ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 26, 2022

የዋጋ ንረት ጉዳይ የፀጥታ አና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን ለማቃለል መንግስት መከለስ ያለበት ቁልፍ የፖሊሲ ጉዳይ።


=========
ጉዳያችን ልዩ
=========

አይኢም ኤፍ የዋጋ ግሽበትን (ንረትን) ሲተረጉም ''በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚለካ አጠቃላይ የዋጋ ንረት ሲሆን ይህ የዋጋ ንረት አጠቃላይ ሀገራዊ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል '' በማለት ይገልጸዋል።የዋጋ ንረት የአዳጊው ዓለም ችግር ብቻ ሳይሆን የበለፀጉትም ሀገሮች እራስ ምታት ነው። ይህ ግን በቃ! በአኛ ሀገር የሚፈታ አይደለም ተብሎ አጅ ተጣጥፎ የሚቀመጡበት ጉዳይ አይደለም። ሲጀምር የአዳጊ ሀገሮች የዋጋ ንረት እና ያደጉ ሀገሮች የዋጋ ንረት በገበያ ባህሪውም ሆነ በሕዝቡ የገበያ የመግዛት አቅም አንዲሁም ያለው ነባራዊ የፖለቲካ፣የማኅበራዊ፣የምጣኔ ሃብታዊ አና የሕዝብ ብዛት (ዲሞግራፊ ) ሁኔታ ሁሉ የተለየ ነው። ስለሆነም ከራሳችን ሀገር አንፃር የችግሩ ዓይነትም የተለየ እንጂ በስመ የዋጋ ንረት በቀጥታ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ መርሆዎች ብቻ ለመፍታት የሚሞከር አይደለም የሚል አምነት አለኝ። ይህ ማለት መሰረታዊ የዋጋ ንረት የተመለከቱ የምጣኔ ሀብት መርሆዎችን መቃረን ማለት አይደለም።ከአዚህ ይልቅ የአኛ ሀገር የዋጋ ንረት ጉዳይ ከምርት ማነስ አና የብር የመግዛት አቅም መውረድ ባሻገር መታየት ያለባቸው ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለማትኮር ነው።

የነፃ ገበያ የተረዳንበት አግባብ ''ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ'' ሆኗል።

የነፃ ገበያ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከተወለደበት ያደጉ ሀገሮች ወደ አፍሪካ አና የአኛ ሀገር ሲመጣ የሆነ ልቅ የሆነ የገበያ አስተሳሰብ አንዳለ ተደርጎ ተተርጉሟል ወይንም ያደጉት ሀገሮች የአኛን ምሁራን ሲያስተምሩ አጋንነው ነግረውብናል አልያም በሚገባ አልተረዳነውም።ነፃ ገበያ ጥሬ ትርጉሙ ዋና ማጠንጠኛ የሚያርፈው ዋጋ የሚወሰነው በፍላጎት ስፋት አና ጥልቀት መሰረት ኩባንያዎች በሚያደርጉት የአርስ በርስ ነፃ ውድድር ነው የሚል ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳቡ ነው። በአዚህ መሰረት ብቻ ነው ግን ያደጉት ሀገሮች የሚሰሩት? የአሜሪካ መንግስት አንዳንድ ኩባንያዎች ከሚገባው በላይ ስያብጡ ከአዚህ በላይ ማበጥ አትችሉም።አደጋ አለው በሚል በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከሩቻቸው አልገታቸውም? 

አሜሪካ አንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1890 ዓም ያወጣችው ''የሻርመን ሕግ'' አንዱ አና በዋናነት የሚያዘው ግዙፍ ኩባንያዎች አና ነጋዴዎች ገበያውን ባላቸው የመቆጣጠር አቅም ምክንያት የዋጋ ንረቱን አንደፈለጉ አንዳያወጡት ብቻ ሳይሆን ገበያውን ሕገወጥ አንዳያደርጉት የታሰበበት ነው።በአዚህ መሰረት አንደማይክሮሶፍት ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎችን የአሜሪካ ፍርድቤት አየጠራ የማስተካከያ የሕግ ''ሞረዱን'' አሳይቷል። አዚህ ላይ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ይህ የሞኖፖል የገበያ ሁኔታ ላይ መች ደረስን? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ጉዳዩ የተነሳው የነፃ ገበያ በመርህ ደረጃ ያለ አንጂ በአውነታው ሲታይ ግን መንግሥታት በተለያዩ ፖሊሲዎቻቸው የዋጋ ሁኔታዎችን የመቆጣጠራቸው ሚና የማይተካ መሆኑን ለማሳየት የቀረበ ነው።የነፃ ገበያ ፅንሰ ሃሳብ አመንጭዎችም ሆኑ አራማጆች ቆይተው የተረዱት ብቻ ሳይሆን አየተገብሩት ያለው።ገበያውን ለነጋዴው ለቆ ቤተመንግስት የከተተ መንግስት ፈፅሞ አንደሌለ አና ወደፊትም ሊኖር አንደማይችል ነው።አዚህ ላይ ያለው ችግር ገበያውን ላቃና ብሎ የሚነሳ መንግስት ሹማንቶቹ በገበያው ገዢዎች የብር አቅም በመማለል የመንግስትን የቁጥጥር አቅም ሽባ የማድረጋቸው አደጋ መኖሩን የሚክድ የለም።ይህ አራሱ አውድ ከሙስና ጉዳዮች ጋር የሚታይ በመሆኑ ወደአርሱ ከመግባታችን በፊት በራሱ የዋጋ ንረት ዙርያ ላይ አንቆይ።

የዋጋ ንረት መዘዝ ቀላል አይደለም።

የዋጋ አለመረጋጋት አና ንረት የዋዛ መዘዝ አያስከትልም።ብዙ ሀገሮችን የተራዘመ አለመረጋጋት ከከተታቸው ውስጥ የዋጋ ንረት አንዱ አና ተጠቃሹ ነው።የማዕከላዊ ባንክ (በሌሎች ሀገሮችም ያሉ) የዋጋ ንረትን የዋጋ ግሽበት በምትል ማቆላመጫ ይጠሩታል።ይህም ችግሩን ከፖሊሲ ውጭ የማራቅያ መንገድ መሆኑ ነው።የብዙ ሀገሮች የፖለቲካ መሪዎች ወደ ስልጣን መውጫ አንዱ መሰላል የዋጋ ንረት አስወግዳለውሁ፣የኑሮ ውድነቱን አሻሽላለሁ የሚሉ የተለመዱ አባባሎች ናቸው።በቅርቡ በአንግሊዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ አንደ ፎጣ በቶሎ ስፋጠን ያየንበት ምክንያት ይሄው የዋጋ ንረት አና አርሱን ተከትሎ በመጣው የኑሮ ውድነት ሳብያ ነው።አንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1974 ዓም በኢትዮጵያ የ1966ቱ አብዮት በፈነዳበት ዓመት የአሜሪካ ፕሪዝዳንት ጂራልድ ፎርድ በአሜሪካ የተከሰተውን የኑሮ ውድነትን ''የህዝብ ጠላት'' በማለት ሰይመውት የነበረው ከጉዳዩ አስከፊነት አንፃር ነበር።

ዛሬም የዋጋ ንረት ሕዝብን ገፋፍቶ ወደ ተሳሳተ አስተሳሰብ የመምራት አደጋ አለው።ሕዝብ የሚመለከተው የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ መሮጥ ላይ አንጂ የነገውን ጉዳይ የመመልከት አቅም ውሱንነት አንደየግንዛቤው ይለያያል።ስለሆነም ተስፋ የሚሰጡ ጮሌዎች በኑሮው ጉዳይ አየገቡ በማታለል ዘለቂታዊ የሀገር ጥቅም ላይ ተረማምዶ ጠንካራ ለሀገር አሳቢ መንግሥታት ላይ በጥላቻ አንድነሳ ይቀሰቅሱታል።በዙምባቤ፣በብራዚል አና ሌሎች ሀገሮች የሆነው ይሄው ነው።ስለሆነም የዋጋ ንረት ጉዳይ የፀጥታ አና የሀገር ህልውና ጉዳይም ነው።

ኢትዮጵያ የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጂን) ለከት የሚለካ ጥብቅ ደንብ ያስፈልጋል።

ትርፍ ማለት በጥሬ ትርጉሙ አንድ የንግድ ድርጅት ወይንም ነጋዴ ጠቅላላ ገቢው ከጠቅላላ ወጪው በልጦ የመገኘቱ ሁኔታ ነው።የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) የትርፉ መቶኛ መገለጫ ነው።ይህ የትርፍ መቶኛ መጠን በቀጥታ ለንግዱ ባለቤት የሚገባ ወይንም ለኩባንያዎች ሲሆን ደግሞ  ለባለ አክስዮኖች የሚከፈለውን መጠን  ወይንም ለኩባንያው አድገት መልሶ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ  ውሳኔ ለመስጠት የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) ማወቅ ይጠቅማል።

የአንድ ነጋዴ የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) ለማግኘት ቀመሩ ጠቅላላ ገቢ ሲካፈል ለትርፍ ሲባዛ ለመቶ ( ጠቅላላ ገቢ /ትርፍ x 100= የትርፍ ህዳግ) ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ መረን የተለቀቀው አና ነጋዴ ይሉኝታ ያጣበት ጉዳይ ይህ ነው።መሰረታዊ ችግራችን የነጋዴዎቻችን የጨዋነት አና የስብዕና ጥራት (ሌላ የተሻለ ቃል ባለማግኘቴ ይቅርታ እየጠየኩ) አጅግ መውረዱ ነው።ነጋዴ (በእንግሊዝኛው ''ቢዝነስ ማን/ዉመን'') የሚለው ቃል የራሱ የሆነ የጥብቅ ስነ ምግባር አና የመታመን መገለጫ ቃልም ነው።በአኛ ሀገር ታሪክም ነጋዴ የሚታመን ለመሆኑ ለዘመናት ብዙ የአደራ ልውውጦች፣መልዕክቶች ሰው ልጁን ሳይቀር ወደ ሌላ ሀገር ሲያሻግር አደራ ብሎ የሚልከው ያለውን ወረት (ገንዘብ) በአደራ የሚያስቀምጠው በነጋዴዎች በኩል ነበር።የቀደሙት ነገሥታቶቻችን ሀገር አልፈው የሚመጡ ነጋዴዎች የሚሰጧቸው መረጃዎች፣ከተመለከቱት አና ካላቸው ልምድ የሚመክሩት ምክር ይደመጣል።አየቆየ ግን ነጋዴ የሚለው ቃል ''የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው'' ዓይነት ምንም ብለህ ምንም አድርገህ ትርፍ አምጥተህ ሃብታም መሆን የሚለው አስተሳሰብ የነጋዴ ነው የሚል የተሳሳተ እሳቤ በህብረተሰባችን ላይ አየተስፋፋ መጣ።

ይህ አስተሳሰብ በተለየ መንገድ የሰፈነው በወታደራዊው በኃላ ደግሞ አጅግ በከፋ መልኩ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ነው።በወታደራዊው መንግስት ዘመን የግል ሀብት የካፒታል መጠን ከግማሽ ሚልዮን በላይ አንዳይወጣ ስለተደነገገ ነጋዴው የሀብት መጠኑን በተለያየ ቦታ መደበቅ ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጩም ''አየር ባየር'' በሚል የንግድ ስም ተቀየረ።ቢሮ የሌላቸው፣ግብር የማይከፍሉ ነገር ግን ቦርሳቸውን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሀብታሞች ተከሰቱ።ይህ ጉዳይ በከፋ አና በአሰቃቂ መልኩ የተከሰተው ግን በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ነው።

በወታደራዊው ዘመን ባለስልጣናቱ በሙስና የሚታሙ አልነበሩም።በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ግን በነጠላ ጥልፍልፍ ጫማ አና መልኩን በቀየረ ጃኬት አዲስ አበባ የገቡት የህወሓት የወቅቱ ''ታጋዮች'' በጥቂት ጊዜ ውስጥ የቅንጡ መኪና ባለቤት ብቻ ሳይሆን የግዙፍ ህንፃዎች ባለቤት ተባሉ።አነኝሁ ዘራፍ ባለስልጣናት፣ካድሬ አና ታጣቂዎች ደግሞ ነጋዴ ተብለው የኢትዮጵያን ገበያ ከታች ችርቻሮ አስቀ ግዙፍ አስመጪና ላኪ ኩባንያዎች ባለቤትነት ያዙት።የዝርፍያቸው መጠን ለማሳየት በዓባይ ግድብ ላይ ሜቲክ የተባለው የህወሓት ሰዎች የሚያሽከረክሩት ድርጅት የሰራው ጥፋት አና የኢትዮጵያን መርከቦች መሸጥ የደረሰ ቡድን አስቀ መፍጠር ተደረሰ።
ከስር የመጣው ትውልድ ነጋዴ ማለት የሚያውቀው ዘራፊ፣ስነምግባር አና ሞራል የተለየው ብቻ ሳይሆን በወገኑ ደም ነግዶ ማትረፍ አንዴ ''ጎበዝ የንግድ ሰው'' የሚያስቆጥር አስተሳሰብ የሰረፀበት ሕብረተሰብ ቆየው።ስለሆነም በኢትዮጵያ ነጋዴ ማለት አና በሌላ ሀገር ነጋዴ ማለት ያሉት ትርጉሞች በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር የሰማይና ምድር ያህል ተለያይተው ተገኙ።ይህ የኢትዮጵያ ነጋዴ የተገለፀበት አገላለፅ ለሁሉም ነጋዴ ይሰራል ማለት አይደለም።ሆኖም ግን መሰረተ ሃሳቡ መናጋቱ አና መልካም ነጋዴዎች ስማቸው በተበላሹት ስም መለወሱ የሚያስማማ ጉዳይ ነው።

ወደ ዋና ፍሬ ነገሩ አንመለስ።የዋጋ ንረት ጉዳይ በኢትዮጵያ ከፈጠሩት በርካታ ምክንያቶች ውስጥ (ምጣኔሃብታዊ ትንታኔው የኢትዮጵያን ነባራዊ የገበያ ባሕሪ ባገናዘበ መልኩ መታየቱ አንዳለ ሆኖ) አንዱ አና ዋናው ምክንያት በወሳኝ አና ስልታዊ የሀገር ምርቶች በተለይ በሁለቱ መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ላይ ማለትም የምግብ አና የመጠለያ ዋጋ  በተመለከተ የነጋደው የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) በመንግስት በጥብቅ መልኩ አለመወሰኑ ነው።ይህ የመንግስት የፖሊሲ ድክመት ነው።

ይህ የትርፍ ህዳግ የመወሰን ሂደት የግል ዘርፉን የማደግ ጣርያ የመገደብ ጉዳይ አይደለም።ይልቁንም በአዚህ ሂደት የበለጠ ትርፋማነት አና ብዙ ነጋዴዎች ወደ ገበያው በተረጋጋ አና በአስተማማኝ መልኩ አንድገቡ ያደርጋል።ይህንን በሰፊው ለመዘርዘር ይህ ፅሁፍ ዓላማው አይደለም።ነገር ግን መንግስት ኢትዮጵያን ካለባት ቀውስ ለማዳን በምግብ አና ከመጠለያ ጋር የተያያዙ ምርቶችን ብቻ ሳይሆን ቀዳሚ ግብአቶች ላይ የትርፍ ጣርያ ልክ ማስቀመጥ አለበት።ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት አሁን ያለው የዋጋ ንረት ሳብያ ነጋዴዎች አያገኙ ያለው ትርፍ ፈፅሞ ምክንያታዊ ያልሆነ፣ካወጡት ወጪ ከአንድሺህ ፐርሰንት በላይ ትርፍ የምያፍሱበት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ አሁን የሚታየው የምግብና የቤት መግዣ ዋጋ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ አና አሜሪካ ካለው የበለጠ አና የተጋነነ ነው።ለአዚህም የብር ዋጋቸውን ወደ ዶላር አና ኢሮ ቀይሮ መመልከት ይቻላል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ከአፍሪካ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የኑሮ ውድነት የሚታወቁት ከተሞች ከጄኔቭ ስዊዘርላንድ፣ኦስሎ ኖርዌይ እና ቶክዮ ጋር ለመድረስ እየተንደረደረ ነው።በአፍሪካ ከተሞች ላይ ያለውን የምግብ እና የቤት ዋጋ ዝርዝር ላይ ስንመለከት አዲስ አበባ ብዙዎቹን በዋጋ ንረት እየጣለች መሄድዋ አሳሳቢ ነው።ይህ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት 2022 ዓም የዓለም የከተሞች የኑሮ ውድነትን የሚያወጣው ''ኑምቦ'' ድረገጽ አዲስ አበባ በሬስቱራንት ዋጋ ያለውን ንጽጽር መመልከት በቂ ነው።

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ፈጽሞ ምክንያታዊ አይደለም።በእዚህ ጽሑፍ ላይ በዋናነት መንግስት በተለየ መልክ የምግብ እና የቤት ዋጋ የትርፍ ህዳግ መወሰን ወሳኝ መሆኑን ለማወቅ እነኝህን ጥያቄዎች እናንሳ:
  • አያት አካባቢ አንድ ቪላ ቤት አዲስ አበባ ውስጥ (ይህ ጽሑፍ ከመዘጋጀቱ በፊት በአንድ ማስታወቂያ ላይ እንደተመለከትኩት) 38 ሚልዮን ብር የሚል ዋጋ ያሳያል።ይህንን ወደ ዶላር እንቀይረው እና በሩብ ሚልዮን ብር እና በግማሽ ሚልዮን ብር ናይሮቢ እና ካምፓላ እንዲሁም አውሮፓ እንበል ውድ የሆኑ ከተሞች እንደ ኦስሎ፣ኖርዌይ ቅንጡ ቤት የሚገዛበት ነው። እዚህ ላይ ጥያቄው አውሮፓ እና አሜሪካ ከአዲስ አበባ በታች በሆነ ዋጋ ቤት የተገኘው የተሰራበትን ወጪ ሸፍኖ የሻጩን ትርፍ ሁሉ መልሶ መሆኑ የታወቀ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ከወጣበት ወጪ በላይ ትርፉ ምን ያህል ተቆጣጣሪ የሌለው እና ይሉኝታ ቢስ እንደሆነ ማየት አይቻልም ወይ?
  • ኦስሎ ኖርዌይ በዓለም ካሉ ከተሞች የምግብ ዋጋዋ ከፍ ካለባቸው ከተሞች ውስጥ ነች። ነገር ግን በኦስሎ ሱፐርማርኬት ውስጥ አንድ ሙል ዶሮ ከሙሉ ብልት ጋር ታጥቦ እና ታሽጎ የሚሸጥበት ዋጋ አዲስ አበባ አንድ ዶሮ ከነነፍሱ ከሚሸጥበት ዋጋ ይቀንሳል። ይህንን ዋጋ ወደ ጀርመን፣ጣልያን እና ሌሎች የአውሮፓ ሃገሮች ስንወስደው በእጅጉ የቀነሰ ነው። እዚህ ላይ ጥያቄው በአውሮፓ ሱፐር ማርኬት የሚሸጠው የዶሮ ስጋ ከማምረት ሂደቱ እስከ ማጠብ እና ማቆያ ብሎም ማጓጓዣ ዋጋ ሁሉ ተጨምሮ እና ትርፉን ጨምሮ የሚሸጥ ዋጋ ሆኖ ነው ከአዲስ አበባ የቀነሰው። አዲስ አበባ ላይ ገና ያልታረደ፣ሽንኩርት ያልወጣለት፣ቅቤ ያልተገዛለት ዶሮ ዋጋ ከአውሮፓ ዋጋ እንዴት በለጠ?
ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ማሳያዎች በተለይ የምግብ ዋጋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በባሰ መልኩ ደግሞ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ውስጥ የጨመረበት ምክንያት ምንድን ነው? የአዲስ አበባ የቤት ዋጋ እና የምግብ ዋጋ ንረት ከአውሮፓ እንዴት ይበልጣል? ብለን ስንጠይቅ አንዳንዶቻችን አውሮፓ በብዛት የማምረት አቅም ስላለ፣ቴክኖሎጂው እና አሰራሩ ወጪውን ቀንሶት ነው ብሎ የሚያስብ ይኖራል። ሆኖም ግን ቴክኖሎጂው ምን ያህል ቢያድግ፣ምርት ምን ያህል ቢጨምር የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) ገደቡን መንግስት ይቆጣጠራል እንጂ ገበያ አገኘሁ ብሎ ነጋዴ እንደፈለገ አይጨምርም።

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በልጓም የሚለጉመው መንግስት ያጣ ነው እንጂ የአቅርቦት እና የፍላጎት መጣጣም ቢመጣም አይገታውም።ምክንያቱም ነጻ ገበያ ማለት መረን የለቀቅ ነጋዴ እንደፈለገ ህዝቡን ሲበዘብዘው መመልከት ማለት ሆኗል።ቀድሞ ነገር ነጻ ገበያ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ያደጉ ሃገሮች ነጻ ገበያ እንዲኖር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ስንቱ ተሟልተዋል? ከ80 በመቶ በላይ በግብርና የሚተዳደር ህዝብ ያላት ሃገር ገበያውን ለጥቂት ''እፍረት የለሽ '' ነጋዴዎች በነጻ ገበያ ሥም እንደፈለጉ እንዲሄዱ ተፈቅዶ ሃገር ሃገር አይሆንም።

ለማጠቃለል፣የዋጋ ንረት ሲነሳ የምርት እጥረት ጉዳይ ብቻ ወይንም የገንዘቡ የመግዛት አቅም መውደቅ የሚሉ አገላለጾች ብቻ የችግሩ መግለጫ ሊሆን አይችልም።ምክንያቱም ምርቱ እየጨመረ ቢሄድም ነገ ዋጋ ከነበረበት አይወርድም።ምክንያቱም ነጋዴው የትርፍ ህዳጉን የሚመጥን ሕግ የለበትም።ሰው በባሕሪው ደግሞ በቃኝ አይልም። አንድ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የሔደ ወዳጄ ምልከታውን ሲነግረኝ። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በደንብ በሚያውቃት የክልልል ከተማው ውስጥ ያሉትን ገበያዎች ተመልክቶ ያለኝ ''እኔ እስከ ገባኝ ደረስ ሁሉም ቦታ ገበያው በሚሸጥ የምግብ እና ፍራፍሬ የተሞላ ነው።እንዲያውም ቀድሞ ከማውቀው በላይ የተትረፈረፈ ነገር ገበያው ላይ ተሰጥቶ ይታያል።ዋጋው ግን ሰማይ ነው።'' ነበር ያለኝ።በነጻ ገበያ አመክንዮ የፍላጎትል እና የአቅርቦት መቀራረብ ዋጋን ይወስነዋል የሚለው ኢትዮጵያ ላይ እንዳይሰራ ያደረገው የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) ልጓም የሚያስገባ የመንግስት ጥብቅ ፖሊሲ ያስፈልጋል። ለነዳጅ ዋጋ ሲወጣ ነዳጁ የመጣበት ዋጋ ሲደመር ነዳጁ ከወደብ የሚጓጓዝበት ከተማ እርቀትን እየለካ እንደእርቀቱ ዋጋው ይለያያል።በእዚሁ መሰረት የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊትማርጅን) በተለይ በተለይ ለምግብ እና ለቤት ዋጋዎች መንግስት በፍጥነት ማውጣት አለበት።

የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) ለምግብ ሸቀጦች እና ለቤት ለመወሰን መንግስት ከንግድ ምክርቤቶች ጋር ቁጭ ብሎ በዝርዝር ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ላይ ይስማም።የዋጋ መስማምያ ነጥቡ የነጋዴውን ምክንያታዊ ትርፍ የማይነካ ነገር ግን በምስኪኑ ህዝብ ላይ ገደብ የለሽ ትርፍ የማይካበትበት የመስማምያ ነጥብ ላይ ይድረስ።እዚህ ላይ መጠንቀቅ የሚገባው የምርቱ ዋጋ የትርፍ ህዳግ ላይ ከመሔድ በፊት ዋና ግብአቱ ዋጋ ላይ ተመን ያስፈልጋል።ለምሣሌ፣ የአንድ እንጀራ ዋጋ ከመተመን በፊት ዋናው ግብአት አንድ ኪሎ ጤፍ ከመመረት እስከ ገበያ ያለው መስመር የሚኖረው ወጪ ተደምሮ የነጋዴው ምክንያታዊ ትርፍ ተጨምሮ ስንት፣የት ከተማ ላይ መሆን እንዳለበት ከንግድ ምክርቤቶች ጋር በጋራ መወሰን ያስፈልጋል። አንድ ቤት ለመስራት የፈጀው ወጪ አንድ ሚልዮን ብር ሆኖ ሳለ የሚሸጥበት ዋጋ 15 ሚልዮን ማለት የትርፍ ህዳጉ ስንት ቢሆን ነው? ከወጪው በላይ 1500 ፐርሰን ትርፍ ምን ማለት ነው? የት ሃገር ነው ይህ የሚፈቀደው? የአንድ ቤት ወጪ ላይ ሻጩ ማግኘት ያለበት ትርፍ ስንት መሆን አለበት? ዝርዝር ወጪው ሲደመር ምክንያታዊ ትርፉ ይሰላ! ምርት ምንም ያህል ቢጨምር ዋጋ አይቀንስም።ነጋዴው የትርፍ ህዳጉ ካልተገደበለት ዋጋ እየጨመረ ይኖራል።በድሃው ህዝብ ላይ በዶላር እና ኢሮ ሲመነዘር እንኳን ትልቅ ገቢ ካለው የአውሮፓ እና አሜሪካ ህዝብ በላይ ዋጋ ተጭኖበት የሚሰቃይ ኢትዮጵያዊ ወሳኝ ውሳኔ ይፈልጋል።

እዚህ ላይ አንድ ሊነሳ የሚችል ጥያቄ ለመመልስ ልሞክር እና ጽሑፉን ላጠቃል።ጥያቄው የትርፍ ህዳግ (ፕሮፊት ማርጅን) በነጋዴው ላይ ሲወሰን ነጋዴው ብዙ እንዳያመርት፣ገበሬው ብዙ እንዳይሰራ አያደርግም ወይ? የሚል ነው። መልሱ አያደርግም ይልቁንም ምርት ያሳድጋል። ምክንያቱም የትርፍ ህዳግ ወሰን መኖር ለነጋዴውም ሆነ ለገበሬው ብዙ ትርፍ የሚመጣው ከብዛት ከመሸጥ እንደሆነ ግልጽ ስለሚሆን ምርት ያድጋል እንጂ አይቀንስም።የትርፍ ህዳጉ መወሰን የገበያውን ፍላጎት ይጨምራል።ዋጋ ሲቀንስ ፍላጎት እንደሚጨምር የምጣኔ ሃብት መሰረታዊ አመክንዮ ነው።ስለሆነም ፍላጎት ይጨምራል።አቅርቦትም እንደ ድሮ ትንሽ በብዙ ዋጋ ሸጦ መቀመጥ በነጋዴው ዘንድ ስለሚቀር።ብዙ በማቅረብ ብቻ የትርፍ ህዳግን ማሳደግ ዋና አማራጭ ይሆናል።ስለሆነም በገበያው ውድድር ላይ በብዛት ማምረት የቻለ ብቻ የሚያተርፍበት ገበያ ይፈጠራል።ይህ ብቻ አይደለም።የትርፍ ህዳጉ የታወቀ እና አስተማማኝ መሆን ብዙዎች ወደ ምርት ገበያው እንዲገቡ ያበረታታል።በመጨረሻም ገበያ ያረጋጋል።የትርፍ ህዳግ መረን ይለጎም።ከአንገብጋቢዎቹ ምግብ እና ቤት ይጀመር።ወደ ልብስ ይቀጥል።ቢያንስ ከአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ የባሰ የኑሮ ውድነት ውስጥ ገብተናል።ዝም ከተባለ ደግሞ ሃገር ያፈርሳል።
 
=================
ጌታቸው በቀለ

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...