልኖረውን የአባቶቹን ታሪክ እየጠቀሱ ያውም በ16ኛው ክ/ዘመን አንድ ሙስሊም ተገድሎ ነበር በሚል አገላለጥ ከላይ የጠቀስኩትን የታክሲ ፖስተር ጋር አያይዘው ግራ እና ቀኙን ያልለየ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እና ክርስቲያን ላይ ለምን የሞት አዋጅ የሚጠራ የቅስቀሳ ፅሁፍ ይፅፉበታል? ለምን? ይህ ከአንድ የሃይማኖት አስተምሮ እንዳለው ከሚናገር ሰው የሚጠበቅ አይደለም።አሁንም ርጋታ፣ማስተዋል እና ወደ በጎ ህሊና መመለስ ጠቃሚ ነው።
በያዝነው ሳምንት ውስጥ ከአንድ ሙስሊም የተላለፈ ታላቅ ምክር፤ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች (ቪድዮ)
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment