ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, May 6, 2019

የአማርኛ ትምህርት ቤት ያለህ! ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ


ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ
ሚያዝያ 28/2011 ዓም (ሜይ 6/2019 ዓም)
የአንድ ሀገር ሕዝብ ስልጣኔ በበሰለ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ በተሸጋገረ የቋንቋው  ጥልቀት እና ምጥቀት ይለካል።ስልጣኔ የህንፃ እና የፋብሪካ መደርደር ብቻ አይደለም።ስልጣኔ የአንድ ወቅት ክስተት ሆኖ እንዳይጠፋ እና ተሻጋሪ እንዲሆን የቋንቋ መኖር አስፈላጊ ነው።ቋንቋ ከቋንቋ አይበላለጥም።ይህ ማለት ግን ጥንታዊ መሰረት የያዘ ፊደል፣የቃላት ሀብት፣በውስጡ የያዛቸው የታሪክ መድበሎች ሁሉ ግን አንዱን ቋንቋ ከሌላው የበለጠ የበለፀገ ነው አይደለም የሚለው አያከራክርም ማለት አይደለም።

የጉዳያችን የዛሬ መነሻ እና መድረሻ ስለ ቋንቋ ለማተት አይደለም። ጉዳዩ የአማርኛ ቋንቋ አሁን ባለንበት ዘመን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት አለው? ብሎ ለመጠየቅ እና የሚመለከታቸው ሁሉ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሹበት  ለማሳሰብ ነው።ጉዳያችን በእዚህ ዓመት አዲስ ሃሳብ በሚል ርዕስ አልፎ አልፎ ሃሳቦችን ለመሰንዘር እና በዓመቱ መጨረሻ ላይ የትኞቹ ተከናወኑ? የትኞቹ የሚሰማቸው አጡ? በሚል ሀሳብ ለማንሸራሸር ማቀዷን እና በእዚህም መሰረት በያዝነው የ2011 ዓም ወደ ሶስት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸው እና አሁን ይህ አራተኛው ሀሳብ መሆኑን ለማስታወስ እፈልጋለሁ።ይህ ማለት በአዲስ ሀሳብ ስር የሚቀርቡትን እንጂ ሌሎች ዘገባዎች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ሳይጨምር ማለት ነው።

የአማርኛ ትምህርት ቤት ያለህ!

በሐያ አንደኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ በሯን ለውጭው ዓለም ለመክፈት እየሞከረች ነው።በቅርቡ በተፈጠረው የመንግስት ለውጥ (ጥገናዊ ለውጥ) ወዲህ ብቻ ኢትዮጵያ ላይ መላው ዓለም ትኩረቱን መድረጉን ብቻ ሳይሆን ከኢንቨስትመንት እስከ ቱሪስት ማዕከል ለመጠቀም በርካታ ዓለም አቀፍ የገበያ አጥኚዎች ትኩረታቸው ሆነናል። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ደርሶ የመጣ አንድ ወዳጄ ምን ተመለከትክ ስለው ከተመለከተው ውስጥ ከዋጋ ንረት በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት ወደ ሀገሪቱ መግባት መውጣታቸውን ነው ብሎኛል።

በጥገናዊ ለውጡ ሂደት ወደፊትም በርካታ የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ማሳያዎች አሉ። ከእነዚህ ማሳያዎች ውስጥ -

  • አፍሪቃውያን ወደ ኢትዮጵያ ካለ ቪዛ እንዲገቡ መፈቀዱ።
  • የቻይና ኩባንያዎች የበለጠ ፕሮጀክቶች እየወሰዱ መሆናቸው፣
  • ለስደተኞች የተሰጠው የመስራት መብት፣
  • የቱሪስት ፍሰቱ መጨመሩ እና 
  • መንግስት ታላላቅ የሀገሪቱ ኩባንያዎችን በከፊል ወደ ግል ለማዞር እያስጠና መሆኑን እና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ የበለጠ የመምጣታቸው ፋይዳ መጨመሩን ነው።
እነኝህ እና ሌሎች ጉዳዮች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ሰላሟን ጠብቃ መሄድ ከቻለች እና የፖለቲካ ሁኔታው በትክክል መስተካከል ከቻለ የብዙ የውጭ ዜጎች መዳረሻ መሆናችን ነው።ይህ በራሱ በበጎ ልንመልከተው የሚገባ ነው።ከውጭ ዜጎች የምንማረው እና የምናገኛቸው በርካታ ነገሮች አሉ።የሙያ ክህሎት፣አሰራሮች፣የስራ ትጋት እና ቴክኖሎጂ ሁሉ የማግኘት ዕድሎች አሉ።በአንፃሩ ሌሎች አሉታዊ ጉዳዮች የሉም ማለት ግን አይደለም።አሉታዊ ጉዳዮች ላይ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ቀድሞ እያጠና የማረም እርምጃ መውሰድ ይችላል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሚገጥማቸው አንዱ ችግር የቋንቋ ጉዳይ ነው።በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የሚነገረው እና የጋራ ቋንቋ ሆኖ ያለው በአሁኑ ሰዓት አማርኛ ነው። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋም ነው።ወደፊት ሌሎች ብሔራዊ ቋንቋዎች ሊኖሩን ይችላሉ።ይህ በራሱ ችግር የለውም።አሁን ግን ስለ አማርኛው እናውራ።

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሀገራቸውን ብሔራዊ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በእየከተሞች ማግኘት ትልቅ እና አድካሚ ሥራ አይደለም።ከስልሳ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ተናጋሪ ያለው አማርኛን ልማር ብሎ አዲስ አበባ ላይ በሥራ የተጠመደ አንድ የውጭ ዜጋ ግን የት ነው ሄዶ የሚማረው? በርካታ ቻይናዎች አማርኛ የተማሩት የት ነው? አሜሪካኖቹ አማርኛ የት ይማሩ? የአፍሪካ ሕብረት አማርኛ መጠቀም አለበት እያሉ የሚሟገቱ አፍሪቃውያን የት ትምህርት ቤት ገብተው ይማሩ? በልማድ በራሳቸው ካልተማሩ ደረጃ የወጣለት አንድ የአማርኛ ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ላይ አለ? ትምህርት ቤቱስ በትምህርት ሚኒስትር ደረጃ ወጥቶለት አማርኛ ለተማረው ሰው ሰርጠፍኬቱ እውቅና አለው? አንድ በአማርኛ ትምህርት በቂ ትምህርት ዕውቀት ያለው ሰው ወይንም ባለ ሀብቶች ሰብሰብ ብለው በብዙ የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ከተሞች  አዲስ አበባን ጨምሮ ቢከፍቱ እና ትምህርት ሚኒስትር ደረጃ ቢያወጣለት ትልቅ ገበያ የለውም? ብዙ አፍሪካውያን፣ቻይናውያን፣ሌላው ቀርቶ ውጭ የተወለዱ በሺህ የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ቤቱን አያጥለቀልቁትም? ባለ ሀብቶች እና ባለ ዕውቀቶች ተጠቀሙበት።ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአማርኛ ደረጃ አውጡለት።ስለ አማርኛ ብዙ እንደምትቆረቆሩ የምትነግሩንም ብዙ ከምታወሩ ይህንን ፍሬ ያለው ሥራ ስሩና ትውልድ አሻግሩ።ሀገር ጥቀሙ። 




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...