Foto : Fana digital
- የቻልን በሀሳብ እና በጸሎት፣ ያልገባን እና የተምታታብን ደግሞ እኪገባን በዝምታ በመቆየት ኢትዮጵያን እናግዛት።
=========
ጉዳያችን ልዩ
=========
ኢትዮጵያ ሐምሌ 8፣2018 ዓም ከሁለት ሺህ በላይ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በአዲስ አበባ ይከፈታል።የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመሰራረትና አደረጃጀት ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት እየገነባቻቸው ያሉት የተቋሞቿ የጥራት ደረጃ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ተቋም የሚለካው ከተቋማዊ መዋቅሩ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከአመሰራረቱ ግልጽነት እና ሒደት ጭምር ነው። ከእዚህ አንጻር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአመሰራረት ሂደትና የያዘው የሰለጠነ የሰው ኃይል ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ የተቀናጀ ነው።
ኮሚሽኑ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ ሆቴል ለሚዲያዎች መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። በዚህም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር)፣ "ዋናው ሀገራዊ ጉባዔ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምር ይካሄዳል" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የመጨረሻው ዋና ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ ከሦስት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል በሚስተዋለው የፖለቲካ አለመረጋጋት መግባት ባለመቻሉ የክልሉን አጀንዳ በአዲስ አበባ ከተማ መቀበሉን፣ በሌሎች ሁሉም ክልሎች በአካል በመንቀሳቀስ መቀበሉን ሲያስታውቅ ቆይቷል። በተያያዘ የቀረቡለት አጀንዳዎቹን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ሀሳብ እየተቀበለ መሆኑን መሆኑን ከሰሞኑ ጭምር ገልጿል።
በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ዳያስፖራዎችም አጀንዳ መቀበሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ መጀመሪያ በተሰጠው ሦስት አመታት ስራው ባለመጠናቀቁ ፓርላማው ለአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ከሰጠው በኋላ፣ ያም ባለመብቃቱ ለሁለተኛ ጊዜ የስምንት ወራት ጊዜ ተጨምሮለት እየሰራ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ከመላው ሀገሪቱ እና ከራሱ ከመንግስትም ጭምር አጀንዳዎችን ከተቀበለ በኋላ አጀንዳዎቹን በሚከተሉት ዋና ዋና ሃሳቦች ጠቅልሏቸዋል።
እነርሱም ፡-
👉 የሀገር ግንባታ
👉 ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና የሰላም ግንባታ ናቸው፡፡
ይህ ጉባዔ የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ማማ መለኪያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ጉባዔ ነገ በአዲስ አበባ ይከፈታል። ህልውናችን፣መጪው ስልጣኔያችን፣ሰላማችን እና ዕድገታችን በእዚህ ጉባዔ ውጤትና ሒደት ይወሰናል። በእዚህ ጉባዔ ከባሕር ማዶ ተቀምጠው አቃቂር የሚያወጡ እና በገዛ እናታቸው ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ላይ የሚሳለቁ ወደ ሕሊናቸው እንዲመለሱ ይመከራሉ። በራስ ላይ መቀለድ ለጊዜው እንደ ቀላል ሕመም ሊታይ ይችላል።በአሁኑ እና በመጪው ትውልድ ላይ ለመቆመር መሞከርና በመዘባበት እንዲሁም ትውልዱ እያደረገ ያለውን ምክክር ለማጣጣል መሞከር ግን እንዲሁ በቀላል መታየት ያለበት ጉዳይ አይደለም። ትውልዱ እራሱ ተዉን! ተመካክረን ችግራችንን እንፍታበት! ብሎ ሊገስጻቸውና ከእዚያም ሲያልፍ መቅጣት መቻል አለበት።
አሁን ኢትዮጵያ እየመከረች ነው። መንግስትም የራሱን አጀንዳ እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል አቅርቦ እኩል የሚወያይበት እና በኢትዮጵያ መጪው የፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጎዳና ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ የሚኖረው ሀገራዊ ውይይት እንዲሳካ እና ለሀገራችን ጥቅቅኖቹም ሆነ ግዙፍ የልዩነት ጉዳዮች መፍትሔ እንዲሰጥ የቻልን በሀሳብ እና በጸሎት፣ ያልገባን እና የተምታታብን ደግሞ እኪገባን በዝምታ በመቆየት ኢትዮጵያን እናግዛት።
=================///////=============

No comments:
Post a Comment