ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 3, 2024

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል።


በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡ 
  • ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ? 
  • የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመረጡ?
  • የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እነማን ናቸው? የትምሕርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸውስ?
  • የኮሚሽኑ ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?
  • የኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው?
  • የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን ምን ምን ናቸው?
  • የምክክር ኮሚሽኑን የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?
  • የውይይት ሰነዶች ከውይይት በኋላ ምን ይሆናሉ?

=========
ጉዳያችን ልዩ 
=========

መነሻ 


ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከመሰረታዊ ችግሮቻችን ውስጥ ደጋግመው የሚነሱት እና ለሀገር መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ደጋግሞ ሲወሳ ከነበረው ውስጥ አንዱ የተቋማት መመስረት እና መጠናከር ጉዳይ ነው። የመንግስት መምጣት እና መሄድ ጉዳይ አንድን ሀገር ለመተራመስ እንዳይዳረግ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የጠንካራ ሀገራዊ ተቋም የመኖር ፋይዳ ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት እያየን ያየነው አንዱ እና በጎ ተግባርም ይሄው የሃገራዊ ተቋማት መፈጠር ነው። ተቋማቱ ደግሞ ካለፉት መንግስታት እጅግ በተሻለ እና አንዳንዶቹ በጥሩ ነፃነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን የተቋማቱ አመሰራረት ሕጋዊ ዕውቅና የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይስጥ እንጂ የተቋማቱ የትኩረት አቅጣጫ፣የመሪዎቻቸው ነፃነት እና የአፈፃፀማቸው ውጤት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። ከእነኝህ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣የምርጫ ቦርድ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን መጥቀስ ይቻላል። የዛሬው ትኩረቴ የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን በተመለከተ በተለይ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ የመረጃ ክፍተት እንዳይኖረው በሚል በእዚህ ጽሑፍ ውስጥ አስፈላጊ መረጃ ይሰጣሉ ያልኩትን ለመግለጽ እሞክራለሁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዴት ተመሰረተ?

ታኅሳስ 1፣2014 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙና አካታች አገራዊ ምክክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይህንኑ ምክክር በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ ላከው።

በእዚህ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት የነበረ ሲሆን በእዚሁ ውይይት ላይ  የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፍትሕ ሚኒስትርና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡በውይይቶቹ ውስጥ ከተነሱት እና አጽንኦት እንዲሰጥባቸው ከተወሱት ውስጥ የኮሚሽነሮች አሰያየም፣ አወቃቀርና የኮሚሽኑ አደረጃጀት ላይ ያላቸውን ሥጋትና የገለልተኝነት ሁኔታዎች ላይ ጥልቅ  ውይይት በኃላ ታኅሳስ 20፣2014 ዓም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 11 ያለመከሰስ መብት ያላቸው ኮሚሽነሮች አሉት።በኮሚሽነሮቹ መብዛት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሃሳብ ሰጥተዋል። የኮሚሽኑ ዋና ተግባር ልዩነትና አለመግባባት ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚሠራ ነው።

የኮሚሽነሩ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመረጡ?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማኅበረሰቡ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነሮችን እንዲጠቁም በማድረግ ከ600 በላይ ዕጩ ኮሚሽነሮች መጠቆማቸውን ይፋ ሆነ።
ከእነዚህ ውስጥም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነር ይሆናሉ ያላቸውን 42 ግለሰቦች ህብረተሰቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ዝርዝራቸውን ይፋ አደረገ።

በመቀጠል ምክርቤቱ ከማህበረሰቡ የተገኘውን ግብዓት መሰረት በማድርግ መስፈርቱን በከፍተኛ ደረጃ አሟልተዋል ያላቸውን 11 ኮሚሽነሮች ሾሟል።

የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እነማን ናቸው? የትምሕርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸውስ?

1.ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ፡

የትምህርት ደረጃ፡ ፒ ኤች ዲ በአእምሮ ህክምና

የስራ ልምድ ፡ በአእምሮ ህክምና ዘርፍ ከ30 አመታት በላይ ያገለገሉ፣ ከ30 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያሳተሙ፣ ብሄራዊ የኤች አይ ቪ ሴክሬታሪያት እንዲቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ፣ በተለያዩ የሀገራችን ከፍሎች በመዘዋወር ሆስፒታሎችን የመሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በአማኑኤል ሆስፒታሎች በኃላፊነት ያገለገሉ፣ በተለያዩ ሀገራዊ የሰላም መድረኮች በሚያቀርቧቸው አስተማሪና መካሪ ሀሳቦች በመነሳት ለሀገራዊ መግባባት እየሰሩ ያሉ፡፡

2. ወይዘሮ ሒሩት ገብረስላሴ ፡

የትምህርት ደረጃ: በህግ ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው
የስራ ልምድ፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ልዩ መልእክተኛ ሆነው ያገለገሉ፤ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሰሩ

3. ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ

የትምህርት ደረጃ: ፒ ኤች ዲ እና ሁለት ማስተርስ በኢኮኖሚክስና ፖለቲካ
የስራ ልምድ፡ በተመድ ልማት ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ፤ በሀገራት የልማት ፕሮግራሞች የመሩ፤ በርካታ ፅሁፎችን ያበረከቱ፤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ፤ የልማት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ያገለገሉ፤ ግጭቶችን ለመፍታት አለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው፤የተመሰከረ የአመራርና የአስተዳደር ክህሎት ያላቸው

4. አምባሳደር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ

የትምህርት ደረጃ: ፒ ኤች ዲ በህግ የስራ ልምድ፡አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ፤ በተለያየ የሀላፊነት ቦታ የሰሩ

5. ወይዘሮ ብሌን ገብረመድህን

የትምህርት ደረጃ: ማስተርስ ዲግሪ

የስራ ልምድ፡የህግ መምህር የነበሩ፤ ያለም አቀፍ ልማት ማዕከል ቢሮ ሀላፊ የነበሩ፤ በቀይ መስቀል ማህበር ውስጥ በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆነው የሰሩ፤ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን እያገለገሉ ያሉ፤

6. ዶክተር ዮናስ አዳዬ

የትምህርት ደረጃ: ፒኤችዲየስራ ልምድ፡ ተመራማሪ እና አሰልጣኝ

7. አቶ ዘገየ አስፋው

የትምህርት ደረጃ: በህግ የማስተርስ ዲግሪ
የስራ ልምድ: ላለፉት 40 አመታት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ አገልግሎት የሰጡ

8. አቶ መላኩ ወልደማሪያም

የትምህርት ደረጃ: በህግ የመጀመርያ ድግሪ
የስራ ልምድ፡ ጠበቃና የህግ አማካሪ፣ በህዝባዊ ተቋማት በርካታ ሁኔታ አገልግሎት የሰጡ፣ በሽግግር መንግሰት ምክር ቤት በህግ አማካሪነት፤ በመንግስት ምክር ቤት በህግ ባለሙያነት፤ በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ዋና ፀሀፊነት፤ በልማት ማህበራት በአመራርነት የሰሩ፡፡

9. አምባሳደር መሃሙድ ድሪር

የትምህርት ደረጃ : በህግ የማስተርስ ድግሪ
የስራ ልምድ፡በምክር ቤት አባልነት፤ በአምባሳደርነት፤ በሚንስትርነት፤ በከፍተኛ አማካሪነት፤ በኢጋድ አስተባባሪነት፤ በሱዳን ልዩ መልእክተኝነትና በአፍሪካ ቀንድ ሰፊ ልምድና እውቀት ያላቸው።

10. አቶ ሙሉጌታ አጎ

የትምህርት ደረጃ፡ በህግ የማስተርስ ዲግሪ
የሥራ ልምድ፡ ለ 4 ዓመታት በከፋ ዞን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እና ፕሬዚዳንት፣ በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጠ/ፍ/ቤት ዋና ሬጅስትራርነት ለአንድ ዓመት የሰሩ፣ በዳኝነት ለሰባት ዓመት የሰሩ፣ በም/ ፕሬዚዳትነት ለሁለት ዓመትና በፕሬዚዳንትነት ለ8 ዓመታት ያገለገሉ

11. ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ

የትምርት ደረጃ: በሶሻል አንትሮፖሎጂ ፒኤችዲ

የስራ ልምድ፡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እና በአሁኑ ሰዓት በሰላምና ዲያሎግ ከፍተኛ አማካሪነት እያገለገሉ ያሉ ፤ በማክስ ፕላንክ የስነ ህዝብ ጥናት ተቋም ያገለገሉ እና በዚሁ ተቋም የማህበራዊ አንትሮፖሎጂ ተቋም በግጭትና ውህደት ክፍል ውስጥ የድህረ ዶክትሬት ጥናት አድርገዋል::

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ርዕይ፣ተልዕኮ፣ዓላማው እና መርሆዎቹ ምንድን ናቸው?

ርዕይ

የኮሚሽኑ ርዕይ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡

ተልዕኮ

በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓ በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፡፡

ዓላማዎች

  • በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፤
  • የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ ማድረግ፤
  • የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት፤
  • ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፤
  • ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር፤
  • ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላድል ማመቻቸት፤
  • ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት መጣል ናቸው።

የምምክር ኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶች

  • ምክክሮችን የሚያመቻቹና ሚያስፈጽሙ፣ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሂዱ እና ምክረ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ኮሚቴዎችን እና የባለሙያ ቡድኖችን ያቋቁማል፤
  • ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን ያጠናል፣ በቀጣይ ለሚያካሂዳቸው ሀገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት ይጠቀማል፤
  • በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም ይለያል፤
  • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አቀጽ (፫) መሰረት በተገለፁት ዘዴዎች የለያቸውን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ የምክክር አጀንዳዎችን ይቀርፃል፣ ምክክር እንዲደረግባቸው ያመቻቻል፣ ምክክሮችን እና ውይይቶችን ያሳልጣል፤
  • ከመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና አካላትን የሚወክል ተሳታፉዎች የሚሳተፍባቸው፣ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በፌደራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ ያመቻቻል፤
  • በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፉዎችን ግልፅ በሆኑ መሥፈርቶች እና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል፣ በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል፤ ይህን የተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ያወጣል፤
  • ምክክሮቹ በኮሚሽነሮች ወይም የኮሚሸነሮች ምክር ቤት በሚሰይማቸው አወያዮች አማካኝነት እንዲመሩ ያደርጋል፤ በአወያይነት የሚመድባቸዉ ሰዎችም በተቻለ መጠን በዚህ ሕግ አንቀጽ ፲፫ ላይ የተመለከቱትን ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸዉን ያረጋግጣል፤
  • በምክክር ሂደቶች የሚደረጉ ምክክሮችን ቃለ ጉባዔ የሚዙ፣ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የሚያጠናቅሩ እና አደራጅተው ለኮሚሽነሮች ምክር ቤት የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ይመድባል፤
  • የጽህፈት ቤቱን የውስጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የምክክር አጀንዳዎች ወይም አርዕስት የሚመረጡበትን የሚመለከት፣ በሀገራዊ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ሥርዓት ለመዘጋትና መሰል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውስጠ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ያወጣል፣ በሥራ ላይ ያውላል፤
  • የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ያቀርባል፤ ለሕዝብም ይፋ ያደርጋል፤
  • መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል፤
  • የምክረ ሃሳቦቹን አፈፃፀም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ዓላማውን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።

የኮሚሽኑ ምክርቤት ተግባርና ሥልጣን

  • የሕዝብ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር በመፈተሽ ምክክር እንዲደረግባቸው መወሰን፤
  • በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስፈፃሚ አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን ዓመታዊ በጀትና ዕቅድ መርምሮ የማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን አጠቃላይ ሪፖርት መርምሮ የማፅደቅ፤
  • አስፈላጊ ኮሚቴዎችን የማቋቋም፤
  • በክልሎች የጽህፈት ቤቱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲቋቋሙ የመወሰን፤
  • የጽህፈት ቤቱን የኦዲት ግኝት መርምሮ የማፅደቅ፤
  • የምክር ቤቱ ዋና ኮሚሽነርና ምክትል ዋና ኮሚሽነር በተመሳሳይ ጊዜ በሥራ ገበታቸው ላይ ለተከታታይ አስር ቀናት ካልተገኙ ከአባላቶቹ መካከል ጊዜያዊ ሰብሳቢ የመምረጥ፤
  • የጽህፈት ቤቱን መዋቅራዊ አደረጃጀት የማፅደቅ፤
  • የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ሹመት የማፅደቅ፤
  • አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን የማውጣት፤
  • የኮሚሽነሮች የሥነ ምግባር መመሪያ የማውጣት፤
  • የጽህፈት ቤቱን የመተዳደሪያ ደንብ የማውጣት፤

የምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላም አንዱ እና ዋናው መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?


የዛሬ ሦስት ዓመታት በታኅሳስ አጋማሽ ላይ የእዚህ ዓይነት ተቋም አስፈላጊነት ላይ ውይይት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‹‹ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዲፕሎማሲና ልማት በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይደረግ?›› በሚል ርዕስ  ምሁራንን ያካተተ የፓናል ውይይት ተደርጎ ነበር።በእዚሁ ውይይት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም መምህርና ‹‹ብሔራዊ ደኅንነት በኢትዮጵያ›› በሚል የጥናት ርዕስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አቶ ዮናስ ታሪኩ ‹‹ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የማንን ደኅንነት እናስጠብቅ›› የሚለው ላይ አለመግባባት መኖሩንና በዚህም ምንክያት የአገሪቱ ደኅንነት ፍትጊያ ውስጥ መግባቱን መናገራቸው ተዘግቧል።

በእርሳቸው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተገለጠው የሃገረ መንግስቱ መጠበቅ የቡድን መብት መጠበቅ ለምሳሌ በቋንቋ እና ማንንነት ላይ ያለው ከለላ ትኩረት እንዲሰጠው የሚፈልጉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ሃገረ መንግስቱ መጠበቅ ላይ ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ይዞ መጓዝ እንዳለበት አጥብቀው የሚያሳስቡ እንዳሉ ገልጠዋል። አቶ ዮናስ ማብራርያቸውን በመቀጠል የሁለቱ ቡድኖች ሃሳብ እርስ በርስ የሚጋጩ አስመስሎ በማቅረብ ችግር የመፍጠር ሁኔታ መሆኑን ገልጠው ይህ ግን ወደ ግጭት ሊያመራ እንደማይገባ አብራርተዋል።ይህ እና ሌሎች ጥናቶች የሚያሳዩት የምክክር ኮሚሽን ተግባር ለኢትዮጵያ የደኅንነት እና ሰላም አንዱ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው።|

የውይይት ሰነዶች ከውይይት በኋላ ምን ይሆናሉ?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ደረጃ የማያግባቡ አጀንዳዎችን መርጦ በሰነድነት አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ አና የሚቋጩትን በመቋጨት ያልተቋጩትን ደግሞ በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ ትልቅ ሀገራዊ አደራ ተቀብሏል። ሌላው እና የኮሚሽኑ ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን የሚያሳየው የኮሚሽኑ ተግባር ደግሞ የውይይት ሰነዶቹ ሂደት ጭምር ለቀጣይ ትውልድ መማርያ እንዲሆኑ በሚገባ በሰነድነት ሰንዶ ለብሄራዊ ቤተ መዛግብት የሚያስረክብ ሲሆን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰነዶቹን በፈለገ ጊዜ ለመመልከት እንዲችል ሁኔታዎች የሚመቻቹ መሆናቸው ነው።

ለማጠቃለል

የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ዓይነት ኮሚሽኖች በበርካታ ሀገሮች ሀገራዊ ችግሮችን ፈትተዋል፣ችግሮች ለመጪው ትውልድ እንዳይሻገሩ እና ከወዲሁ ተፈትተው ትውልድ እንዲሻገር አድርገዋል። በኢትዮጵያም የዛሬ ሀምሳ ዓመታትም ስለችግሮቻችን ብንወያይ መፍትሔው መነጋገር እና የምክክር ኮሚሽኑን ዓይነት አደረጃጀት ይዞ ከመጓዝ ሌላ አዲስ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም። ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በተለይ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የእዚህ ዓይነት በጎ አካሄዶችን ሳይደግፍ፣ሳይሳተፍ እና የመፍትሔ አካል ሳይሆን እንዲሄድ በኋላ ቀር አስተሳሰብ ሊሰብኩት የሚሞክሩትን ያለሁን 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ነኝ።ለመጪው ትውልድ የጸብ ዕዳ አላስተላልፍም! ለልጆቼ ሕይወት ዛሬ የችግር እና የግጭት አጀንዳዎችን ከወዲሁ ዘግቼ የተሻለች ኢትዮጵያን አወርሳለሁ! ብሎ በአንድነት የኮሚሽኑን ተግባር ቢችል በመሳተፍ፣ካልሆነ በማገዝ፣ ይህም ካልሆነ ባለመንቀፍ እና ዝም በማለት መተባበር መልካም ነው።
======================///////==============

የመረጃ ምንጮች ፡ 



No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...