ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 20, 2018

የዘገየ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ለውጥ እንደቀረ ይቆጠራል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከታል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ሕዳር 12/2011 ዓም (ኖቬምበር 21/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚገኙ ሁለት ገዢ  ነጥቦች   • ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?
  •  የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች።ከሁለት ሺህ ዓመታት በዓይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ፣ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ሂደት ጋር ስትወጣ እና ስትወርድ የኖረች ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትሰኛለች።የሶርያ ኦርቶዶክስ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን እንደምትባል፣ "ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀገር ማለት ነች" እንዳሉት ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰኘቷ በብዙ ዕይታ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።

ይህች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከደረሰባት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉት 27 ዓመታት የደረሰባት በቡድን የተደራጁ ዘራፊዎች እና ጎጠኞች ያደረሱባት መቦርቦር እና መጎሳቆል እጅግ ከምንገምተው በላይ የከፋ ነው።የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ ድረስ የግለሰቦች መጠቀምያ ሆኗል፣ዝርፍያው እንዳይደናቀፍባቸው ዘራፊ የጨለማ ቡድ አባላት  ከጳጳሳት ማስደብደብ፣እስከ አጥብያ አስተዳዳሪ በመኪና ለማስገጨት እስከመሞከር፣ከሀገር ማሰደድ እስከ እስርቤት መወርወር ድረስ በአገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን ላይ ፈፅመዋል።ይህ ብቻ አይደለም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ዘመናዊ መልክ ይዞ ለዝርፍያ እንዳይመች ሆኖ ይዋቀር ብለው በከፍተኛ አማካሪዎች ታግዘው ያቀረቡት የማሻሻያ መዋቅር የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከ90% በላይ የደገፉት ቢሆንም አሁንም የዘራፊው እና የጎጥ ቡድን አባላት የማሻሻያ ሃሳብ ባቀረቡት ላይ ከማስፈራራት ጀምሮ እስከ ስም ማጥፋት በፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጭምር ተደግፈው ፈፅመዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?


አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ  የተፈፀመባትን ግፍ የመዘርዘርያ ጊዜ አይደለም።በደረሰባት ግፍ መጠን የግፉ እና የዘረፋውን አካላት የመቁረጫ ጊዜ ግን ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሚከተሉት ተግባራት በቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና በመንግስት መወሰድ አለበት። እነርሱም : -
  • ምእመናንን፣የቤተ ክርስቲያናትን የአገልግሎት አካላት በየደረጃው  እና መንግስትን የሚያነቃ ለተግብራዊነቱ ፍጥነት የሚያሳስብ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ እና የቃል ለቃል እንዲሁም ቤት ለቤት የሚሄድ ቅስቀሳ ማድረግ። ቅስቀሳው ሌቦችን፣ዘራፊዎችን እና በጎጥ ብቻ ተጠራርተው የተሿሹሙትን በሙሉ መንጥሮ ለማውጣት ዘመቻ ስለሚጀመር የስነ ልቦና ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን በየደረጃው የመጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሁሉም ማሳሰብንም ይጨምራል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን የለውጥ ሂደት (አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ) የሚያስተባብር ልዩ ግብረ ኃይል ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ከምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ከሆኑ ከመንግስት አካላት እንዲመሰረት ማድረግ።
  • ግብረ ኃይሉ በመንግስት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን ምዝበራ እና ዝርፍያ የሚያጣራ እና በአጭር ጊዜ ዘራፊዎቹ ከስራ እንዲታገዱ የሚያስደርግ እና ለሕግ (ቤተ ክርስቲያን በፍትሕ መንፈሳውም ልታየው የምትችልበት ልዩ የፍትሕ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ልትዳኘው ወይንም በመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ለሕግ እንዲቀርቡ የማመቻቸት እና አስፈላጊ ከሆነም ከሕግ አካላት ጋር በመሆን ከምእመናን የሚመጡ ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ወደ ፍርድ ቤት የሚወስድ መሆን ይገባዋል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ የማጣራት ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራ ማስኬጃ እና የካህናት ደሞዝ በቀር በዝግ ሂሳብ መያዝ።ይህም በግርግር በርካታ ንብረት እንዳይሸሽ ይረዳል።
  • በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የገንዘብ አስተዳደር በዘመናዊ የአሰራር አግባብ እና የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ ባላፋለሰ መልክ ማደራጀት።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊነት መከታተል ፣ ወንጀለኞችን በፍትህ መንፈሳዊም ሆነ  በተደረሰበት ስምምነት መሰረት መቅጣት።
  • የማሻሻያውን ሂደት በሙሉ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሚገዳቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲከታተሉት ልዩ የሚድያ አገልግሎት መስጠት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የማሻሻያ ለውጡ በፍጥነት ካልተጀመረ የሚከተለው አደጋ 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተንሰራፋውን የጎጥ እና የዘረፋ ቡድን በቶሎ እጅግ በፍጥነት የማምከን ሥራ ካልተሰራ አደጋ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ደረጃም ሊከሰት ይችላል።እርሱም : -

 የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለው የለውጥ ንፋስ ያልተስማማቸው የቀድሞው አረመኔያዊ ዘመን እንዲመለስ የሚመኙ አካላት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ጊዜ እና ወቅት እየጠበቁ ነው።እነኝህ በውሸት ምንኩስና እና ቅስና ተሸፍነው በስለላ እና በዘረፋ በቡድን የሚንቀሳቀሱ አካላት ለተኮላሸው የጎጥ ስርዓት የመጨረሻ ምሽግ እና ታማኝነታቸውን ለመግለጥ እና የለውጥ አሰራሩ እነርሱ ላይ እንደሚያነጣጥር ስለሚረዱ  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ ግጭት ለማቀናበር እና ትኩረቱ ሁሉ ወደዚሁ ግጭት እንዲሆን አይሰሩም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ይህ ደግሞ አደጋው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ከሃምሳ ሚልዮን በላይ ምዕመን ለያዘችው ሀገርም ጭምር ነው። የተሸነፈው የጎጥ ቡድን የዶ/ር አብይ የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ ከመጋቢት 24/2010 ዓም ጀምሮ ለውጡን ለመገዳደር የተጠቀመበት መንገድ ህዝብን በጎሳ ማፋጀት ነበር።ይህ ጉዳይ አለማዋጣቱ እየታየ ስለመጣ ቀጣዩ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይህንን ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ የተዘረጋውን የጎጥ እና የዘራፍ ቡድን ለግጭት ያለፈው ስርዓት አይጠቀምበትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።ለእዚህ ነው እጅግ በፈጠነ መልክ ቡድኑን እና አሰራሩን ማምከን እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመናዊ አሰራር እና መዋቅር ሃያ አንደኛውን ክ/ዘመን ማሻገር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር መሆኑን መረዳት የሚገባው።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ እና ቀኖናዊ ሳይሆን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ በቅድምያ በውስጧ የተሰገሰጉትን የዘራፊ እና የጎጥ ቡድን ነጥሎ ለሕግ ተገዥ ማድረግ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን የሞራል ልዕልና ለአዲሱ ትውልድ የምታሳይ አድርጎ ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ለጎጥ እና ዘራፊው የጨለማ ቡድን ቀናት አይደለም ሰዓታት መስጠት እጅግ ውድ ዋጋ ይስከፍላል።

ቤተ ክርስቲያንን አንተውም ከቶ (ኦድዮ መዝሙር)ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: