ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 2, 2019

የዓማራ ክልል መስተዳድር እና ሕዝብ በሶስት አካላት ውክብያ ውስጥ ገብቷል።

ጉዳያችን/ Gudayachn
ሐምሌ 27/2011 ዓም (ኦገስት 3/2019 ዓም)

የፖለቲካ ለውጥ ግንዛቤ እና የማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ለውጥ በሂደት ልኬት ሲመዘኑ ልዩነት አላቸው።የፖለቲካ ለውጥን በአብዮት ወይንም የነበረ መንግስትን በአንድ ጀንበር ገልብጠህ የምትፈልገውን የፖለቲካ ለውጥ ልታመጣ ትችላለህ። የነበረ የማኅበረሰብ አስተሳሰብን ግን በአንድ ጀንበር አትቀይረውም።በረጅም ጊዜ በብዙ ውጫዊ እና ውስጣዊ ሁኔታዎች እየዳበረ የመጣ የማኅበረሰብ አስተሳሰብ ቤተ መንግስት ውስጥ ስለገባህ ብቻ አትቀይረውም።አስተሳሰቡ በራሱ የብዙ መስተጋብሮች ውጤት ስለሆነ በቀላሉ አይነቀልም።ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንዶች ያልተገነዘቡት ነገር አንዱ ይህንን የጠለቀ ማኅበረሰባዊ ትስስርን በአንድ ጀንበር በፈለጉት መንገድ ለመምራት የመሞከር ስህተት ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ኢትዮጵያዊ እና አገራዊ ስሜትን ከልጅ ልጆቹ እያወራረሰ ከኖሩት ማኅበረሰብ ውስጥ ልክ እንደ ኦሮሞው፣ትግራይ፣ቤንሻንጉል፣ሱማሌው፣አፋሩና ሌላው ሁሉ የዓማራ ማኅበረስብም አንዱ ነው።ይህ ማኅበረሰብ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በሕወሓት መራሹ የኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ እና ሌላም ስም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ እና በብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ጭምር ፈፅሞ የማያውቃቸው የቀደሙ መሪዎች እየተጠሩ ሲወቀስ ከርሟል።ይህ የማጥላላት ስውር እና ግልጥ ዘመቻ ደግሞ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በውሸት ታሪኮች እየተከሸነ ለታዳጊ ወጣቶች ሳይቀር ስለተዘራ ዛሬ ዛሬ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ለፍቶ አዳሪ ሁሉ ነፍጠኛ የሚመስለው የዋህ ትውልድ ሁሉ እንዲፈጠር ከመደረጉ አልፎ ብዙዎች ከኖሩበት ቦታ በውሸት እና የቂም ታሪክ አደግ የአካባቢ ባለስልጣናት ተገፍቶ ከቀየው እስከ መባረር ደርሷል።ለእዚህም ማስረጃ ከጉርዳፈርዳ እስከ ቤንሻጉል የተፈፀሙትን ግፎች መመልከት ይበቃል። 

የዓማራ ክልል መስተዳድር እና ሕዝብ በሶስት አካላት ውክብያ ውስጥ ገብቷል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በፈጣን የማኅበረሰብ የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ ነች።የለውጥ ንቅናቄው የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸውን አካላት በረጋ መንፈስ እና በቅንነት ያለፈ ታሪክ ንትርክ አቁመው መጪውን ያለመ አጀንዳ ላይ ተወያይተው ወደፊት ይሄዳሉ? ወይንስ ልዩነቶችን በሰለጠነ መልክ መፈታት ትተው በተለመደው የኃይል መስመር በሌላ ዙር ግጭት ሀገሪቱን ወደ ባሰ መቀመቅ ይከቷታል ወይ? የሚለው የወቅቱ ጥያቄ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ እንደ ማኅበርሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ሁሉ ትኩረታቸው የዓማራው  ማኅበርሰብ ላይ በሚፈፀም ውክብያ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ ማናጋት ይቻላል።በእዚህም አጀንዳችንን ማስፈፀም እንችላለን በሚል ዕሳቤ የዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ ውክብያ መፈፀም ስራዬ ተብሎ ተይዟል። 

በዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ ውክብያ በመፈፀም ላይ የሚገኙት ሶስቱ አካላት

1) የዓማራ ክልል ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገሩ የማኅበራዊ ሚድያ ''አርበኞች'' 

በእዚህ ስር የሚገኙ በትክክል የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ጥበብ-አልባ አክትቪስቶች፣ ከማኅበራዊ ሳይንስ፣ከታሪክ እና ከፖለቲካ ዕውቀት ውጪ የሆነ የትምህርት ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ይገኙበታል።እነኝህ አካላት ለዓማራ ሕዝብ ምን ቢደረግ ወይንም የፖለቲካ ትግሉ ግብ ምን ለማግኘት እንደሆነ የጠራ ዓላማ ማስቀመጥ ያቃታቸው ግን አንድ ጊዜ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሌላ ጊዜ ኦዴፓ ቆይተው ደግሞ በዓማራ ማኅበረሰብ ስም የተደራጁ ግለሰቦችን አሁንም ሌላ ጊዜ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ የሚይራምዱትን ሁሉ እየወቀሱ እና ''የዓማራ ጠላቶች'' በሚል ፍረጃ ቀን ከሌሊት ሕዝቡን ከሁሉም አካላት ጋር የማጋጨት እና የማስደንበር ሥራ ላይ ብቻ ተወጥረው የሚውሉ ናቸው። 

የእነኝህ አካላት አካሄድ በተለይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የዓማራው  ማኅበረሰብ መጫወት ያለበትን ጉልህ እና ገንቢ መንገድ ለማመላከት የተነሱ ምሁራንን ሁሉ የማሸማቀቅ ሥራ እየሰሩ  የዓማራን ማኅበረሰብ ሽማግሌ እና ዓዋቂ የሌለበት፣ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር  በፍቅር የመኖሩን የረጅም ጊዜ ጥበብ ሁሉ ገደል የከተቱ ናቸው።ለምሳሌ ሰኔ 15/2011 ዓም በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተፈፀሙ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች እና የኢታማጆር  ሹም ግዳይ ላይ ሟችንም ገዳይንም ሲወቅሱ ቆይተው በኃላ ከግድያው በኃላ ሁለቱንም ስያሞግሱ የተሰሙ ናቸው።

2) የፅንፈኛ ኦነግ አፍቃሪዎች እና ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣኖች 

በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት አካላት በተለየ እና በከፋ መልኩ የዓማራ ክልል እና ሕዝብ በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩ የፅንፈኛ ኦነግ አፍቅሪዎች እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።ሁለቱም አካላት ላለፉት አርባ ዓመታት ''የሞኝ ዘፈን ሁሌ አበባዬ'' እንዲሉ ከወጣትነታቸው እስከ እርግናቸው ድረስ ዓማራ፣ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ በሚሉ ቃላት ሲሰክሩ ያደጉ ናቸው።ከእነርሱ ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ መሃል ሀገር መጥተው ዓማራ የተባለው ማኅበረሰብ ከሁሉ በከፋ ድህነት እና በበዛ ትህትና ሌላው ወገኑ ኢትዮጵያዊ እንደሚያከብር ሲመለከቱ የአለቆቻቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተረድተው አመለካከታቸውን አስተካክለዋል።የቀሩት ግን አሁንም ሁለት ፀጉር አውጥተው በስራቸው ያሉትን ወጣቶች በቂም እና በጥላቻ እንዲያድጉ ለማድረግ ሲባዝኑ ይታያሉ። 

የፅንፈኛ ኦነግ አፍቃሪዎች እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ባለፈ የቂም ትርክታቸውን በዓማራው ማኅበረሰብ ላይ በመንዛት ብቻ አልተወሰኑም። ይልቁንም በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ተቀምጠው ዛሬም የፖለቲካ አሰላለፍ ቅኝታቸውን በዘመናዊ ዕሳቤ ላይ ከመመስረት እና ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት ከመውሰድ ይልቅ ዛሬም መለኪያቸው የዓማራውን ማኅበረሰብ ከመግፋት እና ሴራ ከማሴር አንፃር ብቻ መቀመራቸው አሳዛኙ ሁኔታ ነው።እነኝህ አካላት መጪውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደጋ የሚሉት ኢትዮጵያዊነትን እና የህዝብ ለሕዝብ አንድነትን ሲሆን ስኬት የሚሉት ድግሞ የጎሳ ፖለቲካ አብቦ እና አፍርቶ መታየቱን ነው።ስለሆነም የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያቀርቡትም ሆነ የሚያርቁት ምንም በያውቀው በምስኪኑ የዓማራ ማህበረሰብ ላይ  የፖለቲካ ድርጅቶቹ በሚሰሩት የሴራ ፖለቲካ ልክ እየሆነ መምጣቱ አደገኛው የችግሩ ገፅታ ነው።በእዚህም ዙርያ ምሁራኖቻቸውን ወደ መንግስት መዋቅር በማስገባት ርካሽ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። 

በእዚህ ተራ ቁጥር ሁለት ምድብ ውስጥ ያሉት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የዓማራ ክልል እና ህዝብን በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩት በቀጥታ ሳይሆን በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት የማኅበራዊ ሚድያ ''አርበኞች'' ጋር ተቀላቅለው እና እራሳቸውን በአክትቪስት ስም ሰይመው መሆኑ ነገሩን አስቂኝም ያደርገዋል።ከአንድ ዓመት በፊት የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናቶችን የግፍ ተግባር ሲያሞካሹ የነበሩ ዛሬ ስልት ቀይረው የዓማራ ማኅበረሰብ የሚቆረቆሩ ሆነው መስለው ግን ሕዝቡን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር ስያጣሉት መመልከት የተለመደ ሆኗል።ስለሆነም የማወክ ተግባሩ በረቀቀ መልክ እየተፈፀመ ለመሆኑ አንዱ አመላካች ነጥብ ነው። 

የችግሩ ተከታይ ችግር  

ከላይ የተጠቀሱት የሶስቱ አካላት የዓማራ ክልልንም ሆነ ሕዝብ የማወክ ተግባር ተከታይ ችግር ይዞ መምጣቱ አይቀርም። ይሄውም የዓማራን ክልል ሕዝብ ወደ የጦዘ እና አደገኛ የመጠቃት ስሜት እንዲነሳ ያደርገዋል። አንዳንዶች ይህንን የጦዘ የመጠቃት ስሜት እንደ አዎንታዊ የፖለቲካ ዕድል ቆጥረው የክልሉን ሕዝብ ለማነሳሳት  እና ለርካሽ የፖለቲካ ግብ መጠቀምያ ሊያስቡት ይችላሉ። አሁን ባለችውም ሆነ በመጪዋ ኢትዮጵያ የጦዘ የመጠቃት ስሜትን ቀስቅሶ ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚደረግ ሙከራ ሁሉ መጨረሻው የእርስ በርስ እልቂት ነው።ይህ ማለት ማንም ተነስቶ ሌላውን ገፍቶ ለመኖር ሲፈልግ ይፈቀድለት ማለት አይደለም።ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ተከትለው ወደ ስልጣን የተጠጉትም ዘለቄታዊ የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ አጥተው ግራ እንደተጋቡ ማሰቡ ብቻ መንገዱ በራሱ ስህተት መሆኑን መረዳቱ በራሱ ሂደቱ ችግር እንዳለበት ለማወቅ ይረዳል።

 ስለሆነም የችግሩ ተከታይ በራሱ ሌላ ችግር ነው።በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካሎች የዓማራ ክልል እና ህዝብን የማዋከብ ተግባራቸውን ማቆም አለባቸው።ይህንን ለማቆም ደግሞ በመጀመርያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለባቸው። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ ከማሰብ ይጀምራል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡን ወደ ጦዘ የመጠቃት ስሜት እየገፉት መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደ አደጋ የሚያመራት ነው።

መፍትሄው 

ከእዚህ በፊትም ለመግለጥ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ችግር የመፍትሄው ስርም ሆነ መፍትሄው ፖለቲካ ብቻ የተንጠላጠለ አይደለም።ከፖለቲካ ውጭ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ (ጉዳዮቹን አስመልክቶ ከእዚህ በፊት በጉዳያችን  ''ለኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት አደገኛው ፖለቲካዊው ተግዳሮት ብቻ አይደለም። (ጉዳያችን ልዩ ትኩረት)''  በሚል ርዕስ የወጣውን ይመልከቱ)። ስለሆንም የዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ የሚደረገውን ውክብያ ለማስቆም እና ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የሚከተሉት መፍትሄዎች መወሰድ አለባቸው።እነርሱም : - 

  • ምንም ዓይነት ድብብቆሽ እና ማድበስበስ የሌለበት ግልጥ ውይይት በተለይ በዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ የሚደረጉት ውክብያ በሚፈፅሙት የክልሉ ተወላጅ የፈስቡክ ''አርበኞች'' ተግባር የክልሉ ተወላጅ ምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች መከላከል እንዲችሉ መርዳት፣
  • ማንኛውም ዓይነት የትንኮሳ ንግግሮች፣የቢሮክራሲ የሴራ ተግባራት እና የታሪክ ሽምያዎችን ማጋለጥ እና በፈፀሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣
  • የአርባ ዓመቱን የጎሳ ፖለቲካ እና በተለይ የዓማራ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ፀብ ጫሪ ንግግሮች በይፋ መታረማቸው እንዲገልጥ ይህንን ያደረጉም በይፋ ይቅርታ  እንዲጠይቁ ማድረግ እና ለወደፊት የሚያስተጋቡ ካሉ በሕግ መቅጣት፣
  • መንግስት ጥንቁቅ የሆነ የምጣኔ ሀብት ክፍፍል፣የበጀት አደላደል እና የመንግስት ምስረታ ስርዓት ሂደት እንዲከተል ማድረግ፣
  • የእነኝህ ሁሉ ችግር አንዱ  መነሻ የሕገ መንግስቱ ፀብ አባባሽ አንቀፆች በመሆናቸው ህገ መንግስቱን የማሻሻል ሂደት ከምርጫው በፊት ማከናወን እና 
  • ሰፊ፣ጥልቅ እና ሁሉን ያሳተፈ   አገራዊ እና ማኅበራዊ ዕሴት (Social Capital) በእጅጉ የሚያሳድግ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ለሐያ ሰባት ዓመታት የተዘሩ እና ከእዛ በፊት የተዘሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን የማከም ሥራ መስራት የሚሉት ይጠቀሳሉ።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ የሚከሰቱት ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ክስተቶች ለምን ሆኑ ብሎ ለረጅም ጊዜ የማጥናት እና መፍትሄ አምጦ የመውለድ ልማድ ስለሌለ የፊት የፊት ብቻ እያዩ መሄድ ልማድ ሆኖ ነው እንጂ ለችግሮቻችን መፍትሄ የመፈለጉ ሥራ ላይ ሁሉም እኩል ቢሰራ የማይፈታ ችግር የለም።ለምሳሌ ሰኔ 15/2011 ዓም በባህር ዳር እና አዲስ አበባ የተፈፀሙት ግድያዎች ዙርያ የሚወሳው ፖለቲካዊ  ሁነቱ እንጂ የችግሩ መነሻ እና ማኅበራዊ ስሜቱ እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ክፍል የሚያጠናው እና የችግሩ ስር ወደ ሚወስደው ጫፍ ሄዶ የመፍትሄ ቁልፉን ለማግኘት እና መንግስት ለማማከር የሚተጋ የለም።ከእዚህ ይልቅ  በማያልቅ የቃላት ውርወራ ላይ መግባት ፋሽን ሆኖ ተይዟል።ጥናቱ ቢደረግ ግን የጦዘ  የተጠቂነት ስሜት ከላይ በተጠቀሱት ሶስት አካላት ውክብያ ዙርያ በተፈጠሩ ስነ ልቦናዊ ስሜቶች ምክንያት ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። አሁንም ጊዜው አልረፈደም።ወደ ሌላ የጥፋት ምዕራፍ ሳይገባ ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆን ሀገር አረጋጊ፣የህዝብን ስነ ልቦና አካሚ እና በሁሉም ወገን መሐል የመተማመን ስሜት ፈጣሪ አገራዊ ንቅናቄ ከመንግስትም ሆነ ከአገር ወዳድ ምሁራን ሁሉ ይጠበቃል።
=========================/////==========
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ ካቀረበው ዜማ (ቪድዮ) ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...