ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 16, 2018

ድምፃዊት ሚካያ ሞት ባይቀድማት የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ አንድ እርምጃ የመውሰድ አቅሟ ትልቅ ነበር (ጉዳያችን ማስታወሻ)

ጉዳያችን / Gudayachn 
ሚያዝያ 8/2010 ዓም (አፕሪል 17/2018)

ድምፃዊት ሚካያ 
  • ድምፃዊት ሚካያ ብሔር ብሔር በሚባልበት ዘመን ውስጥ ስለ አትዮጵያ ትውልዷን ያስተማረች፣ጠንካራ ትውልድ እንዲመጣ ሕልሟን ያስቀመጠች የሀገር ባለ ውለታ ነች።ዛሬ ኢትዮጵያ ስሟን እንደገና የሚማፀን ትውልድ ብትመለከት እንዴት ደስ ባላት ነበር።
ድምፃዊት ሚካያ ከአምስት ዓመት በፊት በድንገት ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።በዩንቨርስቲ ትምህርቷም ስኬታማ የነበረችው ድምፃዊት ሚካያ ከእዚህ ዓለም በሞት ከመለየቷ በፊት በሴቶች ሕይወት ላይ ያጠነጠነ አዲስ የራድዮ መርሃ ግብር አየር ላይ ለማዋል ዝግጅት ላይ ነበረች።ሚካያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ  ቤተለሄም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በንጉሡ ዘመን GCA (Girls Christian Academy)  በደርግ ዘመን ስሙ የአብዮት ቅርስ በተሰኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጀመርያ ዲግሪዋን በቋንቋዎች ጥናት የያዘች ሲሆን በአንድ ወቅት አለባቸው ቶክ ሾው ላይ ቀርባ የወደፊት ሕልሟን ስትገልጥ በድምፅ ከመጫወት በላይ በፊልም ትወና መስራት እንደምትፈልግ እና ሀገሯን ማስጠራት ሕልሟ እንደሆነ መናገሯ ይታወሳል።

ሚካያ ከእዚህ ዓለም በሞት በ2006 ዓም ታህሳስ ወር ላይ ስታልፍ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማስተርስ ትምህርቷን ልታጠናቅቅ ጥቂት ወራት ቀርተዋት ነበር።አርቲስቷ በአፍሪካ ኮራ የሙዚቃ ውድድር ተመርጣ ከ20 ምርጦቹ ውስጥ ከመሆኗ በላይ የውድድሩ አጋማሽ ድረስ በጥሩ ውጤት ደርሳ ነበር።ለውድድር ከመቅረቧ በፊት ስራዋ በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ቀርቦ አድናቆትን አግኝቶም ነበር።በጥቂት ስራዎቿ የኢትዮጵያን ኪነጥበብ ወደ ዓለም መድረክ ታመጣለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሚካያ በሁለት ሳምንት የተሰማት ድንገት ህመም ሳብያ ሲብስባት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስዳ በ37 አመቷ ሕይወቷ በድንገት አልፏል።ድምፃዊት ሚካያ ብሔር ብሔር በሚባልበት ዘመን ውስጥ ስለ አትዮጵያ ትውልዷን ያስተማረች፣ጠንካራ ትውልድ እንዲመጣ ሕልሟን ያስቀመጠች የሀገር ባለ ውለታ ነች።ዛሬ ኢትዮጵያ ስሟን እንደገና የሚማፀን ትውልድ ብትመለከት እንዴት ደስ ባላት ነበር።
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ አንጋፋዎቹ በሚታሰቡበት ወቅት በአጭር ጊዜ ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ሥራ የሰሩ አርቲስቶችን አለመርሳት ተገቢ ነው።
ከእዚህ በታች የሚካያን ሁለት ዜማዎች በተከታታይ ያድምጡ።
ሀገሬ 

ሰበቤ ሁን ሲልህ 



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments: