ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 20, 2023

ጎሳንና የፖለቲካ ተጽዕኖን መሰረት ያደረገ የጵጵስና ሹመት በመስጠት ቤተክርስቲያን የሲሞን መሰሪን መንገድ አትከተልም።

  • ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን የምትሾመው የፖለቲካው አውድ እንዲፈነጥዝ ወይንም ይህኛው ጎሳ ደስ እንዲለው ሌላው እንዲከፋው አይደለም።
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ሲሞን በሰማርያ ይኖር የነበረ አስማተኛ ሰው ነበር፡፡ ሕዝቡም የሚያደረገውን ምትሐት እያዩ ይከተሉት ነበር በኋላ ግን በፊልጶስ ትምህርት አምነው ሲጠመቁ እሱም ተጠመቀ፡፡ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያት በሰማርያ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን ሲያውቁ ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ዮሐንስን ላኩበቸው፡፡ እነርሱ እጃቸውን በመጫን በሕዝቡ ላይ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ አሳዳሩባቸው፡፡ ይህንን ያየ ሲሞን መሰሪንም ብዙ ገንዘብ አምጥቶ እኔም እጅን የሚጭንበት ሰው መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርበት ይህንን ሥልጣን ስጡኝ አለቸው ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹የእግዚአብሔርን ሥጦታ በገንዘብ ልትገዛ አስበሃልና ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ›› አለው፡፡ ሙሉ ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ሥራ ምዕ 8፣18-23 ላይ ይገኛል።

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የሚያስተምረን ሁለት ቁምነገር አለ። አንዱ መንፈስ ቅዱስን ለማታለል የመሞከር ተግባር ሰይጣናዊ እንጂ መንፈስቅዱሳዊ እንዳልሆነ ሲሆን ሌላው ይህንኑ በገንዘብ እና በሌላ ጥቅማዊ መንገድ የእግዚአብሔርን ሹመት ለማግኘት መሞከር በሐዋርያት ዘመንም ታይቶ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩት ሐዋርያት እንዴት እንደተዋጉት ያሳየናል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው።ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት እየዋሉ እና ካደረበት እያደሩ የተማሩት ሐዋርያት የመጀመርያ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያቸውን በ50 ዓም ካደረጉ ጀምሮ ከእዚያ ቀድሞም ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ስልጣነ ክህነት  መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ሆነች ምስራቃውያን የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት በጳጳሳት ሹመት ሂደት ላይ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ብቻ እንዲሆን እና ምንም ዓይነት የፖለቲካ፣የዘር፣የገንዘብ እና ሌላም  ተጽዕኖ እንዲኖረው አይፈቀድም። ይህ መንፈስ ቅዱስን በውጪያዊ ተጽዕኖ ለማግኘት የሚሞክር ሁሉ የሲሞን መሰሪያዊ መንገድ የተከተለ ተደርጎ ይወሰዳል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እያካሄደች ያለው የርክበካሕናት ጉባኤ ላይ ከቀረቡት አጀንዳዎች ውስጥ በጎሳዊ እና ፖለቲካዊ አድመኝነት የቤተክርስቲያኒቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የሞከሩ እና በኋላም በመግባባት ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተመለሱት ሶስቱ ጳጳሳት በሕገወጥ መንገድ የሾሟቸውን አሁን በቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ሳይመረመሩ እና የሚገባቸውና የማይገባቸውን ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ጉባኤ ጀምሮ የምትመረምርባቸውን የመንፈስ ቅዱሳዊ መንገዶች በመግፋት እንዲሾሙ የሚገፉ ደፋሮች እያየን ያለበት ጊዜ ነው። ይህ ሲሞን መሰሪያዊነት ነው።ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።

ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን የምትሾመው የፖለቲካው አውድ እንዲፈነጥዝ ወይንም ይህኛው ጎሳ ደስ እንዲለው ሌላው እንዲከፋው አይደለም።ማንም ማን ቢሆን መንፈስ ቅዱስ የሚሾመውን ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በእኩል ዓይን አይታ፣መርምራ እና ጸሎት አድርጋ ትሾማለች እንጂ በሆያሆዬ እና የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ የምትሾምበት የጳጳሳት አሿሿም መንገድ የለም።ይህንን ቤተክርስቲያኒቱን በቅርበት የማያውቁ ፖለቲከኞች ጠንቅቀው ሊያውቁት የሚገባ እና በእንቢተኝነት ቤተክርስቲያኒቱን ለማዋከብ ከሞከሩ የሲሞን መሰሪ የተሰጠ ቅጣት ለእነርሱም እንደሚተርፍ ሊረዱት ይገባል።


No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።