ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 16, 2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደህንነቷን ለመጠበቅ በፍጥነት መውሰድ የሚገባት ሁለት የመፍትሄ ርምጃዎች (የጉዳያችን ሀሳብ)



ጉዳያችን / Gudayachn
ህዳር 6/2012 ዓም (ኖቬምበር 16/2019 ዓም)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የለውጥ ነፋስ በነፈሰ ቁጥር የመጀመርያ ኢላማ ስትሆን ኖራለች።በ1966 ዓም የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ መውረድን ተከትሎ ፓትርያርክ ቲዎፍሎስ በደርግ ተገደሉባት፣በ1983 ዓም ኢህአዴግ አዲስ አበባን መቆጣጠሩን ተከትሎ አቡነ መርቆርዮስ ከመንበረ ፕትርክናቸው ተነስተው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሲኖዶስ ተከፍላ ቆየች።በ2010 ዓም ከኢህአዴግ ጥገናዊ ለውጥ በኃላ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት ቢመለስም የቤተ ክርስቲያን መቃጠል፣የምእመናን መገደል እና ስደት በተለይ በኦሮምያ ክልል ተባብሶ ቀጥሏል። ባሳለፍነው አንድ ወር ውስጥ ብቻ በመንግስት የተረጋገጠ ሰማንያ ስድስት ኢትዮጵያውያን በፅንፈኞች መገደላቸው ተገልጧል።

ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለማጥቃት መልካም አጋጣሚ ያገኙ የመሰላቸው የፅንፍ ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን ህንፃዋን ከማቃጠል እስከ ምመናኗን መግደል እና ከይዞታቸው መንቀል ድረስ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል።በእዚህም መሰረት ከሲዳማ ዞን እስከ ባሌ፣አርሲ እና ምስራቅ ሐረርጌ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ሴት ልጅ ጭምር በድንጋይ ተወግራ ተገድላለች፣አዛውንት በስለት ተገድለዋል። ቅዱስ ሲኖዶስም ተከታታይ የምሕላ ፀሎት ከማወጅ ባለፈ ምዕመናንን ወርደው እስከ ማፅናናት ስራዎች እየሰሩ ነው።

በእነኚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ቤተ ክርስቲያን  አፋጣኝ መፍትሄ መውሰድ የሚገባት በተለይ ከደህንነቷ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ምንድነው የሚለውን ጉዳያችን እንደሚከተለው ሃሳብ ታቀርባለች። ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ መመርያ ሰጪነት ሁለት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይገባታል። እነርሱም -

1) የቤተ ክርስቲያን የጥበቃ (የዘበኛ)  ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ  በአዲስ ዲፓርትመንት ማለትም በወታደራዊ ሙያ በሰለጠነ እና ዘመናዊ መሳርያ ትጥቅ ማደራጀት እና  ማዋቀር 

በኢትዮጵያ  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ መንግስታዊ መስርያ ቤቶች የጥበቃ ዲፓርመንት  ራሱን በቻለ ዲፓርትመንት የሚመራ ነው።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምሳሌነት መውሰድ ይቻልል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥበቃ ክፍል አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው መስርያ ቤት  እስከ ጫፍ ዶሎ መና ባሌ ያለው የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ የጥበቃ ክፍል የሚመራው ራሱን በቻለ ዲፓርትመንት ነው። ይህ ማለት የራሱ በጀት አለው፣በወታደራዊ ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች፣የፀጥታ አጠባበቅ መመርያ ሁሉ አለው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል ስንመለከት ይህ አሰራር ወጥነት ባለው እና በቂ በወታደራዊ ሙያ የሰለጠነ እና በቂ ትጥቅ ያለው የጥበቃ ኃይል የላትም። ይህ ግን በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።ከእዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያን  ከላይ በተጠቀሰው ደረጃ የጥበቃ ክፍሏን ያላጠናከረችው  ለሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በቀላሉ ለመንግስት የፀጥታ አካላት ለምሳሌ ለፖሊስ በማሳወቅ ችግሮች ይፈታሉ በሚል ነበር።አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ፖሊስ እራሱ የፀጥታ ችግር በሆነበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያን የራሷን የጥበቃ ኃይል በፍጥነት ማጠናከር ይጠበቅባታል።

በኢትዮጵያ ሕግ ማንኛውም ግለሰብ ቤት ሆነ የእምነት ድርጅት አጥር ግቢ  ካለፈቃድ መግባት ወንጀል ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን ስም በበበሩ ላይ መፃፍ አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።ፅሁፉ እያለ በር ላይ የሚገኘውን የጥበቃ አካል አልፎ ለመግባት በተለይ በኃይል ለመግባት የሚሞክር ማናቸውም አካል ላይ ጥበቃ በያዘው መሳርያ ከማስጠንቀቅያ  ጋር ቤተ ክርስቲያንን ለመከላከል ማናቸውንም እርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ መብት አለው።ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የጥበቃ ኃይሏን መብታቸው እና ግዴታቸውን ማሳወቅ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን።ከጥበቃ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ለምታደርገው የጥበቃ አካላት ስልጠና እና የትጥቅ ማሟላት ሂደት ሁሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል። ለምሳሌ የተቀጠሩትን የጥበቃ አካላት ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ እና ከኃላ ቀር መሳርያ ቢያንስ በክላሽ ደረጃ የታጠቁ የጥበቃ ኃይል እያንዳንዱ አጥብያ ከከተማ እስከ ገጠር እንዲኖር ለማድረግ መንግስት ሕጋዊ ስልጣኑን እና ትጥቅ በግዥም የማቅረብ ሥራ መስራት አለበት።ይህ ሥራ በራሱ የመንግስትን ሥራ በተለይ በፀጥታ በኩል የሚያቀልለት ሥራ መሆኑ እሙን ነው።እዚህ ላይ ቤተ ክርስቲያን የጥበቃ ስራውን እራሷ ባደራጀችው ሕጋዊ በሆነ የጥበቃ አካል እንጂ ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ ድርጅቶች እንደሚያደርጉት ለጥበቃ ኤጀንሲዎች ስራውን ለመስጠት ከሞከረች ትልቅ ችግር ቤትክርስትያን ላይ ሊያስከትል ይችላል።ኤጀንሲዎች ተፈላጊ እንዲሆኑ እራሳቸው የፀጥታ ችግር የሚሆኑበት አጋጣሚ በብዙ አገሮች የታየ ነው።ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በጥንቃቄ በራሷ ልጆች ልፀራው የሚገባ ሥራ ነው።

የጥበቃ ክፍልን (ድፓርትመንት) ቤተ ክርስቲያን በአጭር ጊዜ ለማደራጀት የሚከተሉትን ተግባራት በቶሎ መስራት ትችላለች። እነርሱም -

  • የጥበቃ ክፍሉን በአገር አቀፍ ደረጃ ማዕከላዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ፣
  • ክፍሉ በአገረ ስብከት እስከ አጥብያ የሚወርድ ወጥ የሆነ አሰራር፣አጠባበቅ፣የስልጠና አቅም እና የመሳርያ ትጥቅ ማሟላት፣
  • የጥበቃ ክፍሉ በተለይ በማዘዣው በቤተ ክህነት ደረጃ ያለው የጥበቃ ዋና ክፍል በአገረ ስብከት ደረጃ እና እስከ አጥብያ ድረስ ያለውን የጥበቃ  ሁኔታ ለመከታተል እንዲረዳ ቢያንስ በኮለኔል ደረጃ የሚመራ ይሆናል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅች የሆኑ ነገር ግን በወታደራዊ ስልጠናም ሆነ ስነምግባር የተመሰገኑ መሆን ይገባቸዋል፣
  • የጥበቃ ዲፓርትመንት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አጥብያዎች ስጋት የተደቀነባቸውን እና ቅድምያ ትኩረት የሚሹትን አካባቢዎች ይለያል፣ መረጃ ይተነትናል አስፈላጊ ሲሆን መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ የቅድመ አደጋ ጥንቃቄ ማስጠንቀቅያ ይሰጣል፣
  • የጥበቃ ክፍል ከኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ፈቃድ ያለው የራሱ የመገናኛ ራድዮ መገናኛ ይኖረዋል።በእዚህም መሰረት በአገረ ስብከት ደረጃ እስከ አጥብያ ያለው ጥበቃ ድረስ የሚገናኝበት በመንግስት ፈቃድ ያለው የራድዮ መገናኛ መስመር ይዘረጋል።
  • የጥበቃ ክፍሉ መተዳደርያ ደንቡ በቅዱስ ሲኖዶስ ፀድቆ ሥራ ላይ ሊውል ይችላል።

2) የአይቲ (ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ክፍል በመምርያ ደረጃ መመስረት  

አሁን ባለንበት ዓለም አይደለም ከሃምሳ ሚልዮን በላይ ሕዝብ በስሩ የያዘች እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያለ ትልቅ አደረጃጀት ያላት አገራዊ  አካል ቀርቶ ትንንሽ ድርጅቶችም ከአይቲ (የኢንፎርሜሻን ቴክኖሎጂ) ክፍል በመምርያ ደረጃ በቤተ ክህነት መመስረት እና ክፍሉ ከአገረ ስብከት እስከ አጥብያ ድረስ በኔት ዎርክ ማያያዝ በፍጥነት መሰራት የሚችል ሥራ ነው። የአይቲ ኔትዎርክ መመስረት በጣም ውስብስብ ሥራ እና የማይቻል አድርጎ ማሰብ አይቻልም። 

ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ሁለት ሀብት አላት።አንዱ የሰለጠነ እና የተማረ የሰው ኃይል ሲሆን ሌላው የገንዘብ አቅም ነው። ስለሆነም የአይቲ መረቡን መዘርጋት በቤተ ክህነት ደረጃ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍጥነት መመርያ ቢሰጥበት  ስራውን የሚከታተል ልዩ ኮሚቴ ሰይማ ስራውን የሚሰሩ በአገር ውስጥ ወይንም በውጭ የታወቁ ኩባንያዎች በጨረታ ስራውን መስጠት ትችላለች።የኔትዎርኩ ሥራ በአንዴ ሁሉም ጋር ባይደርስ ደረጃ በደረጃ ለመስራት ስራውን መጀመር ግን ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።የአይቲ መምርያ ማስቀመጥ እና አሰራርን በአይቲ አስደግፎ መስራት ከቤተ ክርስቲያኒቱ የፀጥታ ሥራ ጋር አብፎ የሚታይ ብቻ ሳይሆን መጪውን የዋጀ አሰራር የመዘርጋት ተግባር አካል ነው።የአይቲ መምርያ መስርቶ እስከ አጥብያ ድረስ ስራውን መተግበር ለቤተክርስቲያን  የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጣል። እነርሱም -


  • የቤተ ክርስቲያን የገንዘብ አጠቃቀም፣የአጥብያ ሁኔታ፣ውሎ እና ተግባራት በቀጥታ በደቀቃዎች ውስጥ ሪፖርት ለአገረ ስብከት እና ለቤተ ክህነት ለመላክ ይረዳል፣
  • በእርቀት የሚገኝ አጥብያ የፀጥታ ስጋት ቢኖርበት በደቂቃዎች ውስጥ ለሚመለከተው ሁሉ ለመግለጥ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፣ 
  • ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ አጥብያዎች በኔት ዎርክ እንዲገናኙ ያደርጋል፣
  • ወጥ የሆነ የእቅድ ፎርማት ለመላክ ለሁሉም አጥብያዎች ማድረስ ይቻላል፣
  • አጥብያዎች ወጥ የሆነ እቅድ ትግበራ ሪፖርት እንዲልኩ እና በአገረ ስብከት እና በቤተ ክህነት ደረጃ እንዲገመገም ይረዳል፣
  • ቤተ ክርስቲያን ያላትን የሰው ኃይል፣የገንዘብ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚገባ መዝግባ ለመያዝ እና የንብረቷን ሁኔታ ለመቆጣጠር  ይረዳታል፣
  • እያንዳንዱ አጥብያ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መዋቅር ውስጥ የአይቲ ክፍል እንዲኖረው ቃለ አዋዲው ማሻሻያ እንዲደረግበት ይረዳል። 


ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አሁን የገጠማትን የፀጥታ ችግር ከላይ በተጠቀሱት ሁለት መንገዶች ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችላት እንደሚሆን አምናለሁ።በተለይ የጥበቃ ክፍሉ በዲፓርትመንት (መምርያ) ደረጃ ስትመሰርት በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች ማንቀሳቀስ የምትችልበት ዕድል አላት።በጎ ፍቃድ የጥበቃ አካላት ለማንቀሳቀስ ግን ራሱን የቻለ ጉዳዩን የሚከታተል እና በወታደራዊ ሙያ የሰለጠነ አስተባባሪ ያስፈልጋል። በእዚህ ደረጃ የተጠናከረች ቤተ ክርስቲያንን እሳትና ጎመድ ይዞ ለሚመጣ ፅንፈኛ ከጥበቃ ክፍሉ የሚሰጠውን ምላሽ ስለሚረዳ በቀላሉ አንድ አጥብያ ለማጥቃት አይደፋፈርም። ምክንያቱም  የሁሉም አጥብያ ጥበቃዎች የቤተ ክርስቲያኑን አጥር ጥሶ የሚመጣ ማንኛውም አካል ላይ የመተኮስ እና ቤተ ክርስቲያኑን የመከላከል ሕጋዊ ስልጣን ስለሚኖረው ፅንፈኛም አደብ እንዲገዛ ያስገድደዋል። በሌላ በኩል የጥበቃ ክፍሉ አንዱ አጥብያ ላይ ችግር ካለ ሌላ አካባቢ ያሉ አጥብያ የጥበቃ አካላት በራድዮ መገናኛ ተጠቅመው ችግሩ ያለበት አጥብያ  በፍጥነት የሚደርሱበት ዕድል አለ።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...