ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 30, 2019

አቶ ለማ መገርሳ መደመር እና የኢሕአዴግ ውህደትን አስመልክተው ለቪኦኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ምክንያት ምንድነው? በቀጣይስ ምን ሊከሰት ይችላል?

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ 

ጉዳያችን / Gudayachn
ህዳር 20/2012 ዓም (ኖቬምበር 30/2019 ዓም)

ዓርብ ህዳር 19/2012 ዓም ምሽት ላይ  ቀደም ብሎ ሐሙስ ዕለት በኦስሎ፣ኖርዌይ ጃዋር መሐመድ የሰበሰባቸው የኦሮሞ ኮሚኒቲ አባላት መካከል በኦሮምኛ ከፊት በኩል የተቀመጡ አንዲት እናት የተናገሩትን ድምፁን በመሃል እያቆመ ኦስሎ የሚኖር የኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ወዳጄ እየተረጎመ ያሰማኝ ነበር።እኝህ እናትበጣም አክራሪ ብሄርተኛ እንደሆኑ ከወዳጄ ትርጉም ተረድቻለሁ።በንግግራቸው  ጀዋርን ይወቅሱታል።ጀዋርን የሚወቅሱት ደግሞ ለማ ብቻውን ሆኖ ሳታግዘው መቅረትህ ብቻውን እንዲሆን አርገህ፣ካሉ በኃላ ዓቢይ ማኅበረሰባቸውን (የኦሮሞን ማለት ነው) እንደከዳ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያወራሉ።በመሃል ላይ ንግግራቸው በመርዘሙ ራሱ ጃዋርም እየሳቀ ያያቸው ነበር።አሁንም ይሄው ወዳጄ እንደተረጎመልኝ በቃዎት ሰዓት አበቃ ተብለው ነው ማይኩን የሰጡት።የእርሳቸው ንግግር ግን የውስጥ አዋቂ ንግግርም ይመስል ነበር።ከእዚሁ ወዳጄ ጋር እንዴት ዓብይን በእዚህ ደረጃ እንደከዳ ይቆጥሩታል? በማለት ጥያቄ ሰነዘርኩ። 

ቪድዮውን ማየት ቀጠልኩ በእዚሁ በጃዋር ስብሰባ ላይ የትግራይ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት በአማርኛ ንግግር እንዲያደርግ ዕድል ተሰጠው።አቶ ዳዊት ንግግሩን ሲጀምር ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ''በትግርኛ ተናገር!'' ብሎ ሲናገር በቪድዮው ውስጥ ይሰማ ነበር።ዳዊት ለጥቂት ሰኮንዶች ንግግሩን ቆም አደረገ እና በአማርኛ ቀጠለ። ዳዊት ተሰብሳቢው እና እርሱን የሚያገናኘው አማርኛ መሆኑ ገብቶታል።ዳዊትን ከእዚህ በፊት ሁለት ጊዜ  ኦስሎ ውስጥ በተደረጉ  የማኅበረሰብ ስብሰባዎች አግኝቼዋለሁ።አድ ጊዜ የኢትዮጵያን የጋራ መድረ በኖርዌይ ባዘጋጀው የሁሉም የፖለቲካ አተያዮች መድረክ ላይ ሲሆን ሌላው በቅርቡ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኖርዌይ ባዘጋጀው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነበር።ከእርሱ ጋር  በሃሳብ የማንስማማባቸው ብዙ ነጥቦች ዙርያ ተከራክረናል።ስንከራከር ግን ስርዓት ባለው መልክ ስለነበር የዳዊት ሃሳብ አቀራረብ ከብዙ የህወሓት ደጋፊዎች የተሻለ አቀራረብ ያለው ግን  ያንኑ በመደጋገም የሃሳቡን ስፍራ ላለመልቀቅ የሚሟገት ሰው ነው።በጀዋር ስብሰባ ላይ መገኘቱ እና ንግግር ሲያደርግ በቪድዮ ላይ ሳየው ግን በቅርቡ ስለሞቱት ሰማንያ ስድስቱ ኢትዮዮጵያውያን አንስቶ ጀዋርን ተጠያቂ እንደሆነ ይነግረዋል ብዬ አስቤ ነበር። አላደረገውም።

ወደ አቶ ለማ ጉዳይ ልመለስ።የኦስሎው ስብሰባ ላይ ለማን እያሞገሱ ከተናገሩት ሴት መለስ ስል የማኅበራዊ ሚድያው አቶ ለማ የመደመር ሃሳብ እንዳልተቀበሉ ገለጡ የሚል ዜና ተለጥፎ አየሁ።ወደ ቪኦኤ ገፅ ስገባ ዜናውን አረጋገጠልኝ።ግን ሙሉ ዜናው ስላልነበር ምንም ለማለት አላስቻለኝም። ዛሬ ምሽት ግን ቪኦኤ አማርኛው ሙሉውን ዘገባ ለቆታል። በዘገባው ላይም አቶ ለማ የመደመር ሃሳብ ከመጀመርያው እንዳልተቀበሉት እና እንዳልገባቸው፣ይልቁንም ጉዳዩ የኦሮሞ ሕዝብ  አምኖ የሰጣቸውን እንደመክዳት እንደሚቆጠር ገልጠዋል።የአቶ ለማ ንግግር ለምን ቀድሞ አልተነሳም? በውህደቱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይስ  ድምፃቸውን ሲሰጡ ለምን ተቃውሞ አልተነሳም? በተለይ ዛሬ ዘሐበሻ ዜና ላይ እንደዘገበው የኦዴፓ  ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንዳ ለኤስኢቢኤስ ራድዮ ተናገሩት ባለው ዘገባ ላይ አቶ ለማ ከእዚህ በፊት በየትኛውም ቦታ የውህደቱን እና የመደመርን ጉዳይ አስመልክቶ ተቃራኒ ሃሳብ እንዳላቀረቡ  መግለጣቸውን ዘግቧል።ይህ ከሆነ ዛሬ ለምን አነሱት?

አቶ ለማ ምን ሆነው ነው?

እነኝህን እና ሌሎች ሁኔታዎችን ስንመለከት አቶ ለማ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያዊነት ስሜቱ ይልቅ ያየለባቸው (ያስጨነቃቸው) በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ ከሃዲ ልቆጠር ነው የሚለው ጭንቀት ነው።ከእዚህ ውጪ ከእዚህ በፊት በእየመድረኩ ከነገሩን አንፃር ስናየው የአቶ ለማ ሃሳብ ማጠንጠኛ ምላሽ የሚያገኘው ከመደመር እና ከኢሕአዴግ ውህደት ውጪ የተሻለ የሚያረካቸው ሃሳብ ሊገኝላቸው አይችልም።  እና አሁን አቶ ለማ ለምን እጃቸውን ሲያወጡ ባላፈሩበት ጉዳይ  ዛሬ ተቀይረው ሌላ ሃሳብ አነሱ? ጉዳዩ ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን  የሚከተሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች ጠይቆ ማለፍ ይቻላል። እነርሱም -

  • አቶ ለማ መደመር እና የውህደቱ ሂደት እዚህ ደረጃ እንደማይደርስ እርግጠኛ የሆኑበት የማናውቀው በሚስጥር የያዙት ፕሮጀክት ስለነበር ነው እስከዛሬ ዝም ብለው የቆዩት?
  • አሁን ያ ያሉት ፕሮጀክት መክሸፉን ሲመለከቱ እራሳቸው በቀጥታ ሊገቡበት አሰቡ?
  • ወይንስ እንዳሉት መደመር እና ውህደቱ ሳይገባቸው እና ሳይስማሙበት ቆይተው ነበር?
በማስከተል የሚነሳው ጥያቄ አቶ ለማ ይህንን በማለታቸው በመደመር እና የኢህአዴግ ውህደት ላይ የሚመጣው ተፅኖ አለ ወይ? የሚለው ነው።የውህደቱ ጥያቄ ከኢህአዴግ በላይ እየገፉበት ያሉት የአጋር ድርጅቶች ናቸው።ከእስነርሱ ጋር የውህደት ደጋፊዎች ኢሕአዴጋውያን  እና የጎሳ ፖለቲካ ያሰጋው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከውህደቱ ጋር ቆሟል።ከእዚህ በተጨማሪ የተቃዋሚ የዜግነት እና የአንድነት ኃይሎች ሁሉ የውህደቱን ሂደት ይደግፋሉ። በአንፃሩ የጀዋር የፅንፍ ኃይል እና በኦዴፓ ውስጥ የተሰገሰጉ  የብሔር ድርጅቶች ውህደቱን ይቃወማሉ።ከእነሱ በተጨማሪ ህወሓት ዋነኛ ተቃዋሚ ብቻ ሳትሆን በመጪው ሳምንት ወደ ስድስት መቶ ሰዎች የሚሳተፉበት የፈድራሊስት አስተሳሰብ አራማጆች በማለት የተራቻቸውን አበል እየከፈለች መቀሌ ላይ ለመሰብሰብ አቅዳለች። 

በሌላ በኩል የውህደቱን ሃሳብ ካለምንም ድርድር እንደሚቀበለው በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው የጦር ሰራዊቱ ነው።በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት አደረጃጀቶች የህዝቡ የጎሳ ስሜት ያላጠቃው አካል የሚገኘው በጦር ሰራዊቱ በተለይ በመካከለኛ እና የመስመር መኮንኖች እስከ ተራ ወታደር ያለው የውህደቱን ሃሳብ ይደግፋል። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው።የጦር ሰራዊቱ የአንዲት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚያተኩር ሆኖ የተሰራ እንጂ በብሄር የተከፋፈሉ ፓርቲዎች የራሱ ራስ ምታት እንደሆኑ ስለሚያውቅ ፈፅሞ መከፋፈልን ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የውህደት እና የመደመር ሃሳብ የሚቀበል  ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በጦር ሰራዊቱ መካከለኛ እና የመስመር መኮንኖች ጀምሮ እስከታችኛው ወታደር ድረስ በጣም የሚወደዱ መሪ ናቸው።ስለሆነም የውህደቱ ሂደት ፈፅሞ ሊገታ የሚችልበት ደረጃ አይደለም።  ለእዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የብልፅግና ፓርቲ ገና የምስረታ ጉባኤ ሳይጠራ በኦሮምያ ክልል ያለውን ቢሮ እንዲያደራጅ ሹመት መስጠት የጀመሩት።

በቀጣይስ ምን ሊከሰት ይችላል?

የአቶ ለማ የአመለካከት ለውጥ ትናንሽ ጭረቶችን ከማምጣት ያለፈ በውህደቱም ሆነ በመደመር ሂደት ላይ አንዳች ለውጥ አያመጣም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣት በምንም መመዘኛ ለማየት ብንሞክር ከኢህአዴግ እውነተኛ ውህደት እና ከመደመር እሳቤዎች ውጪ  ህመሟን ልታስታግስበት  የሚችል አንዳች ነገር የለም።ይልቁንም ይህ የመፍትሄ ሂደት በፍጥነት ባይመጣ ኖሮ በኦደፓ እና በአደፓ ውስጥ የገባው የፅንፍ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ወደ አልታወቀ የማዕበል አዘቅት ውስጥ ሊወስዳት ተዘጋጅቶ እንደነበር ለማየት ይቻላል። በሌላ በኩል የአቶ ለማ የሃሳብ ልዩነት ምንም ጭረት አያመጣም ማለት አይደለም።በመጀመርያ ደረጃ አቶ ለማ ለይተው ወደ ፅንፍ ኃይሎች ጎራ ይገባሉ ወይንስ የራሳቸውን አስተሳሰብ ይዘው  የራሳቸውን እና የተከታዮቻቸውን ሃሳብ ይዘው ፓርቲ ይመሰርታሉ? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ጥያቄ ነው።ሌላው ጥያቄ አቶ ለማ በኦደፓ ውስጥ የለዘብተኛ መስመርን ነው ወይንስ የኦነግን መስመር ይከተላሉ? የሚለው  ነው።አቶ ለማ ወደ ፅንፍ ጎራ ይገባሉ ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስልም። ወደ ኦነግ ጎራም ይገባሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም።ምክንያቱም ኦነግ እራሱ የፖለቲካ መሰረቱ ከመናጋት አልፎ ሃሳቡን መግለጥ ሲያቅተው እየተኮሰ እና እያስተኮሰ የራሱን ወገን የሚወጋ  አካል ሆኗል።ስለሆነም አቶ ለማ ለጊዜው የሚያደርጉት አንድ በልዩነት ተቀምጠው ለጥቂት ጊዜ ማየት አልያም የራሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው በምርጫ መወዳደር ሊሆን  ይችላል።አቶ ለማ ሶስቱንም መንገድ ቢሄዱ ግን ኦደፓ ለሶስት መሰንጠቁ የማይቀር ነው።ኦደፓ ለሶስት ተሰነጠቀ የሚል ታሪክ ሳይፃፍበት ብልሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ውህደቱን በማብሰር ያለፈ ታሪኩ ሳይጎድፍ እንዲፃፍ ሊረዱት ይችላሉ። አቶ ለማ ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ ቢረዱ ኖሮ ዝም ቢሉትም ለሶስት ማለትም የውህደት ደጋፊዎች፣የፅንፍ አቅራሪ ኃይሎች እና የለዘብተኛ ብሄርተኞች ክፍል ሆኖ መከፈሉ የማይቀር ነበር።አቶ ለማ ትናንት የሰጡት ሃሳብም የእዚህ የስንጥቁ  አንድኛው ድምፅ ነው።

ማጠቃለያ 

ለማጠቃለል አቶ ለማ መገርሳ የፈለጉትን ሃሳብ መስጠታቸው የሚከበር እና ሊከበር የሚገባ ነው።ግለሰቡ ስብእናቸውም  የሚናቅ አይደለም።ቆራጥ እና ሀቀኝነት የታየበት አሰራር አሳይተዋል።ወደፊትም የኢትዮጵያ የክብር ሰው ሆነው መቀጠላቸው አይቀርም። በተለይ በቅንነት የኦሮሞ ብሔርተኝነት ይጨፈለቃል ብለው ለሚሰጉ እንደ አቶ ለማ ያሉ ኢትዮጵያዊ ሃሳብ ያላቸው ግን ብሔርተኝነትን  በአንክሮ የሚያዩ ሰዎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠቃሚ እንጂ ጉዳይ የለውም። አቶ ለማ አንዴ በጎ ኢትዮጵያዊ ሃሳባቸውን ገልጠዋል።ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚወስድባቸውም ሆነ በችሮታ የሚሰጣቸው የለም። ድሮም አብሯቸው የኖረ  እና ወደፊትም የሚኖር ነው።ይህ ሁሉ ሆኖ አቶ ለማ የሚመዘኑት ከእዚህ በፊት ከሰሩት ይልቅ ከአሁን በኃላ በሚያደርጉት ነው።እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሃሳብ አቶ ለማ የውህደቱን ሂደት የሚያደናቅፍ አንድም ድርጊት ባያደርጉ እና  የመደመርን ሃሳብም በሳይንሳዊ መንገድ ከመተቸት አልፈው ወደ ሌላ አላስፈላጊ ተግባር እንዳይሄዱ  ምክሮች ሁሉ ተሰብስበው መናገር አለባቸው።ኢትዮጵያ በ21ኛው ክ/ዘመን እንደመሆኗ የብሔር ፖለቲካ ደክሟታል። ከእዚህ በላይ ትከሻዋ አይሸከምም።የብሔር ፖለቲካ ቶሎ ቆስሉ ስለማይድን እንጨፈለቃለን ብለው ለሚሰጉ እንደ አቶ ለማ ያሉ ወጣ ብለው ሁኔታውን እየተከታተሉ አገር ያረጋጉ ይህ ክፋት የለውም።የመጨረሻው መጨረሻ ሃሳብ ግን አቶ ለማ ሃሳብ ሌላ ጊዜ ሲኖርዎት እባክዎን የአገር ውስጥ ሚድያዎችን ይጠቀሙ።ይህ ሰነድ ነው።ይህ አገራዊ ጉዳይ ነው። በእዚህ ዘመን ሃሳብን ለመግለጥ የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ ድረስ መሄድ ብዙም አያሳምንም። ይልቁንም አላስፈላጊ የባዕዳን ተወዳጅነት ለማትረፍ የተደረገ ቁጭ ብድግ ያስመስላል።ከእዚህ ውጪ አቶ ለማ በሃሳብዎ ልዩነት እናከብርዎታለን እንጂ አንጠላዎትም።ወደፊት በሚሄዱት አካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመዳኘት በአንክሮ እርስዎን እና ተከታዮችዎን ይከታተላል። ውህደቱ እና መደመር ግን ይቀጥላል። የሚቀጥለው ደግሞ የተሻለ መንገድ ስለሌለ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አዋጪ ስለሆነ ነው።በመጪው ጊዜም በግልጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን የበለጠ የሚገልጥበት ጊዜ ይሆናል።  



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።