ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, November 10, 2022

የናይሮቢው ድርድር ካልተራዘመ ከአሁን በኋላ ህወሓት በዝርዝር የትጥቅ አፈታት ሂደት ላይ ለመስማማት 36 ሰዓታት ብቻ ይኖሩታል።

36

  • የድርድር ጊዜው ካልተራዘመ በቀጣዮቹ 36 ሰዓታት ውስጥ የትጥቅ መፍታት ዝርዝር ሂደቱ ላይ ስምምነት ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል። ስምምነት ባይደረሰም በትግራይ ሰላም የማምጣት ኃላፊነት የወደቀው መከላከያ ትከሻ ላይ ብቻ መሆኑን የትግራይ ህዝብ በተለይ ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ የበለጠ ገብቶታል።
===========
ጉዳያችን ምጥን
===========

ጥቅምት 23/2015 ዓም በፊርማ የተጠናቀቀው በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶርያ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ፌድራል መንግስት እና በህወሓት መሃከል የነበረው ንግግር (ድርድር) የኢትዮጵያ መከላከያ ከፍተኛው እርከን በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ መኮንኖች ከህወሃት መሪዎች ጋር በናይሮቢ እየቀጠለ ነው።

የናይሮቢው ንግግር እንደደቡብ አፍሪካው በዝግ እየተደረገ ሲሆን ትናንት ረቡዕ ይጠናቀቃል ተብሎ ባለመጠናቀቁ እስከ ነገ ዓርብ እንደቀጠለ ከስፍራው መረጃ አገኘን ያሉ የምዕራብ ዜና አውታሮች የገለጹ ሲሆን አሁን ንግገር እየተደረገ ያለው ህወሃት ትጥቅ የሚፈታበት ዝርዝር አካሄድ ላይ እና ለትግራይ የዕለት ደራሽ ምግብ፣ኤሌክትሪክ እና ኢንተርኔት የሚለቀቅበት ጉዳይ ላይ ነው።ይህንኑ አስመልክቶ ዋሽንግተን ፖስት ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ በለቀቀው ዘገባ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግስት ወክለው በድርድሩ ላይ የተገኙት አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰብዓዊ ዕርዳታው በእዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይንም በመጪው ሳምንት አጋማሽ ላይ ትግራይ እንደሚደርስ መናገራቸውን ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ወ/ሮ ሰላማዊት ዛሬ ጧት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ለሰብዐዊ እርዳታ የሚያንቀሳቅስ ልዩ ቡድን መንግስት ማደራጀቱን እና መንቀሳቀሱን ገልጸዋል። በእዚህ መሰረት በአራት ቡድን የተደራጀ የእርዳታውን ሥራ የሚያቀላጥፍ ቡድን በሰሜን ወሎ በኩል እና በሰሜን ጎንደር በኩል እንደተንቀሳቀሰ እና የመሰረተ ልማቶች ግንባታንም መንግስት እያቀላጠፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላም ንግግሩ በጥሩ ሁኔታ ማለቁ እና ህወሃት አሁን የትግራይን ህዝብ ለማዳን ብቸኛ አማራጩ ትጥቅ ፈትቶ ወትሮም ሲጠብቀው የነበረው መከላከያ ሥራውን እንዲቀጥል ማድረግ ወስኛለሁ ያለው ህወሃትም ከእዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ማወቁም መልካም ዕይታ ነው።እዚህ ላይ ይህ ውሳኔ የመጣው የኢትዮጵያ መከላከያ እና ጥምር ጦር አድዋ፣አክሱም እና ሽሬን ጨምሮ በርካታ የትግራይን ከተሞች እና ገጠር አካባቢዎች ነጻ ካወጣ በኋላ ነው። 
 
የስምምነቱ ውጤት ምንም ቢሆን በትግራይ ሰላም የማምጣት ሂደቱ ኃላፊነት የወደቀው መከላከያ ትከሻ ላይ ብቻ መሆኑን የትግራይ ህዝብ በተለይ ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ የበለጠ ገብቶታል።ከቀደመው በላይ የቅርብ ክስተቶች ለትግራይ ህዝብ የሰጡት የሰላም ጭላንጭሎች የበለጠ ግልጽ አድርገዋል።ከእዚህ የሰላም ጭላንጭል ማንም የትም ቢሰለፍ ፈልቅቀው ሊወስዱበት እንደማይችሉ ህዝብ ይገባዋል።ለእዚህም የመከላከያ ሚና እጅግ የጎላ እንደሆነ ከምንጊዜውም በላይ ግልጽ እና ግልጽ ሆኗል።ከእነኝህ ክስተቶች ውስጥ 
  • ህወሃት ትጥቅ የሚፈታ እንጂ አይነኬ አለመሆኑን የትግራይ ህዝብ ከእዚህ ድርድር ተምሯል።
  • መከላከያ የዘር ማጥፋት ፈጸመ እያሉ በውሸት ሲያወሩ የነበሩት ሁሉ ውሸታቸውን ለመሆኑ እራሱ ህወሃት መከላከያ ይጠብቀን የሚል ሰነድ ላይ በመፈረሙ አረጋግጧል። ህወሃት በእዚህ ሰነድ ላይ ሲፈርም ለትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ መከላከያ በላይ ማንም እንደማይደርስለት ለትግራይ ህዝብም ደግሞ ነግሮታል።
  • የትግራይ ህዝብ የማይነኬው ህወሃት ሊወገድ የሚችል መሆኑ ተነግሮታል።የህወሃት ሚድያዎች የኢትዮጵያን መንግስት ''ፋሽሽት'' እያሉ ከሳምንት በፊት ሲጠሩ የነበሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ሲሉ ሰምቷል።
  • የትግራይ ህዝብ በተለይ በውጭ የሚኖሩ እና ከኢትዮጵያ እና የትግራይን ንብረት ዘርፈው የወጡ፣ለትግራይ ህዝብ አንድ ብርጭቆ ንጹህ ውሃ ያልሰጡ የትግራይ ህዝብ ሰላም ሲመጣ ሲቃወሙ አይቶ ከህወሃት በላይ የሆኑ ህወሃቶች ምን ያህል ጠላቱ እንደሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለይቶ አውቋቸዋል።
  • ጥቅምት 24/2013 ዓም ህወሃት በመከላከያ ላይ የፈጸመው ግፍ ምን እንዳስከተለ የትግራይ ህዝብ ተመልሶ ለማየት የበለጠ ፍንትው ብሎ የታየበት ጊዜ ነው።
በመሆኑም መከላከያ አሁን ያለበት አቋም በበለጠ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የመፈለጉ ብቻ ሳይሆን ከመከላከያ ውጭ በትግራይ ማንም ሰላም እንደማያመጣ ከምንጊዜውም በላይ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለህወሃትም ግልጽ ሆኗል። የትጥቅ አፈታቱ ሂደት ላይ ህወሃት ነገሮችን ለማጓተት ቢያስብም ባያስብም በተሰጠው የጊዜ ገደም ውስጥ ካልተከናወነ መከላከያ ወደ መቀሌ የመግባት እና አሁን ከፍተኛ ዝርፍያ በከተማዋ እየተፈጸመ እንደሆነ የሚነገርባትን ከተማ የማዳን ብሄራዊ ሃላፊነት አለበት።

================///==========

No comments: