ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, December 14, 2015

ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያውያንን አትግደሉ ብለው መቃወም አለባቸው! በኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ መነሻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው? መፍትሄውንስ ከምን አንፃር መመልከት ይገባል? (የጉዳያችን ማስታወሻ)


በአገራችን ኢትዮጵያ ሰሞኑ በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ ችግሩ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።የችግሩን ምንጭ አንዳንዶች በእራሳቸው የግንዛቤ ልኬት እንደፈለጋቸው ሊመሩት ይፈልጋሉ።የግለሰብ  እና የአንድ ቡድን የግንዛቤ ልኬት እና የሕዝብ ልኬት የተለያዩ ናቸው።ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው አመፅ በአሁኑ ሰዓት ችግርን በውይይት እና በተጠያቂነት የመፍታት ባህል የሌለው ስርዓት ሰራዊቱን በሙሉ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን መንደር አሰማርቶ በመግደል ችግሩን ለመፍታት ይሞክራል።በዛሬው እለት ብቻ 25 ኢትዮጵያውያን በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።ይህ ቁጥር ከሰሞኑ በእጅጉ ሊጨምር ይችላል።ከእዚህ የከፋ ችግር ሳይፈፀም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያውያንን አትግደሉ ብለው መቃወም አለባቸው።ይህ በእንዲህ እያለ ግን በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ መነሻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?  መፍትሄውንስ ከምን አንፃር መመልከት ይገባል

አሁን የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ የችግሩ ዋና መነሻ:-

1/ የስርዓቱ ዘራፊ ባለስልጣናት ስግብግብነት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የመሬት ዝርፍያው ቅጥ በማጣቱ እና በእያንዳንዱ ገበሬ ህልውና ላይ በመምጣቱ፣
2/ ስርዓቱ 24 ዓመታት ሲያራግብ የነበረው የጎሳ ፖለቲካ መልሶ እራሱንም የሚያገለው እና የሚገፋውን የባሰ የጎሳ የፖለቲካ ጥያቄ ከሀብት (resource) ጥያቄ ጋር አብሮ ጠንክሮ በመምጣቱ ስርዓቱ እና ስርዓቱ ደግሞ በእርጋት የመፍታት ባህሪ ስለሌለው  በኃይል ለመፍታት መሞከሩ፣
3/ የነፃ ሚድያ መረጃ ስለታፈነ ቀድመው የችግሩን መኖር ደረጃ በደረጃ የሚገልጡ እና ህዝቡ ውስጥ የሚንተከተከውን ስሜት ለሁሉም አካል የሚገልጡ ጋዜጠኞች እንዳይናገሩ እና እንዳይፅፉ መታሰራቸው እና መሰደዳቸው እና
4/  የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው ኦህዴድ በእራሱ የዝርፊያው ተዋናይ ስለነበር ከስርዓቱ መሪዎች ጋር የጥቅም ግጭት መግባቱ የሚሉት ናቸው።

የችግሩ መፍትሄ:-

1/ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች መኖራቸውን ማመን፣

2/ ችግሩን በጊዚያዊነት አለባብሶ ለማለፍ አለመሞከር፣

3/ ይህ የተነሳው ችግር ለጊዜው ይዞት የተነሳው የአዲስ አበባ ፕላን ጉዳይ ይሁን እንጂ በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች በእየዘመኑ ከአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ከመኖራቸው በላይ ይብሱን ባለፉት 24 ዓመታት  ውስጥ በተለየ መልኩ የክልሉ ተወላጆች በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከአገሪቱ የስልጣን እርከኖች መራቃቸውን መገንዘብ።
ለምሳሌ ላለፉት 100 ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ብንመለከት የጦር ኃይሉን ከአፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ በፍፁም ኢትዮጵያዊነት  በበላይነት ይመራ የነበረው የክልሉ ሕዝብ ምን ያክል ባለፉት 24 ዓመታት እንደተገለለ እና በስርዓቱ ከፍተኛ ንቀት ይፈፀም እንደነበር መገንዘብ።ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅስብራት’ ነው።በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ዘመንም ሆነ በደርግ ዘመን በጦር ኃይሉ እና ፖሊስ ሰራዊት ከከፍተኛ መኮንኖች እስከ ታች ባሉ ባለማእረጎች የክልሉ ተወላጆች አገራቸውን አገልግለዋል። ይህ ስርዓት በመንገድ ላይ ለማኝ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት ውስጥ በርካቶች የኦሮምኛ ተናጋሪ እንደነበሩ ብዙዎቻችን እንረሳለን።

4/ በየትኛውም አቅጣጫ በስርዓቱ የውስጥ ሴራ የሚነሱ የክልሉን ሕዝብ ከሌላው ጋር ለማጋጨት የሚሞከሩ ማናቸውንም ሙከራዎች ማክሸፍ። ለምሳሌ የሱማሌ ክልልን በኦሮሞ ላይ እንዲዘምት፣የአማርኛ ተናጋሪዎችን ከኦሮምኛ ተናጋሪዎች ጋር ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራ ነቅቶ መጠበቅ እና እንዲሁም የትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ በጠላትነት የሚመለከቱ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎች አሁንም የስርዓቱ አቀንቃኞች ሥራ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት፣እንዲሁም  በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በግንፍልተኞች አንዱን በተለየ መልክ ለማጥቃት የሚደረጉ ሙከራዎች ወይንም ድርጊቶችን  የአጠቃላይ ሕዝብ ሥራ አድርጎ ከማቅረብ መጠንቀቅ እና


5/ ይህንን ከፍተኛ የሕዝብ መነሳሳትን ከመላው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄዎች ጋር ማስተሳሰር እና ከፅንፈኛ የእስልምና አደጋዎች መታደግ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ታኅሳስ 4/2008 ዓም (December 14/2015)

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...